በቅድሚያ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ 80ኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ!!!በዓሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ)፣የድርጅቱ የህትመት ውጤቶች አንባቢያንና ከህትመት እስከ ስርጭት ሂደት የሚሳተፉ አካላትና አባላት ብቻም ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን እንደሆነም ስለማምን እንኳን አደረሰን!!! እላለሁ። በአንባቢነቴ የጋዜጣውን ዕድሜ ግማሽ ያህል ቆይቼያለሁ። ከጋዜጣው መረጃ፣ትምህርትና አዝናኝ ጉዳዮችን አግኝቼበታለሁ።
አንባቢነቴ
ጋዜጣውን ማንበብ የጀመርኩት በተማሪነት ዘመኔ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በምማርበት ወቅት የቅዳሜና የእሁድ የጋዜጣውን ቅጂዎች ለወታደሮች በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ ከሚያከፋፍል ወጣት ተረክቤ አነብ ነበር። የአንዱ ጋዜጣ ዋጋ ያኔ 10 ሳንቲም ሲሆን፤ልጁ ለወታደሮች የሚያከፋፍለው በ15 ሳንቲም ሂሳብ ነበር።
ወደ ሥራ ዓለም ስገባ ተቋሜና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባላቸው ስምምነት የድርጅቱን የህትመት ውጤቶች ለማግኘት አልተቸገርኩም። በሐረር፣በወላይታ ሶዶ፣ በጎባ፣ በነጌሌ ቦረናና በአርባ ምንጭ ከተሞች ስሰራ አዲስ ዘመን ዋነኛ የመረጃ ምንጬ፣ዕውቀት የማዳብርበትና መዝናኛዬ ነበር። የሙያ ብቃቴን ለማሳደግ ያገዘኝ አብሮ አደጌ ነው።
ዘገባዎቹ
ጋዜጣው በ24 ሰዓት ልዩነት የሚወጣ እንደመሆኑ መጠን ትኩስ መረጃ ለማድረስ ሲጥር ቆይቷል። ያለፉት 20 ዓመታት ከመደበኛ የዜና አዘጋገብ ለመውጣት ዜናን በየፈርጁ ለማቅረብ የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሆነ እንጂ፤በእኔ ዕድሜ የማውቀው ቀንና ምሽቱን የተወራውን ጠዋት አትሞ አሰራጭ ሆኖ ቆይቷል። ያም ቢሆንም መረጃ አያቀብልም ማለት አልነበረም። በዚህ ላይ ጥሩ ሰነድ ሆኖ ያገለግላል። ዛሬ ዜና ትንታኔና ዜና ሐተታዎችን እንዲሁም ቃለ መጠይቆች እየተደረጉ የሚወጡበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ከዘገባዎቹ ባሻገር
ጋዜጣው ዘመን የማይረሳቸው ገጾችና ዓምዶች ነበሩት። በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ የሚወጡት ዕትሞች ለጠቅላላ ዕውቀት፣ለአዝናኝነት ብሎም በቁም ነገር የሚወሰዱ ነበሩ። ’’አድማስ’’ያስታውሷል፡’’ሕይወት እንዲህ ናት’’ም አይረሳም። ‘’ቅምሻ’’ም ከስሙ በላይ ነበር ለአንባቢያን።
ከዚህ ውጭ ከሥነ ልቡና ጋር በተገናኘ በሳምንት አንዴ የሚቀርብ’’መፍትሄ ቢሆንዎ’’ የሚል ገጽ እንደነበር አስታውሳለሁ። ጠቃሚ ምክሮችና መፍትሄዎች ለብዙዎች እንደሰጠ አስታውሳለሁ።
በኪነ ጥበባት ዘርፍ ይቀርቡ የነበሩት ጽሁፎች በሳልና ነባር ፀሐፍትን ያሳትፉ ነበር። አንዳንዴም ክርክሮች ተስተናግደዋል። ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎችና ሥራዎቻቸው ተዋውቀውበታል።
እግረ መንገዴን የማስታውሰው የጋሽ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔርን’’ እግረ መንገድ’’ ሳምንታዊ ጽሁፎች ነው። ጋሽ ስብሃት ያለውን ያለ ስስት ሲያቀብለን ኖሯል።
በጤና፣በትምህርት፣በስፖርት መስኮች ተነባቢ ጽሁፎች ከጋዜጣው ስንቋደስ መዝለቃችንን እመሰክራለሁኝ።
ሌሎቹን ሳያቸው
በእኔ ዕድሜ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአማርኛ የሚታተም ሌላ ወንድም ነበረው። ከሰኞ በስተቀር የማይታተም ዕለታዊ ጋዜጣም ነበር። (ምንም እንኳን ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ሰኞንም ቢጨምርም)
‘’የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ’’ የተባለው ጋዜጣ በድርጅቱ እየታተመ ቅዳሜ ገበያ ላይ ይውል ነበር። ጋዜጣው የሳምንቱን ዐበይት ዜናዎች ይዞ ይወጣል። መረጃ ሰጪ፣ትምህርታዊና ጠቅላላ ዕውቀት የሚሰጡ ዝግጅቶችም ነበሩት። ተነባቢነቱና ተፈላጊነቱም ከፍ ያለ እንደነበር አስታውሳለሁ።
‘’ሰሙናዊት’’በሚል ርዕስ ያወጣቸው የነበሩት መረጃዎች አስተማሪና አሳዋቂ ነበሩ። ስሜነህ መኮንን፣አብርሃም ፍሥሐ፣አረጋ ወልደ ቂርቆስ፣መስፍን እንድርያስና ሰለሞን ተስፋዬን አልረሳቸውም።
ጋዜጣው በተከታታይ የሚያቀርባቸው የጥያቄና መልስ ውድድሮችም ነበሩት። ተወዳዳሪዎቹ በፖስታ መልሳቸውን እየላኩ በሚያጠራቅሙት ነጥብ በየዓመቱ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ የሚያገኙት ስማቸው ይገለጽ ነበር። እኔ አንድ ዓመት ተወዳድሬ ስድስተኛ እንደወጣሁ አስታውሳለሁ። ሽልማቱ ዕውቀትን መፈተሽ ብሎም ዕውቅና ማግኘት ነበር። የ100ብር የሞባይል ካርድ ዓይነት ሽልማት ያኔ አይታወቅም።
ዕለታዊው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋዜጣ ‘’The Ethiopian Herald’’ የድርጅቱ ሌላ ዕትም ነው። ጋዜጣው መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች፣ የአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ሰራተኞች፣ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣እንግሊዝኛ ማንበብ ለሚችሉ ኢትዮጵያውያን አገራዊ መረጃ ሲሰጥ ቆይቷል።
ኤፍሬም እንዳለ ያዘጋጀው የነበረው ‘’Between You and Me’’ ዓምድ ዋዛን ከቁም ነገር በማቅረብ ተነባቢ ነበር። ዘንድሮ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ስላነበብኩት ደስ ብሎኛል። ስመ ሞክሼውን ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩን’’not me the golden voiced vocalist’’ የሚላትና የአዲስ አበባ ቢራን የሚያዳንቅበት’’sip of beer’’ የምትመስለኝ ትዝ ይሉኛል። ኤፍሬም በአማርኛ ቋንቋ በሚታተም ጋዜጣ ላይ በሚያዋጣው’’እንጨዋወት’’ዓምድ ‘’ስሙኝማ’’ ማለትን አስለምዶናል።
‘’Just a Few Points’’ ና ‘’ Cultural Front’’ የተባሉ ዐምዶችን በማዘጋጀት የምናውቀው ዐረፈ ዓይኔ ሐጎስም ሌላው ታላቅ ጋዜጠኛ ነው። የመጀመሪያው ቀልዶች፣ጥቅሶችና አባባሎች የሚቀርቡበት ዓምድ ነበር። ቀልዶችን ካነሳሁ አይቀር ዐረፈ ዓይኔ የቡልጋሪያዎቹን የጋብሮቮ ቀልዶች ተርጉሞና እንዳሳተመ አስታውሳለሁ።
በኪነ ጥበብና በባህል ጉዳዮች ላይ ያተኩር በነበረው ሁለተኛው ዓምዱ ፀሐዬ ዮሐንስ የመጀመሪያውን ካሴት ያሳተመው 1ሺህ 500 ብር ተከፍሎት እንደነበር የገለጸበት ጉዳይ ዛሬም አልረሳሁትም። ዘመኑ 1975 ይመስለኛል። በዛሬው ተውትና በያኔውም ድምጻዊውን ጨምሮ ለአንድ ካሴት ዝግጅት ገንዘቡ አይመጥንም።
መጽሔቶቹ
ድርጅቱ ‘’የካቲት’’ተብለው የተሰየሙ የአማርኛና የእንግሊዝኛ መጽሔቶች ነበሩት። ኋላም ’’ሰንደቅ’’፣አሁን ደግሞ ‘’ዘመን ‘’በሚል ስያሜ መጽሔቶችን ያሳትማል። ለእኔ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ጫና ቢኖርባቸው ‘’የካቲት’’ መጽሔቶች ይበልጡብኛል። ቢያንስ ትምህርታዊና መረጃ ሰጪ ሆኖ አልፏል። ልቦለድ ሳይቀር ያቀርብልን ነበር። ለዛና ቁም ነገር ማስተናገዱ በነበረበት ዘመን ሲለካ ፍሬያማ ነበር ብል ማጋነን አይሆንም።
የእንግሊዝኛው ‘’የካቲት’’ መጽሔት ‘’አብዮታዊት ኢትዮጵያ’’ን በአግባቡ አስተዋውቋል። የያዕቆብ ወልደ ማርያም ጽሁፎችም ድንቅ ነበሩ። ዛሬ ያንን የሚተካ መጽሔት መታተም አለበት የሚል ሐሳብ አለኝ።
የአሁኑ ‘’ዘመን’’መጽሔት የህትመት ውጤቶች በፈሉበት ወቅት መውጣቱ ቃለ መጠይቅ የበዛበት አድርጎታል። የራሱ መለያ ቀለም የማጣትና የዋና አዘጋጆች መቀያየር የጎዳው ይመስላል። ሆኖም ከፈሰሰበት ቀለም በላይ ዋጋ እንዳለው መመስከር እችላለሁ። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት የአድዋ ድል የተዘከረበት ዕትም ድንቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አንዳንዴ ወቅቱን ጠብቆ ያለመውጣት ችግር እንዳለ ሆኖ።
ጋዜጣው
ዘንድሮ ስምንት አስርታትን ያስቆጠረው ዕለታዊው ጋዜጣ በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደር እንደመሆኑ መጠን፤ተፈራራቂዎቹን መንግሥታት አገልግሏል። የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ባልተረጋገጠባቸው አገሮች የሚጠበቅ ከመሆኑ አንጻር እምብዛም ላይደንቅ ይችላል። የሕዝብ ድምጽ ለመሆን ጥረት አልተደረገም ባይባልም።
በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት የነበሩት መንግሥታት የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን አንድም መኖሩን አያውቁም። ሌላም እንዲረጋገጥ አይፈልጉም። ጋዜጣው(ከዚህ በኋላ ዕለታዊዎቹና ሳምንታዊው ጋዜጦች) ሙያዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት አቅም የፈቀደውን ጥረት እንዳደረገ እረዳለሁ።
የዴሞክራሲ ባህል ባልተወለደበት፣ባላደገበትና ባህሉ ባልሆነበት አገር መገናኛ ብዙኃን የራሳቸው ነፃነት እንዲኖራቸው መጠበቅ የዋህነት ይሆናል። አዲስ ዘመንና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የህትመት ውጤቶችን ከሌሎቹ የአገራችን የሚዲያ ተቋማት ነጥሎ ማሰብም ያስቸግራል።
መልካምና ደስ የሚያሰኘው ነገር የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ተስፋ ሰጪ የሆነ ዴሞክራሲን የሚለማመዱበትና ሕዝብ አገልጋይ የሚሆኑበት መንገድ ውስጥ መግባታቸው ነው። መንገዱ ሊያንገራግጭ ይችላል። የማይመቻቸው ተሳፋሪዎች ስለሚኖሩ። ሆኖም ፕሬስ መንግሥትን ጭምር የሚተች ተቋም ሆኖ መውጣት የሚችልበት ዘመን ውስጥ ገብቷል። አራተኛው የመንግሥት አካል መሆንም ይችላል።
ጋዜጣው ሕዝብን አንቅቷል። አስተምሯል። የዕውቀት ምንጭ ሆኖም አገልግሏል። አራት ነጥብ። ዘመናትን በተሻገረው አገልግሎቱ የመረጃ ምንጭ፣መማሪያና መዝናኛ ነበር። ወጣ ገባ፤ደመቅ ፈዘዝ ያሉ ዘመናትን እያሳለፈ 80 ሲሞላው።
የ’’ታላላቆች’’ ቤት
በኢትዮጵያ የህትመት መገናኛ ብዙኃን ታሪክ ቀዳሚ ሆኖ የዘለቀውና በህትመት ውጤቶቹ ትውልዶችን የቀረጸው ጋዜጣ ታላላቅ ጋዜጠኞችና ደራሲያንን ያወጣ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል። ጳውሎስ ኞኞ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣በዓሉ ግርማ ፣ደምሴ ጽጌ፣ሙሉጌታ ሉሌ፣መርስዔ ኀዘን አበበ፣ጌታቸው ሰናይና ከበደ በየነን መጥቀስ ይቻላል። የጥንቶቹን ትተን ማለት ነው። እነዚህን ኢትዮጵያውያን ያየ ጋዜጠኝነት ለድርሰት መነሻ እንደሚሆን ያውቃል ብሎም ይነሳሳል ብዬ እገምታለሁ።
እዚህ ግባ በማይባል ደሞዝ፣በሙያ ፍቅር፣በመልካም ሥነ ምግባርና በሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ያገለገሉን ፀሐፍት ብቻ ሳይሆኑ፤የካርቱንና የፎቶ ባለሙያዎችም ናቸው። ምንም ይሁን ምንም በካርቱን ሥራዎቿ ማህሌትን፣በፎቶ ዘርፍ ደግሞ ዳኜና ፀሐይ የሚረሱ አይደሉም። ታላቅ አበርክቶ ነበራቸውና!!!
ጋዜጣው ዛሬ
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከጊዜ ጋር ለመራመድ የሚታትር ሆኖ ለመውጣት እየሰራ መሆኑን እረዳለሁ። በአዲስ መልክ የተቋቋመበት ዓዋጅ፣የተሰየመለት ቦርድ፣ማኔጅመንትና ሰራተኛው በአንድ ልብ ወደ ሥራ የገባ ይመስላል። የቀድሞ ስምና ዝናውን እየመለሰም ይመስላል።
ተቀባይነትና ትርጉም ያላቸው ሥራዎች በማቅረብ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ተቀባይነት ያላቸው ሥራዎች ይዞ መውጣት ጀምሯል። ተወዳዳሪ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል።
በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን በኩልም በተለይ በፌስ ቡክ ያለ ስስት ሥራዎቹን ይዞ ይመጣል። ተደራሽነቱንና ተወዳዳሪነቱን እያሳየ ነው። 24 ሰዓትን ሳይጠብቅ በየደቂቃው ዜና መምጣቱ ከዘመኑ ጋር እየተጓዘ መሆኑን ያሳያል። በዘመኑ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ ለማድረስ አንዱን መንገድ ጀምሮታል። ይበል ያሰኛል።
ሌላው በሲዳምኛና በትግሪኛ ቋንቋዎች የጋዜጦች ህትመት መጀመሩ አንድ እርምጃ ወደፊት ነው። በሶማሊኛ ቋንቋ የታሰበው ሲታከልበት የመረጃ ሰጪነት፣የአስተማሪነትና የማዝናናት ተግባራት በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች በማቅረብ ተደራሽነቱን ያሳድጋልና መልካም ነው እላለሁ።
ቀጣዮቹ ተግባራት
ጋዜጣው የሕዝብ ልሳን መሆን ይኖርበታል። መንግሥትና ሕዝብን በአግባቡ የሚያገናኝ ድልድይ ሆኖ በገለልተኝነት መስራት አለበት።
ሁሉንም አካላት ሙያዊና ገለልተኛ ሆኖ ለማገልገል ሙያዊ ብቃቱ ከፍ ያለ፣በመረጃ ሰጪነት፣ በአስተማሪነትና በአዝናኝነት የምንመርጠው ሚዲያ ሆኖ መውጣት ይገባዋል።
ሕዝብን አገልጋይ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም የህትመት ውጤት ሆኖ መገኘት ይገባዋል።
የጋዜጣው ተደራሽነት የአገሪቱን አራቱንም አቅጣጫዎችን የሚዳስሱ ተጨማሪ ቋንቋዎችን ማካተት ይኖርበታል።
ዘመኑን መመጠን
አንድ ምዕተ ዓመት ለመድፈን እየተንደረደረ ያለው አንጋፋው ጋዜጣ ከእንግዲህ ጉዞው ወደ ተቀናጀ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት (media convergence)እያመራ በመሆኑ በይዘትም በጥራትም ተመራጭ ሆኖ መውጣት ይጠበቅበታል። የህልውና ጉዳይም አለው።
የሽያጭ ገቢና ወጪ ያለመመጣጠን ፣ወጪ ቆጣቢ ባልሆነ መንገድ መሥራት፣ትርፋማ ያለመሆንና መሰል ችግሮች ፈተናዎቹ እንዳይሆኑ ብቁ ማኔጅመንትና ብቃትና ጥራት ያለው የሰው ኃይል እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይዞ መገኘት ይጠይቃል።
ባህላዊ የሚሆነው ጋዜጦችን አትሞ የመሸጥ ዘመን እያበቃ ከመሆኑ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ብሎም የኦዲዮ፣ቪዲዮና የጽሁፍ ሥራዎችን አቀናጅቶ መከወን መልካም አጋጣሚ ሆኖ የመምጣቱን ያህል፤ ፈተናዎችን ማለፍ ይጠይቃልና ጋዜጣው ብሎም ተቋሙ ለዚህ ዝግጁ ሆኖ እንደሚሰራ እምነቴ ነው።
ስሙን ከተግባሩ በማዋሃድ
እንደ ስሙ ዘመናዊቷንና አንድነቷን የጠበቀች ለዜጎቿ የምትመች ጠንካራ አገረ ኢትዮጵያን በታሪካዊነቱ፣በፈር ቀዳጅነቱ፣በተጠቃሽነቱ፣ገናና፣ተወዳጅና ተመራጭ እንደ ስሙ የሆነ ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን፣የሚዲያ ተቋምነትን የያዘ ዓለምን ያወቀና የተረዳ ‘’አዲስ ዘመን’’ በቀጣዮቹ ዓመታት እጠብቃለሁ። እኔ ዕድሜ ሰጥቶኝ ጋዜጣውን ትናንት ከዛሬ፣ዛሬን ከማስበው፤ ነገን ከማልመው ጋር ለማሳየት ሞክሬያለሁ። መልካም የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ!!!መልካም ልደት!!!
ከብርሃኑ ተሰማ (አዲስ አበባ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013