የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማምጣት ብቻ ሳይሆን የት ዩኒቨርሲቲ ይደርሰኝ ይሆን? የት ይመድቡኝ ይሆን? የሚለው የተማሪዎች ፍርሃት የወላጆችም ስጋት ከሆነ ቆይቷል። የስጋቱ ነጸብራቅ ከሆኑት ወላጆች መካከል የቅርብ ወዳጄ አቶ አሸናፊ እንደሻው ይገኝበታል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ይህ ወዳጄ፤ ከሳምንታት በፊት ስልክ ደውሎ ሲያወራኝ ነበር የስጋቱ አካል መሆኑን ለመገንዘብ የቻልኩት። የመንታ ልጆች አባት የሆነው ወዳጄ አሸናፊ፤ ቀደም ሲል በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የወሰዱትን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ ማምጣታቸውን ደውሎ ነግሮኝ ነበር። ይኼንን ሲነግረኝ የነበረው ድምጸት ዛሬም ደጋግሞ ይሰማኛል። በወቅቱ በደስታ መንፈስ ተውጦ በመንፈስ ጥንካሬ ታጅቦ “አኮሩኝ እኮ” ነበር ያለኝ። የወዳጄን ደስታ ከጥረቱ፣ ለቤተሰቡ ካለው ክብርና ፍቅር አኳያ እያሰብኩ በሀሴት ተሞልቼ ነበር የተካፈልኩት። ይህ ወዳጄ በልጆቹ መንታነት ሁሌም ይገረማል። በትምህርታቸው ጉብዝና ሁሌም ይደነቃል፤ ይመካል፣ ይኮራል። ከኩራቱ መለስ ሲል በዛሬ መሽቶ መንጋት የሚወለደውን ነገን ሁሌም በተስፋ ያልማል።
በወጣትነቱ የወለዳቸውን ልጆቹን፤ ሲያሳድጋቸው የአባትነት ክብርን፣ የወንድምነት ፍቅርን፣ የጓደኝነት ቀረቤታን በተላበሰ መልኩ ባሳደጋቸው መንታ ልጆቹ ያረገዘው መንታ ተስፋ ሊወለድ እንደቀረበ ይሰማዋል። ኡደቱንም በደስታ ያስተናግዳል። በተስፋ ተቀብሎ ይሸኛል። ይህ ወዳጄ የዩኒቨርሲቲ ድልድል ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሲደውልልኝ ልጆቹ በከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናቸው ከፍተኛ ውጤት ማምጣታቸውን በገለፀልኝ ድምፀት ልክ አልነበረም። በነበረን የስልክ ጭውውት ደስታው መሰረቁን በሚያሳብቅ ድምፀት፤ ልጆቹ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የደረሳቸው መሆኑን ነገረኝ። አሸናፊ የዩኒቨርሲቲዎቹን ስም አስከትሎ በመግለጽ፤ “ይህ መሆኑ አይከፋም፤ ዩኒቨርሲቲዎቹ ክልል ላይ የሚገኙ መሆናቸው እንጂ” ሲለኝ የስሜቱን መረበሽ የወለደው ምክንያት ተገለጠልኝ። ወዳጄ አሸናፊ ምን ሊለኝ እንደፈለገ ገባኝ።
በዩኒቨርሲቲዎች የነበሩ ግጭቶች ዛሬም ድረስ ወላጆችም ሆነ ተማሪዎች በስጋት ቀንበር ውስጥ እንደወደቁ ቢሰማኝም፤ የእርሱን ሀሳብ ተከትዬ “ታዲያ ምን ወሰንክ?” ስል ጥያቄዬን አስከተልኩ። ˝ከአዲስ አበባ ውጪ አምኜ ልጆቼን አልክም”። “ከቤተሰቤ ጋር የግል ኮሌጅ ከፍለን ለማስተማር ወስነናል” የሚል ምላሽ ነበር ያስከተለው። የአሸናፊን ስሜት ብጋራም፤ ከፍርሃት ወጥቶ ልጆቹን ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ቢልክ ብዙም ችግር ይኖረዋል ብዬ እንደማላስብ በመግለጽ ለማግባባት፣ በሀሳብ ለመሞገት፣ ለማሳመን ጥረት አደረኩ። ከአቋሙ አልተዛነፈም። ̋ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን አይተናል፤ ብዙዎች ለመማር ሄደው ሞተዋል። የትናንቱ ችግር ዛሬ የማይቀጥል ስለመሆኑ ዋስትና የለንም፤ ስለዚህ ለመላክም ፍቃደኛ አይደለንም ˝ሲለኝ ከአቋሙ የማይዛነፍ መሆኑን አረጋገጠልኝ። ይህ ሁኔታ በዩኒቨርሲቲዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ስጋት የመፍጠራቸውን ደረጃ እንዳብሰለስል ያስገደደኝ ነበር። የወዳጄ አሸናፊ አይነት ውሳኔ የብዙ ቤተሰቦች ከሆነ ውሎ ያደረ ሲሆን፤ ይህም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን የሰላም ጉዳይ አሳሳቢነቱ ጣሪያ ከመንካቱ ጋር ይያያዛል። በተለይ ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ስጋት ያረበበባቸው ከመሆኑ ጋር የሚቀዳው ስጋቱ፤ የአምናው ጥቁር ጠባሳ ዛሬ ላይ የሚሰማውን ፍርሃት ወልዷል። በ2012 ዓ.ም በሀገሪቱ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች 22ቱ ግጭት ያስተናገዱ መሆኑን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ዩኒቨርሲቲዎች በፖለቲካ እና በዘር ቆጠራ ተጽዕኖ ስር በመውደቅ፤ ምክንያት አልባ በሆነ መልኩ ከፀብ አልፈው ወደ ሞት መናኸሪያነት እስከ መለወጥ የደረሱባቸውን አጋጣሚዎችን እናስታውሳለን። በተቋማቶቹ የሚከሰቱ ግጭቶች የወለዱት ስጋት ተማሪዎች ከትውልድ ቀያቸው ርቀው ለመማር ፍላጎት እንዳይኖራቸው አድርጓል፤ ወላጆችም ልጆቻቸውን አምነው ለመላክ ድፍረት አሳጥቷል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰሞኑ አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከመጪው ምርጫ በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እንደሚገቡ አስታውቋል። በየዩኒቨርሲቲዎቹ ሲከሰቱ ከነበሩ ግጭቶች በመነሳት ወደ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የሚገቡ በርካታ ተማሪዎች ወደተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት ፍርሀት ውስጥ እንደሚገኙ ይሰማል። ከምደባ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ካቀረቡ 23 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከልም ከ1 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ የምደባ ማስተካከያ የተደረገላቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ ማስታወቁ ይታወሳል። በዚህ ደረጃ ከምደባ ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች የመወለዳቸው አንዱና ዋነኛው ምክንያት በዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ ተደጋጋሚ ግጭቶች የወለዷቸው ስለመሆኗቸው መጠርጠር አይቻልም። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አቶ አሸናፊ እንዳሻው አይነት ወላጆች ደግሞ ከአምናው ጥቁር ጠባሳ ዛሬ ላይ በተወለደ የፍርሃት መንፈስ ልጆቹን ወደ ዩኒቨርሲቲ አልክም የሚል ውሳኔ ላይ የደረሱ ብዙዎች ናቸው።
ስለዚህ መንግስትም ሆነ ዩኒቨርሲቲዎች በማህበረሰቡ ዘንድ በዚህ ደረጃ የተፈጠረውን ጥርጣሬ ማስወገድ፣ የታጣውን እምነት መመለስ የሚያስችል ስራ መስራት የሚገባ መሆኑን ያሳያል። የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አድርገናል! የሚሉ የጋዜጣዊ መግለጫዎች ጋጋታዎችን ሳይሆን ተጨባጭ ስራዎችን ሰርቶ ማሳየትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ መውሰድ ይገባል። ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሚሰጥ ስለመሆኑ በተግባር አሳይቷል። “አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ” የሚሰኘው ይህ “የጎንደር የቃል ኪዳን ቤተሰብ̋ ፕሮጀክት” በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ነበር ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው። በጎንደር ከተማ አስተዳደር እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን ከምርምር ማዕከልነት ወደ ፀብ ማእከልነት መሸጋገራቸው ፕሮጀክቱ ለመወለዱ ምክንያት ሆኗል። በዚህ መሰረት በ2012 የትምህርት ዘመን ከሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት የመጡ አምስት ሺህ ተማሪዎችን በመቀበል ነበር የተጀመረው። ተቋሙ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች የደኅንነት ስጋት እና የቤተሰብ ናፍቆት በማስታገስ ረገድ በታየው ተጨባጭ ውጤት ብዙዎች ከመደነቅ ባለፈ፤ ልዩ አድናቆትን ችረውታል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር የነበሩት ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በተመሳሳይ የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው አድናቆታቸውን ገልፀው ነበር። ፕሮፌሰር ሂሩት፤ ”ይህን የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚያጠናክር ተግባር እንደ አንድ ጥሩ ልምድ በመውሰድና በማሻሻል ፕሮጀክቱ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል“ ሲሉ ቃል ገብተው ነበር። በዚህ ደረጃ አድናቆትን ያገኘው ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በመደረጉ ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ያስቻለ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ በሀገሪቱ ከሚስተዋለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞም የተማሪዎቹ ወላጆች በጎንደር ልጆቻቸውን ከሚቀበሏቸው ቤተሰቦች ጋር ተከታታይ ግንኙነት እንዲኖራቸውና እፎይታ እንዲሰማቸው ማድረግ ያስቻለ መሆኑን ተነግሯል። በተጨማሪም ተማሪዎች ከእውቀት ግብይት ባለፈ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ውጤታማ እንዲሆኑም አድርጓል። ወላጆቹ ደግሞ የተረከቧቸውን የቃል ኪዳን ልጆች በትምህርታቸው እንዲጠነክሩ ከማገዝ ባሻገር ስለ አብሮነትና አንድነት እንዲሁም የሀገር ፍቅር በማስተማር ትልቅ ተግባር መከወን ያስቻለ ሆኗል። በዘንድሮ አመት ዩኒቨርሲቲውን የሚቀላቀሉ አዳዲስ ተማሪዎች በጎንደር ከተማ ቤተሰብ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን አስታውቋል። ይህ ፕሮጀክት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚነሱ ግጭቶን መከላከል የሚያስችል ስለመሆኑም በተጨባጭ ታይቷል።
“በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተግባራዊ የተደረገውን ፕሮጀክት ሀገር አቀፍ ይደረጋል” ሲሉ የቀድሞዋ ሚኒስትር ቃል ቢገቡም እስካሁን የታዩ እንቅስቃሴዎች አለመኖራቸው ግን ያስተዛዝባል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻችን ያረበበውን የጸጥታ ስጋት ለማክሰም የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ፕሮጀክት ሀገራዊ መልክ ሰጥቶ በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል። ይህ መሆኑ እንደ ወዳጄ አሸናፊ አይነት ወላጆችና ተማሪዎች ከስጋት ማውጣት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩትን የሀሰት ትርክቶችን በመናድ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር፣ ጥርጣሬዎችን ማስወገድ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር እንዲሁም ለብሄራዊ መግባባት መንደርደሪያ በመፍጠር ረገድ ትልቅ አቅም ለመፍጠር ያስችላል የሚል እምነት ያሳድራል። ስለዚህ ˝የጎንደር የቃል ኪዳን ቤተሠብ̋” ፕሮጀክትን በሀገር አቀፍ ደረጃ (በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች) ተግባራዊ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ይገባል ባይ ነን።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013