ብድር በንግዱ ዘርፍ ለተሰማራ ማንኛውም ዜጋ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። እንኳን በግልና በቡድን ለሚንቀሳቀስ የንግዱ ማህበረሰብ ቀርቶ መንግሥትም አብዛኞቹን የልማት ሥራዎች የሚያከናውነው በብድር ከመሆኑ አንፃር አስፈላጊነቱ ብዙዎችን ያስማማል። በዋናነት ደግሞ ብድር ከአምና ጀምሮ በሀገሪቱ በተጀመረው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር በመነቃቃት ተሳትፎውን አጎልብቶ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ለሚገኘው በቡናው ዘርፍ ለተሰማራ የንግድ ማህበረሰብ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ታምኖበታል።
ብድር ከግለሰብ ጀምሮ ቡድኖችን፤ ማህበረሰቡን ብሎም ሕዝብንና ሀገርን እስከ መጥቀም ይዘልቃል። ፋይዳው አምና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሀገራችን ከመጣው የባለምርጥ ጠዓም ቡና ቅምሻ ውድድር አንፃር ሲቃኝ በብዙ ምክንያቶች መጉላቱን መካድ አይቻልም። ውድድሩን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትም ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። በዓለም የቡና ታሪክ የቡና መገኛነቷ የተመሰከረላትን ኢትዮጵያን አግልሎ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት እንደነብራዚልና ኮሎምቢያ ያሉ ቡና አምራቾችን ጨምሮ ዘጠኝ የላቲን አሜሪካ ሀገሮችን እንዲሁም ከአፍሪካ ብሩንዲና ሩዋንዳን በድምሩ 11 ሀገሮችን ብቻ ሲያሳትፍ ከመቆየቱ አኳያ ውድድሩ ወደኢትዮጵያ እንዲመጣ የተደረገው ጥረትም ቀላል አልነበረም።
ውድድሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግ በዘለለ በተለይ በቡና ዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦችን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደርጋል። ከዚህ በፊት የማይታወቁ የቡና ዝርያዎችን ለማግኘትና የተሻለ ጠዓም ያላቸውን ቡናዎች ለመምረጥና ዕውቅና በማሰጠት በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ያግዛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናዎች በዓለም ገበያ ለማስገባት ዕድል ይፈጥራል።
የሀገር ገፅታን በመገንባትና ሀገሪቱ ካደጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ዕድል በመስጠትም ውድድሩ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። ይሁንና የባንኮች የብድር አቅርቦትና አሰጣጥ ስርዓት ይሄንን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ታሳቢ እንዳላደረገ የንግዱ ማህበረሰብ ክፍሎች ይናገራሉ። አቅርቦቱም ሆነ አሰጣጡ ችግር እንደነበረበትና እጥረትም እንደሚታይበት ይጠቁማሉ። በተለይ በዘርፉ ቡና በማቅረብ ለተሰማራው የንግድ ማህበረሰብ አሁን አሁን ችግሩ የሚፈታበት አሰራር እየተዘረጋለት ይገኛል። ከለውጡ ወዲህ ደግሞ መንግሥት የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡናን ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ይሁን እንጂ አሁንም ብድር በወቅቱ ከማግኘት ጀምሮ በባንኮች አሰራር በኩል ችግሮች እንዳሉ ይነገራል። ይህም ሥራውን በተፈለገው ልክ ከማከናወንና ለሀገሪቱም ለማስገኘት ከታሰበው የውጭ ምንዛሪ አንፃር ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እንዲሁም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ችግሩን ለመቅረፍ ቢሞክሩም በቂ ሆኖ አልተገኘም።
ቡናን ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡት ውስጥ ሩሙዳሞ እሸት ቡና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አንዱ ሲሆን አምና ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በተካሄደው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር ሁለተኛ በመውጣት አሸንፏል። የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አርሶ አደር ፓስተር ቦጋለ ወልደሐና እንደሚሉት በብድር አሰጣጥና አቅርቦት ማህበሩ ማበረታቻ አላገኘም። በመንግሥትና በግል ባንኮች በኩል ያለው የብድር አቅርቦትና አሰጣጥ ስርዓትም እምብዛም የሚያበረታታ አይደለም፤ ችግሩም አልተፈታም።
ከለውጡ በፊት ቡና አቅራቢው፤ ላኪውም ሆነ አብቃዩና ሌሎች በየደረጃው የተሰማሩ ክፍሎች በአብዛኛው ብድር በተገቢው ሁኔታ ባለመመቻቸቱ ቤታቸውን አስይዘው እስከ መበደር የሚደርሱበትና ለኪሳራ የሚዳረጉበት ሁኔታ ነበር። እስከ አሁን ዕዳ እየከፈሉ የሚገኙም አሉ። ማህበሩም የብድር ሂደቶችን ካጠናቀቀ በኋላ የገንዘብ ግሽበት ተፈጥሯል በሚል ብድር ተከልክሏል። በዚህም ምክንያት ከግለሰብ ተበድሮ ለመሥራት ተገዷል።
በእርግጥ ማህበሩ ከአዋሽ ባንክ ብድር አግኝቶ ብድሩን መልሷል። ዘንድሮም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰነ ብድር ወስዷል። ይሁንና ማህበሩ ሊያከናውናቸው ካሰባቸው ሥራዎች አኳያ ብድሩ በቂ አይደለም። ነጋዴው ብድሩን የሚፈልግበትና ባንኮች ብድሩን የሚሰጡበት ሂደትም አይገናኝም። ሥራው ከተጀመረና ከሁለት ወር በኋላ ሊያልቅ ሲል ብድር የሚለቀቅበት አግባብ ያልሆነ አሰራር ይታያል።
ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደውና በዚህ ወር ይፋ በሆነው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር አንደኛ የወጡትና ታምሩ ታደሰ ኃላፊነቱ የተወሰነ ቡና አቅራቢና ላኪ ባለቤት አቶ ታምሩ ታደሰ የፓስተር ቦጋለን ሃሳብ ይጋራሉ። እንደእርሳቸው ሃሳብ በዘርፉ የተሰማራው ነጋዴ ንብረት አስይዞ የሚበደርበት ቀድሞ የነበረው አሰራር ውጤታማ ስለማያደርገው ለብድር አይበረታታም። የተወሰኑ ባንኮች አሁንም ንብረት ካልያዙ ብድር የማይሰጡበት ሁኔታም አለ። በአሁኑ ጊዜም አሰራሩ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንና በባለድርሻ አካላቶች እየተሻሻለ መጥቷል። ይሁንና የአቅራቢዎች በብድር ዕጦት ችግር አሁንም አልተቀረፈም። ባንኮችም ይህን አሠራር ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። እየተሰራ ያለውን ሥራ በአካል መጥተው ካዩ በኋላ ብድር ቢሰጡና ከቡና ላኪው ጋር ቀርበው ቢወያዩ ይመረጣል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበሌ እንደሚናገሩት ከአርሶ አደር ቡና የሚገዛው በሁለትና ሦስት ወር የተወሰነ ጊዜ ውስጥ ከመሆኑ አንፃር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል። ነጋዴው ከአርሶ አደሩ ቡና በሚገዛበት ወቅት ብድሩን ማግኘት ይኖርበታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብድር ማግኘት ካልቻለም ለመሥራት ይቸገራል። በአብዛኛው ነጋዴው ብድሩ የሚደርሰውም የቡና ገበያ ካለፈ በኋላ ነው። ይህም ነጋዴው በወቅቱ እንዳይጠቀም ያደርገዋል። በመሆኑም ባንኮች ቡና አቅራቢዎች ብድር በሚጠይቁበት ጊዜ ብድሩን ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባቸዋል።
ከዚህ አንፃር ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በብርድ አሰጣጥና አቀራረብ ላይ ያሉ ችግሮችን እየፈታ ይገኛል። አቅራቢዎች፣ ላኪዎች፣ በቡና ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የሚፈልጉትን የብድር መጠን ሲጠይቁ ባለስልጣኑ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ለግል ባንኮች ያከፋፍላል። በዚህ መሰረት ከባንኮች ጋር በማገናኘት ደንበኞቹ ብድር ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓት ዘርግቷል። ብድሩን እንዲያገኙም ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በተለይ ደግሞ በብድር እጦት በብዛት የሚቸገሩት ቡና አቅራቢዎች በመሆናቸው ባለስልጣኑ ችግሩን ለመፍታት አቅራቢዎችን ከላኪዎች ጋር በማስተሳሰር ብድር በቀላሉ እንዲያገኙ የሚደረግበት አሰራር ተዘርግቷል።
በዚሁ አሰራር መሰረትም አቅራቢዎችን ከላኪዎች ጋር በማስተሳሰር ላኪዎች ለአቅራቢዎች ቅድመ ክፍያ በመስጠት ቡና ከአርሶ አደሮች ገዝተው ለላኪዎች ያስረክባሉ። ዘንድሮም በዚህ ትስስር ላኪውና አቅራቢው የብድር ችግሮችን እዛው እንዲፈቱ በማድረግ በመንግሥት ላይ ያለውን የብድር ጫና መቀነስ ተችሏል። መንግሥትም የውጭ የግብርና ምርቶችን በተለይም ቡናን ለመደገፍ በከፍተኛ ደረጃ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ይገኛል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013