የጋራ እሴት ጉዳይ አንገብጋቢ መሆኑ ይታወቃል። በተለይ “እሴት” ከሚለው በላይ “የጋራ” የሚለው ቃል (ጽንሰ ሀሳብ) ይበልጥ ሲያወዛግብ ይታያል፤ ይሰማልም። ይህም የሚሆንበት ምክንያቱ ብዙና ውስብስብ ቢሆንም በቀዳሚነት ግን “የእኔ አይደለም” “የእነሱ ነው”፤ አይ “የእነሱ አይደለም” “የእኔ ነው” ከሚል ፋይዳቢስና ፍሬ ፈርስኪ ክርክርና የተዳፈነ አተያይ የሚመነጭ መሆኑና “እኛ”ን ወይም “የእኛ ነው” የሚለውን አምርሮ የጠላ፤ በተለይ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ አግጥጦ ለእይታ የበቃ አክሳሪ (ግን ደግሞ ለእነ ሆድ አምላኩ አትራፊ የሆነ) የፖለቲካ ፋሽን ነው።
እርግጥ ነው በአንድ አገር ያለ ነገር ሁሉ የእኛ አይደለም። ለምሳሌ የእኔ ቤት (ካለኝ ማለት ነው) የእኔ እንጂ የሌላ ሰው ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ከኢኮኖሚ (መሥሪያ ገንዘቡ)፣ ባህል (አሠራሩ)፣ ቁስ (መሥሪያው – በተለይ በገጠር) እና የመሳሰሉት ግን የጋራ ሀብትና የጋራ እሴት፣ ባህል፣ ሥልጣኔ . . . ናቸው።
አንወሻሽና የዚህ “የጋራ እሴት” ጉዳይ ሁሌም አወዛጋቢ ሲሆን የሚታየው ከሌላ ሳይሆን በአብዛኛው ከግንዛቤ ማነስ ነው። ለምሳሌ ምግባችን እንጀራ በወጥ ነው። ይህን የጋራ እሴት አይደለም ብሎ የሚከራከርን ሰው ከየትኛው ልንመድበው እንችላለን? የግድ መድቡት ከተባልን ልንመድበው የምንችለው ያለ ምንም ጥርጥር ወይ ካውቆ አበድ ነው፤ አልያም ሆን ብሎ ለአላማው ሲል እየታገለ ያለ . . . ነው።
የጋራ እሴት ጉዳይ ሲነሳ ብዙ ጊዜ አጥቦ ማየት የተለመደ ቢሆንም የጋራ እሴት ድንበሩ ሰፊ፤ ዓለም አቀፍ ነው። ምድርን ሙሉ ቢዞሩ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ብዙ ነው። ለሁሉም ሰው እኩል አስፈላጊ፣ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ የጋራ እሴቶች (ቢጠኑ) ሞልተዋልና ይህንንም እያሰብን ለማለት ነው። ምሳሌ ከተባለም፤ “ስፖርት” ማለት ይቻላል።
ወደ ርእሰ ጉዳያችን፤ ወደ “ምርጫ – አንዱ የጋራ እሴት” ስንመጣም ይሄውና የዓለም የጋራ እሴት ሆኖ ነው የምናገኘው። በተለይም ዲሞክራሲ ለመለመ፣ አበበ፣ ጎመራ ወዘተ በሚባልባቸው አገራት ሁሉ ይህ ምርጫና የምርጫ ጉዳይ (ከእነ ስንክ ሳሩ) አለና ተግባሩም ሆነ ሂደቱ፤ ተሳትፎውም ሆነ አላማው አንድ እንደ መሆኑ መጠን እሴትነቱን የዓለም ያደርገዋል – “ምርጫ – አንዱ የጋራ እሴት” ብለን ስንነሳም ዋናው ምክንያታችን ይሄው ነው።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ቢኖር ስለ ምርጫ ስናወራ ስለ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እያወራን መሆኑን፤ ስለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስለ ህዝብ ተሳትፎ፤ ስለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፤ ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሯዊ (ብዙዎች ደስ ባይላቸውም)፣ ፖለቲካዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰብዓዊ . . . መብቶች ሁሉ እያወራን ነውና ርእሰ ጉዳያችን ቀላል አይደለም ለማለት ነው።
ዴሞክራሲ ባህል (ያው እሴት ማለት ነው) በሆነባቸው አገራት በምርጫ ምክንያት ደም መፋሰስ ነውር፣ ፀረ ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ፣ አደናቃፊ ወዘተ ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም። የዚህ አይነቱ ተግባር “የአውሬ ተግባር” ተብሎ ከተፈረጀ ጊዜው ሰንባብቷል። (ነጮቹ እኮ የእኛን ምርጫ “የአፍሪካ ምርጫ” (African election) ነው የሚሉት። ተግባባን??)
ምርጫ የጋራ እሴት ነው ብለን ተነስተናል። ይህን ይዘን ከተነሳን ጉዳዩን ትንሽ ገፋ አድርጎ ማየት ይገባናል።
ምርጫን የጋራ እሴት የሚያደርጉት በቀዳሚነት ለጋራ አገራችን የጋራ መንግሥት ለመመስረት የምናደርገው ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በመሆኑ፤ በዚህም ውስጥ ሂደቱ የጋራ ህዝባዊ ተሳትፎንና እንቅስቃሴን መፈለጉ፤ የጋራ ስሜትን፣ አስተሳሰብን (ምንም እንኳን በድምፅ/ካርድ ብልጫ ቢወሰንም) ባቀናጀ መልኩ መከናወኑ፤ ከሁሉም በላይ የሁሉም የበላይ የሆነውን የሀገር ግንባታ (ኔሽን ቢውልዲንግ) ተግባርን ማስኬድ የሚቻለው በዚሁ፤ ዴሞክራሲን ባህል (እሴት) በማድረግ በመሆኑ ወዘተ ወዘተ ነው። በመሆኑም ምርጫ የጋራ እሴት ነው ማለት ነው። ይሁን እንጂ ደም አፋሳሽ፤ ሀብትና ንብረት አውዳሚ፤ የግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሥልጣን ጥም ማርኪያ፤ ወይም ከጠላቶቻችን ሳንቲም መለቃቀሚያና የሽቀላ ተግባር ከሆነ ዘፋኙ ሁሉም ዜሮ ዜሮ እንዳለው ብቻ ይሆን ከዜሮ በታች ኔጌቲቭ ነውና እጅጉን ያሳስባል፤ ያሳዝናልም።
ምርጫን ወደ ጋራ እሴትነት ማሳደግ እየተቻለና ያ ካልተደረገ፤ በቦታው ተራ ሽቀላ፣ ፋይዳቢስ የዘርም ይሁን ነገድ ስሜት ከነገሠ፣ ምርጫው “እንከን የለሽ” ይሆናል ተብሎ እየተጠበቀ “አበቅ የለሽ” እንኳን መሆን ካልቻለ እውነትም ሁሉም ዜሮ ዜሮ … ነውና፤ በዚህ አይነቱ በእውቀት ላይ ያልተመሠረተ ምርጫና ሂደቱ እንኳን ዴሞክራሲን ባህል፤ ከዛም እሴት ለማድረግ ቀርቶ ሁሉንም ነገር ወደ ኋላ ከመውሰድ አይመለስምና ባለድርሻዎች ሁሉ – መራጭ፣ አስመራጭ፣ ተመራጭ – ከወዲሁ ከልብ ከልብ ልናስብበት ይገባል።
እስከ መቼስ “ዴሞክራሲ ባልዳበረባቸው አገሮች . . .” እየተባልን፣ እስከ መቼስ “የአፍሪካ ምርጫ . . .” እየተሰኘን፣ እስከ መቼስ የዘር ፖለቲካ ቅኔን እያቀነቀንን እንዘልቀዋለን? የሚለው ራስ ምታት የማይሆንብን “ዴሞክራቶች” እንኳን ካለን “ለህዝብ ጥቅም ሲባል . . .” እንደተባለው ለህዝብ ጥቅም ስትሉ ትወጡት ዘንድ “በዴሞክራሲ አምላክ” (በሰለጠኑት አገራት፣ ለምሳሌ ግሪክ – ዴሞክራሲ አምላክ አለው) ትለመናላችሁ እንደተባለው ሁሉ እኛም እንለምናለን።
የዘንድሮው ምርጫ በሁለት መልኩ ይጠበቃል። በሁለት መልኩ ይጠበቃል ስንል ደግሞ በሁለት ወገኖች ማለታችን ሲሆን፤ ሰላም ወዳዱና ሸቃዩ።
ነፍሱን ይማረውና ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በየትኛው ግጥሙ (ወይም ትያትሩ) ይሁን አላስታውስም “እፍ አንቺ መብራት ጥፊ፣ መድረክ ላይ ኩስ ከምትተፊ . . .” የሚለው አባባል (ጉደኛ አገላለፅ) ነበረው። እኛም እንላለን፤ እፍ ጥፉ በዲሞክራሲ ስም መድረክ ላይ . . . .
በዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን፣ አኩሪ ባህላችንን፣ ጨዋነታችንን፣ የዴሞክራሲና ጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤታችንን የምናሳይበት ይሆን ዘንድ የሁላችንም ምኞት ነው።
ዴሞክራሲ ባህላችን፤ ከዛም አልፎ ዘላለማዊ እሴታችን ሆኖ ለማየት ያብቃን!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013