ሀገራችን በታሪኳ በዚህ ደረጃ ገጥሟት በማያውቅ ሁኔታ፤በውስጥ ባንዳዎችና ተላላኪዎች በአራቱ ማዕዘናት ተወጥራ ፤ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የተነሳ ግብጽ ከአሻንጉሊቷ የሱዳን ጁንታ ጋር በተነሳችብን በዚህ ቀውጢ ሰዓት ፤ የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዥ አፈር ልሶ ለመነሳት በሚልፈሰፈስበት ፤ አሸባሪው ሸኔና የጉምዝ ወንበዴ ንጹሐንን በሚገድልበትና በሚያፈናቅልበት ፤ ሱዳን ድንበራችንን በግብጽ አይዞሽ ባይነት በወረረችበት ፤ አለምአቀፉ መገናኛ ብዙኃንና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተብዬዎች ከሱዛን ራይስ ጭፍራዎች የባይደን አስተዳደር ዲፕሎማቶች እና ከአሸባሪው ህወሓት አራጋቢዎች (lobbyists) ጋር ግንባር ገጥመው ሀገሬን መቆሚያ መቀመጫ ባሳጡበት ፤ ሉዓላዊነቷና የግዛት አንድነቷ ተደፍሮ ባለበት በዚህ ጭንቅ ጥብ ወቅት ልዩነቱን አቆይቶ በአንድነት መቆም የማይችል የሀገሬ “ልሒቅ” ከጃርት ያንስብኛል ።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ ማንነትን ኢላማ አድርገው የተፈጸሙ ጥቃቶች ፤ በማንነት ላይ የተዋቀረው ተዋጥኦ ፤ በሀሰተኛ መረጃ የተለወሰው የሴራና የደባ ፖለቲካ ፤ የለውጥ ኃይሉ ጥቃቶችን ቀድሞ መከላከል ፣ ተከስተው ሲገኙም ቶሎ ደርሶ ማስቆም አለመቻሉና ሌሎች ደራሽ ምክንያቶች ተደማምረው ልሒቃኑን ሆደ ባሻና አኩራፊ ቢያደርገውም በእናትና በሀገር ስለማይጨከን ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ልሒቅ ኩርፊያም ሀገር ስትኖር ነውና በሚል በዚህ ክፉ ቀን ከጎኗ በመቆም አለኝታነቱን ያረጋገጠ ሲሆን አብዛኛው ግን ዛሬም በአንድነት መቆም ተስኖታል ። ዛሬም ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠር የሚተጋ ፤ ቀን እንደጎደለባት አይቶ ይሄን ጊዜ ነው እጇን መጠምዘዝ ብሎ የተነሳ እና ሀገራዊ ጥሪ ሲቀርብለት እግሩን እየጎተተ ያለው ልሒቅ ብዙ ነው ። ሆኖም ይህ አደጋ ተገልጦላቸው በዲያስፖራም ሆነ በሀገር ቤት በዚህ ክፉ ቀን ከሀገራቸው ጎን የቆሙቱ ሳይዘነጉና በልካቸው እውቅና ሳይነፈጉ ።
ነገሩ ወዲህ ነው በአንድ እጅግ ቀዝቃዛ በሆነ ክረምት በርካታ እንስሳት በቆፈን አለቁ ። ይህን የታዘቡ ጃርቶች ( ዣርቶች ) ሰብሰብ በማለት በአካላቸው በትንፋሻቸው ሙቀት በመፍጠር ቆርጦ የሚጥለውን ቅዝቃዜ ወደ ሙቀት ቀየሩ ። በዚህም የሚቆረጥመውን ቅዝቃዜ ተከላከሉ ። ነገር ግን እሾሃቸው /ወስፌአቸው/ እየወጋ ያሳምማቸው ፣ ያደማቸውና ያቆስላቸው ጀመረ ። በእሾሀቸው የተነሳ እንደገና መራራቅ ሲጀምሩ ቅዝቃዜው አንዳንድ እያለ አመናመናቸው ። አሁን ያላቸው አማራጭ የእሾሃቸውን ህመም በመቻል በህይወት መኖር አልያም እሾሀቸውን በመፍራት በመራራቅ በቅዝቃዜ አንድ በአንድ ማለቅ ሆነ ።
ቁጭ ብለው ከተነጋገሩ በኋላ እሾሃቸው የሚያስከትለውን ቁስልና ህመም ታግሰውና ጥርሳቸውን ነክሰው ችለው ክፉውን ቀን ሰብሰብ ብለው በአንድነት አንተ ትብስ አንቺ ትብሺ ተባብለው በአንድነት አንዳቸው ለሌሎች ሙቀት በመሆን ፤ በትንፋሻቸው እየተሟሟቁ ክፉውን ቀንና ሞትን ለማለፍ ተስማሙ ። የተዋጣለት ማህበራዊ ግንኙነት ማለት እንከን ድክመት ከሌለባቸው ሰዎች ጋር መኖር አይደለም ።የአብሮነት ጥበቡ እያንዳንዱ ሰው ፍጹም አለመሆኑን ተረድቶ ተቻችሎና ተከባብሮ አብሮ መኖር መቻሉ ላይ ነውና ።
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሻውያን /ሺአውያን / millennials የሚላቸው እኤአ በ1980ዎችና 90ዎቹ የተወለዱ በአሁኑ ዘመን ዕድሜያቸው በ30ዎቹ ለሚገኙ ወጣቶች በተለይ ለከተሜዎች “ ጃርት “ን ምን አልባት ለማያውቁ የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ፤ “ እሾኻማ የዱር አውሬ ፣ ካፍንጫው በቀር በጠጉር ፈንታ ኹለንተናው ነጭና ጥቁር ወስፌ የኾነ ጠላት በመጣበት ጊዜ እሾኹን የሚያራግፍ ።
“በዚሁ መዝገበ ቃላት የመጣጥፌ ዋና ቃል የሆነውን “ልሒቅ “ ደግሞ ፤ አዋቂ ፣ ቁንጮ በማለት ሲበይነው ፤ የእንግሊዘኛው ሜሪያም ዌብስተር ደግሞ ፤ elite ወይም “ልሒቅ “ የሚለውን ቃል ፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠውና ባለጠጋ የሆነ ፤ የሰመረለትና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነ ሰው ሲል ይተረጉመዋል ። ለመጣጥፌ ይህን ብያኔ ሰፋ አድርጌ በመመልከት እጠቀምበታለሁ ። ከዚያ በፊት ብያኔው አንጻራዊ መሆኑን ማለትም እንደየ ሀገራቱ ፣ እንደየ ዘርፉና እንደየ አካባቢው የሚለያይ መሆኑንና ሁሉም የየራሱ ልሒቅ እንዳለው ልብ ይሏል ። ዩኒቨርሲቲ ፣ ፖለቲካ ፣ ሀይማኖት ፣ መዝናኛ ፣ ስፖርት ፣ ኪነ ጥበብ ፣ ሳይንስ ፣ ሕክምና ፣ ምህንድስና ፣ ሕግ ፣ ጋዜጠኝነት ፣ ወዘተረፈ የየራሳቸው ልሒቅ አላቸው ። ከሀገር እስከ ቀዬ ድረስ በየደረጃው ልሒቅ አለ ። ሆኖም አካዳሚያዊ ፣ የሕዝብ እና የፖለቲካ ልሒቃን የመጣጥፌ መሰናዘሪያ ናቸው ።
በሰሞነኛውም ሆነ በቀደመው አክራሞታችን ላይ ተመስርቼ ልሒቃንን ከእነዚህ ጃርቶች ሥራና ግብር ጋር አነጻጽራለሁ። ከ13ኛው መክዘ እንኳ ብንነሳ የመጀመሪያና ፋና ወጊ ሊባል የሚችለውን ታላቁን የሰውን ልጅ የነጻነት ሰነድ ማግኛ ካርታን ያበረከተልን የዘመኑ ልሒቅ ነው ። ይሄንኑ አበርክቶ አምርሮ ይቃወመው የነበረውም የገዢው መደብ ልሒቅ ነው ። የዘመኑ የእንግሊዝ ልሒቃን ጃርቶች ወስፌአቸው የሚያመጣውን ህመም ተቋቁመው ክፉውን ቀን እንዳለፉት ሁሉ እነሱም ልዩነታቸውን በማክበር አልፈውታል ። ሶሻሊዝምንና ኮሚኒዝምን በአንድ በኩል ነጻ ገበያንና ዴሞክራሲን በሌላ በኩል ያልነበረው ይሄው ልሒቅ እንጂ ሕዝብ አይደለም ። የምዕራቡ ዓለም ዜጎችም ሆኑ የሶቬት ሕብረት ሕዝብ የርእዮተ አለሙ ተራ ወታደር እና ሰለባ ሆኑ እንጂ ኋላ ላይ የተከሰተውን ቀዝቃዛውን ጦርነትም ሆነ የበርሊንን ግንብ አፍርሶ ምድራችንን ከቆፈን የገላገላት ሌላ ማንም አይደለም ልሒቁ ራሱ እንጂ ። እንዲሁም ዘረኝነትን ፣ አክራሪነትንና ሽብርተኝነትን ለአለማችን ያስተዋወቀውም አለማዊው ፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ልሒቅ እንጂ ሕዝቡ አይደለም።
1ኛውን ፣ 2ኛውን ፣ 3ኛውንና 4ኛውን የኢንዱስትሪ ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የሰው ሰራሽ ክህሎት የፈጠረው ያስፋፋው ልሒቁ ነው። ከዚህ በተጻራሪ የ1ኛውን፣ የ2ኛውን ጦርነት የቀሰቀሰው ልሒቁ የተዋጋው ህይወቱን አካሉን የገበረው ደግሞ ተራው ዜጋ ነው ። በእያንዳንዱ ሀገርና ሕዝብ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ የልቦና ውቅር ቀረጻ የልሒቃን ተፅዕኖና አበርክቶ ከፍ ያለ ነው ። እንደተቀረው ዓለም ሀገራችንን ጠፍጥፎ በመስራትም ሆነ መልሶ አፍርሶ ከዜሮ በመነሳትም የልሒቃኑ ሚና ከፍ ያለነው ።
ከዘመነ መሳፍንት የስልጣን ሽኩቻ ፤ ከቱርክ ወረራ በኋላ የቋራው ካሳ ሀይሉ ተቀናቃኞቹን ሁሉ ድል በመንሳት እኤአ በ1855 አፄ ቴዎድሮስ ተብሎ ከነገሰበት እስከ ደርግ ወደ ስልጣ መምጣት ያለውን ዘመን ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ጊዜ አድርገው ይወስዱታል ። ይህ የዘመናዊዋ ኢትዮጵያን ልሒቃንን ነው እኔም ለመጣጥፌ መነሻ ያደረ ግሁት ። ምንም እንኳ ስንክ ሳሯ የበዛ ቢሆንም” ዘመናዊዋ “ኢትዮጵያ ዛሬ ድረስ እየተፍገመገመች አለች ። ወደፊትም ወጀቡንና ውሽንፍሩን ተቋቁማ ትኖራለች ። ከዘመናዊ ኢትዮጵያ ጀምሮ ሀገራች ኢትዮጵያ የመጣችበትን መንገድ የተተለመው በልሒቃን ነው ። ዘውድ በኪሱ ይዞ እየዞረ በየአካባቢው ራሱን እያነገሰ የኢትዮጵያ አንድነት ያዳከመው ፣ አንድነቷ የተረጋገጠ ዘመናዊ ኢትዮጵያን የመገንባት የአፄ ቴዎድሮስን ህልም ያጨነገፈው ፤ የአፄ ዩሐንስን አዲስ አይነት የሀገረ መንግሥት ምስረታ በአጭር የቀጨው እና ንጉሱን ለህልፈት
ያበቃው ፤ የዘመኑ ልሒቅ እንደ ጃርት ወስፌውን ችሎ በአንድነት ባለመቆሙ ነው ። የዘመኑ ልሒቃን ወስፌዎች የስልጣን ሽኩቻ ፣ ግዛትን ማስፋፋት ፣ ግብር አለማስገባት ፣ ከሀገር አንድነት ይልቅ የራስን ዝና ማስቀደም እና አውራጃዊነት ናቸው ። የዛሬው ልሒቅ ወስፌ ደግሞ ዘረኝነት ፣ ዳር ቆሞ ተመልካችነት ፣ ፍርሀት ፣ ራስ ወዳድነት ፣ ወዘተረፈ ናቸው ። በሌላ በኩል በዚህ ሁሉ ዘመን ሀገር በነጻነት ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ያደረገው ፣ አኩሪውን የአድዋ ድል የተቀዳጀው ፣ የዛሬውን ቅርጸ ሀገረ መንግሥት ያቆመው ፣ ስዩመ እግዚአብሔር ዘ ነገደ ይሁዳ እያለ በሀገሪቱ ለግማሽ ክፈለ ዘመን ያህል የንጉሳዊ አገዛዝ የጫነው ፤ የራሷ ፊደል ፣ የዘመን አቆጣጠር ፣ ስነ ጹሑፍ ፣ ቋንቋ እንዲኖራት ያደረገው ፤ የአክሱምን ስልጣኔና ኃያል መንግሥት ተክሎ የኖረው ፤ ግዛቱ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ፣ ሱዳን አልፎ አስፋፍቶ የነበረው ጥንታዊ ዘመናዊ መንግሥት የመሰረተው ፤ የአክሱም ሀውልትን ያቆመው ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከአለት የፈለፈለው ፣ ፋሲልን የገነባው ፣ ወዘተረፈ የየዘመኑ ልሒቅ ነው ።
ይህ የሀገሪቱ ልሒቃን ታላቁ ተቃርኖ አንዱ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል ። በዚህ ሁሉ ረጅም ሒደት የሕዝቡ ተሳትፎ በመከተልና በመፈጸም መሀል የሚንጠራወዝ ነው ። ልሒቃን ተነስ ሲሉት ይነሳል ፣ ተከተለኝ ሲሉት ይከተላል ። ክተት ሲሉት ይከታል ። አሀዳዊ መጣብህ ሲባል ያለውን ይዞ ይወጣል ። ልትዋጥ ነው ፣ ሊያጠፉህ ነው ሲባል ዘራፍ ይላል ። እንግዲህ ሀገራችን እንዲህ ያለ ልሒቃንና ተከታይ ነው ያፈራችው ። አሳሯን እያበዙት ያሉት እነዚህ ኃይሎች ናቸው ።
ከጥንታዊው የሰው ልጅ ታሪክ አንስቶ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሀሳቦችና ፈጠራዎች እርሾ የሚጣለው ፣ ጥንስሱ የሚጠነሰሰው በልሒቁ ሲሆን አቡክቶ የሚጋግረው ፤ ጠምቆ የሚጠጣው ግን ሰፊው ሕዝብ ነው ። የሕመማችን የፈውሳችን ምንጭ ራሱ ልሒቁ ነው ። ሞታችንም ህይወታችንም ፣ እድገታችንም ውድቀታችንም፣ነጻነታችንም ባርነታችንም፣ ብልፅግ ናችንም ድህነታችን ፣ ሰላማችንም ጦርነታችን ፣ አንድነታችንም ልዩነታችንም ፣ እውቀታችንም ድንቁርናችንም ፣ ፍቅራችንም ጥላችንም ፣ ሴራችንም ቅንነታችን ፣ የሀገር ፍቅራችንም ቸልታችንም ፣ ጀግንነታችንም ፍራታችንም ፣ የእርስበርስ ፍቅራችንም ጥላቻችንም ፣ ወዘተረፈ በልሒቃኑ እጅና መዳፍ ስር ነው ።
ስለሆነም ለሀገሩና ለሕዝቡ ሲል እንደ ጃርት ፈተናዎችን ፣ ተግዳሮቶችን ፣ ልዩነቶችን ተቋቁሞ እና ከአዙሪቱ ሰብሮ በመውጣት ሀገሩን ከከበባና ከጥቃት ሊያድናት ይገባል። ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው በአንድነት ሊረባረብና ለእስከ ዛሬው ጥፋቱም እናት ሀገሩንና ሕዝቡን ሊክስ ይገ ባል ። ከዚህ ጎን ለጎን ብዙኃን መገናኛዎች ፣ የሲቪል ማህበረሰቦችና የሙያ ማህበራት የሕዝቡን የፖለቲካ ግንዛቤ ( ፖሊቲካል ሊትረሲ ) ማሳደግና ማጎልበት ላይ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013