ኤሌክትሪክ አምራቹ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሃይል ልማት፣ በኢንቨስትመንት ፣ ሃይል ማመንጫዎች በግንባታ ፣ በአሠራር እና በሃይል ማመንጫዎች ፣ የሃይል ማመንጫ ማስተዳደር እና በሃይል ማስተላለፊያ ግንባታ ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።
ተቋሙ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የሃይል ጫና እና መቆራረጥ ችግሮችን ለመቀነስ እንዲሁም ለከተሞችና በዙሪያቸው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሃይል ፍላጎት ምላሽ ለማሟላት የተገነቡ የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከነዚህ የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል አንዳንዶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን ቀሪዎቹ በመገባደድ ላይ ይገኛሉ።
በ2013 በጀት ዓመት የ 14 የማከፋፈያ ጣቢያ የአንድ ሺህ 304 ነጥብ ሁለት ኪ.ሜ የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል። የሚገነቡት የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች የተለያየ መጠን ያለው ኪሎ ቮልት የሚያስተላልፉ ናቸው።
በመገባደድ ላይ ካሉት የከፍተኛ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል በሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የወልዲያ ባለ 400 /230/33/15 ኪ.ቮ. የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አንዱ ነው። የፕሮጀክቱ አማካይ አፈጻጸም 48 በመቶ መድረሱን የባህርዳር-ኮምቦልቻ -ወልዲያ ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የሳይት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ሀብታሙ ተሾመ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዘግቧል።
አቶ ሀብታሙ እንደገለጹት፤ እስከ አሁን የኤሌክትሮ መካኒካልና የብረታ ብረት ተከላና ለኤሌክትሪክ ገመዶች ቀበራ የሚውል ግንባታ ተጠናቋል። በተጨማሪም ሁለት የባለ 75 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ተከላና ሁለት የባለ 500 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር መትከያ የመሰረት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።
የመቆጣጠሪያ ቤት፣ የሠራተኞች መኖሪያ ቤት፣ የጥበቃ ቤት፣ የስዊች ጊር ቤት ግንባታ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታ የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል። በቀጣይም የጠጠር ንጣፍ፣ የውስጥ አጥር፣ የሲዊች ያርድ ግንባታ እና የኬብል ዝርጋታ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ መሃንዲሱ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሀብታሙ ማብራሪያ፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን የመገጣጠምና የብረታ ብረት ስራዎች ተጠናቀዋል። በቀጣይ የስዊች ጊር ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ መሆናቸውን የሳይት መሐንዲሱ ተናግረዋል።
ማከፋፈያ ጣቢያው 500 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች እና 150 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ባለ 75 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች የሚኖሩት ሲሆን፤ ለማከፋፈያ ጣቢያው የሚያስፈልጉት የተለያዩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ከ 40 በመቶ በላይ ወደ ግንባታ ሥፍራው ተጓጉዘው የደረሱ ሲሆን ቀሪዎቹም ተፈብርከው በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ የትናየት ይመር በበኩላቸው የማከፋፈያ ጣቢያውን ስራ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከ 913 ሚሊዮን ብር በላይ ፋይናንስ መበጀቱን ጠቁመው፤ ግንባታውን ሻንጋይ ኤሌክትሮ ግሩፕ የተባለ የቻይና ኩባንያ ሲያከናውን የአማካሪነት ስራውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌከትሪክ ኃይል እያከናወነ ይገኛል ።
የማከፋፈያ ጣቢያው ስምንት ባለ 33 ኪሎ ቮልት እና ስምንት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች የሚኖሩት ሲሆን አማካይ አፈጻጸሙ ከ48 በመቶ በላይ ደርሷል። ማከፋፈያ ጣቢያው ሲጠናቀቅ የወልዲያ ኢንዱስትሪ ፓርከ፣ የባቡር ፕሮጀክቱ እና የወልዲያ ከተማና የአካባቢውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል። ከዚህም ባሻገር አስተማማኝ ኃይል እንዲኖር በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013