ኢትዮጵያ በአማካኝ ከ100 ሚሊዮን በላይ የህዝብ ብዛት አላት። በአሁኑ ወቅት የህዝብ ቁጥሯ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መጥቷል። ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞም ለዜጎች አስፈላጊና መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረግ ከባድ እየሆነ መጥቷል። በተለይም ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች መካከል የመኖሪያ ቤትን ተደራሽ ማድረግ ፈታኝ ሆኗል ።
አብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ የሚኖረው ኢ መደበኛ በሆኑ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው። ይህም የዜጎችን ስነልቦና ከመጉዳት ባለፈ በከተማዋ ገጽታ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። ታድያ በሀገሪቷ ተንሰራፍቶ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ያስችላል፤ የሀገሪቷን ሶሾ ኢኮኖሚ ያረጋጋል፤ በአይነቱ ልዩና ትልቁ ፓን ኢትዮጵያ (ሀገር አቀፍ) የፋይናንስ ተቋም ይሆናል የተባለው ሰላም የመኖሪያ ቤት ባንክ ከሰሞኑ ተመስርቷል።
ህብረተሰቡ ያለበትን የመኖሪያ ቤት ችግር በማቃለል ትርጉም ያለው ለውጥ አመጣለሁ በማለት አቅዶና አልሞ የላቀ ራዕይ አንግቦ የተነሳው ሰላም ባንክ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቋቋመ የመኖሪያ ቤት ባንክ ነው። የባንኩ መስራቾችና አደራጆችም በተሰማሩበት ሥራ ውጤታማ የሆኑ በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው።
ሰላም የቤቶች ብድር አቅራቢ ባንክ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለመሆን የተዘጋጀ ባንክ ስለመሆኑ ከመስራቾቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ያስረዳሉ ። ባንኩ ዛሬ በሀገሪቷ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለዜጎች ተደራሽ የማድረግ ዓላማን የያዘ ከመሆኑም በላይ በቀጣይ አምስት ዓመታት ለመቶ ሺ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ብድሮችን ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ባንኩ በአማካኝ እስከ ሁለት መቶ ሺ ብር የሚያወጡ ቤቶችን ፋይናንስ ለማድረግም ነው አቅዶ የሚንቀሳቀሰው ። ባንኩ መቶ ሺ የመኖሪያ ቤት ብድር መስጠት ከቻለ ደግሞ ሁለት መቶ ቢሊዮን ሀብት በሀገሪቱ መፍጠር ይቻላል ማለት ነው።
የሪልስቴት ገንቢውን፣ መንግሥትንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የሚንቀሳቀሰው ሰላም የቤቶች ባንክ ሀገሪቱ እያደገች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ የዜጎች አንገብጋቢ ጥያቄ የሆነውን መኖሪያ ቤት ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል። ይህን ተግባራዊ በማድረግ ሀገሪቷንና ህዝቡን ተጠቃሚ ያደርጋል። ዛሬ ላይ በሀገሪቷ ቤት ገዝቶም ይሁን ሰርቶ መኖር የሚችለው ሦስት ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆኑን ጥናቶች የሚያሳዩ ሲሆን ይህም ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት መኖሩን ያመላክታል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሪያ ቤት አልሚዎችና ብድር አቅራቢ ባንኮች በስፋት ባለመኖራቸው ወጣቱ ትውልድ ከከፍተኛ ትምህርት ቤት መልስ ሥራ ይዞ በኪራይ ቤት ያፈራርቃል። ስለዚህ ባንኩ በተለይም ሴቶችና ወጣቶች ከኪራይ ቤት የሚላቀቁበትንና በቀላሉ የራሳቸው የሆነ መኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት አሁን ያለውን ሲስተም ለመቀልበስ የሚሰራ ይሆናል። በመሆኑም አንድ ሰው ከየትኛውም ባንክ ሼር ሲገዛ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ነው። ነገር ግን ማንኛውም ሰው ሰላም ባንክ ገንዘቡን ሲቆጥብ ቤቴን የሰራልኝ ባንክ ነው ብሎ የባለቤትነት ስሜት ይሰማዋል።
ባንኩ ልምድ ካላቸው ገንቢዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ትስስር ፈጥሮ የሚሰራ በመሆኑ ከዚህ በፊት የተሰሩ ሥራዎችን በማየት የውል ስምምነት ይፈጥራል። ከስምምነት ውጭ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ቅጣት ይኖራል። ከዚህ ውጭ ደግሞ የፋይናንስ እጥረቱ ያመጣውን ችግር በመቅረፍ በተለይም አሁን ያለውን አዳዲስ ቴክኖሎጂ በማስመጣት ገንቢው በወቅቱ መገንባት የሚችልበትን ተነሳሽነት ይፈጥራል። በተጨማሪም በዘርፉ ትልቅ ሚና ያለውን መንግሥት አጋር በማድረግ መሬት በማቅረብም ይሁን በሌሎች ድጋፎች ሚናውን እንዲወጣ በማድረግ በጋራ ይሰራል።
መንግሥት የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን በቤት ልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ፍንጭ የሰጠ በመሆኑ ሰላም ባንክም ከመንግሥት ፈቃድ ካገኘ የውጭ ሀገር ገንቢዎችን ለማምጣት ዕቅድ ያለው መሆኑን አቶ ዘመዴነህ ሲያስረዱ፤ በዓለማችን አሉ ከሚባሉት በተለይም ባደጉ አገራት ውስጥ መኖሪያ ቤት ላይ የሚሰሩ ባንኮችን ለማምጣት ያላቸውን ዝግጁነት ተናግረዋል። ይህም በፋይናንስ እጥረት የሚያጋጥሙ የግንባታ መጓተቶችን ይቀርፋል ብለዋል።
በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተመሰረተው ሰላም የቤቶች ባንክ ለመነሻ የተፈቀደው ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር ይሁን እንጂ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዷል። ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ የሚችል ሲሆን በተለይም ዜጎች የቤት ባለቤት መሆን እንዲችሉ ዕድል ይሰጣል ። ሰላም ባንክ ሙሉ ለሙሉ ለቤት መስሪያ የገንዘብ ብድር በመስጠት የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ ዓላማው አድርጎ ተነስቷል። ይህም በሀገሪቱ ከሚገኙ የግል ባንኮች ቀዳሚ ባንክ ያደርገዋል።
በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ካሉ አገራት በሙሉ መኖሪያ ቤት ለማግኘት የሚያስችል እጅግ ዝቅተኛ አቅም ያላቸው ዜጎች ያሉባት ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች በቅርብ ጊዜ ውስጥ የወጣ ጥናት ያሳያል ያሉት አቶ ዘመዴነህ፤ ዛሬም ያለው የቤት አቅርቦትና ለመኖሪያ ቤት የሚሰጠው የብድር አቅርቦት በቂ አለመሆኑን አንስተዋል። አፍሪካ ውስጥ የተካሄደው ሌላው ጥናት ደግሞ በኢትዮጵያ ደረጃ በትንሹ 330 ሺ ብር የሚያወጣ መኖሪያ ቤትን መግዛት የሚያስችል አቅም ያለው ሰው አፍሪካ ውስጥ ምን ያህል ናቸው ሲባል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቁጥር አሁንም እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ነው።
መነሻውን አዲስ አበባ ላይ ያደረገው ሰላም የመኖሪያ ቤት ባንክ በቀጣይስ እያደጉ በመጡት የሀገሪቷ ከተሞች ላይ ምን እንደታሰበ ላነሳነው ጥያቄም አቶ ዘመዴነህ ሲመልሱ፤ ሰላም ባንክ ዓላማ አድርጎ የተነሳው መላው ኢትዮጵያን የሚያዳርስ ቤት ባንክ ነው። ምክንያቱም በአሁን ወቅት ሁሉም የሀገሪቷ ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ናቸው። አንዳንድ አፍሪካ ሀገራትን ስንመለከት አንድ ከተማ ብቻ አላቸው። ኢትዮጵያ ግን በርካታ ከተሞች አሏት። ስለዚህ በሁሉም የሀገሪቷ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ጥያቄያቸው ተመሳሳይ በመሆኑ ባንኩ በመላው ሀገሪቷ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል። አሁን ያለው ከ 100 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ22 ዓመት በኋላ 181 ሚሊዮን ህዝብ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ። ይሄ የህዝብ ቁጥር ደግሞ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ የሚገኝ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ይፈለጋል።
ስለዚህ የሰላም ባንክ ሞዴል ዋናው መስሪያቤት አዲስ አበባ ይሁን እንጂ በመላው ሀገሪቱ ባሉ ከተሞቹ ሁሉ ቅርንጫፎች ይኖሩታል። በተለይም የክልሎች ዋና ከተሞች ላይ ቅርንጫፍ ይከፈታል። ከዚህ ባለፈም ባንኩ ባህላዊ የሆነ የባንክ ዘዴን ብቻ የሚጠቀም እንዳልሆነ አቶ ዘመዴነህ ይገልጻሉ። 52 ሚሊዮን የቴሌኮም ሰብስክራይበር ያለበት ሀገር ነው።ከእነዚህም መካከል አብዛኛው ሰው በሚባል ደረጃ ዘመናዊ ስልክ አለው። ስለዚህ በቴክኖሎጂ በእጅ ስልክ የተለያዩ አገልግሎቶችን መጠቀም የሚያስችል አፕሊኬሽኖች ተግባራዊ ይሆናሉ።
ባንኩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሪያ ቤቶችን ከሚገነቡ ልምድ ካላቸው አካላት ጋር የሚሰራ በመሆኑ ወጣቱንና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። አዲስ ወደ ሥራው ዓለም የሚመጡት ወጣቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርበውን ቤት የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። በተጨማሪም የረጅም ጊዜ ብድር የሚሰጥ ባንክ እንደመሆኑ እስከ 30 ዓመት የሚቆይ ብድር ይሰጣል። ስለዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የግንባታ ወጪውን በመቀነሰና የረጅም ጊዜ ብድር በማበደር መጠነኛ የሆነ ቤት ለወጣቱ ተደራሽ ማድረግ ይቻላል።
ሰላም የቤቶች ባንክን ከመሰረቱት መስራቾቹ መካከል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ግርማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሪያ ቤት ማግኘት እጅግ ከባድና ውድ መሆኑን አንስተዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ኮንስትራክሽኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመደገፉና ወደ ማስ ፕሮዳክሽን አለመግባቱ ነው። ሰላም ባንክም ለችግሩ መፍትሔ በማምጣት ቀዳሚ ሆኖ ይሰራል። በመሆኑም ሰፋፊ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ፋይናንስ ያደርጋል።
በሌላው ዓለም የጋራ መኖሪያ ቤቶች በትክክለኛው መንገድ ተግባራዊ ሲሆን ይታያል። ነገር ግን በኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች ይገጥሙታል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ኢንቨስተሮች፣ ፋይናንሰሮችና የቤት ባንኮች ገብተው የታሰበውን ዓላማ ማሳካት የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂ መጠቀም ባለመቻላቸው ነው። የዛሬ 20 እና 30 ዓመት እና አሁን በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለው ግንባታ በብሎኬት ነው። ዓለም ግን ከዛ በላይ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ስለዚህ ሰላም ባንክ ሰፋፊና የተለያዩ የቤት አማራጮችን በማገዝ፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በዲዛይን እንዲመጡ የማድረግ ሥራ ይሰራል። ካምፓኒዎቹ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግና እጅግ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ ግንባታ እንዲገነባ የሰላም ባንክ ዋናው ሥራ ይሆናል።
በሀገሪቷ ከፍተኛ የሆነ የቤት ፍላጎት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ከአራት መቶ ሺ በላይ አዳዲስ ቤቶች የሚፈለጉ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ከዚህ ባለፈም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለይም በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ላይ ያልተመለሰና የተከማቸ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ መኖሩን በመረዳት ችግሩን በማቃለል የበኩሉን ሊወጣ ሰላም የቤቶች ባንክ አዲስ መላ ይዞ ብቅ ብሏል። መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግ በቀጣይ አምስት ዓመታት ለ100 ሺ ቤቶች ግንባታ ለማበደር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ።
ሰላም የመኖሪያ ቤት ባንክ በሀገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እና መጪውን ጊዜ በመልካም የኢንቨስትመንት አጋጣሚ በማየት ለመኖሪያ ቤቶች የረጅም ዘመን ብድር ፍላጎትን የሚያሟላ 15 በመቶ በሚደርስ ቅድሚያ ክፍያ እንዲሁም ለ30 ዓመት የሚቆይ ብድር ያበድራል። ባንኩ በዋናነት ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ ወደ ሥራ ዓለም የሚቀላቀሉ እና አዲስ ኑሮ መስራቾችን ፍላጎትና አቅም ያገናዘበ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013