ደብረ ማርቆስ ከተማ የአይረሴውና የዘመን አይሽሬው የስነጽሁፍ ቀንዲሉ የፍቅር እስከ መቃብር ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ የበቀሉባት ናት። ታዋቂና ስመጥር ደራሲያን፣ ተዋንያን፣ ገጣሚያን የተገኙባት ከተማ ናት። በስራቸው አንቱ የተባሉ ሀገር ወዳድ ዜጎች የተፈጠሩባት ጥንታዊት ከተማ ናት። ለቤተክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከቱ ሊቃውንትና ቅኔ መገኛ የሆነችው ደረ ማርቆስ በአማራ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዷ የሆነች የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ናት። የተመሰረተችው በ1845 ዓ.ም በደጃዝማች ተድላ ጓሉ ነው። በ1847 ዓ.ም የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት መቀመጫ ያደረጓት በመሆኗ ታሪካዊት ከተማ ናት። ስትቆረቆር የነበራት የቆዳ ስፋት 272 ሄክታር ሲሆን የነዋሪዎቿ ቁጥርም ከሁለት ሺ አምስት መቶ አይበልጥም ነበር።
ዛሬ ላይ የከተማዋ የቆዳ ስፋት 17 ሺ ሄክታር የነዋሪዎቿ ቁጥርም 261 ሺ ደርሷል። የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ አወቀ ሲያስረዱ ደብረማርቆስ ከተማ ለኢንዱስትሪ የተመቸችና ብዙ ፀጋዎች አሏት። አዳዲስ የዘይት ፋብሪካዎችን ጨምሮ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች በተፈጠረ የሥራ ዕድል እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግና በማዕድን ኢንዱስትሪ መበልፀጓ ማሳያ ነው። በተያዘው በጀት ዓመት ለ11 ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠሩ እየተገባደደ የሚገኝበት የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሥራ ዕድል መፍጠርያ ስትራቴጂም ሌላው ነው። ትልልቅ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን መገንባት የሚያስችሉ የኖራ ድንጋይና ለዚሁ ግብዓት የሚሆኑ ሌሎች ሀብቶቿን መጥቀስ ይቻላል።
የሴራሚክ ፋብሪካ ለመክፈት የሚያስችልም የግራናይት ማዕድን የሚገኝባት ከተማ ስትሆን በተደረገው ጥናቱ መሰረት የብረትና የወርቅ ማዕድናት ይገኝባታል። ከባህል አንፃርም ከፍተኛ ወጪ የተደረገበት የጎጃም ባህል ማዕከል እየተገነባ ይገኛል። ከመስረተ ልማት አኳያ ስትቃኝ በእርግጥ ቀደም ብሎ ከአዲስ አበባ ባህር ዳር የሚያልፈው ዋና መንገድ ተጠቃሚ ነበረች። መንገዱን በቀጣይ ዓመት በስፋትም በጥራትም ዕድገቷን በሚመጥን መልኩ ለመገንባት ጨረታ ተዘጋጅቷል። ከማርቆስ በመነሳት በደብረ ኤልያስ አድርጎ ከህዳሴ ግድቡ የሚገናኝ መንገድ ሥራ ተጀምሯል።
ከደብረ ማርቆስ ሞጣ የሚዘልቅና የባህር ዳርን ጉዞ የሚያሳጥር አማራጭ መንገድም የፌዴራል መንግስት ጨረታ አውጥቷል። የመንገዶቹን መብራት ደረጃ ለማሳደግ፣ ለማስፋትና የነዋሪውን የውሃ ችግር ለመፍታትም ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በብዛት የሚገኙባት በመሆኗም በአልሚዎች ተመራጭ መሆኗን ይናገራሉ።
የንጉስ መቀመጫ የነበረች፣ የአባይ ተፋሰስና የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ በቅርቧ የሚገኝ መሆኗ ለጎብኚዎች ቀልብ ይምትስብ መሆኗ ተመራጭነቷን አጉልቶታል። ከከተማዋ ነዋሪ 80 በመቶ በላይ ነዋሪም በንግድና በሌሎች አገልግሎት ሰጪ የሥራ መስኮች የተሰማራ ሲሆን ገቢዋም ቢሆን ከዓመት ዓመት እያደገ መጥቷል። በ2013 በጀት ዓመት 400 ሚሊዮን የሚጠጋ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራች ትገኛለች።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ እንደሚሉት ከተማዋን ወደ ሪጅኦ ፓሊታን ከተማነት ለማደግ ያስቻላትም ይሄው ነው። ከተማዋን ወደ ሪጂኦ ፖሊታን የማደጓን ጥያቄ ከውሳኔ ሃሳብ ጋር በማያያዝ ለክልሉ መንግስት ያቀረበው ከተማ አስተዳደሩ ነበር። የክልሉ ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ተቀብሎ የጥናት ስታንዳርድ ላከለት። ደብረማርቆስ አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታም ተጠና። ጥናቱ በመስፈርቱ መሰረት የቆዳ ስፋቷን፣ የህዝብ ቁጥሯን የገቢ አቅሟን፣ ታሪካዊነቷን ከግምት በማስገባት ተካሄደ። አስተዳደሩ ከተማዋ የደረጃ ሽግግር የሚገባት መሆኑን አመነበትና ለክልሉ ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ላከው። ቢሮው ጥናቱን ከገንዘብና ኢኮኖሚ፣ ከገቢዎችና ከሌሎች አካላት ጋር በማጥራት ጥናቱን ይፋ የሚያደርግበት መድረክ አመቻችቶ ደብረ ማርቆስ ከተማ ወደ ሪጂኦ ፖሊታን ከተማነት አደገች። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ እንደሚሉት ከተሞች በአራቱም አቅጣጫ ቢሆን ይመረጣል። ወደ ክብነት ቢቀያየርም የተሻለ ነው። ሆኖም ደብረ ማርቆስ አሁን ካላት አቀማመጥ አንፃር ወደ ሰሜን አቅጣጫ እየሰፋች ያለች ከተማ ነች።
ከተማዋ ከሀገራችን ዋና መዲና አዲስ አበባ 295 እንዲሁም ከምትገኝበት ከአማራ ክልል ከተማ ባህር ዳር 265 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። ለሁለቱም ከተሞች ማዕከል ናት የሚያሰኝ ቅርበት አላት። የግብርና ምርቶች ማዕከል ሆናም ለአዲስ አበባ በማቅረብም አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች። አሁን ላይም የግብርና ምርት ጨምሮ የማዕድን ምርቶችን በማቀነባበር አስተዋጽኦዋን አጠናክራ ለመቀጠል እየሰራች ትገኛለች። የዕድገቷ ትርክትም ከዚሁ ጋር ይሰናሰላል። በሂደቱ የ23ኛ ከንቲባዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ አወቀን ጨምሮ የቀደምቱ 22 ከንቲባዎቿ ሚና የጎላ ነው።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ እንዳጫወቱን ከእሳቸው በፊት የነበሩት 22 ከንቲባዎች ዛሬ ላለችበት ዕድገት እንድትበቃ በየዘመናቸው የየራሳቸውን አሻራ አሳልፈዋል። እሳቸውም በፊናቸው ይሄንኑ አበርክቶ ለማድረግ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። በተለይ ከተማዋ ያለፈው 27 ዓመት ስርዓት ጨቆናቸው ተብለው ከሚታወቁ የሀገሪቱ ከተሞች አንዷ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ከገባችበት እንድትወጣ ተግተው የመሥራት ዕቅድ ሰንቀዋል።
በቅርቡ ደብረ ማርቆስ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ያደገች መሆኗም የመሰረተ ልማት ችግሮቿን ከመቅረፍ ጀምሮ የሰነቁትን ዕቅድ ከዳር ለማድረስ እንደሚያግዛቸው ያምናሉ። ለዚህ አሁን ላገኘችው ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ዕድገቷ ውሳኔ ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው ድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉም ያስባሉ።
‹‹ይህ ታሪካዊ ውሳኔ እኔ ከተማዋን በምመራበት ዘመን መሆኑ የበለጠ ለከተማዋ ዕድገት እንድንሰራ መነሳሳት ፈጥሮብኛል›› ብለውናል። በተጨማሪም በክልል አመራሮች ላይ ዕምነት እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል። የህዝብ ጥያቄ የሚረዱና የሚመልሱ አመራሮች መሆናቸውን አምነው ለነዋሪው እንዲያስረዱ የሚያስችልም አቅም ሆኗቸዋል። ልፋታቸው ብዙም ሆነ ትንሽ ውጤት አፍርቶ ማየትን የመሰለ አስደሳች ነገር እንደሌለ ሁሉ ከተማዋ ለደረሰችበት የዕድገት ደረጃ መድረሷ ደስታ ፈጥሮባቸዋል። ‹‹ስሜቱም ማርቆስን እንደገና አምጦ እንደመውለድ ያክል ነው›› ብለውናል።
ሌላዋ አስተያየታቸውን የሰጡን የደብረማርቆስ ከተማ በተለምዶ ፒኮክ ሰፈር እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ አዲስ ታደሰም ከተማዋ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ከማደጓ ጋር ተያይዞ የሰጡን አስተያየት ከተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ ጋር ተመሳሳይነት አለው። አሁን ላይ ያገኘችው ደረጃ ከተማዋ ዕድሜ ጠገብ ቀደምትና የጥበብ መፍለቂያ እንዲሁም ታሪካዊ ከመሆኗ ጋር ሲነፃፀር ዘግይቷል ማለት ይቻላል። በተለይ ለአዲስ አበባም ሆነ ለክልሉ መዲና ቅርብ ከመሆኗና ካላት አስተዋጾ ጋር ሲታይ ቀደም ብሎ የሚገባት ነበረች። ቢሆንም በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት ዕድገቷ በብዙ አቅጣጫ የተስተጓጎለና የተጎተተ ብሎም ከተጨቆኑት የሀገሪቱ ከተሞች አንዷ ናት።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ግን ብዙ ለውጦች ታይተውባታል። ከህንፃና ከሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታዎች መካሄድ፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስፋት፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት መሳለጥ አኳያ የተሻሻሉ ተግባራት ተከናውነዋል። እየተከናወኑም ይገኛሉ። ‹‹የተሰማራሁት በመንግስት ሥራ ላይ ነው። ቢሆንም እንደ ከተማ ነዋሪነቴ ከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው የሚያወጣውን በጀትን የተመለከተ የአፈጻጸም ሪፖርት እከታተላለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ አዲስ ከተማ አስተዳደሩ ከሚያወጣው የተለያዩ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቶች እንደተገነዘቡት ታዲያ ገቢዋም ቢሆን ከፊት ከነበረው በእጅጉ የጨመረበት ሁኔታ መኖሩን መመልከት ችለዋል።
በከተማዋ ትላልቅና ትናንሽ የንግድ ማዕከላት መገንባቱ ለገቢው ማደግ እራሱን የቻለ አስተዋጾ አድርጓል። የግብር ከፋዩ መጠን ጨምሯል። ይህም ከተማዋ ወደ ትልቅ ከተማነት ለማደግ አንዱ ምክንያት ሆኗል። በህብረተሰቡ ዘንድ በዚሁ ዙሪያ በከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪውና ለነጋዴው የሚሰጠው ግንዛቤ ማስጨበጫ ውጤት ማምጣት ከቻሉት ተግባራት አንዱ ነው። ይሄ ከነጋዴውም ሆነ ከሰራተኛውና ከከተማዋ ነዋሪ የሚሰበሰበው ግብር ለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያደርገው አስተዋጾ ከፍተኛ ነው። አሁን ላይ ከተማዋ እንደነ ባህርዳር፣ ጎንደርና ደሴ የከተማነት ዕድገት ደረጃ ማግኘቷ ደግሞ ዕድገቷን ለማፋጠን ዓይነተኛ መሣሪያ ይሆናል የሚል ዕምነት አላቸው።
ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ጎጃም አልቃድር ከተማዋ የኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ በውስጧ እየተፈጠረ ያለውን ሰፊ የሥራ ዕድል በማድነቅ ነው አስተያየታቸውን የጀመሩት። ወይዘሮዋ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች በኩል እየተፈጠረ ያለው ዕድል በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይ በዚህ በኩል ኢንተርፕራይዞች ሲሸጋገሩ ለሌሎች ቦታ የሚለቁበትና የሚተካኩበት በከተማዋ ያለው የንግድና ሌሎች አገልግሎቶች እየሰፋ የሚመጣበት ተከታታይ ሂደት አለ። በአጠቃላይ ግን ከሥራ ፈጠራ አንፃር በሁለቱም የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ሲታይ እጅግ ሰፊ ነው። የነዋሪው ቁጥርም የዚያኑ ያህል ከስር እየጨመረ ነው። በመሆኑም ከተማዋ ይህን ማስተናገድ በሚችል መልኩ መደራጀትና መዋቀር ያስፈልጋታል።
ከዚህ አንፃር ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ማደጓ ተገቢም ነበር። ለማደግ ያስቻላትም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና በመንቀሳቀስ አቅሟ ነው ባይ ናቸው ወይዘሮ ጎጃም። የንጉስ መቀመጫ የነበረች የመሆኗን ታሪካዊነትም ካስመረጣት መስፈርት አንዱ ሊሆን ስለመቻሉ ይጠቅሳሉ። የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ እንደሚሉት አንድን ከተማ ወደ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማነት ለማሳደግ የከተማው ወጪን የመሸፈን አቅም ዋነኛ መስፈርት ነው። ደብረ ማርቆስም ያደገችው ከዚህ አንፃር ባላት የጎላ ዕድል ነው።
አንድ ከተማ አስተዳደር በራሱ ወጪውን የሚሸፍን ከሆነ የሠራተኛ ደመወዝን ጨምሮ እሱ ለሚያወጣቸው የሥራ ማስኬጃ የካፒታል በጀት የሚጠይቁ ሥራዎች ውጤታማ ይሆናሉ። ገቢ የመሰብሰብ አቅሙ የዚህኑ ያህል ይጠናክራል። ከተሞች ያላቸውን የገቢ አማራጮች ሁሉ አሟጠው ተጠቅመው የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የከተማ አስተዳደሩ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን እንዲሰሩ ዕድል ይሰጣቸዋል። የከተማውንም ኢኮኖሚ ያሳልጣል። የንግድ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴን፣ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በአጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴን ያፋጥናል። በአካባቢው የማኑፋክቸር ኢንዱስትሪዎችን መስፋፋት እንዲሁም ከዚሁ ጎን ለጎን የከተማው ነዋሪ ኑሮ የሚሻሻልበትን የከተማዋና የክልሉ ብሎም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያድግበትን ሁኔታ ይፈጥራል።
የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይትባረክ አወቀ
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013