
አዲስ አበባ:- በደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ከጀመሩ ሁለት ሼዶች ከ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ፓርኩ አስታወቀ። ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተገልጸ።
የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት ያልሞላው ቢሆንም ለአንድ ሺ 132 ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ምርት ወደ ውጭ በመላክ 17 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት ችሏል፡፡
ከአምስቱ ሼዶች ውስጥ በአንዱ የእስፔን ባለሀብት በሹራብ ሥራ ተሰማርቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገባ ነው፡፡ ሥራ በጀመረ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገባት ችሏል ብለዋል፡፡
የፈረንሳይ ኩባንያ ቡርቱማርት ከ2013 ዓ.ም ጥር ወር ጀምሮ በወር ወደ ሦስት ሺህ ቶን ብቅል በማምረት በየወሩ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያስገባ ይገኛል ያሉት አቶ የሺጥላ ፣ ኩባንያው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ማስቻሉን ጠቁመዋል ፡፡
ከቀሪዎች ሦስት ሼዶች መካከል አንዱን የታይዋን ኩባንያ እንደያዘው ገልጸው ፤ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ የማሽን ተከላ ጨርሷል፡፡ በቅርቡ ቅጥር በመፈጸም ወደ ሥራ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ በእስከአሁን ሂደት ለአንድ ሺ 132 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አመልክተዋል፡፡
የልማት ተነሺ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በተለያዩ ዘርፎች ለ580 የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በሦስት ፈረቃ እንደሚሠራ አመልክተው ፤ ለ13ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ኩባንያዎች እያመረቱ ያሉት መሥራት ከሚችሉት አቅማቸው ከ60 እስከ 70 በመቶ ድረስ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላሉ ያሉት አቶ የሺጥላ፣ በ2014 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ለስድስት ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ጠቁመዋል፡፡
የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ 100 ሄክታር መሬት ተቀብሎ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፤ 75 ሄክታሩ ላይ ግንባታው እንደተካሄደበት ከፓርኩ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ሞገስ ጸጋዬ