በኢትዮጵያ ካለው ህዝብ ከ65 ከመቶ በላይ የሚሆነው የባንክ አገልግሎት የማያገኝ ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ከባንክ ውጪ ናቸው ተብለው የሚታሰቡት የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች ፣ የገጠር ነዋሪዎች ፣ ስደተኞችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ናቸው። የዓለም ባንክ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ደሃ ተብሎ የሚታሰበው በቀን ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ የአሜሪካን ዶላር ያነሰ ገቢ ያለው ሰው ነው። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የገንዘብ ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ድህነትን ለመቀነስ ፣ ምርታማነትን ለመጨመርና ደህንነትን ለመጠበቅ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው።
ደሃው ማህበረሰብ እንዴት የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ መሆን አለበት በሚሉና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ፕሪሳይስ የተባለው ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራ የግል አማካሪ ድርጅት ጥናት አድርጓል። ድርጅቱ ድህነት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የገንዘብ ተቋማት አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል በቀረጸው ፕሮጀክት ከጥቅምት 2013 ዓ.ም እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ ድረስ ባከናወነው ጥናት የባንክ ሂሳብ የሌላቸው እነማን ናቸው የሚለውን በመለየት ወደ ባንክ ሥርዓት እንዳይመጡ ማነቆ የሆኑባቸውን ጉዳዮች በማጥናት መፍትሔዎችን ጠቁሟል።
የፕሪሳይስ የፋይናንስ አማካሪ ወይዘሪት ቅድስት ተስፋዬ እንዳሉት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መደበኛ የባንክ ሒሳብ የለውም። የባንክና ኢንሹራንስ አካውንት
ያለው ሰው ከ30 እስከ 35 በመቶ ያህል ብቻ ነው። በርካታ ከከተማ ውጭ የሚኖሩ ሰዎች ፣ ሴቶች እና የትምህርት ዕድል ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ ተቋማትን አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም ይላሉ።
ድርጅቱ ባደረገው ጥናት የፋይናንስ አገልግሎት ለማያገኙ ሰዎች ለምን የባንክ ሒሳብ አልከፈታችሁም በሚል ላቀረበው ጥያቄ ‹‹የባንክ ሒሳብ በመክፈት ተቀማጭ የምናደርገው ገንዘብ የለንም ፤ ከተማ ውስጥ ካልሆነ በገጠራማ አካባቢዎች ባንኮች ባለመኖራቸው ሂሳብ መክፈት አልቻልንም እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ስላለን የባንክ ሂሳብ መክፈት ለሀብታሞች እንጂ ለእኛ የሚቻል አይመስለንም›› የሚሉ ምላሾች ማግኘቱን ይናገራሉ። በተለይ በግንዛቤ ረገድ ያለው ክፍተት ከፍተኛ ነው። ብዙ ሰዎች የባንክ ጥቅም ገንዘብ ለማስቀመጥ ብቻ ነው ብለው ያስባሉ። እውነታው ግን የባንክ ሂሳብ የከፈተ ሰው ብድርና የመድህን አገልግሎት ማግኘት ይችላል። ይህ ሰፊ ቁጥር ያለው የአገሪቱ ህዝብ በመደበኛ ኢኮኖሚው ውስጥ ተሳታፊ ሆኖ ከሚያገኘው ገቢ ላይ መቆጠብ መቻል አለበት ይላሉ።
የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው የጥቃቅንና አነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት በ2012 መጨረሻ በቁጥር 41 የደረሱ ሲሆን ጠቅላላ ካፒታላቸው በ17 ነጥብ 3 ዕድገት አሳይቷል። 19 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ሲደርስ ጠቅላላ ሀብታቸው በ10 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት አሳይቶ 92 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በተመሳሳይ መልኩ የቁጠባ መጠናቸው በስድስት ነጥብ ሰባት በመቶ አድጎ 44 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ ተሰብሳቢ ብድራቸውም በ10 ነጥብ 5 በመቶ አድጎ 64 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ፕሪሳይስ ያከናወነው ጥናት የጥቃቅንና አነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት የፖሊሲ ማነቆ እንዳለባቸው ያሳያል። ተቋማቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላት እያሏቸው እንደ ባንክ አይታዩም። ወይዘሪት ቅድስት የጥቃቅንና አነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ያስችላል በሚል በጥናቱ የተጠቆሙ አቅጣጫዎችን ሲጠቅሱ “በእነዚህ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የሚገለገሉ ዜጎች በሂደት አቅማቸውን ገንብተው ከፍ ያለ ወለድና የብድር መጠን ወዳለው ባንክ ሊሸጋገሩ ይችላሉ። ስለዚህ በርካታ ሰዎችን ለሚያስተናግዱት አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የብድር አቅርቦቶች መንግስትና የግል ባንኮች የተወሰነውን ድርሻ የሚጋሩበት መንገድ ተፈጥሮ አቅማቸውን እንዲገነቡ ቢደረግ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ዜጋ በስፋት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል” ይላሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ ብዙሃኑን የአገሪቱን ዜጋ ተደራሽ የሚያደርጉ አዳዲስ አሰራሮችን ለሚያስተዋውቁ አካላት አሰሪ የህግ ማዕቀፎች ቢዘጋጁ ፤ የደንበኞች የብድር መረጃ ታሪክ የሚመዘገብበት ሥርዓት እንዲቀለጥፍ ብሔራዊ መታወቂያ ስራ ላይ ቢውል ፤ የባንክ አሰራሮች ሙሉ ለሙሉ ዲጂታል እንዲሆኑ እና በሞባይል የሚደረግ የገንዘብ ልውውጥ እንዲስፋፋ ቢደረግ ከባንክ ሥርዓት ውጭ የሆነውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ይላሉ።
ኬንያ ኤምፔሳ የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት ተግባራዊ ካደረገች ከ14 ዓመታት በኋላ 72 በመቶ የሚሆኑት ኬንያውያን እየተገለገሉበት ነው። በኡጋንዳ ከጠቅላላ ህዝቡ የባንክ አካውንት ያለው 11 በመቶ ሲሆን በእጅ ስልኩ ኤምፔሳን የሚጠቀመው ዜጋ ግን ከ 42 በመቶ በላይ ነው። እነዚህ ተሞክሮዎች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆነውን ሰፊ ማህበረሰብ በፋይናንስ አግልግሎት ተደራሽ በማድረግ ጤነኛ የሆነ የፋይናንስ ፍሰትና ዘለቄታዊነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እንዲያግዝ ለማድረግ የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ይጠቅሳሉ።
የትናየት ፈሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013