የኢትዮጵያ ባህርሃይል ታሪክ የሚጀምረው ከ 3 ሺ ዓመታት በፊት መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ላይ ተጽፎ ይገኛል። ይህም ቢሆን ግን ባህርሃይል በኢትዮጵያ በዘመናዊ መልክ የተቋቋመው እኤአ በ1956 በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነመንግስት በምጽዋ ወደብ ላይ ሲሆን በመጀመሪያ የእጩ መርከበኛ መኮንኖች ማሰልጠኛ ማዕከል በማደራጀት የተለያዩ ስልጠናዎችም ይሰጡ ነበር።
ስልጠናው ይሰጥ የነበረው ተመርጠው በመጡ አሰልጣኞችና አማካሪዎች ሲሆን የመጡትም ከቀድሞ ዩጎዝላቪያ፣ አሜሪካና ፈረንሳይ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ከአሜሪካ ከብሪታንያና ከህንድ ጋር ስምምነትን በመፍጠር በዘርፉ ብቃት ያላቸው አሰልጣኞች በዘለቄታዊነት በማስመጣት ስልጠናው በተጠናከረ መንገድ ይሰጥም እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። ይህን መሰል ስራዎች ደግሞ በወቅቱ ባህርሃይሉ አቅሙን በማሳደግ አገራዊ ግዳጁንና ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ አስችሎታል።
በወቅቱ የአስተዳደር ለውጥ መጥቶ ደርግ ስልጣን ሲይዝ የባህር ሃይሉን አደረጃጀት በማስፋትና በማጠናከር ዘመናዊ የሆኑ ወታደራዊ ትጥቆችን በማዘጋጀት ከወዳጅ አገራት ጋር ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር ከአፍሪካ ተወዳዳሪ የሆነ ባህርሃይል ለመመስረትም ተችሏል።
ከደርግ ውድቀትና አገሪቱ የሥርዓት ለውጥ ካደረገች በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በህዝበ ውሳኔ በመለየቷ ምክንያት ወደብ አልባ በመሆኗ የባህርሃይሉ ከሰራዊት አደረጃጀት ውጪ እንዲሆን በመደረጉ ለመፍረስ ችሏል።
ይህ ሆኖ ሳለ ግን በ2011 ዓ.ም የሰራዊት አደረጃጀትና የመዋቅር ለውጥ በመምጣቱ እንዲሁም ወቅታዊና አገራዊ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ የባህርሃይል አስፈላጊነት ታምኖበት በአዋጅ ቁጥር 1100/2011 እንደገና እንዲቋቋም ተወስኗል። ይህንን ተከትሎም ባህርሃይሉ በፍጥነት እንዲደራጅ ለማድረግ አባላት በመመደብ በባህርሃይል የረጀም ጊዜ የስራ ልምድ ያላቸውን ነባር አባላትና አመራሮች በአማካሪነት እንዲሰሩ በማድረግና ከወዳጅ አገራት ጋር ትስስር በመፍጠር ባህርሃይል የመከላከያው አንድ አካል ሆኖ እንዲደራጅ የማድረግ ስራው እየተከናወነ ይገኛል።
እኛም ባህርሃይሉን እንደገና የማደራጀቱ ስራ ምን መልክ አለው ስንል የኢፌዴሪ የባህርሃይል ምክትል አዛዥ የሎጂስቲክ ሃላፊ ከሆኑት ኮሞዶር ዋለጻ ዋቻ ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ እስቲ ኮሞዶር ዋለጻ ማናቸው ለሚሉ አንባቢያን በሰራዊቱ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንዳገለገሉ በምን በምን ሃላፊነቶች ላይ እንደቆዩ ቢነግሩኝ?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ በሰራዊቱ ውስጥ 30 ዓመታትን አገልግያለሁ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ አብዛኛውን የስራ እድሜዬን ያሳለፍኩት አየርሃይል ነው። በዚህም ከተራ ቴክኒሻንነት ጀምሮ እስከ ሱፐርቫይዘርነት የሰራሁ ሲሆን ወደ አመራር ከወጣሁ በኋላም ከዝቅተኛ አመራር እስከ ትልቁ የአመራር እርከን ድረስ ደርሼም ሰርቻለሁ።
በትምህርት መስኩም በአቪየሽን ኢንጂነሪግ ፣ በማኔጅመንት እንዲሁም በሰው ሀብት አመራር ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ተምሬያለሁ።
አዲስ ዘመን ፦ አየርሃይል ላይ በርካታ ዓመታትን እንደማሳለፍዎ አየርሃይሉ የመጣበትን ርቀት አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ አየር ሃይል እንደሚታወቀው በአፍሪካ ስመጥርና ጠንካራ የሆነ ነው፤ የማድረግ አቅሙም አስተማማኝና ከውስጥም ከውጭም የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከትና ተመጣጣኝ አጸፋዊ ምላሽን ለመስጠት የሚያስችል አቅም ያለው ነው። በቂ የሚባሉ በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአካላዊ ብቃት እንዲሁም በአገር ፍቅር የታነጹ አባላት ያሉት ነው።
ይህ ደግሞ ምናልባትም ከደርግ ዘመን ጀምሮ አብሮት የመጣ ዝናና ገናናነት ሲሆን አሁን በተጨባጭ ያለው አየርሃይላችንም የትኛውንም ዓይነት ጠላት ድባቅ መምታት የሚችል ከመሆኑ አንጻር ኢትዮጵያን ሊተናኮል ያሰበ አካል ካለ ሁለት ሶስት ጊዜ ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበት የሚያስገነዝብም ነው። ምክንያቱም በአየር ላይ ውጊያም ሆነ መከላከል በኩል በየትኛውም አቅጣጫ ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት ለመመከት የሚያስችል አቅምና ዝግጅት ያለው ነው። ይህንንም ባሳለፍኩት የስራ ዘመኔ ያረጋገጥኩት እውነት ነው። አሁን ደግሞ ከምን ጊዜውም በላይ ጠንክራ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ አየርሃይል ነው ያለን።
አዲስ ዘመን ፦ ረጅሙን የስራ ጊዜዎን አየርሃይል ላይ አሳልፈው አሁን ደግሞ አዲስ እየተቋቋመ ወዳለው ባህርሃይል መጥተዋልና ምን ፈጠረቦት? እንዴትስ መጡ?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ መንግስት ይሰራልኛል ብሎ ያመነበትን ሰው በሚፈልገው ቦታ መድቦ ያሰራል። እኔም ረጅም ዓመት በአየር ሃይል ነው ያገለገልኩት። ነገር ግን ከ 2010 ዓ.ም አገራዊ ለውጥ ተከትሎ ከዚህ በፊት ተበትኖ የነበረውን ባህርሃይል እንደገና ለማቋቋም ሲታሰብ እኔም ወደ ቦታው መጥቼ እንዳደራጅ ሆኗል። በዚህም ደስተኛ ነኝ።
ከዚህ ቀደም አገራችን ስመ ጥርና ጠንካራ የሆነ ባህርሃይል ነበራት። ነገር ግን እንዲፈርስ ሆኗል። ለውጡን ተከትሎ የሪፎርሙ አካል ከሆኑት ነገሮች መካከል ባህርሃይሉ አንዱ ስለነበርና በአዲስ መልክ ሲቋቋም እንዲያቋቁሙ የሆኑት አካላት ከተለያዩ የሰራዊቱ ክፍሎች ውስጥ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በአገልግሎታቸውና በብቃታቸው ባህር ሃይልን ሊያስቀጥሉ ይችላሉ የተባሉ አመራሮች እንዲሰባሰቡ ሲደረግ እኔም ወደዚህ እንድመጣ ሆነ። በመምጣቴም በጣም ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም አገርና ህዝብ የሰጡንን አደራ በተሰጠን ሃላፊነት ልክ ሰርተን ባህርሃይልን ለማቋቋም ዝግጁነቱም ቁርጠኝነቱም ስለነበር አደራውን ተረክበን ወደ ስራው ገብተናል።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ባህርሃይሉን እንደገና በማቋቋም ሂደት ውስጥ ምን ዓይነት ተግባራት እየተከናወኑ ነው? ምን ያህል ርቀትስ ሄደናል?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ አዎ፤ ይህ መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው። በአዋጅ ከተቋቋመና እንደ ሃይል ተዋቅሮ ወደ ስራ ነው የገባው። ከዚህ በፊት ባህርሃይል አየርሃይልን ልዩ ሃይሎች የሚባሉ ነበሩ። አሁን ግን የአንድን አገር ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የአገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ተጣምሮ መስራት ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር ምድር ሃይል፣ አየር ሃይል፣ ባህር ሃይል ፣ ሳይበር ሃይል እንዲሁም ስፔስ ኮማንድ በሚል በአምስት አውዶች ተዋቅሮ ነው ጠንካራ ስራ እየተሰራ ያለው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የመከላከያው አንድ ሃይል ሆኖ የተቋቋመው ባህርሃይልም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል። የመጀመሪያውና ትልቁ ስራ የነበረው መዋቅሩን (ስትራክቸሩን) መስራት ነው። ባህርሃይሉን ለማደራጀት ከተለያዩ የጦር ክፍሎች የተውጣጡ አካላት በመሆናቸው ያሉት እነዚህን አካላት በተገቢው ሁኔታ መርቶ አደረጃጀቱን የባህርሃይል ቁመና ለማስያዝ የተወሰኑ ልምዶችንም መቀመር ያስፈልግ ስለነበር ከተለያዩ ወዳጅ አገራት ጋር የመገናኘትና ልምዶችን የማሰባሰብ ተግባርም ተከናውኗል።
በዚህም በተለይም መዋቅሩን ለማስራት የሚያስችሉ ጠንካራ አመራሮችን ከወዳጅ አገራት በማምጣት ፣ የቀድሞ ባህርሃይል ላይ በከፍተኛ አመራርነት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችን በማካተትና አማካሪ በማድረግ አብረውን እንዲሰሩ በማስቻል የመጀመሪያውን ስትራክቸር ሰርተን አጠናቀናል። ቀጥሎም ይህንን መዋቅር በተግባር የሚለውጥ የሰው ሃይልን የማሰባሰብ ስራም መከናወን ስለነበረበት በዚህም ላይ በትምህርት ዝግጅት በእድሜ በጾታ ስብጥር በማድረግና አጠቃላይ ባህርሃይሉን ሊያስቀጥል የሚችል ሰው የማካተት ስራው በተገቢው ሁኔታ ተከናውኖ ወደ ስራ ተገብቷል።
ይህ ስትራክቸር ጸድቆ ወደ ስራ ስንገባ ቀጥሎ የነበረው ተግባር ይህንን ስትራክቸር ተግባር ላይ የምናውልበት አካባቢ (ኦፕሬሽናል ቤዝ) ያስፈልግ ነበር፤ የትና እንዴት መሆን አለበት የሚለውን ለመመለስ በተለይም ባህር በር ሳይኖራቸው ጠንካራ ባህርሃይል ያላቸው አገሮች በርካታ በመሆናቸው የእነሱን ተሞክሮ ወደ እኛ በማምጣትና ከዚህም ጋር ተያይዞ እኛም በአቅራቢያችን ካሉ ባህር በር ካላቸው ጎረቤት አገሮቻችን ጋር በመስማማትና በሊዝ በመክፈል መጠቀም እንደምንችል በጥናት የማረጋገጥ ስራ ሰርተናል። ከዚህ አንጻር በአቅራቢያችን ያሉትን ወደቦች በሙሉ ለማየት ሞክረናል፤ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር እዛስ ያሉ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ምንድን ናቸው? የሚለውንም ሰርተናል። እነዚህን ሁሉ ሰርተንም ውሳኔ ለሚሰጠው አካል አቅርበናል። ይህ ውሳኔ ሲያገኝ ደግሞ ቀጥሎ ወደሚሰሩት ስራዎች እንሻገራለን።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ባሀርሃይል እንደ ሃይል ከተደራጀ የራሱ ሁለንተናዊ የሆነ መለያ የደንብ ልብስና ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት እንዲሁም ተግባቦት ያላቸው ማዕረጎችም ያስፈልጉት ስለነበር እነዚህን ለማሟላትም በጥናት የተደገፈ ስራን በመስራት የራሱ የሆነ መለያ ያለው የደንብ ልብስ እንዲኖረው ሆኗል። የማዕረግ ምልክቶቹም ከምድርሃይልና የአየርሃይል የተለዩ በመሆናቸው እነዚህም ከታች መሰረታዊ ወታደር አንስቶ እስከ ጀነራል ድረስ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ተሰርቶ ጸድቆ ስራ ላይ ውሏል።
የባህርሃይል ስራ (የኦፕሬሽን ስራ) የሚሰራው በአገር ውስጥ ባለመሆኑ ከየትኛውም አገር ባህርሃይል ጋር እርስ በእርስ በሚገናኙበት ጊዜ በቀላሉ መግባባት የሚያስችላቸው ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ማዕረግ እንዲኖር ሆኗል።
በሌላ በኩልም ባህርሃይልን በማደራጀት ሂደት ውስጥ የስልጠና ማዕከላት እንዲኖሩ የማድረግ ስራ አንዱ በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ መሰረታዊ ባህረተኞችን የሚያሰለጥንበት ማዕከል ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመነጋገር በቢሾፍቱ ቦታ ተመርተን የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል። በዘንድሮው ዓመት የሰውሃይልን ከማብቃት አንጻር ከ 200 በላይ ሰልጣኞችን በመቀበል መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፤ ከዚህ ወር መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ከ50 በላይ የሚሆኑትን በቢሾፍቱ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ስልጠናቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ባህርተኛ መኮንኖችን የሚመረጡበት አካዳሚ ደግሞ በባህር ዳር ቦታ ተመርተን እዛም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ ወደ ግንባታ ለመግባት ስራዎች እየተሰሩ ነው። በጠቅላላው ቀጣይ የሚሰጡ ግዳጆቻችንን ለማሳካት የሚያስችል ቴክኒካል ብቃት ያላቸውን ሰዎች ማፍራት አንዱና ዋነኛው ስራ በመሆኑ አሁን ላይ ወዳጅ አገራት ላይ ስልጠና ላይ ያሉ በርካታ ልጆች አሉን። መርከብ ላይ በቀጥታ እየሰለጠኑ ያሉ ፓይለቶች አሉ።
አሁን ባለንበት ሁኔታ ጠንካራ የሚባል መሰረት ተጥሏል ፤ የሰው ሃይል የማብቃት ስራዎቹም በጣም ጠንካራ ናቸው። በተለይም አካዳሚውን ለማጠናከር ሥርዓተ ትምህርቶችን የመቅረጽ ስራዎች ተከናውነው ወደ ስራ ገብተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ስልጠናዎችን በጣና ሀይቅ ላይ የሚለማመዱባቸው ፈጣን ጀልባዎች በሰኔ ወር አካባቢ ይገባሉ። እነዚህ ሲገቡ ደግሞ በአገር ውስጥ የመጀመሪያውን ፈጣን ስልጠና በጣና ሀይቅ ላይ የምናደርግበት ሁኔታ ይኖራል። ኦፕሬሽናል ኤሪያ ብለን ለይተን ያቀረብናቸው አካባቢዎች ላይ ያለው ሁኔታ ሲመቻች ደግሞ በቀጣይ ዓመት የትምህርትና ስልጠና ስራዎች በጅቡቲ፣ በሱዳን፣ በኤርትራና በሶማሌላንድ ይሰጣሉ።
በጠቅላላው ግን በአሁኑ ወቅት ባህርሃይልን እንደ አንድሃይል ለማደራጀት የሚያስችሉ ስራዎች በሙሉ ተሰርተዋል። በቀጣይ በተለይም በአስር ዓመቱ እቅዳችን ጋር ተያይዞ በየዓመቱ የሚያድግ የሚለወጥና የሚታሰበውን ቁመና ለማምጣት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ፦ የቀድሞው በጣም ጠንካራና ስመ ጥር የሆነ ባህርሃይል በመፍረሱ እንደ አገር ምን አሳጣን? አሁን ደግሞ ከዜሮ ተነስተን ባህርሃይልን ማቋቋም ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ የኢትዮጵያን የባህርሃይል ታሪክ በምናይበት ጊዜ ባህርሃይሉ በዘመናዊ መልክ ተቋቁሞ ወደስራ የገባው 1948 ዓ.ም በምጽዋ ነው። ከዛ በኋላም እራሱን እያጠናከረ መጥቶ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስከብር ደረጃ የደረሰም ነበር። ከዛ በኋላ ግን የደርግ ሥርዓት ሲመጣም ባህርሃይሉ ዘመናዊ በማድረግ ጠንካራና በአፍሪካ ተወዳዳሪ እንዲሆንም አድርጎት ነው እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የቆየው።
1983 ዓ.ም በአገራችን በተከሰተው የመንግስት ለውጥ ምክንያትና ኤርትራም አንዲት ሉአላዊት አገር ሆኗ ራሷን ችላ ስትወጣ አገራችን ወደብ አልባ ነው የሆነችው። በወቅቱ የነበሩት የፖለቲካ አመራሮችና ውሳኔ ሰጪዎችም ባህርሃይሉን እያዳከሙ እያዳከሙ በማቆየት በ1986 ዓ.ም በህጋዊ መንገድ የፈረሰበት ሁኔታ ነው ያለው።
ጠንካራ የሚባል የአገሪቱን ሉአላዊነትና ጥቅሟን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ባህርሃይል ነው እንዲፈርስ የሆነው ፤ ይህ እንደ አገርም ትልቅ ኪሳራን ያስከተለም ነበር። ከዚህ ሁሉ ኪሳራና ከረጅም ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ የዛሬ ሁለትና ሶስት ዓመት ገደማ በመጣው ለውጥ ምክንያት ባህርሃይል እንደ አዲስ እንዲቋቋም ሆኗል።
አዲስ የባህርሃይል የማቋቋም ጉዳይ በተለይም አሁን ያለው ጂኦ- ፖለቲክስ ሁኔታዎችን የማስተካከል ጉዳይም ያለበት ነው። ሌላው የአገራችን የወጪና ገቢ ንግድ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚመላለሰው በውሃ ላይ ነው፤ በውሃ ላይ እየተስተዋለ ያለ ውንብድና ደግሞ ዓለምን የሚያሰጋም ጭምር ነው። ይህ ሁኔታ ባለበትና በዚህን ያህል ባህርን የምንጠቀም ሆነን ሳለን የገቢ ወጪ ምርቶችን ደህንነት የመጠበቅ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያ አንዱ ስትራቴጂያችን ነው። ከዚህ ውጪ ደግሞ አገራችን ከጎረቤት አገሮች ካሉ ወደቦች 60 እና 65 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው እርቃ የምትገኘው፤ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ከባህር ላይ ተነስቶ በአገራችን ላይ የሚቃጣ ጥቃት ካለ በቀላሉ ለመከላከል ያስችለናል።
በጠቅላለው ባህርሃይሉ መጠናከሩ የአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ወጪና ገቢ ምርቶቻችን በሰላም እንዲጓጓዙ በማድረግ በኩል ትልቅ ፋይዳ አለው። በሌላ በኩል ደግሞ ምድርሃይል፣ አየርሃይል ፣ ባህርሃይል ፣ ሳይበርና ስፔስ ኮማንድ በአንድ ሲጠናከሩ ብቻ ነው አንድ አገር ደህንነት ዋስትና ሊኖረው የሚችለው። በመሆኑም ባህርሃይል በዚህ መልኩ ትንሳኤው መምጣቱ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅ፣ ሉአላዊነታችንን የማረጋገጥ ከየትኛውም አካል የሚሰነዘርን ጥቃት የመከላከል ጉዳይ በመሆኑ ጥቅሙም በዚህ ልክ ነው ሊታይ የሚገባው።
አዲስ ዘመን ፦ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ መሬት መውረሯ ይታወቃል፤ ይህ ሁኔታ መነሻው ምናልባትም ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሮቿ ምክንያት ተዳክማለች ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው፤ ከዚህ አንጻር አሁን ላይ እንደ አገር ራሳችንን የመከላከል አቅማችን ምን ደረጃ ላይ ነው ይላሉ?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ በነገራችን ላይ ጠላቶቻችን አሁን ባለው ሁኔታ ቀጥታ ውጊያ እየገጠሙን አይደለም፤ ከዛ ይልቅ የእኛን ውስጣዊ ክፍተቶቻችንን እየተጠቀሙ ጥቃት የመፈጸም ሰላማችንን የመንሳት ሃሳብ ላይ ናቸው። በዚህ ውስጥ ደግሞ ሰራዊታችን በመደበኛነት ከሚያደርገው የአገርን ዳር ድንበር የማስጠበቅ ስራ ውጪ እነሱ የሚፈጥሯቸውን ችግሮች በማርገብ ላይ እንዲጠመድ አድርገዋል። ነገር ግን ይህም ቢሆን አሁን ያለው የሰራዊታችን ጥንካሬና አንድነት ከምንም በላይ የጠነከረና የዳበረ ነው።
እንደ ዜጋም በውስጣችን ምንም ዓይነት የፖለቲካ የአስተሳሰብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን በአገራችን ጉዳይ ላይ አንድ ነን፤ ሰራዊታችን ደግሞ ከአቀራረጹም ጀምሮ የተጠና በመሆኑ አሁን ላይ የማንም ፖለቲካዊ ድርጅት አስተሳሰብ የለውም፤ ከዛ ይልቅ የአገርን ሉአላዊነት ዳር ድንበር የማስጠበቅ ሃላፊነት ብቻ እንዳለው ተረድቶ በዛው መንገድ ነው ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለው።
በሌላ በኩልም አየርሃይል፣ ምድርሃይል፣ ባህርሃይልና ሌሎቹም የውጊያ አውዶች በመጣመር እና ተደራጅተው በመንቀሳቀስ የአገሪቱን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ አቅም ላይ ናቸው። በዚህም የትኛውም አይነት ጠላት በየትኛውም መንገድ ቢመጣ ሊደፍረን አይችልም። ምክንያቱም ቁመናችን እጅግ አስተማማኝ ነው። ባህር ሃይልም እንደ ባህርሃይል አሁን ያለው ዝግጁነት ቀጣይ ሊመጡ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ዛሬ ሳይሆን ነገ ከነገወዲያ በባህር ላይ ሊመጣ የሚችልን ጥቃት ለመከላከል የሚችል ቁመና እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራ ነው።
ይህንን ስራ ባህርሃይል ብቻውን አይደለም የሚሰራው። አየርሃይል፣ የምድርሃይል ሌሎቹም ደግሞ ተናበው የሚሰሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ የትኛውም ዓይነት ጠላት ኢትዮጵያን ለመውረር ወይንም ደግሞ ጥቃት ለማድረስ ሲያስብ ሁለት ሶስት ጊዜ ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚያስገድድ ቁመና ላይ እንገኛለን።
በነገራችን ላይ አሁን ባለው ሁኔታ አየርሃይላችንን እና ባህርሃይላችንን ብናይ አለ የሚባል ዝግጅት ቴክኖሎጂ የተላበሱ በአካል ብቃትና በሥነ ምግባር የታነጹ በመሆናቸው የትኛውንም ጠላት ለመመከት የሚያስችል አቅም አላቸው።
ባህርሃይልም ላይ ቢሆን የተመረጡ ለሙያው የሚገቡ ሰዎችን ከመመልመል ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ አገርም እየወሰዱ ያሉት ስልጠና እጅግ የተጠና ብሎም ውጤታማ የሚያደርግ ከመሆኑ አንጻር ባህርሃይላችንም በቀጣይ ትልቅ ስራ የሚሰራ እንደሚሆን ያሳያል። አሁን እንኳን ባለንበት ወቅት አገራችንን እየተገዳደሩ የሚያስቸግሩ ጠላቶቻችንን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመከት የሚያስችል ከሌሎች ሃይሎች ጋር ተጣምሮ ግዳጅን ለመወጣት የሚችል በቂ ሞራልና ዝግጁነትና ብቃት ያለው ባህርሃይል እንዳለን መናገር እችላለሁ።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ መልኩ የራሳችንን አቅም ከማጠናከራችን ጎን ለጎን የጠላቶቻችንን አቅም ማጥናት ደግሞ ወታደራዊ ሳይንሱ የሚያዘው ተግባር ይመስለኛልና እንደው በዚህስ ላይ ያለን ዝግጁነት ምን ደረጃ ላይ ነው?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ እውነት ነው የሃይል ሚዛንን መጠበቅ እንደ አንድ ወታደራዊ ሳይንስ የሚታይ ነው። በዚህም የትኞቹም ጎረቤረቶቻችንን በአገራችን ላይ በአንድም ይሁን በሌላ መልክ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስቡ እንዳሉ ስለምናውቅ የእኛ አቅምና እነሱ ያሉበት ወታደራዊ ብቃት ምን ይመስላል የሚለውን ማየት መሰረታዊ ነገር ነው። በመሆኑም አሁን ይህ ነው ይህ ነው ብዬ ዘርዝሬ ባልነግርሽም ከዚህ አንጻር አቅማቸውን በደንብ አድርጎ የሚለይ ስራዎች ተሰርተዋል።
ከሰራነው ስራ ተነስተን የራሳችን አቅም ስናየው ደግሞ እጅግ አስተማማኝ ነው። ይህም ቢሆን ግን ጎረቤቶቻችን ከእኛ ጋር ያለባቸውን ችግር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመነጋገርና በመደማመጥ መፍታትን ደግሞ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ይሆናል። ከዛ አልፎ ግን በሉዓላዊነታችን በብሔራዊ ማንነታችን ላይ የሚቃጣ ጥቃትና የሚመጣ ሃይል ካለ ደግሞ በአስተማማኝ ሁኔታ መመከት የሚያስችል እነሱ ካላቸው አቅም አንጻርም በቂና ተመጣጣኝ ብቃት ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡– ብዙ ልምድ ያላቸውን የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህርሃይሎችን በመጠቀሙ በኩል ያለው ስራ ምን ይመስላል?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ ከመነሻውም እንደ ማሳያ ወይንም ምርጥ ተሞክሮ አድርገን የተጠቀምናቸው እነሱን ነው። አሁን ላይ በእድሜም የገፉ ቢሆንም የትምህርት ቤቱን ሥርዓተ ትምህርት ከመቅረጽ የአየርሃይል አባል ለመሆን በትምህርት ዝግጅትና በእድሜ እንዲሁም በአካል ብቃት ምን አይነት ሰው ሊመረጥ ይገባዋል የሚለውንም ምክር በመለገስ በኩል ትልቅ ሚና ነበራቸው።
እኛ ከተለያየ የጦር ክፍል የመጣን ነን። የባህርሃይል መሰረታዊ ስልጠናም የለንም። ግን ደግሞ ከተለያዩ አገሮች የወሰድነው ልምድ ከውጭ አገር በአማካሪነት የመጡ ባለሙያዎች ቢኖሩም እነዚህ የቀድሞ የባህርሃይል አባላት ያደረጉት አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም።
በመሆኑም ከነበረው ከቀድሞ ባህርሃይል ተነስተው አሁን የተሻለ ባህርሃይልን ለመገንባት ቁጭትም ስለነበራቸው እኛንም በሞራል እየደገፉ ትልቅ ስራ ሰርተዋል።
አዲስ ዘመን፦ ኮሞዶር እርስዎ እንግዲህ ብዙ የስራ ዘመንዎን አየርሃይል ላይ ነው ያሳለፉት፤ አሁን አየርሃይላችን ደግሞ እጅግ በዘመነ በረቀቀ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ በአፍሪካም ስመ ጥር የሆነ ተቋም ሆኗልና ባህርሃይሉም እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ አየርሃይል አሁን ላለበት ደረጃ ለመድረሱ በየሥርዓቱ ተደማሪ እየሆነ መምጣቱ ጠቅሞታል ፤ እንደ ባህርሃይልም በአንድ ወቅት ተቆርጦ የቀረም አይደለም። አሁን ላይ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ድሮኖች ሁሉ ጥቅም ላይ በማዋል የአገርን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው።
አሁን ባህርሃይል መሰረቱ እየተጣለ ነው ፤ የመጀመሪያውን አስር ዓመት ጠንካራና ተጽዕኖ ፈጣሪ ባህርሃይልን ለማደራጀት የሚያስችል ስራዎች ነው ዛሬ ላይ እየተሰራ ያለው። ይህ ደግሞ በትጥቅ፣ በሰው ሃይል ዝግጅትና ስልጠና፣ በጠቅላለው ዙሪያ መለስ የሆነ ስራን ሰርተን ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ባህርሃይል ለመገንባት ወሳኝ ስራዎችን እየሰራን ነው።
ይህ እንዲመጣ ግን እዚህ ባህርሃይል ላይ የተመደበው ሰው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ድጋፉን ሊያደርግ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ዘርፉ እንዲጠናከር ከፍተኛ ድጋፍና ጥረት እያደረገ ነው ፤ መከላከያም የትኛውንም ጥያቄያችንን በማስተናገድና ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ነው።
በመሆኑም እዚህ ያለው ሃይል እንዲጠናከር የተጀመረው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ይቀጥላል ፤ በዚህ መንገድ ደግሞ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የባህርሃይል ትንሳኤን እናበስራለን ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ኢትዮጵያ የባህር በር ስለሌላት የባህርሃይል ምን ያደርግላታል? እንዴትስ ትጠቀምበታለች? የሚሉ አሉና እርስዎ በእዚህ ላይ ያለዎች አስተያየት ምንድን ነው?
ኮሞዶር ዋለጻ፦ ባህር በር ሳይኖራቸው ጠንካራ ባህርሃይል ያላቸው በአፍሪካም፣ በኢዢያ፣ ላቲን አሜሪካም ብዙ አገሮች አሉ። ለምሳሌ አሁን ላይ ጅቡቲ ላይ የሰፈሩ 26 እና 27 አገሮች አሉ እነዚህ አገሮች ደግሞ ከአገራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ነው እዛ የሰፈሩት፤ እኛ ደግሞ ከድንበራችን ወደብ ላይ ለመድረስ 60 ኪሎ ሜትሮችን ብቻ ነው መጓዝ የሚጠበቅብን፤ ይህ ባለበት ሁኔታ ባህር በር የለንምና ባህር ሃይል አያስፈለገንም ማለት አለማወቅ ነው።
በጀመርነው ሁኔታ ከጎረቤት አገሮቻችን በሊዝ ቦታዎችን በመግዛት እንደ ማንኛውም አገር የራሳችንን ግዛት መመስረት ይቻላል። ሌላው የእኛ እድል ደግሞ በአራቱም አቅጣጫ ያሉት ጎረቤቶቻችን ለዚህ ስራ ምቹ መሆናቸው ነውና ይህንንም ማየት ያስፈልጋል። በመሆኑም የአገራችን ወጪና ገቢ ምርቶች የሚጓጓዙበትን አካባቢ የመለየት ስራዎች ተሰርተዋል። የትኞቹ ወደቦችም ያስፈልጉናል የሚለውም ተጠንቶ ቀርቧል። ይህ ጥናት ውሳኔ ሲያገኝ መሰረተ ልማቶቻችንን አሟልተን የምንሰራበት ይሆናል።
በነገራችን ላይ አገራችን እያደገች ስትሄድ ጠላቶች ይበዛሉ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከባህር ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከልና የራስን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ ባህርሃይል ትልቅ ሚና ያለው ነው። ከዚህ ባሻገር የምናስገባውም የምናስወጣውም ምርት ሰላማዊ ፍሰት እንዲኖረው ያደርጋል፤ በአሁኑ ወቅት በውሃ ላይ ወንበዴዎች እየበዙ ከመምጣታቸው አንጻር መርከቦቻችን እገታ ቢያጋጥማቸው የሌላ አገር ባህርተኞችን እባካችሁ አስለቅቁልን ማለት ከባድ ነው፤ በመሆኑም እራሳችንን ለመከላከል ሚናው ቀላል አይደለም።
ወደብ የለንም የሚሉ ሰዎች አዎ የለንም፤ ግን ደግሞ ባህር በር የሌላቸው በባህር ሃይላቸው ስማቸው የሚጠራ በርካታ አገሮች አሉ። በመሆኑም እኛም ባህር በር ስለሌለን ባህር ሃይል አያስፈልገንም ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ኮሞዶር ዋለጻ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013