በዓለም አቀፍም ይሁን በሃገር አቀፍ ሕግጋት እውቅና ተሰጥቷቸው ጥበቃ ከሚደረግላቸው መብቶች አንዱ የግል ነጻነት መብት ነው:: የግል ነጻነት መብት ሲባል በግለሰቦች ንብረት ወይም የይዞታ መብት ላይ የሚደረግን አግባብነት የሌለው ጣልቃ ገብነት ለማስከበር ሲባል የተቀመጠ መብት ነው:: ሁከት በማንኛውም ሕጋዊ ሰብአዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ መብት ላይ የሚደረግ ወረራ ወይም አግባብነት የሌለውና ያልተፈቀደ ጣልቃገብነት ነው::
ሁከትን ወይም በይዞታ ላይ የሚደረግ ወረራ መከላከልና ማስከበርን በሚመለከት በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገመንግስት እንዲሁም ሃገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በተለይም በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ፣ የማሕበራዊና የባሕል መብቶች ስምምነት ጥበቃ የተደረገለት ከመሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች አንዱ ነው::
ሁከት በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ገጽታዎች አሉት። ነገር ግን በመሰረታዊነት ጥበቃ በሚደረግለት መብት ባሕርይ ግን ተመሳሳይነት አላቸው:: ይሕም ንብረትን በነጻነት የማስተዳደር፣ የመቆጣጠርና የመጠቀም ወዘተ መብቶችን ያጠቀልላል። ከዚህ ባለፈ የይዞታ መብትን ማስከበር የንብረት ባለቤትነት መብትን ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ በንብረት ወይም በይዞታ ላይ ለተመሰረቱ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ሰላማዊነትም የራሱ አወንታዊ ድርሻ አለው:: ይህ የሆነው ባለይዞታ የሆነ ሰው የንብረቱ ባለሃብት እንደሆነ ስለሚገመትና ሁከትን በሕግ መከልከልም ማሕበረሰባዊ ደሕንነትና ሰላምን ለማስጠበቅ የሚረዳ በመሆኑ ነው:: ይህም ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 686 መገንዘብ እንደሚቻለው ሁከት በሌላ ሰው ሰላማዊ ይዞታ ላይ በኃይል ድርጊት፣ በዛቻ፣ በመሳሪያ በቡድን ሊፈጸም የሚችል በመሆኑ ነው::
በሰዎች ግላዊና የኢኮኖሚ መብቶች ላይ የሚደረግ ሕጋዊ አግባብነት የሌለው ጣልቃ ገብነት ወይም ወረራ ወይም ሁከት በፍትሐብሔርና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚኖረውን ገጽታ በተመለከተ ሕብረተሰቡ ግንዛቤ ሊኖረው እና መብቱንና ግዴታውን አውቆ እንዲጠቀምበት ማድረግ ያስፈልጋል::
በጥቅሉ ሲታይ በሁከት በሚንቀሳቀሱ ወይም በማይንቀሳቀሱ ንብረቶቸ ላይ ወይም ይዞታዎች ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ነው:: ይህ ሲባል የጣልቃ ገብነቱ አይነትም የንብረቱን ሁኔታ ወይም ይዘት በመለወጥ፣ ንብረቱን በኃይል በመያዝና በመድፈር፣ ያለሕግ ወይም ያለፈቃድ በመውረርና በመቆጣጠር፣ ከሕጋዊው ባለመብት ወይም ባለይዞታ ላይ በመንጠቅና በመሰወር ወዘተ ሊፈጸም ይችላል።
በተጠበቁና በተከለሉ ቦታዎች ላይ ዛቻና ማስፈራራትን፣ መሳሪያን ወይም ሌላ ማንኛውንም ኃይል በመጠቀም የሚደረግ የሁከት ተግባር የፍትሐብሔር ብቻ ሳይሆን የወንጀልም ኃላፊነት ሊያመጣ ይችላል። ምክንያቱም ይሕ አይነት ሁከት በንብረት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ግላዊ ነጻነትን በመግፈፍም ጭምር ሊፈጸም የሚችል በመሆኑ ነው:: በተፈጠረው ሁከት ላይ የሚወሰዱ የፍትሐብሔርም ይሁን የወንጀል እርምጃዎችም እንደተፈጠረው የሁከት አይነት የሚወሰኑ ናቸው::
በወንጀልና በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች የሚጋሩት የጋራ ባሕርይ ቢኖርም የሚለያዩባቸው ሁኔታዎችም አሉ። በፍትሐብሔር ጉዳይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች ጣልቃ-ገብነቱ በማያሻማ ወይም በማያጠራጥር የሌላ ሰው ይዞታ ላይ የተደረገ ከሆነ ነው። በሌላ በኩል በአንድ ይዞታ ላይ ሁከት አደረሰ የተባለው ሰው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት ቢኖረው እንኳን ባለቤቱ በተመሳሳይ ጊዜና ሁኔታ የንብረቱ ትክክለኛ ባለይዞታ እስካልሆነ ድረስ ሁከቱን አያስቀረውም።
የንብረት ባለቤት የሆነ ሰው በተመሳሳይ የባለይዞታነት መብት ከሌለው ንብረቱን በእጁ አድርጎ በያዘው ሰው ላይ የመፋለም ክስ ከማቅረብ ውጭ ሁከት ተፈጥሮብኛልና ሁከቱ ይወገድልኝ ብሎ ጥያቄ ማቅረብ አይችልም:: ይዞታው በምክንያታዊ ሰው እይታ ወይም አስተሳሰብ ለተራዘመና ላልተለመደ ጊዜ ከቆየ በባለይዞታውና በንብረቱ መካከል የነበረው ግንኙነት እንደተቋረጠ ስለሚቆጠር ይዞታ አለ ለማለት ያዳግታል::
በሌላ በኩል አንድ ይዞታ ሕጋዊ ነው የሚባለው በሰላማዊ ሁኔታ የተያዘ ከሆነ ነው:: በሌላ አገላለጽ ሁከቱን በኃይል ወይም በሌላ መንገድ ለማስወገድ ይዞታው ራሱ በሌላ ሁከትና ኃይል የተያዘ መሆን የለበትም:: ሁከቱ የተፈጠረው ጉድለት በሌለበትና ባለይዞታው በእውነት ይዞት በሚገኘው ይዞታ ላይ ከሆነ ማለትም ንብረቱ በኃይል ወይም በሌላ ሕገወጥ ተግባር ያልተገኘና የማያጠራጥር ወይም የማያሻማ እንዲሁም ለረዥም ጊዜ ያልተቋረጠ ወይም ያልቀረ ከሆነ ሁከት ተፈጠረብኝ ማለትና ሁከት ይወገድልኝ ማለት ይችላል::
የይዞታን እውነተኛነት በተመለከተም ባለይዞታው ይዞታውን በእጁ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ አያይዞም በተረጋገጠና ባልተጭበረበረ መንገድ ወይም በማናቸውም ሁኔታ ሕገወጥ ባልሆነ መንገድ ያልተያዘ መሆን ይኖርበታል። እዚህ ላይ ሁከት ተፈጥሯል አልተፈጠረም የሚለውን ጉዳይ ለመወሰን ባለይዞታው ንብረቱን እጁ ያደረገበት መንገድ መረጋገጥ አለበት። ለምሳሌ የኪራይ ውል አስፈላጊ አይደለም በሚል ክርክር ይቀርብበታል። ነገር ግን ከባለይዞታነት የተሻለ የባለሃብትነት መብት ካለ ይዞታ ይለቀቅልኝ የሚል ጥያቄ ከማቅረብ የሚያግድ ነገር የለም። የንብረት ባለቤትነትም ከንብረት ባለይዞታነት አንጻር ሲታይ ሰፋ ያለ መብትን የሚያጎናጽፍ ነው::
የሕጉ ዓላማና መንፈስ የሚያሳየው ባለቤትነት ስላለ ብቻ አንድን ሕጋዊ ባለይዞታ በሁከት ይወገድልኝ ጥያቄ ወይም በኃይል ማስለቀቅ አይቻልም:: ከዚህ ይልቅ ሁከት ተፈጠረብኝ የሚል አካል ይዞታውን ያገኘበት ሕጋዊ አግባብና በእውነት የያዘ መሆኑን ግንዛቤ መወሰድ አለበት::
በወንጀል ጉዳይ ሁከት ተፈጥሯል የሚባልባቸው ሁኔታዎች ደግሞ የሁከት ማድረግ ወንጀል በማይንቀሳቀስ ንብረት ማለትም በቤት፣ በይዞታና መሬት እንዲሁም በሕንጻ ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንዱ መሆኑን የወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 685 እስከ 687 አስቀምጧል። ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ የሕግ ሳይንስም ይሁን የእኛ ሀገር ሕግ ሁከት የግል ነጻነቶች መገለጫ በሆኑ የግል ቤቶችና ሌሎች የተከለሉ ወይም የተከለከሉ ቦታዎች ላይ የሚፈጸም የመድፈር ተግባርም (Invasion of Privacy or Trespass) በነዚህ ይዞታዎች ላይ ሁከት በማድረስ ሊፈጸም ይችላል።
ሁከት የፈጠረው ሰው ወደ አንድ ይዞታ ወይም የተከለከለ ስፍራ ለመግባት ወይም ገብቶ ለመቆየት በሕግ ወይም በሌላ አግባብ ያልተፈቀደለት ሆኖ፤ ወደ ይዞታው ለመግባት ወይም ለመቆየት የሚያስችል ቅድመ-ሁኔታ የሕግ፣ የጥንቃቄ እርምጃ ወይም ስነ-ስርዓት አለመሟላት በወንጀል የሚያስጠይቅ ሆኖ ተቀምጧል። በሌላ በኩል ምንም እንኳን ይዞታው ለመግባት የተፈቀደ ቢሆንም ወደይዞታው ለመግባት የሚፈልግ አካል ግን ለመግባት ወይም ለመያዝ ወይም በይዞታው ለመቆየት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ሊጠበቅበት ይችላል። ለምሳሌ ያሕል የተፈቀደለት ልዩ ባለሙያ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል።
በሌላ በኩል የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ሲገባ የመንግስት ሰራተኛ ወይም የሰራዊት አባል ሊፈጸም የሚችል ሲሆን፤ ይዞታውን ለመቆጣጠር ከሚያስችል ኃይል በላይ ወይም በሕግ ከታዘዘው ወይም ከተፈቀደው ስርዓት ውጭ የሰውን ንብረት መያዝን ወይም መውሰድን ይመለከታል። ይሕ በሆነ ጊዜ በሁከት ማድረግ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገልና የግል ይዞታዎችን በመድፈር ወንጀልም ሊያስጠይቅ ይችላል::
ሁከት በማንኛውም ሕጋዊ ሰብአዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ መብት ላይ የሚደረግ ወረራ ወይም አግባብነት የሌለውና ያልተፈቀደ ጣልቃገብነት በመሆኑ፤ በወንጀልና በፍትሐብሔር ህጎች የሚያስጠይቅ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
ምንጭ፡- ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013