የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፖሬሽን በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ከተለዩት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቁልፍ ችግሮች ውስጥ አንዱና ለዘርፉ ዕድገት አስፈላጊ የሆነውን የማምረቻና መሸጫ ቦታዎችን በማልማት ለኢንዱስትሪያሊስቶች በኪራይ በማስተላለፍ፤ ዘርፉ የነበረበትን የመስሪያ ቦታ ችግር በማቃለል በቀጣይ የታቀደውን ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት አስተዋፅዖ እንዲያበረክት በደንብ ቁጥር 83/2009 የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ የተቋቋመ ነው። ቆየት ብሎ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 67/2012 ደግሞ የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በመባል እንዲዋቀር ተደርጓል።
በዚህም መሠረት ኤጀንሲው በ2012 በጀት ዓመት የመጨረሻ ሁለት ወራት የሽግግር ሂደቱን በማጠናቀቅ ከሐምሌ 2013 ጀምሮ በማቋቋሚያ አዋጁ የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባራት ለመፈፀም የሚያስችለውን ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል። ኤጀንሲ ከተቋቋመ ወዲህም ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ ሲሆን በዚህም ላይ የከተማዋ ምጣኔ ሀብት ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኤጀንሲው የመስሪያ ቦታዎች አሰጣጥና አስተዳደር መመሪያ፣ የመስሪያ ቦታዎች አሰጣጥና አስተዳደር ክትትል እና ቁጥጥር መመሪያና የመሥሪያ ቦታዎች አጠቃቀም ስታንዳርድ እንዲሁም ማኑዋሎችን ለማዘጋጀት አስፈላጊ መረጃዎችና ሰነዶች ያለው ቢሆንም በዚያው ልክ ለመስራት ፈተናዎች በርትተውበታል። በአሰራር መሰረት አንድ ኢንተርፕራይዝ አምስት ዓመት ከሞላው በኋላ ወደ ሌላ መሸጋገር ቢገባውም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ባለበት እያዘገመ ሌሎች አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ሼድ ያለመልቀቅ ኤጀንሲው የተቀላጠፈ ሥራ እንዳያከናውን እንዲሁም የመሰረት ልማቶች አለመሟላት ለኤጀንሲው እክል ከሆኑበት ዋንኛ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። በእነዚህ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐሺቅ በድሩ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡– ተቋሙ መቼና እንዴት እንደተቋቋመ ቢገልጹልኝና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ሐሺቅ በድሩ፡– በአዲስ መንገድ በ2012 በጀት ዓመት ሁለት የተለያዩ ተቋማትን አንድ ላይ ለማምጣት ታስቦ በኤጀንሲ ደረጃ የተቋቋመ ነው። በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ደረጃ የጥቃቅንና፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ የተደራጁትን መሬት በማዘጋጀትና ለመስሪያ ቦታዎች በጀት በመመደብ ሲሠራ ነበር። እነዚህን ሃብቶች በተለያዩ ተቋማት ይተዳደሩ ስለነበር ለአሠራር አስቸጋሪ ሲሆን፤ ግጭትም ይፈጥር ነበር። ግን ለኢንተርፕራይዞች አመቺና ደረጃውን የጠበቀ የመስሪያ ቦታ ለመፍጠርና የተሳለጠ ተግባር ለማከናወን የታሰበ ነው።
ቀደም ሲል ሥራ ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ሥር አንድ ዘርፍ የነበረውን የአነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ቦታ ማቅረብ በሚል ተደራጅቶ የነበረውን የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን አንድ ላይ በማምጣት በኤጀንሲ ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል። ይህ መደረጉ ከጥቃቅን እስከ መካከለኛ ሽግግሩን ጠብቆ በደረጃቸው የመስሪያ ቦታ እንዲሰጥና እንዲሳለጥ፣ በከተማ አስተዳደሩ ያለው ሃብት በወጥ ሃብት እንዲተዳደርና በአግባቡ ለመጠቀም ታስቦ በከተማ አስዳደሩ ተወስኖ ወደ ሥራ የተገባ ነው።
በአዲስ መንገድ ከተደራጀ በኋላም የመስሪያ ቦታዎች ብዛት፣ የኢንተርፕራይዞች ብዛት በአግባቡ ተለይቷል። በዚህም ተለጣፊ ሱቆችን ጨምሮ 19ሺ በላይ መስሪያ ቦታዎች እንዳሉ ማወቅ ተችሏል። ከተለጣፊ ሱቆች ውጭ 4ሺ300 መስሪያ ቦታዎች አሉ። 3ሺ331 ሼዶች፣ 154 ደግሞ ወርክሾፕ እና ባለ አራት ወለል ህንጻዎች ናቸው። 337 አውቶብሶች ሸገር ዳቦ ስርጭት አገልግሎት እየሰጡ ነው። በዚህም 23ሺ500 ዜጎች ተደራጅተዋል፣ አንቀሳቃሾች ደግሞ 48ሺ ሲደርሱ ከዚህ በተጨማሪ ተቀጥረው የሚሰሩም በርከት ያሉ ዜጎች ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ምን ተጨማሪ አቅም እንዳለ እና ምን መሰራት እንዳለበት በጥናት እየተለየ ነው። በአጠቃላይ ለአሠራር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ አደረጃጀቱን መቀየር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ባለው አሠራር የኢንተርፕራ ይዞች ፍላጎትና የኤጀንሲው እንቅስቃሴ ተጣጥሟል ብለው ያስባሉ?
አቶ ሐሺቅ፡– መንግስት የሚያቀርበው የመስሪያ ቦታና ፍላጎት አለመጣጣሙ ነገር ከፍተኛ ነው። በዚህም በመረጃ የለየነው ከመስሪያ ቦታ ድጋፍ ጋር ሦስት መሰረታዊ ችግሮች አሉ። አንደኛው ማልማት ሲሆን ይህም መሬት ልየታ ጀምሮ ችግር አለ። ይህን ለመለየት የሚያስችል ዝግጅት አጠናቀን ወደ ሥራ ገብተናል። ለንግድ የሚውል ቦታ መምረጥ ይጠይቃል። በተገኘ ቦታ ላይ መሥራትና ወጣት ሥራ ማስጀመር ነበር። አንዳንድ ቦታ መስሪያ ቦታ እያለ ለተጠቃሚ መፀዳጃ የለም። መስሪያ ቦታ እያለ ምርት ማከማቻ የላቸውም፤ አንዳንዶቹ መስሪያ ቦታ እያላቸው የሠራተኛ መመገቢያና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና መስጫ ቦታ እንኳ የላቸውም። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ነገር ይጎድለዋል። በዚህም ከቦታ መረጣ ጀምሮ እንዴት መደራጀት እንዳለበትና ለምን አገልግሎት መሆን አለበት የሚለው ላይ በጥናት ተመስርቶ ለመፍታት ደረጃ እየወጣ ነው።
ከቦታ አስተዳደርና መስሪያ ቦታ ሲሰጥ አስፈላጊውን ደረጃን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት። ለምሳሌ በጨርቃጨርቅ የተሰማራ አንድ ዜጋ ከነመስሪያ ማሽኑ ንግድና ኢንዱስትሪ ባወጣው መሰረት አራት ካሬ ነው። በጥቃቅን ከተደራጀ ደግሞ እስከ አምስት ነው፤ አነስተኛ ካልን እስከ ሦስት ሲሆን መካከለኛ ካልን ደግሞ ከ30 እስከ 100 ሰዎችን ያካትታል። ግን ይህ ወጥ በሆነ መንገድና በኢንቨስትመንት ህግ አኳያ በቂ አይደለም። በዚህም ደረጃ እየተሠራ አይደለም።
ይህ ሽግግሩ እንዲንቀራፈፍና ሀገሪቱ መጠቀም ካለባት አኳያ ዝቅተኛ እንዲሆንና ቦታ እንዲባክን አድርጎታል። ዜጎችም ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። ተጠያቂነት ያለውና ከፍትሃዊ የመስሪያ ቦታ መስጠት አኳያም አመራሩ የሚሰራው ሥራ በቂ አይደለም። አመራሩና ፈፃሚውም በዚህ ደረጃ መገንዘብ እንዳለበት በማሰብ ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ይህንንም ለማሻሻል በአሰራር ሥርዓት እንዲስተካከል የተደረገ ጥሩ ጅምር አለ። ቦታ የሚሰጥና የሚያደራጅ አካልም በተጠና መንገድ እንዲካሄድ አሰራሮች እየተበጁ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኤጀንሲ ዓለም አቀፍ ደረጃ የተላበሱ ኢንተርፕራይዞችን ለማብቃትና በአንድ ቦታ ለማሰባሰብ የሚያስችል አሰራር ለምን አይከተልም?
አቶ ሐሺቅ፡– ብዙ አዳዲስ አሰራሮች እየተተገበሩ ነው። ዘመናዊ የክላስተር ማዕከላት ተለይተው ከሚቀጥለው በጀት ዓመት ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገቡበት ዘመናዊ ክላስተር ይገነባል። ነባር የሆኑ 15 ማዕከላትን የማዘመን ሥራ ይሠራል። በመሃል ከተማ የቦታ እጥረት ባለባቸው ከግል ባለሃብት ጋር በመሆን ዘመናዊ ሞሎችን ለማልማት የሚያችስል ሥርዓት ወደ ተግባር ይገባሉ። እርጅና የተጫጫናቸውን ደግሞ በዘመናዊ መንገድ በማደስ ለከተማዋ የሚመጥን አደረጃጀትና መሥሪያ ቦታ ይሠራል። የከተማዋ ፕላን የሚመጥን ሜጋ ፕሮጀክት የሚሰራ ሲሆን 100 ሄክታር ላይ የሚያርፍ ክላስተር ማዕከል ለመገንባት ታስቧል።
ከተማ አስተዳደሩም በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ ለመግባት ከጫፍ ተደርሷል። ለዚህም ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ተወስዶበታል። ለዚህም ግንባታ ማኑፋክቸሪንግ ሼዶችና ህንፃዎች፣ ኬሚካል፣ አግሮ ፕሮሰሲን፣ ምግብ ማቀናባሪያ የሚሰሩበት ሲሆን ሁሉም በአስፈላጊነቱ ይከፋፈላል። በዚህም የራሱ የሆነ ኃይል ማከፋፈያ፤ ሕፃናት መዋያ፣ አዳዲስ ሃሳብ አፍላቂዎች ወደ ቴክኖሎኖጂ ልማት የሚገቡበት ምቹ ሁኔታ አለው። መሸጫና እና ማሳያ፣ ካፌዎችን ቢሮዎችንና ሌሎችን ግንባታዎችን ያካተተ ነው። ይህም የሚገነባው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነው። በዚህም ለ40ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን ለ800 ኢንተርፕራይዞች የሚሆን ነው።
ይህ ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀ በመሆኑ ለከተማ አስተዳደሩ በተለያየ መንገድ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ አለው። በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማት ትኩረትም ወደ አዲስ አበባ እንዲያደርጉ ሚናው ከፍ ያለ ነው። ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ትልቅ ነው። ተበታትነው የተቀመጡ ኢንተርፕራይዞችም በአንድ አካባቢ ለመሰባሰብ ጥቅም አለው። ለአሰራርና ድጋፍ ለማድረግም ይህ ምቹ ሁኔታን ይፈጥል።
ለዚህ አጠቃላይ ሥራ አምስት ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። ግንባታውን ለማከናወንም ብዙ አሰራሮች የሚኖሩ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ በራሱ ወጪ የሚያከናውነው ሊሆን ይችላል። ይህም ካልሆነ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከውጭ ብድር አግኝተው የተገነቡበት መንገድም ሌላኛው አማራጭ የመሆን ዕድል አለው። ከግል ባለሃብቶች ጋርም በጋራ ለመስራት የሚያስችል አሠራር ሊሰሩበት የሚችሉበት መንገድም ዝግ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– 100 ሄክታር መሬት ለመረከብ ካሣ መክፈል፣ ወሰን ማስከበርና ተያያዥ ጉዳይ እንዲህ ቀላል ይሆናል?
አቶ ሐሺቅ፡– ይህ ቀደም ሲል 42 ሄክታር በሌላ ፕሮጀክት ካሣ ተከፍሏል። ዋናው ነገር ይህ የኢንዱስሪ ክላስተር ሲለማ የሚኖረው ፋይዳ ነው። ክላስተሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዕድገት ወሳኝ ነው። የተቀናጀ ድጋፍ ለማድረግም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ኢኮኖሚያዊ መሰረት ይዞ የሚሄድ ሲሆን ዘርፈ ብዙ ትርጉም ይኖረዋል። በመሆኑም ካሳ መክፈሉ ከሚሰጠው ጥቅም አኳያ ሲታይ ብዙም አነጋጋሪ የሚሆን አይደለም። በዚህም ካሳ መክፈሉ ተገቢ ይሆናል። በዚያው ልክ ከዚያ የሚነሱትም ተተቃሚ የሚሆኑበት አሰራር አለ።
አዲስ ዘመን፡– በርካታ የመስሪያ ቦታዎች ካርታ እንደሌላቸው ይነገራል። ይህ ለምን ሆነ?
አቶ ሐሺቅ፡– ትክክል ነው። አብዛኛው ቦታ በጊዜያዊነት ተሰርቶ ወጣቱ እንዲገባበት የተደረገ ነው። በዚህም የቦታ ባለቤትነት ካርታ መያዙ ላይ ችግር አለ። ባደረግነው ቆጠራ ካሉት መሥሪያ ቦታዎች ካርታ ያላቸው 28 ከመቶ የሚሆኑት ናቸው። አንዳንዱ በጊዜያዊነት የተሰጠ ስለሆነ ካርታ ላይኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ በጋራ የመኖሪያ ቦታዎች አካባቢ ክፍት ቦታዎች ላይ ብሎኬትና ፕሪካስት እንዲያመርቱበት እናደርጋለን። ይህ ቦታ ግን የትምህርት ቤት፣ አረንጓዴ ቦታ ሊሆን ይችላል። መሰል ቦታዎችን ለይተን ካርታ የማናገኝባቸውንና የማይገቡንን እየለየን ነው። በሌላ ጎኑ በርካታ ቦታዎች እየለየን ካርታ የሚመለከተንን እንድንጠቀም እያደረግን ነው። ካርታ የማናገኝበትን ደግሞ ለመሬት ባንክ እያስረከብን ነው። በዚህ ዓመት 29 መስሪያ ቦታዎች ለይተን የመስሪያ ቦታዎች ካርታ አግኝተናል።
አዲስ ዘመን፡– ከመስሪያ ቦታዎች አኳያ የባለቤት ጥያቄ የሚነሳባቸው ስለመኖራቸው ይነገራል። ይህ አንዴት ሊሆን ቻለ?
አቶ ሐሺቅ፡– መስሪያ ቦታ ቆጠራ አካሂደን ብዙ ነገሮችን አይተናል። ዘመናዊ አድርገን ማልማት ያለብን አለ። ካርታ መያዝ ያሉብን አሉ። በአዋጅ ስልጣን ተሰጥቶን ያልተረከብናቸው ችግር የሆኑብን ባለቤት አልባ የሆኑ ሱቆች አሉ። በሊዝ ውል ለአምስት ዓመት የተሰጡ ሼዶችም አሉ። የመሬት ልማት ማናጅመንትም መሰል ቦታዎችን ለእኛ እንዲያስረክብ መመሪያው ፀድቆ ሲጠናቀቅ የሚከናወን ነገር ይሆናል። በመመሪያው መሰረት በባለቤትነት የምንመራው ሲሆን ለጊዜው ለአሰራር እየተቸገርን ነው። ከዚህ በዘለለ ግን ህግን ተከትለው የማይሰሩ ኢንተርፕራይዞች አሉ። ውል መዋዋል የማይፈልጉና መኖራቸውን በመገንዘብ ወደ ህግ አግባብ የሄደ አለ። አሁን ባለው ሁኔታ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ የምንገኘው አለ። የፍትሃብሄር ጉዳይ ስለሆነና የኮረና ቫይረስ ሥርጭትም ተደማምሮ ረጅም ጊዜ ወስዷል። ከዚያ ፍርድ ቤት በሚወስነው መሠረት ወደ ሥራ እንገባለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ለኤጀንሲ ትልቁ ፈተና ምንድ ነው?
አቶ ሐሺቅ፡– ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ተገንብተው የተቀመጡና መሰረት ልማት ያልተሟላቸው 500 መስሪያዎች ነበሩ። ቀደም ሲል ክፍያ የተፈፀመባቸው ከ48 ትራንስፎርመሮች እንዲገጠሙ በታቀደው መሠረት 48 ሙሉ በሙሉ ተገጥመው ኢነርጃይዝ ተደርገዋል። 365 ቆጣሪዎችም ጭምር ተገጥመው ኢነርጃይዝ ተደርገዋል። በ2013 በጀት ዓመት ብቻ ለኃይል አቅርቦት የሚያገለግሉ 22 የተለያዩ መጠን ያላቸው ትራንስፎመር እና 193 ባለ 3 ፌዝ እና ሲንግል ፌዝ ቆጣሪ ግምት እንዲገመት ግብ የተቀመጠ ሲሆን በዕቅዱ መሠረት የ22 ትራንስፎርመሮች እና 193 ቆጣሪዎች ግምት እንዲገመት ታቅዶ የ22 ትራንስፎርመሮችና 115 ቆጣሪዎች ግምት የተሰራ ሲሆን የ15 ትራንስፎርመር እና የ97 ቆጣሪዎች የግምት ሥራ በሂደት ላይ ይገኛል።
በሌላ በኩል ከግምት ባሻገር ክፍያ ተፈጽሞ ወደ ተግባር በመግባት 17 ትራንስፎርመሮች በየሳይቱ ተገጥመው ኢነርጃይዝ የማድረግ ሥራ ማከናወን ተችሏል። በተጨማሪም በመስሪያ ቦታዎች ትራንስፎርመሮች እንዲገጠሙና ኢነርጃይዝ እንዲደረጉ ክትትል በማድረግ ማረጋገጥ አቅደን ስንሠራ የነበረ ሲሆን በየወሩ ሁለት ጊዜ የጋራ መድረክ ላይ በመገኘት ትራንስፎርመሮችና ቆጣሪዎች ኢነርጃይዝ እንዲደረጉ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
በዚሁ መሰረት 65 ትራንስፎርመሮችን በመትከል እና 383 ቆጣሪዎችን በመግጠም ኢነርጃይዝ የማድረግ ሥራ የተሰራ ሲሆን፤ የ15 ትራንስፎርመሮችና 97 ቆጣሪዎች የመግጠም ሥራ በሂደት ላይ ይገኛል። ይህም የክትትልና ድጋፍ ሂደቱ ጥንካሬ እና የተግባሩ ይህ ዋንኛው ለኢንተርፕራይዞች ችግር መሆናቸውን ተገንዝበን እየሰራን ነው። ሆኖም አሁንም ድረስ በመብራት ረገድ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በመገንዘባችን እየሰራን ነው።
በአጠቃላይ ተከማችተው የነበሩና ክፍያ የተፈጸመባቸው 52 ትራንስፎርመሮች እና 276 ቆጣሪዎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 33 ትራንስፎርመሮች ተተክለውና ኢነርጃይዝ የተደረጉ ሲሆኑ 15 ትራንስፎርመሮች ሳይቱ ድረስ ሄደው እንዲተከሉ ተደርጓል። እንዲሁም 4 ትራንስፎርመሮች ተመድበው የቅድመ ተከላ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ከ276 ቆጣሪዎች ውስጥ 93 ቆጣሪዎች ተለጥፈውና ኢነርጃይዝ ተደርገው ለአገልግሎት ዝግጁ የተደረጉ ሲሆን 183 በተለያዩ ግብዓት ችግር ምክንያት የዘገዩና ለመለጠፍ ዝግጁ የሆኑ ናቸው። ሆኖም አሁንም ቢሆን 20 የሚሆኑ ሳይቶች መብራት የማሟሏት ሥራ ይቀረናል።
አዲስ ዘመን፡– ከህግ አግባብ ውጭ የተያዙ ለሦስተኛ ወገን የተላለፉ ሼዶች መኖራቸው በተደጋጋሚ በቅሬታ የሚነሳ በመሆኑ በዚህ ላይ ምን እየተሰራ ነው ?
አቶ ሐሺቅ፡– በዚህ በጀት ዓመት በስፋት መሥራት እንዳለብን በማሰብ፤ ህጋዊነትን ያልተከተሉ 1000 በላይ ኢንተርፕራይዞችን ቦታ ማስለቀቅ ተችሏል። በዚህም 58ሺ ካሬ ቦታ ለ1ሺ719 ኢንተርፕራይዞች አስተላልፈናል። በዚህም 6ሺ600 አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል። በእርግጥ ህወገጥነትን መከላከል የኤጀንሲው ሥራ ብቻ አይደለም። በአሠራሩ መሰረት በአንድ መስሪያ ቦታ አምስት ዓመት የቆየ መሸጋገር አለበት። እንዲሸጋገር ቦታ መዘጋጀት አለበት ለዚህ ግን በቂ ቦታ የለም። መሰረተ ልማት ማሟላት ላይም ችግሮች አሉ።
በሌላ ጎኑ ደግሞ የመስሪያ ቦታ የሸጡና ለሌላ አካል ያስተላለፉ አሉ። እነዚህን በህግ አግባብ ክስ መስርተን ወደ ፍርድ ቤት ስንወስድ ደግሞ ሁኔታዎች እየተወሳሰቡ ጊዜ እየወሰደ ነው። ሆኖም ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች አካላት ጋር በመሆን የጋራ ሥራ እየሰራን ነው። ሆኖም አሁንም ቢሆን ችግሮች መኖራቸውን አይካድም። አምስት ዓመት ሞልቷቸው በዚያው የሚረግጡና መሸጋገር የማፈይልጉም መኖራቸው ለማየት ችለናል። 3ሺ350 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞችን በጥናት ለይተን በጥናታችን 2ሺ800 የሚሆኑት ወይንም 78 በመቶ የሚሆኑት በአሁኑ ወቅትም ሳይሸጋገሩ በዚያው በጥቃቅን ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። በመሆኑም በዘላቂነት መፍትሄ ለማበጀት ቅንጅታዊ አሠራር መከተል አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ያሉት ኢንተርፕራይዞች ለከተማዋ በሚመጥን ዕድገትን ማመንጨት በሚገባቸው ገቢ ልክ የተደራጁ ናቸው ?
አቶ ሐሺቅ፡– ከቦታ አሰጣጡ ጀምሮ ላለፉት 15 ዓመታት የተከማቹ ችግሮች አሉ። እንዲህም ሆኖ ቀላል ሚና የላቸውም። 23ሺ ኢንተርፕራይዞች አሉ። በዚህ 48ሺ ዜጎች ተደራጅተዋል። በየቤተሰቡ ያለው አምስት ሰው ቢሆን 200ሺ በላይ ሰዎችን መመገብ የቻለ ነው። ከዚህ አልፈው ደግሞ ዓለም አቀፍ ገበያ ድረስ ሰብረው የገቡ አሉ። የህክምና መሳሪያዎችን እያመረቱ ወደ ውጭ የሚልኩ አሉ። ከዚህ መለስ ደግሞ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። መሸጋገር ያልቻሉት ደግሞ ቢያንስ የዕለት ጉርሳቸውን ይሸፍናሉ። ግን እነዚህን ቦታዎች ራዲካል በሆነ መንገድ ለመለወጥ መሥራት እንደሚገባ ግልፅ ነው። ለዚህም አሰራር እየዘረጋን ነው። በዚህ ረገድ ስናይ ለከተማዋ የሚጥን ነው ወይ ብሎ ለመናገር ጥናት ቢያስፈልግም የራሱ የሆነ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ማመን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በአሁኑ ወቅት ባለው አሠራር ኢንተርፕራይዞችን ወደተፈለገው አቅጣጫ ማሸጋገር ይቻላል?
አቶ ሐሺቅ፡– አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቀደም ሲል የነበረው አሠራር መቀጠል አለበት ብለን አናስብም። አሰራሮችን በማስተካከል ተወዳዳሪነት የታከለበት ስልት መከተል አለብን። በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ባሉበት ከተማ ሳይሸጋገሩ የሚቆዩ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸው ለሀገርም ሆነ ለራሳቸው ጠቃሚ አይደለም። ለዚህ ድጋፍ አድርጎ የጎደሉትን በማሟላት የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይገባል። የመስሪያ ቦታዎችም ሥራ ፈላጊዎች ስለተደራጁ ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪ የሆኑትን ማስቀደም ያስፈልጋል።
ከመስሪያ ቦታዎች ግንባታ አኳያም በመንግስት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ባለሃብቶች ሊሳተፉበት የሚችል አሰራር መዘርጋት ተገቢ ነው። ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የተላበሱ ኢንተርፕራይዞችን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ማከናወንም ይገባል። ኢንተርፕራይዞችን አቅም የሚፈጥርና ችግራቸውን የሚፈታ አሰራር መከተል ተገቢ ነው። በዚህ ደረጃ እያሰቡ መስራትና መትጋት ግዴታ ነው። በስትራቴጂክ እቅዱም ይህን ታሳቢ የተደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ይህ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– ከከተማዋ ዕድገት አኳያ የኤጀንሲ የስትራቴጂክ እቅድ ምንድን ነው?
አቶ ሐሺቅ፡– ኤጀንሲው በቀጣይ 5 እና 10 ዓመታት ሊደርስበት የሚፈልገውን ደረጃ ለመተለምና ይህንንም ለማሳካት የልማት ዕቅድ ለማዘጋጀት በተቀመጠው ግብ መሠረት የ5 እና የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ረቂቅ አዘጋጅቷል። ረቂቁ ለማኔጅመንት ቀርቦ አስተያየት እንዲሰጥበት ከተደረገ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች መሠረት ሰነዱን የማዳበር ሥራ ተሠርቷል። በማኔጅመንት በተሰጡ አስተያየቶች መሠረት የዳበረው ስትራቴጂክ ዕቅድ የኤጀንሲው ሠራተኞች እንዲሁም የክፍለ ከተሞች አመራሮችና ባለሙያዎች በተሣተፉባቸው ውይይቶች የተገኙ ግብዓቶችን የማካተት ሥራ ተሠርቷል። በዚህም በቀጣይ ሊሰሩ የሚችሉ ነገሮችን የሚያመላክት ሲሆን አስፈላጊ ስራዎች ይሠራሉ። በአጠቃላይ ለዘመነች ከተማ የሚመጥኑ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ የሚገቡበትና የተወዳዳሪነት መንፈስ የተላበሱ አንቀሳቃሾች እንዲበራከቱ በ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅዱ በስፋት የሚከናወን ሥራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ሐሺቅ፡– እኔም አመሠግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013