ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ አስከአሁን በአንድነት ባደረጉት ተጋድሎ የአገራቸውን ሉዓላዊነት ሳያስደፍሩ ቆይተዋል። የአገር ደንበር ጥሶ የመጣውን የውጭ ወራሪ ኃይልም መክተውና አሳፍራው መልሰዋል። በአገኙት አኩሪ ድልም የኢትዮጵያን አንድነትና ነፃነት አስጠብቀው ቆይተዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቀኝ ያልተገዛች አገር ተብላ የምትታወሰውም አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነትና ባሳዩት ህብረት የመጣ ስኬትና ድል ነው።
ዛሬም ኢትዮጵያ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟታል። ግብፅና ሱዳን ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ሴራ እየጎነጎኑብን ይገኛሉ። አሜሪካም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ገብቼ ካልፈተፈትኩና የታላቁ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ በሚመለከት ለግብፅ ውግንናዬን አሳያለሁ እያለች ትገኛለች። ሰሞኑን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር በባለስልጣናት ላይ የጉዞ ክልከላና ተያየዥ ማዕቀብ ጥላለች። ይህን ተገቢ ያልሆነ ጫናም በአገርም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሟቸውን እያስሙ ይገኛሉ። በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግሥትን አቋም በመደገፍ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና በመቃወም በጣሊያን ፣ በካናዳ፣ በስዊድንና በአሜሪካ ከተሞች ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት፣ የሱዳንን የድንበር ወረራ እና በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ሱዳን እና ግብፅ እየሄዱበት ያለውን ሴራ እና የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ከሞያ ስነምግባር ባፈነገጠ መልኩ የሚያቀርቡትን ዘገባ ተቃውመዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከምዕራባውያን ጫና ሊደረግባቸው ሳይሆን ለተፈናቀሉ እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እገዛ የሚፈልጉበት ወቅት መሆኑንም ገልጸዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ሙሌት በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድና ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።
ዲያስፖራው በአገሩ ላይ የሚያደርገው የልማት ሥራና ተሳትፎ በተለይ ከለውጡ በኋላ እየጨመረ መጥቷል የሚሉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት፤ ዘንድሮ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ግዢ በመፈጸም ድጋፋቸውን ማሳየታቸውን ግልጸዋል።
በ2012 ዓ.ም 800 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መሰብሰቡን አስታውሰው፤ ዘንድሮ በስምንት ወራት ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ከዲያስፖራው መሰብሰቡን ነው የነገሩን። ከዓምናው ጋር ሲነጻጸርም ልዩነቱ ከፍተኛ መሆኑንም አውስተዋል።
ዲፕሎማሲውን ከመደገፍ አንጻርም ዲያስፖራው የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው። በተለይ የታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ የሚደርሱ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ከመከላከል አኳያ በአረብ ሚዲያዎች የሚተላለፉ የተዛቡ መረጃዎችን በማረቅና የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋም በማንጸባረቅ ረገድ በአረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው። በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ዲያስፖራዎችም ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታና ከህግ ማስከበሩ ዘመቻ ጋር በተያያዘ የሚነዙ የሀሰት መረጃዎችን ተከትሎ በአሜሪካ የሚደርሱ ጫናዎች በመቃወምም ሆነ እውነታውን በማሳወቅ ረገድ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ ነው ሲሉ ገልጸውልናል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መግባቷ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከመዳፈርም ባለፈ አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ይፈታሉ የሚለውን
እሳቤ የሚጎዳና የናቀ ነው በሚል መቃወማቸውን አመልክተው፤ ዲያስፖራው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እገዛ እንዲደረግ፣ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል እንዲሁም የኢትዮጵያ አንድነት ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን እንደሚቆሙ እና መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቃል መግባታቸውን አውስተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ዕቀባ መጣሉንና በሃገሪቱ እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባቱ ከሉዓላዊነት ጋር የሚፃረር አደገኛ አካሄድ መሆኑን ሠልፈኞቹ በጽኑና በአንድነት እንዳወገዙ ገልጸውልናል።
የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች መሠራታቸው ለዓለም ማህበረሰብ ግልጽ ሆኖ እያለ፣ የአሜሪካ መንግሥት ይሄንን ወደ ጎን በመተው በሉዓላዊ ሀገራት ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ የመግባቱ ጉዳይ በቀጣናው ላይ ከፍተኛ የፀጥታ ችግሮችን የሚያስከትል መሆኑንም ጭምር ያንጸባረቁበት ሰልፎች መካሄዳቸውን ነግረውናል። ዲያስፖራዎች አሜሪካ እጇን ከኢትዮጵያ እንድታነሳ ለአሜሪካም ሆነ ለሌሎች መንግሥታት የፃፉትን የተቃውሞ ደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት በመስጠት ጭምር ትግል እያካሄዱ እንደሚገኙ ጠቅሰውልናል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በትግራይ ክልል አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ያደረሰውን ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን የሕግ ማስከበርና ወንጀለኞቹን ለሕግ የማቅረብ ሕጋዊ ርምጃ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአሜሪካን መንግሥት እውነታውን በትክክል ሳይመረምር በተሳሳተና እውነትን መሠረት ባላደረግ ሁኔታ የኢትዮጵያን መንግሥት ከአሸባሪዎች እኩል በመመልከት ማዕቀብ መጣሉ ስህተት መሆኑንም መግለጻቸውን አስታውሰዋል።
ሰልፈኞቹ በመልዕክታቸው ወቅቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ የዜጎቿን ድጋፍ የምትፈልግበት ጊዜ መሆኑን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም የሃይማኖት፣ የብሔርና የፆታ ልዩነት በአንድነት በመቆም ድጋፉን ማድረግ እንዳለበት፣ አሜሪካም ሆኑ ሌሎች ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ የሚፈልጉት ሀገሪቱ ደሃ በመሆኗ መሆኑን፣ መንግሥት ሃገሪቷን ከድህነት ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት በተለያየ መንገድ እንደሚደግፉና ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ብቻ እንደሚልኩ አረጋግጠዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ሙሊቱ እንዲካሄድና ፕሮጄክቱም እንዲጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ በመጨረሻም ሰልፈኞቹ በሀገራቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና እስካልቆመ ድረስ ተመሳሳይ ዝግጅቶችን በሰፊው ለመቀጠልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ ለመሆን ቃል መግባታቸውን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያዊያን መካከል የፖለቲካ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ልዩነቱን ማንጸባረቅ የምንችለው አገር ስትኖር ነው የሚሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ የትኛውም አካል ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት የአገርን ገጸታ ማበላሸትና ለውጭ ኃይል አሳልፎ መስጠት ሳይሆን አገርን ክብርና መልካም ገጸታ ጠብቆ ልዩነቶችን በውይይት መመፍታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ስለዚህ በየትኛውም አገር ያለ ዲያስፖራ የአገሩን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013