ከሰሞኑ የሀገራችን ዋና የመወያያ አጀንዳዎች መካከል በአሜሪካ የተጣለብን ማዕቀብ ጉዳይ ተቀዳሚ ተጠቃሽ መሆኑን ልብ ይሏል። ውይይት ከማለት ይልቅ ቁጭት ያዘለ የጥቃት ምላሽ አስተያየቶች ማለቱ ይቀላል። ዜጎች በተገናኙ ጊዜ ሁሉ ዋና የውይይት ርዕሰ ጉዳይ አድርገው ሲነጋገሩ የሚስተዋለውና የሚደመጠው በዚሁ “የተጠቃን ጉዳይ ዙሪያ” መሆኑ የጉዳዩን አሳሳቢነት አመላካች ነው። በአዲስ አበባ ስቴዲዬም የተደረገው የሕዝባዊ ተቃውሞ ትዕይንተ ሕዝብም ከዚሁ የዜጎች ቁጣ የገነፈለ ስሜት ውጤት ነው። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የኢትዮጵያዊንና የትውልደ ኢትዮጵያዊያን መሰል ቁጣ ገላጭ ሕዝባዊ ትዕይንቶች እየተደረጉ ያሉትም ብሔራዊ ጥቃትን ርቀት እንደማይወስነው ጥሩ ማሳያ ነው። ኢትዮጵያዊያን በክፉ ቀን ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድ ላይ ለመቆማቸው ጥሩ ማስረጃና ማሳያ ስለሆነም በትልቅ አክብሮት ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው።
ሀገራዊ ሚዲያዎቻችን በተመለከተ ግን ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኞቹ ከሞላ ጎደልና በነካ ለቀቅ ርዕሰ ጉዳዩን እየጣሉና እያነሱ ከመነካካታቸውና ከመዳበሳቸው በስተቀር የሕዝቡን የቁጣ ግለትና ስሜት እንደሚገባው እያንጸባረቁ ነው ለማለት በግሌ አልደፍርም። ሙከራቸውና ጥረታቸው ባይከፋም ብዙዎቹ የሀገራችን መገናኛ ብዙኃን ከያዛቸው አጠቃላይ የጋራ ድብርት ሙሉ ለሙሉ ተላቀው ራሳቸውን ነፃ የሚያወጡበትን ጊዜ ብንናፍቅ አይፈረድብንም።
በዚህ ጸሐፊ ግርድፍ ዳሰሳ መሠረት ዓለምን ከዳር ዳር ያነጋገረው ይህን መሰሉ የአሜሪካ ውሳኔ “ሦስተኛዋ የዓለማችን የዲፕሎማቲክ ማዕከል” እያልን በምናንቆለጳጵሳት አዲስ አበባችን ውስጥ ለሚገኙት የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ምን ትርጉም እንደሰጣቸውና ምን መልእክት እንዳስተላለፈላቸው ትንታኔያቸውን ወይንም ሃሳባቸው እንዲገልጹ ሚዲያዎቻችን ደፍረው ሁኔታዎችን ለምን ሊያመቻቹ እንዳልሞከሩ ግልጽ አልሆነልኝም። ለመሆኑ “አንድ ከተማ የዲፕሎማቲክ መናሃሪያ” ነች ማለቱ ብቻ ለእንዲህ መሰሉ ከፍ ያለ ተግዳሮት ጥቅም ላይ ካልዋለ በስተቀር ምን ፋይዳ ይኖረዋል? የግድ እድሉን ከቱሪዝም ሃብት ምንጭነትና ከፖለቲካ ድል ጋር ብቻ እያስተሳሰርን እስከ መቼ ስንፎክር እንኖራለን።
እንኳንስ የወዳጅ ሀገራትን ዲፕሎማቶች ቀርቶ ለፍላጎታችን ተጻራሪ በሆነ አመለካከት ውስጥ ያሉትን እንኳ በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ቀርበው ሃሳባቸውን ቢገልጹና ዜጎች ሙሉ እውቀት እንዲኖራቸው ቢደረግ ክፋቱ ምኑ ላይ ነው? አብዛኞቹ ጋዜጠኞቻችንስ ከባዕዳን ቋንቋዎች (እንግሊዝኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ቻይንኛም ሆነ ሩሲያኛ ወዘተ.) እስከ መቼ እንደተኳረፉ ይኖራሉ።
በዩኒቨርሲቲያቸው ስኬት ነጋ ጠባ የሚያደነቁሩን የሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቋንቋ ጥናት መስክ አፍርተው ወደ ገበያው ውስጥ የሚቀላቅሏቸውን “ልጆቻቸውን” ሲያስተውሉስ ምን ይሉ ይሆን? በግሌ አዲስ አበባ የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ መዘውር (Hub) ነች እያልን ማቅራራቱን ገታ አድርገን ምን ተጠቀምንበት ብሎ መጠየቁ አግባብ ይመስለኛል። የጋዜጠኞቻችን የቋንቋ ክህሎት ጉዳይም ከመንግሥት ተቀዳሚ አጀንዳዎች አንዱ ሆኖ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል ባይ ነኝ።
የብዙ ሀገራት ልምድ የሚያሳየው ሚዲያ የማሕበረሰቡ መሪና አቅጣጫ ጠቋሚ እንጂ በመሪዎችም ሆነ በፖለቲከኞች ሳንባ እየተነፈሰ “ይደልዎ!” በማለት ሲያሞግስ ወይንም “እርግማን እያዥጎደጎደ” ሲኮንን የሚውል “ሥራ ቤት” አይደለም። ለመንግሥታትና ለፖለቲካ ቡድኖች አጀንዳ በመስጠት ሲያሾራቸውና ሲሞግታቸው የምናስተውለው እውነታ ይሄንንው ነው። በዚህም ጠንካራ አቋማቸው ምክንያት የምርጫ ምልክት አውለብልበው በመመረጥ ሳይሆን የተጽእኖ ፈጣሪ “ጡንቻቸው” ከማየሉ የተነሳ ብቻ “ሚዲያ የማሕበረሰቡ አራተኛ መንግሥት ነው” የመሰኘትን “ሥልጣን ብቃት” ሊጎናጸፉ ችለዋል። የእኛዎቹን በተመለከተ ግን “ተከድኖ ይብሰል” ብሎ ማለፉ ይሻል ይመስለኛል።
ለአብነት ያህል የዚህቺን አሜሪካ ተብዬዋን “ጉዲት” ታሪክ ብንፈትሽ እንኳን ፖለቲካዋን፣ የውጭ ግንኙቷን፣ አጠቃላይ ማኅበራዊ ተራክቦዋን እየመራና እያስቀዘፋት ያለው የሚዲያው ዐውሎ ነፋስ እንጂ የፖለቲካው ጡንቻ ብቻ ያለመሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል። አንዱን ማሳያ ለማመላከት ያህል በአሜሪካ ታሪክ “የወተር ጌቱ ቅሌት” በመባል የሚታወቀውና የወቅቱን የፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን (እ.ኤ.አ 1972 -1974) ከምርጫ ጋር የተያያዘ ውርደት በረቂቅ የምርመራ ዘገባ ያጋለጡት ለሙያው የተሰጡ ጋዜጠኞች ነበሩ። ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣናቸው ፈንግሎ ያስወገዳቸውም ጠብመንጃ ሳይሆን የጋዜጠኞቹ የብዕር ብርታት ነው።
በሚዲያ ሙያ ላይ የተሰለፉ በርካታ የየሀገራቱ ትንታግ ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት በዘርፉ ያላቸውን ዲፕሎማና ዲግሪ ደረታቸው ላይ ለጥፈው “እዩልኝ ስሙኝ” በማለት ሳይሆን በተግባራቸው አቅም ልክ ነው። ያገዘፋቸውም የሰለጠኑበት የወረቀት ማስረጃቸው ብቻ ሳይሆን ተግባራቸውና ውጤታቸው ጭምር ነው።
የአሜሪካዎቹ CNN, FOX TV, NBC, CBC፣ የእንግሊዙ BBC፣ የፈረንሳዮቹ France 24, Euronews, የሩሲያው RT, የኳታሩ Al Jazeera፣ የቻይናው CNC World ወዘተ. መንግሥታቸውንና ሕዝባቸውን ብቻም ሳይሆን መላዋን ዓለም እንደ እንዝርት በአየራቸው ላይ እያሾሩ ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ዲፕሎማሲውን ሲንጡትና ሲዘውሩት ማስተዋል እንግዳችን አይደለም። አልፎም ተርፎ የራሳቸው ገመና እያረረ እንኳን የሌላውን ሀገር ጓዳ ለማተራመስ መትጋታቸውም የአደባባይ እውነታ ነው። በዚህ ዘመነ ሉላዊነት አሜን የሚሰኝለት የእውነት ዜና ብቻ ሳይሆን በሸፍጥ የተቀባባ ታሪክ ፈጣሪ “ጉልበተኞችም” ዙፋን ተዘርግቶላቸው ሲመለኩ የምናስተውለው በእነዚህ መሰል መሪ የሚዲያ ተቋማት አማካይነት መሆኑም ውሏቸው ምስክር ነው።
ሆደ ባሻዎቹ የሀገሬ መገናኛ ብዙኃን “ይሄና ያ አልተሟላልንም፣ የሰለጠንበትን የሰርተፊኬት ዋጋ ያህል ክፍያና መብታችን አልተከበረልንም ወዘተ.” እያሉ በብሶት ከመነፋረቅ ነፃ ወጥተው ልባቸውና ፊታቸው እንደፈካ መቼ “ሥልጣነ ብዕራቸውን” ወደ ተግባር እንደሚለውጡ ከመገመት ይልቅ የእንቆቅልሹን ፍቺ ለትውልድ አስተላልፎ ለጊዜ ጊዜ መስጠቱ ይቀል ይሆንን ብዬ አስባለሁ። “የቸገረው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ መሆኑን ሳልዘነጋ።
ሀገራችን ዛሬ በተለያዩ ውጥረቶችና ወጣሪዎች ተከባ እያለች እንኳ ወደ ቀልባቸው ተመልሰው የአየር ሰዓታቸውንና የኅትመት ውጤቶቻቸውን ገጾች በይፋ ወደታወጀብን “የጦርነት ግንባር ለማሰለፍ” ያለመቻላቸው ከትዝብት ያለፈ ሕዝባዊ ቅይማት እንደወደቀባቸው የተረዱት አይመስልም። የተጠናወታቸው የእንቅልፍ አዚምም በቀላሉ ይለቃቸዋል ተብሎ የሚገመት አይመስልም። በአብዛኞቹ የሀገራችን ባህሎች ውስጥ በራስ ቤት ቀርቶ በቅርብ ጎረቤት ዘንድ እንኳን ሀዘንና መከራ ሲደርስ የችግሩ ተካፋይ መሆንን ለማረጋገጥ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድምጽ ወይ ይቀነሳል አለያም ከነጭራሹ እንዳይከፈት ይደረጋል። ዘፈንና አስረሽ (“ረ” ይጠብቃል) ምቺውማ የሚሞከር አይደለም።
የሀገራችን ሚዲያዎችም ቢያንስ ቢያንስ ለዚህን መሰሉ ባህላዊ እሴት ዋጋ ሰጥተው ያለመፍጨርጨራቸው እነርሱ ባይረዱትም የእኛ የተራ ዜጎች ቆሽት ማረሩ የገባቸው አይመስልም። ኢትዮጵያችን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ታሪካዊ ጠላቶቿና ጊዜ ወለድ አጥቂዎቿ ካራቸውን ስለውና ጡንቻቸውን አፈርጥመው ከበባ በማድረግ “ሊውጧት” እየጎመዡ ባሉበት ፈታኝ ውቅት ለአውሮፓ የእግር ኳስ ክለቦች መውደቅና መነሳት የሚሰጠው የአየር ሰዓት ወይንም “ለእርዬ እርዬ” ሙዚቃዎችና ፌዞች የተመደበው ፕሮግራም ማስተካከያ ተደርጎበት የሀገር መከራ መወያያ መድረክ ሊሆን ባለመቻሉ ለእነርሱ “ልክ” ለእኛ ደግሞ መራራ እውነታ ሆኖብናል።
በዚህ ወቅት ከመዝናኛና ከማደናገሪያ ፕሮግራሞቻቸው፣ ከመሰዳደቢያና ከስፖርት ሜዳ ሽሙጦች ይልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሙሉ ኃይላቸውን አስተባብረው ለምን ላለመዝመት እንዳቅማሙ አዋቂው ፈጣሪና ልባቸው ነው። የወደረኞቻችንና የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሚዲያዎች ስለ ሀገራቸው እብሪትና ጥጋብ ነጋ ጠባ ሳይታክቱ ሲያገሱ እያስተዋልን የእኛዎቹ ሚዲያዎች ግን “ለሽ” ብለው ተኝተው እያንኮራፉ ይገላበጣሉ። ለኅሊናቸው ሳይሆን ለርካሽ ጥቅም የሰገዱ በርካታ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ባለሙያዎችና “የእኛዎቹ ስደተኛ የእንግዴ ልጆች” የኢትዮጵያን ጉዳይ ነጋ ጠባ በምላሳቸው ላይ አንጠልጥለው ሃሰተኛ ውንጀላቸውን ሲያጧጡፉ እያስተዋልን የሚገባውን ምላሽ ባለመስጠታችን እነሆ ውጤቱን ቢመረንም ልናጣጥም ግድ ሆኗል። ለዘብተኞቹ የእኛ ሚዲያዎች እስከ መቼ እንዲዚህ እንደሚቀጥሉ ግን ግራ ያጋባል።
በዚህ ክፉ ወቅት አየሩን ለዘፈን ምርጫ ገምሶ መስጠቱ፣ ለእንቶ ፈንቶ ዝባዝንኬ አትረፍርፎ መመደቡ፣ ለአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጎች ማበዱና መፈንጠዙ የሚያዋጣ ከሆነ ውጤቱን ወደፊት በጋራ እናየዋለን። የየሚዲያ ተቋማቱ ኃላፊዎችና የመገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ዝምታም በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ትዝብታችን ቁጣ ወልዶ ወደ ሾማቸው “የበላይ ጡንቸኞች” ሊወነጨፍ እንደሚችል ቢረዱት አይከፋም።
መዝሙረኛው ዳዊት “ጨካኝ ጉባዔተኞችም ክፋት መከሩብን” እንዳለው ይህ ወቅት ሀገራችንን በታሪኳ አጋጥሟት በማይታወቅ ሁኔታ (የንጉሥ ዳዊትን አባባል እንዋስና) “ ክፉ ጉባዔተኞችም ጥፋት የደገሱልን” ወሳኝ ወቅት ነው። ጠላቶቻችን የልብ ልብ ተሰምቷቸው ሰይፋቸውን በግላጭ የሚስሉት፣ ጠብመንጃቸውንም በአደባባይ የሚወለውሉት በማን አይዞህ ባይነት ተደፋፍረው እንደሆነ እውነቱ እየተገለጠልን መጥቷል። የእርስ በእርሳችን መናቆር የጠላቶቻችንን ልብ እንደ እንደ ፊኛ (ባሉን) እንዲያብጥ እንዳገዛቸውም ምሥጢሩ ተተርትሮልናል። በፖለቲከኞችም ሆነ በሃይማኖት መሪዎች አንደበት ሆን ተብለው የሚሰጡ አፍራሽና አዋራጅ አስተያየቶች ለከበቡን ኃይላት ምን ያህል የሞራል ስንቅ እንደሆናቸው ግምት ሳይሆን እውነታው ገሃድ እየወጣ ነው። “ጠልቶ ለጠላት፤ አስሮ ለእስራት ሰጡን” ይሏል የሀገሬ ሰው።
“ጠላት ሲነሳብህ የወዳጆችህን ቁጥር አበርክት!”
– ሀገራዊ ብሂል፤
አሜሪካ በሰብዓዊ አያያዝና በዲሞክራሲ አከባበር ዙሪያ ራሷን “የምድራችን መሲህ” አድርጋ ከሾመች ዘመናት ነጉደዋል። መሪዎችን ለማውገዝና ለመባረክ፣ ሀገራትን ለማክበርና ለማዋረድ ምልዑ በኩለሄ “ሥልጣነ ክህነት” እንዳላት በመቁጠር ዓለምን እያተራመሰች መሆኗ የአደባባይ ሐቅ ነው። “ዶላሯንና ኒኩሌሯን” በመተማመንም የእብሪት መለዮዋን ደፍታ “ራሷን በራሷ የዓለማችን ፖሊስ አድርጋ ሾማለች።”
እንደ ቅዱስ መጽሐፉ አገላለጽ “ለከበቡን ውሾች” የተጋጠ አጥንት እየወረወረች ጃስ በማለት ሉዓላዊነታችንን እንዲለክፉ አሳብዳቸዋለች። “የክፉዎች ጉባዔተኞችም” በስውርና በግልጽ ሲማማሉብን ኪዳን እያስገባች ታቆርባቸዋለች። በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ፊታቸውን ከፊታችን እንዲያዞሩ ለምትፈጽመው ደባና ሴራም እንደ ጥንቱ በረቀቀ ስልት የሚገለጽ ሳይሆን በይፋ የሚፈጸም ግብሯ ሆኗል።
እውነቷም እውነታችንም ይሄው ነው። ችግሩ የሩቅና የቅርብ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የተረዱት በተሳሳተ ግምት መሆኑ ላይ ነው። ለጉድለታችን እርዳታቸው ያስፈልገናል? አዎን ምን ያጠያይቃል። ከእኛስ በኩል መታረም የሚገባቸው ሀገራዊ ህፀፆች የሉም? ሞልተዋል እንጂ። ይሄ ሁሉ እውነታ እንዳለ ቢሆንም የሉዓላዊነታችን ክብር ግን በማንምና በምንም እንዲሸረሸርና እንዲረገጥ የምንፈልግ ቅኝ ተገዢዎቻቸው እንዳልሆንን በግልጽ ቋንቋ ሊነገራቸው ይገባል።
የእነርሱን የጥፋት ስንዝር የሚመክተው የአንድነታችን አቅምና የሰላማችን ዋስትና ስለሆነም በመጀመሪያ እኛ የእኛን የቤት ሥራ ሰርተን የወዳጅ ሀገራትን ቁጥር በማበራከት ይህንን የሚያልፍ ወጀብ ልንሻገር ያስፈልጋል። በፈጣሪ ተራዳኢነትም ስለምናምን ለፈርዖን ልጆች፣ ለማሃዲስቶቹም ሆነ ለያኒኪዎቹ ሰሞንኛ ‹ጠብ ያለሽ በዳቦ› ባዮች በጆሮ ሹክሹክታ ሳይሆን በሚያስተጋባ ነጎድጓድ ድምጽ “እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን! ሀገራችን ከእናንተ በፊት ነበረች ወደፊትም ትኖራለች! ትምክህታችሁና ሴራችሁ ለእኛ ውድቀት ሳይሆን ለራሳችሁ ውርደት እንዳይሆን ተጠንቀቁ” ብለን ልናረጋግጥላቸው ይገባል። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013