
አዲስ አበባ ፦አገሪቱን የሽብር ቀጠና ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ እና በጥብቅ ሲፈለጉ የነበሩ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት በጅቡቲ መንግስት በቁጥጥር ስር ውለው አዲስ አበባ መግባታቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን እንዳስታወቀው ፣ በትግራይ ክልል በሰሜን ዕዝ ላይ እና በፌዴራል ፖሊስ አባላት ላይ ድንገተኛ ጥቃት አድርሰው ወደ ጎረቤት ሀገር ከሸሹ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት መካከል 1ኛ.ሀብቶም ገብረስላሴ ወልዩ፣ 2ኛ. መሰለ ታመነ እሼቱ እና 3ኛ. ኮነሬል መሀመድ በሪሁ ኑር የተባሉት የወንጀሉ ተጠርጣሪዎች በጅቡቲ መንግስት በቁጥጥር ስር ውለው ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አመልክቷል።
በቁጥጥር ስር የዋሉትን የህወሓት አሸባሪ ቡድን አባላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተጠርጣሪዎችን ተረክቦ ጉዳዩን በህግ አግባብ የሚያጣራ መሆኑን ገልጿል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የደህንነትና የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው መያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸውን የህወሓት አመራሮችና የጦር መኮንኖችን ከተደበቁት ስፍራ በማደን ለህግ ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ. ም