
አዲስ አበባ ፦ ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋገጡ ። በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን አስታወቁ ።
ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ ትናንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ ጋር በተወያዩበት በወቅት እንዳስታወቁት ፣ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ ናቸው።
በአፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በተሰጣቸው ማብራሪያ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለመረዳት እንዳስቻላቸው አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በውይይቱም አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ በህዳሴ ግድብ፣ በህግ ማስከበር፣ በሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት ፣ ከሱዳን ድንበር ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ ያለበትን ደረጃ እና እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ የሙሌት ሥራ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኗን ገልጸው፣ ሙሌቱ የተፋሰሱን ሃገራት ጥቅም በማይነካ መልኩ እንደሚፈጸም ገልፀዋል።
ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አፈ ጉባዔው፣ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችም ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል።
ውይይታቸው ከሀጋራዊ ጉዶዮች በተጨማሪ ቀጠናዊና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ. ም