
አዲስ አበባ፡- የሃሳብ ድርቅ የመታቸው ሃይሎች ወደፊትም አደናጋሪ መረጃ ሰርተው ሊለቁ ስለሚችሉ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አስታወቁ።
ዶክተር ቢቂላ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ባለፉት ቅርብ ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ከዲጂታል ሚዲያው መስፋፋት ጋር በተያያዘ ሐሰተኛ መረጃዎችን ፈጥሮና ፈብርኮ፤ ቆርጦና ቀጥሎ እንዲሁም ገጣጥሞና አቀነባብሮ ፈጽሞ ሐሰት እና መሰረተ ቢስ የሆኑ መረጃዎችን ማሰራጨትና ህዝብን ማደናገር እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ነው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም ቦታ ማግኘት ያልቻሉ እንዲሁም የሃሳብ ድርቅ የመታቸው ኃይሎች ከቀናት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ነው ብለው ቆርጠውና ቀጥለው እንዲሁም ገጣጥሞና አቀነባብሮ ፈጽሞ ሐሰት እና መሰረተ ቢስ መረጃ መልቀቃቸውን ያስታወሱት ዶክተር ቢቂላ፤ መሰል አደናጋሪ መረጃ በቀጣይም ሊለቁ ስለሚችሉ ዜጎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
የሰሞኑን የሀሰት ቅንብራቸው የጥፋት ኃይሎች ከዚህ በላይ የሆነ ነገር ወደፊት ሊሰሩ እንደሚችሉ የሚያመላክት ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ፣ ይህን የሚያደርጉት በምንም አይነት በሃሳብ ፖለቲካው፣ በመርህ፣ በፖሊሲ፣ በስትራቴጂ በልጠው ተገኝተው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚገባቸውን ቦታ ማግኘት የማይችሉና የሃሳብ ድርቅ የመታቸው ስለሆኑ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ሐሰተኛ መረጃ መልቀቅ በተለይ በከፍተኛ ሁኔታ በዓለም ደረጃ ለሚዲያው ትልቅ ፈተና እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው። ይህ ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥም በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በብዙ እየጣረች ባለችበት በዚህ ወቅት በጣም የተረጋጋና እውነተኛ የሆነ የመረጃ ስርጭት በሚያስፈልግበት ወቅት እነዚህ አካላት ፍጹም ሐሰት የሆኑ እና መሰረት የሌላው መረጃዎችን በመፍጠር ህዝብን ማደናገር የጀመሩበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ውስጥ ሾልኮ የወጣ በሚል ሰሞኑን እነዚህ ሃይሎች የለቀቋቸው መረጃዎች በስብሰባው ላይ ያልተነገሩ ፤ በተለያዩ ወቅቶች፣ በተለያዩ መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጓቸውን ንግግሮችቸ ድምጾችን ቆራርጠው በመገጣጠም ሙሉ ዓረፍተ ነገር እንዲሆን በማድረግ የሰሩት እጅግ በጣም የወረደ፣ በጣም ተራና መሰረተ ቢስ ስራ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ሐሰተኛ መረጃ አቀናባሪዎቹ ይህን በሚያደርጉበት ወቅት የኢትዮጵያን ጥፋትና ውድቀት ከሚመኙ የውጭ ኃይሎች ጋር በእቅድ፣ በተግባር በፋይናንስ ተባብረው ሊሰሩ እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ አሁን የሆነው ነገር በአንድ በኩል ትልቅ ትምህርት ነውና ተሞክሮ ሊወሰድበት ይገባል ብለዋል።
ለወደፊት እንዲህ አይነት ነገር በቀላሉ ስለማይቆሙ እና ሊቀጥልም ስለሚችል ከዚህም የባሰና የተቀነባበረ ብሎም የተፈበረከ መረጃ ዜጎቻችንን ሊያጋጥማቸው ስለሚችል መንግስት የሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግሮች አዋጁን መሰረት አድርጎ የሚወስደው የማስተካከያ እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ዜጎች ራሳቸውን መጠበቅ እና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
መንግስት ህጋዊና አስተዳደራዊ አሰራር ተጠቅሞ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል፤ ነገር ግን ዜጎቻችንን እውነተኛ መረጃ የሚሰራጭበት ብቻ ሳይሆን ሐሰኛ መረጃም እጅግ በጣም ፈጣን በሆነ በብርሃን ፍጥነት እየተሰራጨ ያለበት ወቅት ስለሆነ በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በዲጂታል ሚዲያው የሚተላለፉ መረጃዎችን ትክክል ነው ብለው ከማመናቸው በፊት ምንጩን በሚገባ መመርመር፣ ማሰላሰል እንዲሁም ከሁለትና ከሶስት ምንጭ እውነተኝነቱን ማጣራት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል። መረጃውን በሚገባ ሚዛናዊነቱን አጣርተው እንዲቀበሉም ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት በለውጥ ሂደት ውስጥ አንዱ ተቋማዊ በሆነ መንገድ መመራት አለበት፤ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሂደቱ በእውነተኛ እና በሚዛናዊ በሆነ መረጃ መደገፍ አለበት ብሎ ከሰራቸው ስራዎች አንዱ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ቁጥጥር አዋጅ ማውጣቱ ነው። የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ቁጥጥር አዋጁ በዚህ መንገድ ምንጩ እውነት ያልሆነ፣ የተሳሳተና ህዝብ የሚያደናግር እንዲሁም ያልተገባ ስሜትና ግንዛቤ የሚፈጥር መረጃ በተለይ የመረጃው ባለቤቶችንም ሆነ ግለሰቦችንም ሆነ ተቋማትን ተጠያቂ የሚያደርግ የህግ አሰራር አለው ብለዋል።
ይህ የህግ አሰራር በተግባር መዋል ጀምሯል። በተለያየ አጋጣሚ ተለይተው እርምጃ የተወሰደባቸው የማህበራዊ ሚዲያዎችም ሆኑ ግለሰቦች አሉና ይህ ወደፊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
መንግስት ህግ የማስከበርና በዚህ መንገድ ህዝብን ለማደናገር፣ ግጭትና አለመግባባትን ለመፍጠር፣ በህዝብና በመንግስት መካከል ጥርጣሬን ለመዝራት የሚደረጉ ኃላፊነት የጎደላቸውን አሰራሮች ከዚህ ድርጊት ጀርባ ያሉ አካላት፣ ግለሰቦችንም ሆነ ተቋማት ለይቶ ህግ የማስከበርና በህግ አግባብ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚደረገውን አካሄድ ይከተላል። ይህንኑ አጠናክሮም እንደሚቀጥል አምናለሁ ብለዋል።
ዶክተር ቢቂላ፣ ከምንም በላይ ግን ዜጎች በግላቸው ኃላፊነትን መውሰድ አለባቸው። ዘመኑ የሚሰማው ነገር ሁሉ አሳሳች የሆነበት ጊዜ ነው። እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚፈበረኩ መረጃዎች በመኖራቸው በየትኛውም መንገድ የሚነገሩ መረጃዎችን ከመቀበላችን በፊት ደጋግሞ ማየትና እውነትነቱን ማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ. ም