
ወልቂጤ፡- የጉራጊኛ ቋንቋን ጠብቆ ለማቆየት፤ ወደፊትም የትምህርት፣ የስራና የቴክኖሎጂ ቋንቋ እንዲሆንና ከትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር እንዲቻል ቃላት የማሰባሰብ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ሃብቴ ዱላ ገለጹ፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጉራጊኛ ቋንቋ ኮርስ ቫሊዴሽንና የፎክሎርና የጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍልን ለመክፈት እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡
በዚህ ወቅት ዶክተር ሀብቴ እንደገለጹት፤ ዩኒቨ ርሲቲው በቴክኖሎጂ በመታገዝ የትኛውም ማህበረሰብ የጉራጊኛ ቃላትን ትርጉም የሚያገኝበትን ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል፡፡ ቴክኖሎጂው አማርኛ ቋንቋን ወደ ጉራጊኛ፣ እንግሊዝኛን ወደ ጉራጊኛ፣ ጉራጊኛን ወደ አማርኛና ጉራጊኛን ወደ እንግሊዝኛ መተርጎም የሚቻልበትን አቅም ለመፍጠር ያስችላል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በአ ዋጅ ሲቋቋሙ ከሚሰጣቸው ተልዕኮዎች መካከል የሚገኙባቸውን አካባቢ ማህበረሰብ በተለያዩ ጉዳዮች በትብብር አገልግሎት መስጠት ነው፡፡
የአካባቢውን ማህበረሰብ ቋንቋና ባህል መጠበቅና ማሳደግ የዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ተግባርና ኃላፊነት እንደመሆኑ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጉራጊኛና ሌሎች በአካባቢው የሚነገሩ ቋንቋዎችን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በአካባ ቢው ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ ባለመሆኑ በተለይ አዲሱ ትውልድ ከቋንቋው እንዳይርቅ የጉራጊኛ ቋንቋ እንደሚጀመር አመልክተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ህጻናት የጉራጊኛ ቋንቋ የሚማሩበትን የቋንቋ ቦርድ እንዲዋቀር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ለጉራጊኛ ቋንቋ ዕድገት መሰረት በሚሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመመርኮዝ የተካሄደው ውይይት ማህበረሰቡ በቋንቋው እንዲጠቀም፣ ቋንቋው ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ እንዲሸጋገር በሚያስችል መልኩ ግብአቶች ማሰባሰብ የተቻለበት እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒውቲንግና ኢንፎር ማቲክስ ኮሌጅ ዲን መምህር ኮራብዛ ሸዋረጋ እንደገለጹት፤ የጉራጊኛ ቃላት በኦን ላይን ሁሉም ማህበረሰብ ተሳትፎበት እንዲሰባሰብና ማዕከላዊ በሆነ ቋት ውስጥ እንዲቀመጥ ማድረጊያ ፕሮጀክት ነው፡፡
በኮሌጁ በልጽጎ በተለቀቀው የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነ ማህበረሰብ የትኛውም ቦታ ሆኖ የሚፈልገውን ዘዬ መርጦ ቃሉን እንዲያስገባ ያደርጋል፡፡ ተግባሩ አደጋ ላይ ያለውን የጉራጊኛ ቋንቋ እንዳይጠፋ ለመጠበቅና ለማቆየት ያግዛል፡፡ ወደፊትም የትምህርት፣ የስራና የቴክኖሎጂ ቋንቋ እንዲሆን ታስቦ የተጀመረ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቃላቱን ለማሰባሰብ የተለያዩ መንገዶችን እንጠቀማለን፡፡ ትክክለኛ ያልሆኑና ያልተጣሩ መረጃዎች ቢገቡ የማጥራት ስራ በመስራት ጥራት ያለው መረጃ ወደ ቋቱ እንዲገባ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ከኦን ላይን የማሰባሰቢያ ዘዴ በተጨማሪም በአካል በመንቀሳቀስ የተለያዩ ከአካባቢው ማህበረሰቦች ጋር ገጽ ለገጽ በመገናኘት ቃላቱን የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት፡፡ ለመነሻ ያህል ከ41 ሺ በላይ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቃላትን ወደ ሲስተሙ የማስገባት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም