
አዲስ አበባ:- በካናዳ፣ ኖርዌይና ጣሊያን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በሰላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል፡፡
በካናዳ አልበርታ ግዛት በካልጋሪ፣ ሌትብሪጅና ፎርትማክመሪ የሚኖሩ ኢትዮ- ካናዳውያን የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የጉዞና ተያያዥ ማዕቀብ በመቃወም በካልጋሪ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በሰልፉ ላይ በትግራይ ክልል አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ኢ-ሰብዓዊ ጭፍጨፋ ተከትሎ መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበርና ወንጀለኞቹን ለህግ የማቅረብ ህጋዊ እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ይህን ክስተት ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት እውነታውን በትክክል አልመረመረም ብለዋል፡፡ በተሳሳተና እውነትን መሰረት ባላደረገ ሁኔታ የኢትዮጵያን መንግስት ከአሸባሪዎች እኩል በመመልከት ማዕቀብ መጣሉ ስህተት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሰልፈኞቹ በመልእክታቸው ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ የዜጎቿን ድጋፍ የምትፈልግበት ጊዜ መሆኑን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም የሃይማኖት፣ የብሔርና የፆታ ልዩነት በአንድነት በመቆም ድጋፉን ማድረግ እንዳለበት፣ አሜሪካም ሆኑ ሌሎች ምእራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ የሚፈልጉትት ሃገሪቱ ደሃ በመሆኗ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
መንግስት ሃገሪቷን ከድህነት ለማውጣት የሚያደርገውን ጥረት በተለያየ መንገድ እንደሚደግፉና ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ብቻ እንደሚልኩም አስታውቀዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለበት የጊዜ መርሃ ግብር መሰረት ሙሌቱ እንዲካሄድና ፕሮጀክቱም እንዲጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመጠቆም፤ የሀገራቸው የካናዳ መንግስትም በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ መሰረት እንዲይዝ እንዲደግፍና አላስፈላጊ ጫና ኢትዮጵያ ላይ ከማሳረፍ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
በሌላ ዜና በኖርዌይ ኦስሎና አካባቢው ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኤርትራ ኮሚዩኒቲ በጋራ በመሆን የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ሰሞኑን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም በኦስሎ የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት በመገኘት የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።
በዕለቱ በኖርዌይ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሲቪል ማህበረሰብ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ ደስታ የአሜሪካ ሰኔት (S.Res 97) በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ኢ-ፍትሃዊ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ፣ የሀገሪቱ መንግሥት በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናትና ወታደራዊና የደህንነት አባላት ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሉን አስታውሰው፤ በሁለቱ ሀገራትና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባቱ ከሉዓላዊነት ጋር የሚፃረር አደገኛ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፤ ሠልፈኞቹም በጽኑና በአንድነት እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን እያራመደች በመሆኑ ይሄንኑ በአፋጣኝ እንድታሻሽል፣ የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ በህውሓት ሽብርተኛ ቡድን በሚነዛው የተሳሳተ መረጃ ላይ በመመርኮዝ ያስተላለፈውን ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ እንዲያነሳ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በአሸባሪነት ከፈረጀቻቸው ድርጅቶች ጋር እንድትደራደር እየቀረበ ያለው ጥሪ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵ ያውያን የመንግስትን አቋም በመደገፍ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና በመቃወም በጣሊያን ሮም ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት፣ የሱዳንን የድንበር ወረራና በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ሱዳን እና ግብፅ እየሄዱበት ያለውን ሴራ አውግዘዋል።
እንዲሁም የምዕራባውያን ሚዲያዎችን ከኢዲቶ ሪያል ፖሊሲ ያፈነገጠ ዘገባ ተቃውመዋል። አሁን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከምዕራባውያን ጫና ሳይሆን ለተፈናቀሉ እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እገዛ የሚፈልጉበት ወቅት መሆኑን በአፅንዖት አንስተዋል።
የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድና ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
ከሰልፉ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ አስር ሺህ ዩሮ ለግድቡ ቦንድ በመግዛት አጋርነታቸውን ገልጸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም