
አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ ከእንጉዳይ ምርት ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም ሲል የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክር ቤት ገለጸ፡፡ ግንቦት 23 ቀን በየዓመቱ የእንጉዳይ ቀን በሚል ስያሜ እንዲከበር ተወሰነ፡፡
የምርምር ምክር ቤቱ ሴክሬታሪያት ዋና አስተባባሪ ዶክተር መኩሪያ ታደሰ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የእንጉዳይ ምርት ለምግብና ለመድሃኒት አገልግሎት ይውላል፡፡ ሃብቱን ወደ ውጭ በመላክም የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል።
በዓለም ገበያ 56 ቢሊዮን ዶላር የእንጉዳይ ምርት ይቀርባል፡፡ ቻይና በዓመት ወደ ውጭ በምትልከው የእንጉዳይ ምርት 25 ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች፡፡ በሀገራችን በእንጉዳይ ምርት ዙሪያ የተወሰኑ ምርምሮች ቢኖሩም ከዘርፉ መገኘት የሚገባውን ያህል እየተገኘ አይደለም ብለዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በእንጉዳይ ዘርፍ የተቀዛቀዘውን እቅስቃሴ ለማነቃቃት በማሰብ ግንቦት 23 ቀን 2013 የእንጉዳይ ቀን ተብሎ ተወስኗል፣ በየዓመቱም የእንጉዳይ ቀን ይከበራል፣ በዘርፉ የተሰሩ ስራዎች ይገመገማሉ፣ የማሻሻያ ሃሳቦች ይቀርባሉ፣ አቅጣጫም ይሰጥበታል፡፡
የእንጉዳይ ምርትን ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚከታተል እስካሁን ድረስ ባይኖርም በአንዳንድ ባለሀብቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ የእንጉዳይ ምርት ዘር የሚያመርቱ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ፣ እቅዶችም ተዘጋጅተው ወደፊት ለመሄድ እቅድ መኖሩን እና የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ይሄንን ማጠናከር ይፈልጋል ብለዋል።
እስካሁን በምርምር ማዕከላትና ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ዓይነት የእንጉዳይ ዝርያዎች ተሰብስበዋል ያሉት ዋና አስተባባሪው፤ ከተሰበሰቡት መካከል ለምግብነት በሚውሉ ሶስት ዓይነት የእንጉዳይ ዝርያዎች አመራረትና የገበያ አቅርቦት ላይ በቂ እውቀት መኖሩን አመልክተዋል። በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦች፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የእንጉዳይ ምርት ይመረታል ሲሉም አስታውሰዋል።
የእንጉዳይ ምርት ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ አንጻር ለሴቶችና ወጣቶች በስራ ፈጠራ በኩል ውጤታማ እንደሆነ አስታውሰው፤ ሲምፖዚየሙም ዘርፉን በማሳደግና ለሀገር ጥቅም እንዲውል በማድረግ መካሄዱን አመልክተዋል። በተለይ ስራ አጥ ለሆኑ ሴቶችና ወጣቶች ዘር በመስጠት እና የምርት ቦታ አዘገጃጀት ስልጠና በመስጠት የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም