
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን የስራ ፈጠራን ችግር ለመፍታት ሀገር በቀል መፍትሄ ያስፈልጋል ሲሉ የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። በሆልቲካልቸር፣ በወተትና በስንዴ ምርት ዘርፎች ሰፊ የስራ እድል መኖሩ ተገለጸ።
በስራ ፈጠራ ኮሚሽን የስራ እድል ፈጠራ አማካሪ ምክር ቤት ሶስተኛ ዙር ውይይት አካሂዷል። የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የሀገራችንን የስራ ፈጠራ ችግር ለመፍታት ሀገር በቀል መፍትሄ ያስፈልጋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ኮሚሽኑን ለማገዝ የተቋቋመው የስራ እድል ፈጠራ አማካሪ ምክር ቤት ብዙ ችግር ፈች ጥናቶችን በማቅረብ የስራ አማራጮችን ሲጠቁም መቆየቱን ገልጸው፤ በከተማና በገጠር በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድልን ለመፍጠር የሚያግዙና ፖሊሲዎችን ሊያስቀይሩ የሚችሉ ጥናቶች ቀርበዋል ብለዋል። የተጠኑ ጥናቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር ችግሮች ቢኖሩም እውቀት ሁሌም አሸናፊ በመሆኑ ልትበረቱ ይገባል ሲሉም መክረዋል።
በየዓመቱ አዳዲስ ወደ ስራ ገበታ ለማስገባት የታቀደውን 2 ሚሊዮን ዜጎች፣ እስከ 2017 ዓ.ም ለ14 ሚሊዮንና እስከ 2022 ዓ.ም ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን አስታውቀዋል። ዕቅዱ እውን የሚሆነው ሀገር በቀል የምርምርና ጥናት ስራዎች ሲሰሩ በመሆኑ ካውንስሉ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
‹‹በታዳሽ ሀይሉ ዘርፍ ያሉ የስራ እድሎች›› በሚል ርዕስ ለመወያያ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የፕሪሳይስ ኮንሰልቲንግ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ማርኬት አክስሌተር ፕሮግራም ማናጀር አቶ አህመዲን አህመድ እንደገለጹት፤ በገጠራማው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ታዳሽ ሀይልን በመጠቀም እስከ 200 ሺህ የሚጠጋ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል አቅም አለ።
በሆልቲካልቸር፣ በወተትና በስንዴ ምርት ዘርፎች ብቻ ስራ ለመፍጠር የሚያስችል ሰፊ እድል አለ። በግብርናው፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በንግዱ ዘርፍም ስራ መፍጠር የሚያስችል ሀብት መኖሩን ተናግረዋል።
መፍጠር ከሚያስችለው ከ200 ሺህ የስራ እድል ውስጥ በሆልቲካልቸር 130 ሺህ፣ በሶላር የሚሰሩ ወፍጮ ቤቶችን በመጠቀም ከ50 ሺህና በሌሎች አነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ከ11 ሺህ በላይ ስራ እድሎችን መፍጠር እንደሚቻልም አመልክተዋል።
ታዳሽ ሀይልን በመጠቀም፤ የጸጉር ስራና የውሃ ፓምፖችን በማንቀሳቀስ ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የሚያስችል አቅም እንዳለ አቶ አህመዲን አብራርተዋል።
እንደ አቶ አህመዲን ገለጻ፤ ታዳሽ ሀይል ቴክኖ ሎጂዎችን ወደ ህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ። ቴክኖሎጂዎች በዋጋቸው ውድ ናቸው። የታዳሽ ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ የሚደግፍ ፖሊሲም የለም።
የአመለካከት ችግሮች ባሉ እምቅ እድሎች ላይ ስራ ለመፍጠር እንቅፋት እየፈጠሩ ናቸው ብለዋል። በተቋማት በኩልም የታዳሽ ሀይል ቴክኖሎጂ ጠቀሜታቸው ዙሪያ የመረጃ ክፍተት መኖሩን አንስተዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም