ቆዳ በሀገራችን ባህል መሰረት በርካታ ጥቅሞች አሉት። በገጠር ለመኝታ፣ ለስልቻ፣ ለፈረስ ኮርቻ፣ መስሪያ ያገለግላል፡፤ አለንጋ፣ መጫኛ፣ ቀበቶው ከቆዳ ነው የሚሰራው። ለልብስ፣ ለጫማ መስሪያ ሲያገልግል ኖሯል። ለመቀመጫ የሚሆን ድብዳብ ለመሥራት፣ አገለግል ለመለጎም ይውላል። በብርዳማ አካባቢዎች እረኞች የበግ ለምድ ለብሰው ነው ከብት የሚጠብቁት። የብራና መጽሐፍት የሚዘጋጁትም ከቆዳ ነው። ሌሎችም በርካታ አገልግሎቶች አሉት።
በዚህ ዘመን ደግሞ የቆዳ አገልግሎቱ ሰፍቷል። ይበልጥም ዘምኗል። ቆዳ ጫማ በአይነት በአይነት ማምረት ያስችላ። ቆዳ ለጃኬትና ኮት፣ ለተለያዩ የቦርሳ አይነቶች፣ ለወንበር ልብሶች፣ ለቀበቶ፣ ለጓንት ያገለግላል። እነዚህ የቆዳ ውጤቶች በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚመረቱ ሲሆን፣ በዋጋቸውም የማይቀመሱ አይነት እየሆኑ መጥተዋል።
የአንበሳ ጫማ ፋብሪካ በቆዳ ምርት ውጤቶቹ ዘመናትን የተሻገረ መሆኑ ይታወቃል። ለብዙ ዓመታት በመንግሥት ይዞታ ሥር የቆየ ሲሆን አሁን ወደ ግል ዞሮ እየሠራ ይገኛል። ምርቶቹን ከሀገር ውስጥ አልፎም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ይታወቃል።
የፋብሪካው የምርት ዕድገት ኃላፊ አቶ ፊሊፕ ቻርሊዮስ እንደሚሉት፤ ከቆዳ ፋብሪካዎች ምርቶች 50 በመቶ ያህሉ ለቆዳ ጫማ፣ ለቦርሳ፣ ለጃኬትና ለመሳሰሉት ግብአት የሚሆኑ ናቸው። ለዚህም የበግ፣ የበሬ፣ የፍየል ቆዳ ለጫማ ለጃኬትም ለቦርሳም ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ፊሊፕ ገለፃ፤ ቆዳ ፋብሪካዎች ቆዳ ሲያመርቱ ቀለሙን ይወስናሉ፤ አንዳንዴም የቆዳ ጫማ አልባሳት ፋብሪካ ያላቸው ቆዳ ፋብሪካ ሄደው የምርቱን ዓይነት ስትራክቸር አስወስነው ማስመረት ይችላሉ። የበሬ ቆዳ ገበያ ላይ ፍላጎቱ ካለ ጨምረው ያመርታሉ። ቆዳ ፋብሪካዎች ራሳቸው የራሳቸውን ዲዛይን ያቀርባሉ፤ ብዙ የጫማ ፋብሪካዎች ሊወስዱት ይችላሉ።
የአዞ ቆዳ የሚመስል የሰጎንን መልክ የሚመስል የእንስሳትን መልክ ያለው ቆዳ አምርተው ገበያ ያቀርባሉ። ይህ ሲሆን ገበያው በስፋት ይገኛል፤ ቆዳው ጥሩ ተቀባይነት ካለው ወደ ምርት ተጠናክሮ ይገባል፤ ገበያው ሲጠነክር ደግሞ ከቆዳው የሚመረተው ምርት እንደ ፋሽን ሆኖ ተቀባይነት ይኖረዋል።
በፋብሪካው ዲዛይን የሚሠሩ ሠራተኞች ከመኖራቸው በተጨማሪ የገበያ ጥናት ክፍል እንዳለም ይናገራሉ። አንበሳ ጫማ ፋብሪካ በሀገሪቱ ወደ 300 መሸጫ መደብሮች አሉት። አዲስ አበባ ላይ ወደ 30 መደብሮች አሉት ያሉት አቶ ፊሊፕ፣ ደንበኞች ወደ መደብሩ ሲገቡ ሃሳብ የሚሰበሰብበትና ሰዎች ሃሳብ የሚሰጡበት ምቹ ሁኔታ እንዳለም ይናገራሉ። ያ ሃሳብ ተሰብስቦ ሰው ምን ዓይነት ነገር ይፈልጋል የሚለው ይታያል ይላሉ። ከዛ ወደ ምርት ልማት በመሄድ ያንን በመከተል ማምረት ውስጥ እንደሚገባ ይህም ጥሩ ፋሽን ሆኖ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ይገልፃሉ።
እንደ አቶ ፊሊፕ ማብራሪያ፤ የአንበሳ ቆዳ ጫማ ፋብሪካ የዴቨሎፕመንት ቡድን ዲዛይነሮች በሚሰጣቸው ሃሳብ መሠረት አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ፤ ምርቱ በገበያ ተቀባይነት ካለው የበለጠ ወደ ምርት ይገባሉ። ፋብሪካው ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በፋሽን ዲዛይን የተመረቁ ከቂሊንጦ እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ በፋሽንና ዲዛይን ላይ የሚሠሩ ወደ ስድስት ሠራተኞችም አሉት ።
‹‹ዋናው ግባችን ደንበኞቻችንን ማርካት ነው። አንድ ሰው አንድ ጫማ ብቻ አድርጎ አይዘልቅም›› የሚሉት ሃላፊው፣ በሠርግ፣ በምርቃ፣ በክረምት፣ በበጋና በመሳሰሉት የሚገዛቸው የሚጫማቸው ጫማዎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ። ያንንም ተመርኩዘን ዲዛይን እንሠራለን የሰውም እንቅስቃሴና ፍላጎት ከቀን ወደ ቀን ይጨምራል ይላሉ። የጣሊያን ዲዛይነሮች እንዳሉት የህንድም ዲዛይነሮች እንደነበሩትም ያመለክታሉ። በዓለምአቀፍ ደረጃም ለፋሽን ቅርብ የሆኑ ሞዴሎችን እናመርታለን በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የጣሊያን ኩባንያዎች መጥተው ምርቶቻችን ይወስዳሉ ሲሉ ይጠቅሳሉ ።
ፋብሪካው በቆዳ ውጤቶቹ በሴቶች ላይ ከዚህ በፊት ብዙ ዲዛይኖች እንዳልነበሩት ገልፀው፣ አሁን ግን ብዙ ሴቶችን ያማከሉ ፋሽን የጠበቁ ዲዛይኖች እንዳሉት ነው ያመለከቱት። ወጣቶችንም አዋቂዎችንም ያማከሉ ፋሽኖች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ለእዚህ አገልግሎት የሚውሉ ፋሸኖችን ከውጭ በማስገባት ጥሩ ሶሎችን በመጠቀም አዳዲስ ዲዛይኖችን እያሳደግን ነው ይላሉ። ያለን ተቀባይነት በሴቶች ደረጃ አሁን ጥሩ ነው። ፋብሪካው ቦርሳ ማምረት ከጀመረ ሁለት ሦስት ዓመት ይሆነዋል የሚሉት አቶ ፊሊፕ፤ ቀበቶ የኪስ ቦርሳ (የሴትም የወንድም) የትምህርት ቤት ቦርሣዎች ለጉዞ የሚያስፈልጉ ሻንጣዎች እንደሚያመርትም ይገልፃሉ።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ የቆዳ ውጤት ምርቶቹ ገበያ ላይ ያላቸው ተቀባይነት በጣም ጥሩ ነው፤ የፋብሪካው ዲዛይነሮችም ያለውን ፋሽን ተከትለው የሚሠሩ ወጣቶች ስለሆኑ ገበያ ላይ ያለውን ነገር በደንብ ተረድተው፤ የወጣቱንም የአዋቂውንም ሴቱንም ወንዱንም ፍላጎት የሚከተሉበት መንገድ በጣም ጥሩ ነው።
“ለሥራችን ግብረመልስ የምናገኘው በዋናነት ከደንበኛ ስለሆነ ግብረመልሱን መሬት አውርደን ስለምንተገብረው፤ ገበያ ላይ ሲገባ ተቀባይነቱ ጥሩ ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳል›› ይላሉ። በፋሽን በኩል ያለውን ተቀባይነት አስመልክተው ሲያብራሩም “ በዋነኝነት በድርጅቱ ውስጥ በምንሠራበት ጊዜ አዳዲስ ነገሮችን አይተን ወደ ትግበራ እንቀይራቸዋለን። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ድርጅቱ አዳዲስ ዲዛይኖችን ለመፍጠር እየሞከረ ይገኛል›› ብለዋል።
አቶ ፊሊፕ እንደገለጹት፤ የዛሬ አንድ ዓመት አንበሳ ጫማ ፋብሪካ ምርቶቹ ጥራትና ጥንካሬ ዲዛይን ከአፍሪካ ሦስተኛ ትልቁ ብራንድ ተብሎ ተመርጧል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቆዳ ጫማ ማምረት ሲታሰብ ካለው አቅም አንፃር ማንኛውም ሰው የሚያስበው የአንበሳ ጫማን ነው። ፋብሪከው በውጭ አገር ያለውን ስም ለማጉላት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ባዛሮች አገር አቀፍ ዐውደርዕዮች በመሳተፍ ራሱን እያስተዋወቀ ይገኛል። የተለያዩ ወደ ውጭ የሚልካቸውን ጫማዎች በኢትዮጵያ የተሠሩ ተብለው ስለሚላኩ ራሱን አገሩንም ያስተዋውቃል።
‹‹የኢምፖርት ኤክስፖርት ዲፓርትመንት አለን፤ ድረገጽ አለን እዛ ላይ የምንሠራቸውን ምርቶች እናስተዋውቃለን፤ የውጭ ገበያም እንስብበታለን›› ያሉት ሃላፊው፣ ትልቁ አቃቂ ያለው ፋብሪካ ዋናው የተቋቋመበት ዓላማ ኤክስፖርት መሆኑን ይገልፃሉ። ፋብሪካው ምርቶቹን ወደ ፈረንሳይ እና ኔዘርላድ እየላከ መሆኑን ጠቁመዋል። ለፌዴራል መንግሥት ፖሊሶች እና ወታደሮች ጫማ እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ የምርቶቹ ዲዛይንም የፋብሪካው መሆኑን ይገልፃሉ። በውድድር እየሠራን ነው ሲሉ ይገልፃሉ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013