የሳምንቱ መጀመሪያ በሆነው እለተ ማክሰኞ “11 ኛው ሚዩዚክ አዋርድ” ተካሂዷል። ባለፈው ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በማሪዮት ሆቴል በድምቀት በተካሄደው በዚህ መድረክ በተለያዩ ዘርፎች እጩዎች ቀርበው ከፍተኛ ፍልሚያ አድርገዋል፤ አሸናፊዎችም ተለይተዋል።
በዚህም መሰረት የአመቱ ምርጥ ክሊፕ የሳያት ደምሴ “እስክሽር” የተሰኘው የሙዚቃ ክሊፕ ሲያሸንፍ፣ አርቲስት ዘቢባ ግርማ ደግሞ “ገራገር” በተሰኘው ሙዚቃዋ የአመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ ሽልማትን የግሏ አድርጋለች።
በሚውዚክ አዋርድ ለአልበም ስራም እውቅና ተሰጥቷል። በዚህም በሙሉ በአልበም ዳዊት ፅጌ “የኔ ዜማ” በሚለው ተወዳጅ ስራው ያለምንም ተቀናቃኝ ከድል ማማው ላይ ከፍ ብሎ በመውጣት የመራጮችንም የአድማጭንም ቀልብ መግዛት ችሏል።
የምርጥ አልበም አሸናፊ የሆነው ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ “ባላገሩ አይድል” በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይተላለፍ በነበረ የሙዚቃ ውድድር ከአመታት በፊት አሸናፊ ነበር።ውድድሩ ሲጠናቀቅም ለአሸናፊው የሙዚቃ አልበም ማዘጋጀት የሽልማቱ አካል ስለነበር፤ በውድድሩ ዳዊት ያሳየው ድንቅ ችሎታ በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ አልበሙ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።
እናም እንደተጠበቀው «የኔ ዜማ » በሚል መጠሪያ የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሙን ለአድናቂዎቹ እንካችሁ ብሎ ነበር። አስራ አራት የሙዚቃ ስራዎች የተካተቱበት የዳዊት ፅጌ “የኔ ዜማ” አልበም ዳዊት ጽጌ ውድድሩን ካሸነፈ ከአራት አመታት በኋላ የወጣ በመሆኑ የሙዚቃ አልበሙ ዘግይቷል የሚሉ ብዙዎች ነበሩ።
ነገር ግን በውድድሩ የተለያዩ አንጋፋና ወጣት ድምፃውያንን ሙዚቃ ይጫወት ስለነበር የአራት አመት ቆይታው የራሱን የሙዚቃ ቀለም ፈልጎ ለማግኘት የጣረበት እንደነበርም ድምፃዊው በአንድ ወቅት ለጀርመኑ ራዲዮ ጣቢያ (ዶቼ ቬሌ) ገልጿል። ለዚህም አንጋፋው የሙዚቃ ሰው አበበ መለሰ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎለታል። በዳዊት ፅጌ “የኔ ዜማ” አልበም የአብርሃም ወልዴ አሻራ ያረፈበት ሲሆን፣ “ባላገሩ” ቁጥር አራት በዚህ አልበም ተካቷል። “አስመሪኖ” በሚለው ዜማው ደግሞ ፀሀይቱ ባራኪን የመሳሰሉ አንጋፋ የኤርትራ ድምፃውያን ተዘክረውበታል።
“ባላገሩ አይድል” በሚለው የሙዚቃ ውድድር በነበረው ቆይታ በሙዚቃ አፍቃሪዎች ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዞ የቆየው ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ፤ በቅርቡ ያወጣው አዲሱ አልበም በአድማጩ ዘንድ ጥሩ ምላሽ ሲቸረው ቆይቷል፤ ይህ አልበም በአዲስ ሚዩዚክ አዋርድም አሸናፊ ሆኗል።
ልክ እንደሌሎቹ ተወዳጅ የሽልማት ሥነ- ሥርአቶች ሚውዚክ አዋርድ በየአመቱ በዘመናቸው ዝናን ያተረፉና በስራቸው አንቱ የተባሉትን ያመሰግናል። በዘንድሮው “የህይወት ዘመን ባለውለታ” ላይም የብስራት ሱራፌል አባት ሱራፌል አበበ ተሸላሚ ሆነዋል።
በእለቱ በታዳሚው ዘንድ ሀዘንና ደስታ የፈጠረው የዘመን ባለውለታ ነበር። ሙዚቃን በከፍተኛ ኪነት ውስጥ በታዳጊነት ዘመኑ የጀመረው አርቲስት ሱራፌል “ልጅ እያለሁ ለድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ልዩ ፍቅር ነበረኝ” ይል እንደነበር ታዛ መጽሔት በአንድ ወቅት ዕትሙ አስነብቧል። በቀበሌ ከፍተኛ ኪነት ቡድኖች በመጫወት ችሎታውን አዳብሮ በ1972 ዓ.ም. በተቀጠረበት ራስ ቲያትር ረዘም ላሉ ዓመታት በድምጻዊነት እና በተወዛዋዥነት አገልግሏል። በ1979 ዓ.ም. ከሮሃ ባንድ ጋር የሰራው “ታድለሻል” የተሰኘው አልበሙ ከቲያትር ቤት መድረክ በተጨማሪ ለህዝብ ጆሮ ያደረሰው የበኩር ሥራው ነው።በ1980 ዓ.ም. ደግሞ ከሌሎች ድምጻዊያን ጋር በጋራ ተጫውቷል። ከስራዎቹ መካከል “ሳዱላዬ፣ እንደኔ ነው ወይ፣ ይገርማል፣ የማር ወለላ” የተሰኙት ተጠቃሾች ናቸው።
አርቲስት ሱራፌል ከ1970 ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ፊቱን ወደ ግጥም እና ዜማ ድርሰቱ መልሷል። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ በ70ዎቹ እና 80ዎቹ ደማቅ ስም ካላቸው እና ጉልህ አሻራቸውን ካሳረፉት የዜማ እና ግጥም ደራሲዎች ማለትም አበበ መለሰ፣ አበበ ብርሃኔ፣ ሞገስ ተካ፣ ዘላለም መኩሪያ ጋር ተሰልፎ ዘመን የማይሽራቸው ስራዎቹን አበርክቷል። በብዙዎች ዘንድ እውቅና ያተረፈለት እና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ በስራ ላይ የነበረው በሙዚቃ ድርሰት ሙያው ነው። ነጻነት መለሰ፣ ገረመው አሰፋ፣ ራሄል ዮሀንስ፣ ምናሉሽ ረታ፣ መሀሪ ደገፋው፣ ሻምበል በላይነህ፣ ትዕግስት ወይሶ፣ ሐመልማል አባተ፣… የግጥም እና ዜማ ድርሰቱን ከተጫወቱ ድምጻዊያን መካከል ይገኙበታል።
በሙያ አጋሮቹ አመለ ሸጋ መሆኑ የሚነገርለት አርቲስት ሱራፌል አብዛኛዎቹ የግጥም እና ዜማ ሥራዎቹ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እና ተደማጭነት አግኝተውለታል። ከእነዚህ መካከል፡- ቴዎድሮስ ታደሰ “ጥፋተኛው ገላ”፣ ማርታ አሻጋሪ “ደማይ ደማይ”፣ ጸጋዬ እሸቱ “ተጓዥ ባይኔ ላይ”፣ ኩኩ ሰብስቤ “ዘንድሮ”፣ ሕብስት ጥሩነህ “እምዬን አደራ”፣ ዳዊት ጽጌ “የኔ የኔ” ተጠቃሾች ናቸው።
የድምጻዊ ብስራት ሱራፌል አባት የሆነው አርቲስት ሱራፌል አበበ በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር አጋማሽ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የሚታወስ ነው።ይህ ባለሙያ በ11ኛው አዲስ ሙዩዚክ አዋርድ የዘመን ባለውለታ ሽልማትን አሸንፏል።
የአዲስ ሙዩዚክ አዋርድ የድምጽ አሰጣጡ በአጭር መልዕክት በ8022 እና አዲስ ሙዩዚክ ዶት ኦርግ በሚለው በበየ መረብ ላይ በተላኩ በአድማጭ ተመልካች ድምጾች እንዲሁም የባለሙያዎችን ነጥብ ታክሎ አሸናፊው የተለየበት ውድድር ነው።
አዋርዱ በሙዚቃ ዘርፍ ቢሆንም በዚህ አዋርድ የትያትር ዘርፍን በማካተት ለፊልም ጥበባዊ ውጤቶችም እውቅና ተሰጥቷል። ይህን በማስመልከት በትወና ማርታ ጎይቶም “የአመቱ ምርጥ ተዋንያን” በሚለው ዘርፍ የአንደኝነት ካባን ደርባለች።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2013