ሰዓሊውን አገኘሁ

ሰዓሊው- ከእንቆቅልሽ መጨረሻው ጋር ተያይዞ ከሄደ እልፍ ዓመታት ባእተዋል:: ስሙ ግን ዛሬም ድረስ ከምድሩ ነፋስ ጋር እየነፈሰ፣ ከሰማዩ ዝናብ ጋር ሁሉ ይዘንባል:: ከጉና ተራራ አናት ጉብ ብሎ ቁልቁል ሀገሩን ይመለከታል:: ከራስ ዳሽን ማማ እስከ ደብረ ታቦር ተራራና ኮረብቶች ድረስ እየተንሳፈፈ ይከንፋል:: ሰዓሊው የተዋቡ እጆች ባለቤት፣ የዘመናዊ አሳሳል ፈር ቀዳጅ ፊታውራሪው አገኘሁ እንግዳ ነው:: ከጥበብ ጥበብን፣ ከዕውቀት ዕውቀትን፣ ከፍቅር የሀገር ፍቅርን ችሮ ገና በማለዳው ብሩሽ ያስጨበጠው የዘመን ጎህ ነበር::

የአገኘሁ ስምና ዝና ብዙ ዘመን ወደኋላ ይወስደናል:: ፎቶ ምስሉ ይናገራል:: ጠይም ዘለግ ያለ፣ ጸጉሩን አፍሮ ችምችም አጎፍሮ ሸንቀጥ የሚል ተራማጅ፣ ላየው ዓይነግቡ ሰው አክባሪ፣ መልከ መልካም:: ከደረሱበት ግን ለመብቱ ፈቀቅ የማይል ልበሙሉ የጥበብ ሰው:: ሲስል በዝምታ፣ ብሩሹን ጨብጦ ውስጡን ብቻ የሚያደምጥ፣ ከሰው የሚግባባ ሰው መውደድ ያለው ነበር:: በማንም ይሁን በማን መጥፎ በደል ሲፈጸምበት ማየት ዓይኖቹን ያጥበረብሩታል:: ልቡ አምርሮ ይቃወመዋል:: ነገር አዋቂም ነውና ፊት ለፊት ከመታገል፣ ቆሞ ከመሞገት ወደኋላ አይልም:: ባለሥልጣናቱ ልክ ያልሠሩ መስሎ ሲሰማው እንኳን በግልጽ ሃሳቡን መሰንዘርና የሚሰማውን መናገርን አይፈራም:: በዚህም አመሉ ከንጉሣዊያኑ ጋር እስከመካረር አድርሶታል:: ሰዓሊው እንደ አፈንጋጭም ተቆጠረ::

ሞገደኛው ሰዓሊ፤ አገኘሁ እንግዳ የትውልድ ቀዬው በቀድሞው የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ነበር:: ጎንደር ዘልቀው ከደብረ ታቦር ተራሮች የሚነፍሰውን ነፋስ እየተጋፉ አቅጣጫውን ተከትለው የሄዱ እንደሆን፤ የአገኘሁ የትውልድ አምባ የሆነችውን ማኅደረ ማሪያምን ያገኟታል:: በ1905ዓ.ም የተወለደው አገኘሁ፣ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ለጥበብ ገጸ በረከት ካደረጋቸው ጠቢባን መሃል አንደኛው ነው:: ያ ዘመን ሲታሰብ እንዲህ ላለው የስዕል ጥበብ ቀርቶ፣ ደብተር አንጠልጥሎ ከአንደኛው የመንደር ትምህርት ቤት መዝለቅም አዳጋች የነበረበት ነው:: ‹እገሌን ተመልክቼ…እንደ እገሌ ለመሆን እፈልጋለሁ› የሚሉት ተምሳሌት እንኳን ከጎን የማይታይበት ነው:: ምክንያቱም ‹የተማረ ሊቅ ነው፤ ድንቅ ሰዓሊ ነው› በማለት ጅግናችን የምናደርገው፣ ምሳሌነቱን እየተከተልን ጥበብን ከእርሱ ለመቅሰም የምንችለውን ሰው ምናልባት በስም ካልሆነ በስተቀር በአጠገባችን የምናገኘው አይደለም:: በክፍለ ሀገራት ውስጥ ለሚገኙ ልጆች ደግሞ የባሰ ችግር ነበር:: የተማሩ ጥቂቶች ቢኖሩ እነርሱም ከተማ ወይንም በውጭ በሌላ ትምህርት ላይ ናቸው:: ከየኔታ እግር ስር የቅኔን ምንጭ ቢጠጡ እንጂ፤ ሰዓሊነትን ሊጎናጸፉ ከሁሉም የከበደና ድልድዩን የሸፈነ ኩሬ ነው::

ይሁንና አገኘሁ የአስኳላ ትምህርቱን በመከታተሉና ያለውን ተሰጥኦ በማውጣቱ ረገድ ዕድለኛ ነው እንድንል ያደርገናል:: ምክንያቱም ልክ እንደርሱ ተሰጥኦዎቻቸውን ከልጅነት ህልማቸው ጋር ሲሞነጫጭሩ፣ ደጋፊ በማጣት ይዘውት ይሞታሉ:: አንዳንዶችም እስከናካቴው ረስተውት በሌላ ሕይወት ይጠመዳሉ:: ሌሎችም ብሩህ ቀን ሲጠባበቁ ያረፍዳሉ:: እናም ከእነዚህ አንደኛቸውን አለመሆን መታደልም ጭምር ነው:: አገኘሁ ከትውልድ ስፍራው ማኅደረ ማሪያም ተነስቶ አዲስ አበባ ለመዝለቅ ጊዜ አልፈጀበትም:: ያኔ ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ነበር፤ ጊዜው ደግሞ ጃንሆይ ገና ከመንበረ ዙፋናቸው ይፋ ያልወጡበት:: ቢሆንም ግን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ወደ ፈረንሳይ ሄደው ዘመናዊ ዕውቀትና ጥበብ እንዲቀስሙ፣ መንገዱን በሌጋሲዮን አመቻችተው ነበር:: ይህን ዕድል ለመጠቀም ግንባር ቀደም ከሆኑት ውስጥም አንደኛው አገኘሁ እንግዳ ነው::

ለትምህርት ወደ ባሕር ማዶ የተላኩ ሌሎች ተማሪዎች ቢኖሩም፤ ከመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ወጣ ብሎ የተሰጥኦን መንገድ በመከተል ደረጃ ግን ፊተኛው አገኘሁ እንግዳ ነበር:: ለዚህም ነው፤ በሀገራችን የሥነ ስዕል ታሪክ ውስጥ ‹ዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ› ለመማር የቀደመው እንደሌለ የሚነገርለት:: በ1919 ዓ.ም ወደ ፈረንሳይ ሀገር በማቅናት “Ecole des beaux Arts” ከተሰኘው ትልቅ የስዕል ትምህርት ቤት ተቀላቀለ:: አገኘሁ ቀድሞም ቢሆን ብሩሾቹ ለስዕል ጥበብ የተከረከሙና የተሞረዱ፣ እጆቹ የሠለጠኑና የቀለማትን ውበት በጥንቃቄ የሚመለከት ነበር:: ‹ላለው ይጨመራል› ማለት ለገንዘብ ሳይሆን ለዕውቀትና ለጥበብ ነውና አገኘሁ ያለችውን ለማዳበር ሰባት ዓመታት ያህል በማሰባት ፓሪስ ስኬታማ ነበር:: ልምዱን በዕውቀት ኮትኩቶ፣ የስዕል ጥበቡን አለምልሞበታል:: ከሀገር በወጣ በሰባተኛው ዓመትም፣ በ1926ዓ.ም ተመልሶ ወደ ሀገሩ ገባ::

እንኳንስ ከሀገር ወዳዱ አገኘሁና ሀገሩ ባሕር ማዶ ድረስ ሰዳ ካስተማረችው ከማንም ቢያንስ አንድ ትልቅ ነገር መጠበቅ አይቀርም:: ካስተማረው ሕዝብ ተቆርሶ ለተሰጠው ስንቅ ምላሹ፣ ለራስ የስደት ምሽግ ማበጀት መሆንም የለበትም:: ከአንደበቱ ባያወጣውም ከልቡ ግን ሃሳቡ እንዲሁ ነበር:: እናም የውለታውን ምላሽ፣ የታላቅነቱን ጉዞ አንድ ብሎ ጀመረ:: በዚህ ጅምሩ የሠራው የመጀመሪያው ነገርም ለአዲሶቹ የኢትዮጵያ የብር ኖቶች የሚሆን የስዕል ንድፍ መንደፍ ነበር:: ግሩም በሆነ መልኩም ተልዕኮውን ፈጸመው:: ለሀገር ጉዳይ በሚውል በአንድ ነገር ላይ ንድፍ ከማዘጋጀት ረገድ አገኘሁን የሚስተካከል ያለ አይመስልም:: የጦር መኮንኖች የደንብ ልብስ ሲዘጋጅም የተጠራው አገኘሁ ነው::

በሌላ ጊዜ ጃንሆይ በካቴደራል ውስጥ አንድ ነገር ለመሥራት አሰቡ:: ሃሳቡም በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ለሀገራቸው ለደከሙ ባለውለታዎች የሚሆን ቆንጆ የመቃብር አጸድ ማዘጋጀት ነበር:: ለታላላቆች በሚሠራው በዚህ ሥራም የአገኘሁ የጥበብ ልፍትና አበርክቶ ትልቅ ነበር:: ከመካነ መቃብሮቹ ላይ ያረፉትን ስዕሎች ውብ አድርጎ የሠራቸው እርሱ ነው:: ቅድስት ሥላሴ ካቴደራልን አሳምሮ ሌላ የተለየ ገጽታ እንዲኖረው አድርጎታል:: በቀድሞው የዘውድ ፓርላማ ውስጥ የነበሩትን ድንቅ ስዕሎችን ስሎ የነበረውም ራሱ ነው::

ሰዓሊው የብቃቱን ወሰን ከገለጠባቸውና ስሙ ከፍ ብሎ ከሚጠራባቸው ስፍራዎች አንዱ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ነው:: ምክንያቱም በጊዜ ርቀት ከዓይን ሊሰወሩ የማይችሉ ድንቅ ስዕሎችን ነድፎ፣ በህብር ቀለማት ነብስ እየዘራ ከየማዕዘናቱ ላይ ሰቅሎባቸዋል:: በተለይ በየግርግዳዎቹ ላይ የነበሩ አብዛኛዎቹን አሳምሮ ያዘጋጃቸው አገኘሁ እንግዳ ነው::

እርሱ ሰዓሊ ብቻ አይደለም:: በቲያትር ቤቶች ውስጥና በሌላም የቲያትር ማስታወቂያዎችን ሲፈለጉ ‹አገኘሁ የት ነው?› የሚባል ነበር:: የውስጡን ሃሳብ በብዕር ቁጭ ማድረግ የሚችል ገጣሚም ጭምር ነው:: ይህም በቃኝ ሳይል እንደገና በገና ይደረድራል:: ትልቁ የልብ ሙያው ግን ሀገሩ ናት:: ‹ሀገሩን ሲወድ ከአንጀት ከሆዱ ነው› ይሉታል::

19941ዓ.ም ሌላ አዲስ ምዕራፍ የገለጠበት ነበር:: ባለው ጥበብ መሥራት ብቻ ሳይሆን፣ ዕውቀትና ልምዱን በማጋራት ሂደት ውስጥ ቀድሞም ምስጉን የነበረ ቢሆንም፤ በትምህርት ሚኒስቴር ተመድቦ፣ በቋሚነት የሚንቀሳቀስበት መንገድ ተከፈተ:: በሥነ ጥበባት ዘርፍ የማዕከላት አስተባባሪ ሆኖ መሥራት ጀመረ:: በተለያዩ ጊዜያት የስዕል ኤግዚቢሽኖችንም ያዘጋጅ ነበር::

አገኘሁ እንግዳ በባህሪው በብዙ ባለሥልጣናት የጥርስ ንክሻ ቢያስገባውም፣ የልብ ወዳጅ የሚላቸው ትላልቅ ሰዎች አጠገቡ ነበሩ:: ለመብታቸው ተጋፋጭ ስለሆነ በብዛት ከታች ባሉት ዘንድ ከልብ ተወዳጅ ነው:: በብዛት ግን ከመሰሎቹ ጋር ከሙያቸው ጋር የማዘውተር ልማድ ነበረው:: ከየትኛውም በላይ በቁጥር አንድ የሚያስቀምጣቸውና የሚያስቀምጡት ወዳጁ ብላቴን ጌታ ወልደ ማሪያም ነበሩ:: ታዲያ በአንድ ወቅት አንድ ክፉ አጋጣሚ ተከሰተ:: ብላቴን ጌታ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ:: በመሃል ውዝግብ ተፈጠረ:: ‹ሞቱ› እና ‹ተገደሉ› በሚሉ ሃሳቦች መካከል:: በርግጥ ብላቴን ተገድለው ነበር:: እንቆቅልሽ የሆነው ግን፤ ማን ገደላቸው? የሚል ነበር:: ወዳጁን የተነጠቀው አገኘሁ ግን በነገሩ ማመንታት ሳይታይበት ‹የተገደሉት በባለሥልጣናቱ ናቸው› በማለት በአደባባይ ተቃውሞ ከፈተ:: አንድ ወይንም ሁለት ጊዜ ብሎት አላቆመም፤ በየዕለቱ የሚያሰማው ድምጽ ይሄው ነበር:: ማን ትክክል፣ የቱ ጋር ልክ እንደሆነ እውነታውን ለማውጣት የቻለ ግን አልነበረም:: ለአገኘሁም ቢሆን ይባስ የከፋ ነገር ውስጥ እንዲዘፈቅ ከመሆኑ በቀር ጠብ ያለለት የገሀድ ምስል አልነበረም::

አንዳንድ ጊዜ በደህና ቆመው ሲሄዱ ለሚታዩ ለአንዳንዶች ሞተ መልዓክ በአካል ተገልጦ በጆሮ ሹክ የሚላቸውና የሞታቸውን ቀን የሚያረዳቸው ይመስላል:: አገኘሁም ይህን የሚመስል ነገር ነበር እስከ ዕለተ ሞቱ ሲያስተናግድ የቆየው:: በወቅቱ በትዳር የተጣመራት ሚስቱ አሰለፈች በዕድሜ ከእርሱ የምታንስ ገና ወጣት ነበረች:: አንዲት ሴት ልጅም ወልደዋል:: ሁለተኛውን ነብሰጡር ሳለች ግን ድንገት ከፊቱ ድቅን የሚል የሞት ጥላ ሽው! ይልበት ነበር:: ለብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ይህንኑ እያነሳ ሁሌም እንደሚጠራት ባለቤቱን “አሰለፍ…” ይላትና እንደቀልድ ይነግራታል:: ከዕለታት በአንዱ ምሽት ግን እንደልማዱ ስሟን ጠራና ጠንከር ያለ አንድ ነገር አላት፤ “ዘንድሮ እንደምሞት እኔ ታውቆኛል:: እኔም ያደግሁት በችግር ነውና ልጆቼ የተቸገሩ እንደሆን እንዳታዝኚ” አላትና እንደገና ሆዷን ተመልክቶ እየመጣ ያለውን ልጅ በማሰብ “የምትወልጂው ወንድ የሆነ እንደሆን ‹አለምበቃኝ› ብለሽ ስም አውጪለት” ሲል የሀዘን ድባብ በሰፈነበት አኳኋን ተናገራት::

ከዚያን ምሽት በኋላ የሰማይ የምድር ሌሊቱ ነጋ እንጂ፤ በአገኘሁ ውስጥ ግን እየጨለመና በምሽት ላይ ምሽት እየተደራረበ የሄደበት ነበር:: በቅጽበት ስሜቱ ይለዋወጣል:: ያ የሰውን ውስጠት አንብቦ የልብን ሲነድፍ የነበረው አገኘሁ ድምጽ ለመስማት እንኳን ይረብሸዋል:: በስዕል ጥበብ ብቻ ሳይሆን በማንነቱ ውሃ የሚያረጋው ሰው ‹ውሃ ቀጠነ› ማለትን አበዛ:: የራሱን ስሜትና ሃሳብ እንኳን ለመያዝ ተሳነው:: ብቻውን ቁጭ ብሎ መተከዝ፣ ብቻውን ማውራትም ዳዳው:: ሌላ ባሕሪ ሌላ ሰው መሰለ:: የሆነ መጥፎ ነገር ከፊቱ እየገሰገሰ መሆኑ ታውቆት ነበርና ለዚያም ነው አላመሉ አመል ማውጣቱ::

አገኘሁ ለባለቤቱ የተናገራቸው ነገሮች ሁሉ መገለጥ እንጂ ከፍርሃት የመነጩ ስሜቶች ብቻ አልነበሩም:: ሞት ይበልጥ እየተቃረበው በመጣ ጊዜ ግን ራሱን ማጀገን ጀመረ:: በግልጽም እየታየው ‹ይኸው እንካ! ና ውሰዳት ሥጋዬን!› እያለ ይመስላል:: ገጣሚም ነውና በግጥሞቹም ሳይቀር ይናገራል::

“ከሞት ጋር ቀጠሮ አለኝ

ቢያልፈኝ ልከሰው

ቢተወኝ ልጠይቀው” ብሎ ነበር::

ታዲያ ስለ አገኘሁ መጨረሻ የሚናገሩ ብዙ ጉዳዮች ከሕይወቱ ጀርባ ተጽፈው ይገኛሉ:: በመጽሐፍም ቢሆን በሌላ ታሪኩ ተሰንዶለታል:: ከዚሁ ውስጥ ከሞት ጋር ፊት ለፊት የተገናኘባት ምሽትም አንዷ ናት:: አገኘሁ ምንም እንኳን በባሕሪ ለውጥና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ቢሆንም፤ ከሚወደው ጥበብ ጋር ግን አልተኳረፈም ነበር:: ከጭንቅ ሀሩር መሸሸጊያ ጥላው ነበረች:: አጠገቡ ያሉት ጥበብና ባለቤቱ ብቻ ናቸው:: በዚያች ሰዓትም የነበረው ከሁለቱ ጋር ነበር::

ከሰዓታት በፊት አገኘሁ ከቤቱ ውስጥ ሆኖ ስዕል በመሳል ላይ ሳለ የቤታቸው የአጥር በር ተንኳኳ:: ከውጭ በሩን ሲያንኳኳ የነበረው ሰውም “ምሽት ላይ ከቤተ መንግሥት ትፈለጋለህና እንዳትቀር” በማለት የቃል መልዕክት አስቀምጦለት እንደሄደ ይነገራል:: ሃሳቡ ለሁለት የተከፈለው አገኘሁም፣ አመሻሹን የሚስለውን ስዕል ገታ አድርጎ ተመልሼ ስመጣ እስልዋለሁ በማለት ለባለቤቱ ተናግሮ ከቤቱ ወጣ:: ከዚያ መልስ ወዴት ሄዶና ከማን ጋር ይገናኝ የሚያውቅ የለም::

ያለውና የጠበቀው ነገር ግን የተቃጠሩበትን ጊዜና ቦታውን ጠብቆ፣ ሰዓትና ኬክሮንዋን እንኳን ሳያረፍድ መጣ:: ነገር ግን መጥቶ እንደሚወስደው እንጂ መምጫ መንገዱን አልነገረውምና ጊዜና ቦታ፣ ሰበቡ ምን ይሆን የት አገኘሁ የሚያውቀው የለም:: ይህ ሰበብ ግን፤ የዚያን ምሽት ርምጃዎቹ ነበሩ:: በግንፍሌ ጎዳና ላይ ሲሄድ ነበር፤ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው፣ ያልገመተውና ሊገምተው የማይችለው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ደረሰበት:: ተገጨ:: ተፍገምግሞ ለመነሳት ሲል ግን መኪናው እንደገና ደገመው:: የአገኘሁ ሰውነት በቅጽበት እንዳልነበር ሲሆን ነብሱም ከዚህ የማምለጥ አቅም አልነበራትም:: በዚሁ ሰበብ ከዓለም ሕይወቱ፣ ከነብስ ጥሪው ተሰነባብቶ ላይመለስ እስከ ወዲያኛው ሄደ:: ከኑሮ አጥር ዘሎ፣ ከሕይወት ድንበር ተሻግሮ ከሙታን መንደር ከሞት ደጃፍ ተገኘ:: 1950ዓ.ም አገኘሁ በ45 ዓመቱ የሞትን ጽዋ ተጎነጨ::

የእዚያ የወዳጁ የብላቴን ወልደ ማሪያም ዕጣ ፈንታ ከእርሱም ጋር ተጋጠመ:: በሁለቱ አማሟት መካከል የነበረው ልዩነት አንዱ በጓዳ ሌላኛው በአደባባይ መሆኑ ነው:: ልክ እንደ ወዳጁ ሁሉ የእርሱም አማሟት ውዝግብ የታየበት ነበር:: ጥቂት የማይባሉ ‹ሆነ ተብሎ በመንግሥት የተፈጸመ ግድያ ነው› ብለው ሲናገሩ ተደምጠዋል:: ለወዳጁ እንዳደረገው በአደባባይ የሚሟገትለት ግን አልተገኘም::

“የሚሰማ ጆሮ ቢኖር ኖሮ” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ስለ አማሟቱ፣ ከገጾቹ በአንደኛው “አንድ ቀን ወደማታ እንግሊዝ ተማሪ ቤት ወደ ቤታቸው ሲሄዱ አንዲት መኪና ገጭታ በመጣል አለፈች:: አቶ አገኘሁ ከወደቁበት ሲነሱ መኪናዋ ተመልሳ ለሁለተኛ ጊዜ ገጨቻቸው:: ደግሞም ሳይነሱ በመቅረታቸው አካባቢው ላይ የሚገኙ ሰዎች ተጋግዘው ምኒልክ ሆስፒታል አደረሷቸው:: በዛም ብዙ ሳይቆዩ ሕይወታቸው አለፈ” የሚል ነው:: እምቢ! ብሎ ሞትን አንድ ጊዜ ታግሎ ሁለተኛውን ዕድል አጣና ስምና ሥራዎቹን አደራ ብሎ ብቻ ከእስትንፋሱ ተቋረጠ:: ለሞቱ ሰበብ በአንደበቱ የተናገራቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ በብሩሹ የሳለቸው ስዕሎቹም ሊሆኑ ይችላሉ:: ምክንያቱም በአሳሳሉ ምጸታዊ ተምሳሌቶችን የሚጠቀም ነበር:: በቅርብ ያውቁት የነበሩም ከእነዚህ ስዕሎቹ መካከል “ስዕል ቁጥር 12” ሲል የሰየመው አህዮች የሚታዩበት ስዕሉ እንደሆነ ይናገራሉ::

ያም ቢሆን ይህ ግን አገኘሁ በሙያው ጥበብ ለሀገሩ ብዙ የደከመ ሰው ነበር:: ‹ፍትህ ለአገኘሁ!› ብሎ ለነብሱ እረፍትና ፍትሕ የሚጠይቅለት ግን ሳይታይ፣ ‹የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ነው› የተባባሉበት ይመስል ቄሱም መጽሐፉም ዝም ሆነ:: ተድበሰበሰናም ታለፈ:: አገኘሁ ግን ሁሉ ነገሩ እንግዳ የሆነ፣ በራሱና በማኅበረሰቡ የሕይወት ፍልስፍና ውስጥ የኖረ ተራማጅ ነበር:: ድንቅ ሥራዎቹ ዛሬም ድረስ ሲዘክሩት አሉ::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You