
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በታህሣሥ 17 ቀን 1936 በቦነስ አይረስ አርጀንቲና ውስጥ በሆርጌ ማሪዮ ቤርጎሊዮ የተወለዱ ሲሆን በመጋቢት 13 ቀን 2013 የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 266ኛ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዋል። ከ12 አመታት አገልግሎት በኋላ ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል። ከመላው ዓለም በጎረፉ በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ምዕመንና የሌላ ዕምነት ተከታዮች፤ከ50 በላይ የሀገራት መሪዎች፤የ145 ሀገራት ልዑካን እና 10 ነገሥታት፣ንግሥታትና ልዑላን በተገኙበት ትናንት የቀብር ስርዓታቸው ተፈጽሟል። በነገራችን ላይ ከላቲን አሜሪካ የመጡ የመጀመሪያው ጳጳስ፣ የመጀመሪያው የየሱሳውያን ጳጳስ እና ከ1200 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ያልሆኑ ጳጳስ ነበሩ።
የእሳቸው መመረጥ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረን አሠራርና ልማድ ለውጧል። በቤተክርስቲያኗ ተሀድሶ አምጥተዋል። የድሆች፣ የስደተኞችና አድልዎና መገለል ለተፈጠረባቸው ድምጽ በመሆን አዲስ ንቅናቄ ፈጥረዋል። በዓለማችን ጦርነቶች እንዲቆሙ ሰላም እንዲመጣ ሌት ተቀን ጥረዋል። ለህጻናት ለአጠቃላይ ምዕመኑ ቅርብ ነበሩ። ለዚህ የሕዝቡ ጳጳስ እስከመባል የደረሱት። ትሁትና ቀለል ያለ የአኗኗር ዘይቤ የነበራቸው ጳጳስ ነበሩ። ከተቀናጣው ቪላ ይልቅ ሁለት ክፍል ያለውን የእንግዳ ማረፊያ መርጠው በዚያ ይኖሩ ነበር። አለባበሳቸው እንዲሁ ቀለል ያለ ነበር። የሚመገቡት ከሰራተኞች ጋር በካፍቴሪያ ነበር።
ከሞቱ በኋላም ጳጳሳት በሚቀበሩበት በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ወይም ባሲሊካ ሳይሆን መቀበር የፈለጉት ከቫቲካን ውጭ አነስ ባለች ቤተ ክርስቲያን ነው። ምክንያቱም ቅዱስ ጴጥሮስ ቢቀበሩ ብዙ የፕሮቶኮልና የጸጥታ ቅድመ ሁኔታ ስላለ ምዕመናን በቀላሉ ሊያገኟቸው አይችሉም። የአስከሬን ሳጥኑም በጣውላ ብቻ የተሰራ ተራ ሳጥን እንዲሆን በተናዘዙት መሰረት እንዲያ ነው የሆነው። በአጠቃላ ከእሳቸው በፊት ከነበሩት ጳጳሳት በላይ በዓለማችን ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ነበሩ። እንደ እሳቸው በመላው ዓለም ተዘዋውሮ ወንጌልን ፍቅርንና ሰላምን የሰበከ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።
- ውልደት እና አስተዳደግ
ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ የተወለዱት በአርጀንቲና ውስጥ ከጣሊያን ስደተኛ ቤተሰቦች ነው። ያደጉት ዝቅተኛ የሕብረተሰብ ክፍል በሚኖሩበት ሰፈር ነው። አባት የባቡር ሀዲድ ሠራተኛ ነበሩ ፣አስተዳደጋቸው ጠንካራ የሥራ ባህሪ እና ለድሆች ጥልቅ ርህራሄ እንዲኖራቸው የራሱ ሚና ነበረው። በወጣትነታቸው ኬሚስትሪ ያጠኑ አልፎ ተርፎም በኬሚካል ቴክኒሻንነት የሰሩ ናቸው ፤በ1958 ወደ ክህነት መጡ።
- የቦነስ አይረስ ሊቀ ጳጳስ እና ካርዲናል፦ በ1998 ቤርጎሊዮ የቦነስ አይረስ ሊቀ ጳጳስ ሆኑ። በ2001 በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል 2ኛ ወደ ካርዲናልነት ከፍ ብለዋል ። እንደ ካርዲናል፣በትንሽ አፓርታማ ውስጥ ይኖሩ ነበር፣ የራሳቸውን ምግብ ያበስላሉ፣ ለትራንስፖርት የህዝብ ማመላለሻን ይጠቀሙ የነበር ሲሆን፤ሁል ጊዜም ለድሆች የሚያዝኑ ትሁት አባት ነበሩ። ለዚህ ነው የድሆች ጳጳስ ይባሉ የነበሩት።
- የጳጳስ ምርጫ፦ ፓፕ በነዲክት 16ኛ ከ600 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈቃዳቸው ከኃላፊነት ሲለቁ፤በ2013 ጉባኤ በተካሄደ ሚስጥራዊ ምርጫ እነሱ ኮንክሌቭ ይሉታል ቤርጎሊዮን ጳጳስ አድርጎ መረጠ። ለጵጵስናቸው “ፍራንሲስ” የሚለውን ስም መረጡ። እንደ ቅዱስ ፍራንሲስ ድሆችን የተረሱትን የተተዉትን አገለግላለሁ ለማለት ነው ይሄን ስም የመረጡት። ስሙ ራሱ አብዮታዊ እና ተምሳሌታዊ ነበር፣ ይህም ካለፈው መላቀቅ እና ወደ ትህትና፣ ሰላም እና የአገልግሎት መሰረታዊ እሴቶች መመለሱን ያመለክታል።
- የአመራር ዘይቤ እና ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች፦ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አመራር በአካታችነት እና በተሀድሶ የተቃኘ ሲሆን፤ስለ ጵጵስና የነበረውን ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ ቀይረዋል። የተወሳሰበ ስርዓትን አሠራርን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ትህትናን የጵጵስናቸው መነሻ አድርገዋል። ከሐዋርያዊ ቤተ መንግሥት ይልቅ በቫቲካን የእንግዳ ማረፊያ መኖርን፣የእስረኞችንና የስደተኞችን እግር በማጠብ፣ጉዟቸውንና ትኩረታቸውን ከበለጸገው ዓለም ይልቅ በድህነትና በኋላቀርነት ወደ ሚቆራመደው ዓለም አደረጉ።
የእሳቸው ዋና ዋና ትኩረት፦
– ድሆችን እና የተገለሉ ሰዎችን ማገልገል፤
– በሃይማኖቶች መካከል ውይይትን ማበረታታት እና ስለ ሰላም መሥራት፤
– የዓለምን እኩልነት ማቀንቀን እና የአየር ንብረት ለውጥን አሳሳቢነት ማሳሰብ፤
– የቫቲካንን ቢሮክራሲ ማሻሻል፤
– የጾታ ጥቃትን ፊት ለፊት መጋፈጥና ማውገዝ፤
- ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ፦
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በጥልቅ የካቶሊክ ሥነ-መለኮት ውስጥ የተመሰረቱ ቢሆንም፣በወቅታዊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እና ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው አባት ነበሩ። በ2015 አካባቢን መንከባከብ ድሆችን መንከባከብ ነው በሚል ዓለም አቀፍ ንቅናቄን እስከማቀጣጠል ደርሰው ነበር። ስግብግብነት ከሸማችነት ተጃምለው የአየር ንብረት ለውጡን እያባባሱት ነው በሚል በተደጋጋሚ ትችት ያቀርቡ ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ገንዘብን እንደ ጣዖት ማምለክን እና ድሆችን የሚያገል ኢኮኖሚያዊ ስርዓትን በአደባባይ ያወግዙ ነበር። ሀገራት ግድግዳዎችን ሳይሆን ድልድዮችን በመገንባት
ስደተኞችን እንዲቀበሉም ጥረዋል። እንዲሁም በምድራችን ሰላም እንዲሰፍን፤ጦርነቶች በሰላም እንዲቋጩ ከጁባ እስከ ካርቱም፤ከኪየቭ እስከ ሞስኮ፤ከደማስከስ እስከ ካራከስ ወትውተዋል።
ቫቲካን እንደምትለው በመላው ዓለም 1.4 ቢሊዮን ካቶሊኮች አሉ፣ይህም ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ 17 በመቶውን ይይዛል። የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በአውሮፓውያኑ 2024 እስያን ሲጎበኙ በምሥራቅ ቲሞር የሚኖሩ ሰዎች በአጠቃላይ አደባባይ ወጥተው ተቀብለዋቸዋል ። በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ኪንሻሳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። እነዚህ የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎች ናቸው ይለናል ቢቢሲ።
ሊቀ ጳጳሱ ከቤተ ክርስቲያኑ ባሻገር ቫቲካንንም ያስተዳድራሉ። መንበረ ጵጵስና የሚባለው ይህ ሥፍራ በዓለም አቀፍ ሕግ እንደ ሉዓላዊ ግዛት ነው የሚቆጠረው። ከ184 ሀገራት እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያደርጋሉ። በተባበሩት መንግሥታት ድምጽ መስጠት ባይችሉም የቋሚ ታዛቢነት ሚናም አላቸው። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውይይቶች ላይ በመሳተፍ አቅጣጫ ማስያዝ የሚችሉበት አቅም ይሰጣቸዋል። በ2015 የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ሲፈረም ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ በቂ ትኩረት አልሰጡም ብለው ተችተዋል። ሀገራት ምድርን ለማትረፍ ጥረት እያደረጉ እንዳልሆነ እና “በትዕቢት የተሞላ ችላ ባይነት” እንዳሳዩ ተናግረው ነበር። የሚያደርጉት ንግግርም በተለይም በደቡባዊ የዓለም ክፍል ላሉ ሀገራት ጠቃሚ እንደሆነ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል። በ2024 የአየር ንብረት ለውጥ ውይይት በመንግሥታቱ ድርጅት ሲካሄድ የሴቶች መብት ጉዳይ እንዳይነሳ ሆሊ ሲ ማገዱ ይታወሳል።
በአውሮፓውያኑ 2014 በኩባ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲታደስ ለማድረግ ጳጳሱ የተጫወቱት ሚና አይዘነጋም። የቀድሞው ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማ እና ራውል ካስትሮ በአደባባይ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን አመስግነዋል። ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ለሁለቱም ሀገራት ደብዳቤ በመጻፍና በቫቲካን ምሥጢራዊ ውይይት በማዘጋጀት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲታደስ አስችለዋል። አሜሪካ ይሄንን ስምምነት በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመን ውድቅ አድርጋዋለች።
በበርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሆለንባክ እንደሚሉት፣ ባለፉት 25 ዓመታት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሚና ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ ማድረግ ነው። በ1960ዎቹ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ሲካሄድ ቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮቷን ከልሳለች። ለሰብአዊ መብት እና ለሃይማኖት ነጻነት የምትሰጠው ዋጋ ከፍ ያለ እንደሆነ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህም በከፍተኛ ሁኔታ አቅጣጫ የለወጠ ውሳኔ እንደነበር ፕሮፌሰር ዴቪድ ይናገራሉ።
የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ሳሙኤል ሀንቲንገን እንደሚሉት፣ ዳግማዊ ጆን ፖል ሊቀ ጳጳስ ሳሉ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ ከተሻገሩ ሀገራት መካከል ሦስት አራተኛው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው የተለወጡት። ስፔን እና ፖርቹጋል ከፍራንኮ እና ሳልዛር አስተዳደር ከወጡ በኋላ ወደ ላቲን አሜሪካም ለውጡ ተስፋፍቷል። ካቶሊኮች በብዛት በሚኖሩባቸው ፊሊፒንስ እና ደቡብ ኮሪያም ተፅዕኖው ታይቷል” ይላሉ ፕሮፌሰር ዴቪድ። ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ በትውልድ ሀገራቸው ፖላንድም ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ጫና በማሳደር ይታወሳሉ። የሶቪየት ኅብረት እንዲወድቅ እና ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ በማስቻልም ስማቸው ይነሳል።
ቫቲካን በሁሉም ሀገራት መሪዎች ላይ ጫና ታሳድራለች ማለት ግን አይደለም። የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ካቶሊክ ቢሆኑም ስደተኞችን ከሀገር እያባረሩ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም ሳይቀር ስደተኛ ነው በሚል ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለደረሰባቸው ትችት የአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ ሹም የሆኑት ካቶሊኩ ቶም ሆማን “ጳጳሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ያስተካክሉ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የአማዞን ደን ጥበቃ እንዲደረግለት ማሳሰባቸውን ተከትሎ፣ በ2020 የብራዚል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ “ጳጳሱ አርጀንቲናዊ ቢሆኑም ፈጣሪ ብራዚላዊ አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ በጽንስ በማቋረጥ እና በሴቶች የሥነ ተዋልዶ መብት ላይ ወግ አጥባቂ አቋም ነው የያዘችው በሚል በአውሮፓ ያላት ድጋፍ ቀንሷል። ይህ ወግ አጥባቂነት ከ21ኛው ክፍለ ዘመን አይጠበቅም ሲሉም ቫቲካንን ይተቻሉ። ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሴቶች ዲያቆን፣ ቄስ እና ሌላም የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው ባለመፍቀድም ይተቻሉ። በላቲን አሜሪካ አሁንም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጫና ብታሳድርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፅዕኖዋ እየቀነሰ መጥቷል። ጽንስ ማቋረጥን በላቲን አሜሪካ በመገደብ ቫቲካን ስሟ ይነሳል። ባለፉት 20 ዓመታት ግን ኡራጓይ፣ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲና እና ኮሎምቢያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮትን ችላ በማለት የጽንስ ማቋረጥ ተደራሽነት እንዲስፋፋ አድርገዋል።
በርካታ ካቶሊኮች በሚኖሩባት ብራዚል በቀጣይ አምስት ዓመታት በርካታ ተከታዮች ያሉት ሃይማኖት ሆኖ እንደማይቀጥል ተንታኞች ይገምታሉ ። በቤተ ክርስቲያኗ ቀሳውስት የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች አደባባይ መውጣታቸው ሲቀጥል የቤተ ክርስቲያኗ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትም እየተሸረሸረ ነው ። ሆኖም ግን የትኛውም ሊቀ ጳጳስ በመሪዎች ላይ የሚያሳድሩት ጫና እንዳለ ይቀጥላል። የክርስትና ሰፊው ቅርንጫፍ የሆነውን ሃይማኖት ከመምራት ባሻገር እንደ ሉዓላዊ አስተዳደርም መቀጠላቸው አይቀርም። በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ተዋጊዎች እግር ላይ መውደቅ፣በግሪክ ስደተኞች መጠለያ ያሉ ስደተኞችን በማጽናናት እና በሌሎችም ክንውኖች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ሚና ማሳያ ናቸው።
ከአውሮፓ ውጪ በመመረጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመምራት የመጀመሪያው የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በ88 ዓመታቸው አርፈዋል። ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ያላትን ቤተክርስቲያን ለ12 ዓመታት የመሩት ፖፕ ፍራንሲስ አርጀንቲናውያን ቤተሰቦቻቸው ያወጡላቸው ስም ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ የሚል ነበር። ስለ ጳጳሱ ብዙም የማይታወቁ አንዳንድ እውነታዎችን እነሆ፦
የምሽት ክለብ ጋርድ ነበሩ፦
ቤርጎሊዮ በአርጀንቲና ዋና ከተማ በቦነስ አይረስ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኬሚስትሪ ዲፕሎማ በማጠናቀቅ በነገረ መለኮት ዲግሪ አግኝተው ሥነ-ጽሁፍ እና ሥነ ልቦና አስተምረዋል። በአውሮፓውያኑ 2010 በሰጡት ቃለ ምልልስ 13 ዓመት ሲሆናቸው ሥራ እንዲጀምሩ ያበረታቷቸው ስለነበረ በአንድ የሹራብ ፋብሪካ ውስጥ በጽዳት ሠራተኝነት እንዲቀጠሩ አደረጓቸው። ከዚያም በኋላ ከጽዳት ሥራው በተጨማሪ በምሽት ክበብ ውስጥ ጋርድ (የጥበቃ ሠራተኛ) ሆነው መሥራታቸውን ሮም ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲናገሩ ብዙዎችን አስደንቀዋል። በተጨማሪም በአንድ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ ሠርተው ነበር።
የእግር ኳስ አፍቃሪ ነበሩ፦
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በልጅነታቸው የሚደግፉት የአካባቢያቸው የቦነስ አይረስ ቡድን የሆነው የሳን ሎሬንዞ ደ አልማግሮ የዕድሜ ልክ ደጋፊ ነበሩ። በአውሮፓውያን 2014 ሳን ሎሬንዞ የኮፓ ሊበርታዶሬስን የተባለውን የደቡብ አሜሪካ የክለቦች እግር ኳስ ውድድር ላይ እጅግ የተከበረውን ዋንጫ ሲያሸንፍ በክለቡ የ106 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛው ውጤት ነበረ። ጳጳሱ ለክለቡ ያላቸው ድጋፍ ለድል አድራጊነቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ወይ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ “በጣም ደስተኛ ነኝ፣ ግን አይደለም፣ ይህ ተአምር አይደለም” ብለዋል።
ቡድኑ በዚያው ዓመት የአርጀንቲናን ከፍተኛ ዲቪዚዮን አሸናፊ በመሆን የቡድኑ አባላት ከጀርባው “ፍራንሲስኮ ካምፔዮን” ወይም ሻምፒዮኑ ፍራንሲስ የሚል ጽሁፍ የሰፈረበት የቡድኑን ማሊያን ለጳጳሱ አበርክተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በተጨማሪም ሊዮኔል ሜሲ እና ሟቹ ዲያጎ ማራዶናን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን እንዲሁም ስዊድናዊው ኮከብ ተጫዋች ዝላታን ኢብራሂሞቪች እና ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎን ጋር ተገናኝተዋል። የጳጳሱ ህልፈት ይፋ ከሆነ በኋላ ለሰኞ ዕለት ታቅደው የነበሩ አራት የጣሊያን ከፍተኛ የእግር ኳስ ሊግ ሴሪኤ ጨዋታዎች ተሰርዘው ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለረጅም ጊዜ አገልግሎታቸውን እና እንቅስቃሴያቸውን ቀለል ያለ በማድረግ ሥነ ምግባራቸው ይታወቃሉ። ለዚህም የመጓጓዣ ምርጫቸው ማሳያ ነው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ወዲያውኑ ለጳጳስ የተዘጋጀውን ቅንጡ ሊሞዚን ከመጠቀም ይልቅ ከካርዲናሎቻቸው ጋር በአውቶብስ ነበር የሄዱት። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከመሆናቸው በፊት በቦነስ አይረስ በአስቸጋሪ የሕይወት ዘይቤያቸው ይታወቁ የነበሩ ሲሆን ካርዲናል እና ሊቀ ጳጳስ የሆኑትም እዚያው ነው። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ፍራንሲስ በአውቶብሶች እና በከተማ የምድር ውስጥ ባቡሮች አዘውትረው መጓዝን የሚመርጡ ሲሆን፣ወደ ቫቲካን በአውሮፕላን ሲጓዙ በአንደኛ ማዕረግ ሳይሆን በመደበኛው የኢኮኖሚ ክፍል ውስጥ ቦታ ይዘው ነበር የሚሄዱት።
በጵጵስና ዘመናቸውም የቅንጦት መኪናዎችን የማይጠቀሙት ፍራንሲስ ውድ ያልሆኑትን የጣሊያን ስሪት ፎርድ ፎከስ ወይም በአውሮፓውያኑ 2015 አሜሪካን ሲጎበኙ ፊያት 500 ኤል ያሉ ሞዴሎችን በመምረጥ ይታወቃሉ። ብዙ ጊዜ በጉብኝት ወቅት ሰዎችን ሰላምታ ለመስጠት “ፖፕሞባይል” የተባለውን ግልጽ መኪና ይጠቀሙ ነበር። ነገር ግን በእሳቸው እና በተሰበሰቡ ምዕመናን መካከል ጥይት መከላከያ መስታወት ያላቸውን ተሽከርካሪዎች አይወዷቸውም። እንዲህ ያለውን ሁኔታ “በሰርዲን ጣሳ” ውስጥ ያሉ ያህል እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ቀልድ አዋቂ ነበሩ፦
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በተገኙባቸው ስፍራዎች ሁሉ በቀልድ እና በሳቅ ይታወቃሉ።
በአውሮፓውያኑ 2024 ከ15 ሀገራት የተውጣጡ ጂሚ ፋሎን፣ ክሪስ ሮክ እና ሁፒ ጎልድበርግን ጨምሮ ከ100 በላይ ኮሜዲያንን በቫቲካን አስተናግደዋል። ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በየቀኑ “አቤቱ፣ ጌታዬ ሆይ፣ ጥሩ ቀልድ ለዛሬ ስጠኝ” እያሉ ይጸልዩ እንደነበር ለኮሜዲያኑ ተናግረዋል። ይህም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ በሀገር ክህደት የተገደለው እና በኋላም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ተብሎ የተሰየመው የቶማስ ሞር ጸሎት አካል ነበር። በወቅቱ ለኮሜዲያኑ የተነበበው ጸሎት እንዲህ ይላል፡- “ቀልድ እንዳገኝ፣ በሕይወት ውስጥ ትንሽ ደስታን እንድገነዘብ እና ከሌሎች ጋር ለመካፈል እንድችል ፀጋውን ስጠኝ” የሚል ነው። በተጨማሪም “በእርግጥ በአምላክ ላይም መሳቅ ትችላላችሁ። ይህ ደግሞ ማዋረድ አይደለም” በማለት ይህንንም “የምዕመናንን ሃይማኖታዊ ስሜት ሳያስከፋ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል።
ከፍተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታይ አፍርተዋል። በ2018 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በይነመረብን (ኢንትርኔት) “የእግዚአብሔር ስጦታ” ነው በማለት ገልጸውት፣ ነገር ግን “ታላቅ ኃላፊነትን” እንደሚጠይቅም አሳስበዋል። ከሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ ጳጳስ ትዊተርን (አሁን ኤክስ) የሚባለውን በአውሮፓውያኑ 2012 ከፍተዋል፣ ነገር ግን የተከታዮቹ ቁጥር ፍራንሲስ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። የጳጳሱ ኤክስ አካውንት በእንግሊዝኛ፣ በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛ፣ በፖርቱጋልኛ፣ በፖላንድኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በአረብኛ እና ላቲን ዘጠኝ ቋንቋዎች መልዕክት የሚያጋራ ሲሆን በአጠቃላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።
የጳጳሱ ኢንስታግራም አካውንት 9.9 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ሲሆን በቅርቡ “አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን” መጠቀም “የሰውን ግንኙነት እንደማይተካ፣ የሰውን ክብር የሚያስከብር እና የዘመናችንን ቀውሶች እንድንጋፈጥ የሚረዳ” በማለት ጸሎት ተጋርቶበታል። ፖፕ ፍራንሲስ ለመጨረሻ ጊዜ በኤክስ ገጻቸው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ከህልፈታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የፋሲካ ዕለት ነበር። በመልዕክታቸውም “ክርስቶስ ተነሥቷል! እነዚህ ቃላት የመኖራችንን አጠቃላይ ትርጉም ይይዛሉ፣ ምክንያቱም እኛ የተፈጠርነው ለሕይወት እንጂ ለሞት አይደለም” ብለው ነበር።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም