
ማን አልሞሽ? ያሏት ከእንቡጥ አበባ የተገኘች እጹብ ቅመም መሳይ…ታለመች በፍቅር፣ ታለመች በጥበብ፤ መጣች ደግሞ ከሰለሞን መጎናጸፊያ ንጥት! ፍክት! ያለውን የጥበብ ቀሚሷን ለብሳ፣ ጸአዳ ነጠላዋን አገልድማ፣ ውብ ደመግቡ ፊቷን በማይለያት ፈገግታ የመስከረምን ፀሐይ አስመስላ። “ቆንጆ ብቻ ሸጋ ብቻ፤ ኸረ ያለው ማነው?” በእርግጥም አዎን…ቆንጆ ሸጋ ብቻ አይደለችም። ማናልሞሽ ዲቦ የባሕል ሙዚቃ ልዕልት፣ የአውዳመት የልብ ትርታ፣ በእግዜር የጥበብ እጆች የተቀመመች ማጣፈጫ ቅመም ናት።
“…እሰይ መጣልን አውዳመት፣ በዓላችን አውዳመት፣ ለዚህ ላበቃን አውዳመት፣ አምላክ ይመስገን አውዳመት…”
የሚለውን ውብ ስርቅርቅ ድምጿን ለመስማት፣ አውዳመት በሰጋር ፈረሱ ላይ ተቀምጦ ሽምጥ እየጋለበ ሲገሰግስ ደርሷል። እዚህም ቤት፣ እዚያም ቤት ውስጥ አውዳመትን ለማስተናገድ ሽር ጉዱ ይላሉ። ቀዬው መንደሩ፣ ሳር ቅጠል ሀገሩ፣ ከተሜና ባላገሩ ሁሉም ለዚህ እንግዳ ዝንጥፍጥፍ! እያለ ባለው አቅሙ ያስተናግደዋል።
“ጤና ለሰጠው ሰው፣ ዕድሜውን ላደለው፤ አውዳመት ደስታ ነው፣ አውዳመት ጸጋ ነው” ከዚህ ሙዚቃ ጋር ቤቱ ሙሉ ነው። ቢኖርም ባይኖርም፣ ቢትረፈረፍ ቢያንስ…ይህቺን እየሰሙ የአውዳመት ሽታው ልብን ማወዱ አይቀርም። ጆሮና ልብ ከጠገቡ ቀሪው እዳው ገብስ ነው።
“አሳ አበላሻለሁ፣ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ…” ብሎ ጸጋዬ ዘርፉ ሲያንጎራጉር፣ አክሊሉ ስዩም ደግሞ “ጠይም አሳ መሳይ፣ የውብዳር የውብዳር ውቢቷ፤ ጎንደር ደምቢያ መስኩ፣ ጣና ዳር ነው ቤቷ” ያላት ጠይሟ አሳ መሳይ ፍልቅልቅ፣ ደምቢያ ላይ ከጣና ወንዝ ዳር የምትቦርቅ ትንሽዬ ልጅ ነበረች። ከጣና ሐይቅ ዳር ተወልዳ፣ ከዓባይ ወንዝ ጋር ተከትላው አብራው ስትከንፍ ላደገችው ማናልሞሽ ዲቦ ሙዚቃዎቹ ለእርሷ ናቸው። እንደ አሳው ስትንቦራጨቅ አድጋበታለችና ለሐይቁ ያላት ስሜትና እስትንፋሷም እንዲሁ እንደ አሳው ነበር። ገና በስድስት ዓመቷ የአባቷን ከብቶች ጭራ ይዛ እየነዳች ከወንዙ ዳር፣ ከሐይቁ ዙሪያ ታሰማራለች።
ከወዲያ ግድም ከሚመጡና ከመንደሯ ማቲዎች ጋር ሰብሰብ ብለው፣ ከዚያ ከግጦሹ ላይ “አሳ በለው በለው፣ አሳ በለው፤ እንዲያው አሳ በለው…” እያሉ ይጨፍራሉ። ተያይዘው ሲሮጡ ከዳገቱ ሽቅብ ወጥተው፣ ቁልቁለቱን ተንሸራተው ሲቦርቁ ውለው ነገን እንደናፈቁ፣ የከብቶቻችውን ጭራ ተከትለው ከየቤታቸው ይገባሉ። የማናልሞሽ ናፍቆት ግን ዛሬም ነገም “አሳ በለው በለው” እያሉ ማንጎራጎር፣ ሐይቁን እየዞሩ ብቅ ጥልቅ ከሚሉ አሳዎቹ ጋር ማዜም ነበር። ያኔም የሚስረቀረቀው ድምጿ ከጣፋጭ የልጅነት አንደበቷ ጋር ተዳምሮ፤ ከሐይቁ ውስጥ ያሉ ነብሳት ጆሯቸውን አቁመው፣ አሳዎቹም እየፈነደቁ የሚሰሟት ይመስላል። ልጅነቷ በዚህ ሙዚቃዊ የባሕል ጨዋታ ተማርኮ፣ በስተመጨረሻም ዝነኛ አድርጎ መታወቂያ ስሟ “አሳ በለው” ሆነ።
ትንሽዋ ማናልሞሽ ገና ስምንት ዓመቷ ነበር። አሁንም ያንን ዜማ እያዜመች ከእረኝነቷ ጋር ናት። በየዕለቱ የምታዘወትረውና የምትወደው ነገርም ይሄው ነው። ሌላ ስለየትኛውም ሕይወት የምታውቀው ነገር የላትም። ሕይወት ምን ትሁን፣ አሁንም ሆነ ወደፊት ምን ይጠብቃት እንደሆን ለማወቅ ዕድሜዋ ገና ነበር። ዳሩ ግን በዚሁ ዕድሜዋ ምኑንም ከማታውቀው አንድ ከባድ ነገር ጋር ተፋጠጠች። የስምንት ዓመቷ ማናልሞሽ ለባል ታጨች። ለአንዳንዶቻችን ለማመን የሚከብድ እውነት ቢሆንም፤ ለማናልሞሽና ለአካባቢዋ እኩዮች ግን የተለመደ የባሕል ወጋቸው ነው። ይህ የባሕል እሴት እንደሌላው ዓይነት ጋብቻ ሳይሆን ‹የማደጎ ጋብቻ› ነው።
በባሕሉ መሠረት ባል ከወሰደ በኋላ፤ እስክትጠነክር ድረስ ሴትነቷን ሳያይ፣ ከቤቱ ውስጥ እየተንከባከባት ይቆያል። አሊያም እንደሁኔታው ከራሷ ወይም ከእርሱ ቤተሰቦች ዘንድ ትሆናለች። ለማታውቀው ምናልባት አንድም ቀን እንዳየችው ትዝ ለማይላት ሰው ድንገት ሚስት ሆና ትገኛለች። ማናልሞሽን የጠበቃት ነገርም ይሄው ነው። ይህ በሆነ በሁለተኛው ዓመት፣ በአሥር ዓመቷ ጊዜው ደርሶ ከባልዋ ጋር ተጠቃለለች። “ያሆ በል! ያሆ!…አሃሃይ ጉማ!…” ተባለላት። ተደገሰ። ተበላ። ተጠጣ። ተጨፈረላት…ፈረሱ ላይ ጉብ አድርጎ ይዟት ሄደ።
ከትዳር ጎጆ ውስጥ ከገባች ጊዜው አልራቀም፤ እንዲያውም ገና አልሄደም…ለባል የተሰጠችው ምንም እንኳ በለጋነት ዕድሜዋ ቢሆንም፤ ሲያያት ውሎ ይዟት የሄደው አሞራ ግን ክፉ አልነበረም። እንደ አንዳንድ አቻዎቿ ያለ ዕድሜዋ እያረገፈ፣ ያለ አቅሟ ሸክም ቆልሎ ለሰቆቃ አልዳረጋትም። እንዲያውም ለደረሰችበት ሸጋ ጥበብ መንገድ ሆናት። መንገዱም ወደ አዲስ አበባ ነበር።
ማናልሞሽን ያገባው ሰው ማሲንቆውን አንግቶ፣ ማሲንቆ የሚኮረኩር ባለ ማሲንቆ ነበርና ጥበብ ሁለቱንም ጠራቻቸው። ከወደ አዲስ አበባ፣ ከእንጦጦ ተራራ ላይ ቆማ ነጋሪት እየጎሰመች፣ መለከቷን ነፋች። “አሞራ በሰማይ ጅብ ይሄዳል በምድር፤ ሰጥ ያለው ከተማ ሸዋ ነው በጌምድር” እያለች ስታዜም፣ በማሲንቆው አጅቧት ተያይዘው አዲስ አበባ ገቡ።
ማናልሞሽ ለሙዚቃ የተፈጠረች መሆኗን የምታውቀው ያኔ ገና ጣና ዳር ሆና ስታንጎራጉር ነበር። ቤሰቦቿም ሆኑ የቀዬው ሰውም ችሎታዋን የሚመለከተው ነበር። ምናልባት ለዚያም ይሆናል ለባለማሲንቆ የዳሯት። ጥንዶቹ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ያመሩት፣ ቦሌ ላይ ወደሚገኝ ወደ አንድ የምሽት ክበብ ነበር። እርሷ ድምጿን እያስረቀረቀች፣ እርሱም ማሲንቆውን እየገዘገዘ፣ በትዳር ብቻ ሳይሆን በሙዚቃም ኮከባቸው ገጠመ። እሳቱ ተቀጣጥሎ ቦግ ብሎ እንደ ችቦ እየበራ፣ ድምቅ ብሎ እንደ ጨረቃ ወርቃማውን የብርሃን ቀለም መፈንጠቅ ጀመረ። “አሳ በለው በለው” ይሄኔ ነበር።
ከየትኛዎቹም ከምትጫወታቸው ሙዚቃዎች፣ የዚህ ሙዚቃ ነገር ለምሽት ክበቡ ታዳሚም አልሆንልህ አለው። በድምጿ ተማርኮ፣ በሙዚቃው ፍቅር ወድቆ፣ ያለዚህ ሙዚቃማ እንዴት ማለት ጀመረ። “ያቺ ‹አሳ በለው በለው› የምትለው ልጅስ? …ሳቂታዋ? ጠይም አሳ መሳይ?…” ተወዳጅና ተናፋቂ ሆነች። በመሃል ግን ማናልሞሽ ከቤቱ የለችም። ሌላ አጋጣሚ፣ ሌላ አንድ ነገር ተከትላ ሄደች።
ከዚያ ቤት ውስጥ የተመለከተቻት አንዲት ዕውቅ ድምጻዊት ጠጋ ብላ “አንቺ የሀገሬ ልጅ ነሽ። የሀገሬ ልጅ ብቻ ሳትሆኚም ጎረቤቴ ነሽ። ጎረቤት ማለት ደግሞ ዘመድ ማለት ነውና ስለዚህ ከእኔ ጋር አብረሽ ሥሪ?” ስትል ጠየቀቻት። ማናልሞሽ ስታስበው ነገሩ እውነት አለው፤ ቢከፋም ቢለማም የቀዬ ሰው ይሻላል ብላ መስማማቷን ገለጸች። ያቺ ሴትም የሙዚቀኛ መፍለቂያ ከሆነው ቤቷ ይዛት ሄደች። እርሷም ብርቱካን ዱባለ ነበረች። እሳት እሳትን ወለደ እንዲሉ የብርቱካን ልጅ ደግሞ መሰሉ ፋንታሁን ናት። በቤቱ ውስጥ ከሚገኙት መካከል የኔ ጌጤ የተባለው ድምጻዊም የብርቱካን ዱባለ የባሏ ልጅ ቢሆንም ልጇ ነው። ማናልሞሽ የተቀላቀለችው ይህንን ቤተሰብ ነበር።
በዚያም በብዙ ነገሮች መልካም ጅምር ነበራት። አብረው እየሠሩም በመሃከል ብርቱካን ለሦስቱ ልጆች ሀሳብ አቀረበች። ለምን አብራችሁ አንድ ካሴት አታወጡም የሚል ነበር። ሀሳቡ ለማናልሞሽ የመልካም አጋጣሚ ነበር። በሌላ በኩል ባሉት ዘንድ ግን ነገሩ ትንሽ የቅሬታ አዝማሚያ ታየበት። “በእኔ መጨመር ደስተኛ ስላልሆኑበት አይሆንም ብለው ተቃወሙ።
ሀሳቡን ያመጣችው ብርቱካንም የእነርሱን ሁኔታ ስታይ በኋላ ወደ እነርሱ አዘነበለች” ስትል በአንድ ወቅት ገልጻው ነበር። በእርሷና በሁለቱ ወንድምና እህት መካከል ለመስማማት ባይችሉም፤ የግጥምና ዜማዎቹ ደራሲ የነበረው ዘላለም መኩሪያ አስቀድሞ ማናልሞሽን አግኝቷትና እንድትሠራም አውርተው ነበር። ነገር ግን ሥራውን ወንድምና እህት ለብቻቸው ጀምረውት ነበር። ማናልሞሽ እንዳትሠራበት የፈለጉበት ትልቁ ምክንያት ካሴቱ “የብርቱካን ፍሬዎች” በሚል ስያሜ ስለሚታተም ነበር። የእርሷ መካተት ቤተሰባዊ መልኩን ይቀይረዋል ከሚል ስጋትም ጭምር ነው። ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን ሲያውቅ ዘላለም “አሳ በለው ከሌለችበትማ በጭራሽ አይሆንም” ሲል ተቃወመ። በኋላ የብርቱካን ባለቤት በነገሩ ገባበትና ማናልሞሽ መካተት አለባት ሲል ድምጹን ሰጥቶ ሞገተላት። በመስተመጨረሻም በመካተቷ ተወሰነና ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀመጡ።
ለሦስት የተሠራው ካሴትም ወጣና ከአድማጭ ጆሮ ደረሰ። በጊዜው ተወዶ በበርካቶችም ዘንድ ተደመጠ። እንደብዙዎች እምነትም የዚህ ካሴት ምሰሶ ማናልሞሽ ነበረች። ምክንያቱም ለካሴቱ ተደማጭነት ምክንያት ከሆኑ ሙዚቃዎች መካከል የእርሷ “አሳ በለው” ግንባር ቀደሙ ነበር። አሳው በለውና ማናልሞሽም በዝና አብረው መገማሸር ጀመሩ። በተለይ ከአንድ አጋጣሚ መልስ “በቴሌቪዥን ከተቀረጽኩ በኋላ…” ነበር ያለችው።
በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብላ፣ የዓባይ ዥረት ዥረት ሽቅብ እንደሚፈስ ነገር ድምጽዋ ከሆዷ መጥቶ መጥቶ ከጉሮሮዋ ሲደርስ ግንፍል! ቁርጥርጥ! እያለ ሲስረቀረቀ ብዙሃኑ እያየ አደመጣት። በዚህ ሙዚቃ ባለ ማሲንቆው ባለቤቷም በማሲንቆው አጅቧታል። ማናልሞሽ የ1990ዎቹ የባሕል ሙዚቃ ፈርጥ ሆና ብቅ አለች። ቅመም ሆና ሙዚቃን አጣፈጠች።
ማናልሞሽ የተወደደላት ነገር ድምጷ ብቻ አልነበረም። አንድ ሲከውኑት ደስ የሚያሰኝ እንቅስቃሴ ከእስክስታዋ ጋር ነበር። በሙዚቃው ውስጥ ከሚታየው የውዝዋዜ እሽክርክሪቷ ጋር ብቅ ጥልቅ ስትል የተመለከታት በእንቅስቃሴው ተማርኮ ልምዱ አደረገው። “አሳ በውሀ ውስጥ ይሽከረከራል። እኔም አሳ በለው እያልኩኝ ስሽከረከር እንደ አሳው ለመሆን ነበር።” ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ‹እንዲህ ነው አሳ በለው…” እያሉ እልፎች እየተከተሉ፣ አድናቂና ወዳጆቿ ሆኑ።
ለእርሷም የኑሮዋ የገነት በር ተከፈተ። መንገድ ላይ ስትሄድ እንኳን የተመለከታት “ይህቺ አሳ በለው አይደለች?” እያለ ሲጠያየቅና እያስቆመ አድናቆትና ፍቅሩን ሲገልጽላት እንደነበረም በማስታወስ ተናግራው ነበር። ይህን በመሰለ መንገድ ውስጥ አልፋ ከፍታ ላይ መድረሷን ባስታወሰችበት ቅጽበት ሁሉ የምትለው ምን ይሁን? “ገና በጠዋቱ የተጣፈ እንጀራዬ ጠራኝ” ይሄው ነው ቃሏ። ከጣና ሐይቅ ውስጥ ከተገኘው ጣፋጭ አሳ ጋር የሚበላ ጣፋጭ እንጀራ።
“ካላጡ ካልተቸገሩ፣ መኖር ማን ይጠላል ባገሩ” የምትለዋን ስንኝ እየደጋገሙ አብረው በስሜት ፍስስ የሚሉ…በምናብ ባሕር ተሻግረው እየመጡ፣ በምናብ ወንዙን ተሻግረው ወዲያ ማዶና ወዲህ ማዶ እየተመላለሱ ብዙዎች ዛሬም ያስታውሷታል። አሁን ግን ድምጿን እየሰማን በስሜት የምንናጥ፣ ከደስታ ጋር ፍንትው ብለን ሀሴት የምናደርግ ሁላችንም ነን። በእኛ አውዳመት፣ የእኛ ድምቀት እሷው ሆናለች።
ከ2001 ዓ.ም በኋላ የነበረው የማናልሞሽ ሕይወት ደህና አልነበረም። ድንገት ሰማዩ ግም እያለ በመብረቅ ብልጭታው ይደውላል። ቀስተደመና እያሸተረ በአንዳች አስፈሪ ምልክትን ያስጠነቅቃታል። በዓይኖቿ ጉም ያልፋል። ለካስ በከባድ የአንጀት ካንሰር ተይዛ ስቃይ ላይ ነበረች። ባደረገቻቸው ብዙ ሕክምናዎች ካንሰሩን ለመግታት ግን አልተቻለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ከቀን ወደ ቀን እየከፋባት መጣ።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ በነበረችበት ወቅት ግን በሁሉም አቅጣጫ አቅሟ የተሟጠጠ መሰለ። ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ መታከም ቢኖርባትም፤ ለሕክምናው የሚሆናትን ገንዘብ ግን አጣች። በስተመጨረሻ አማራጭ ስታጣ በሙዚቃ ሲስረቀረቅ በነበረው ድምጽዋ በአሳዛኝ የይድረሱልኝ ቅላጼ ተውጦ “የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ያገሬ ልጆች…” ስትል ተማጸነች። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሆስፒታሉ ብቅ ያለው ቴዲ አፍሮ ነበር። ከእርሱ በኋላ ብዙ አርቲስቶችና ባለሀብቶች ተከታትለው ወደ ሆስፒታሉ አመሩ። እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ጨምሮ ብዙዎች የተቻላቸውን ያህል እጅ ቢዘረጉላትም፤ ለሕክምናው የሚያስፈልጋትን የገንዘብ መጠን ማግኘት ግን አልቻለችም። ከዚህ በኋላ ነበር፤ ባለሀብቱ ሼህ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲን የደረሱት። እርሳቸውም እኔ አሳክማታለሁ አሉና ማናልሞሽ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንድትሄደ ተደረገ።
በስቃይ፣ በመከራና በችግር ውስጥ ተኮራምታ፣ ገና ብዙ ሕልም እንዳላት ስታስብ ከዓይኖቿ እንባ እየቀደማት፣ አሁን ግን አንዳች የተስፋ ብርሃን የተመለከተች መስሏት ፈገግ ለማለት ሞክራ ፈገግታን የማይጠግቡ የነበሩ ጥርሶቿ መገለጥ አቃታቸው። ቤተሰቦቿም የሙዚቃ አፍቃሪውም ‹ማናልሞሽ ድና ትመጣለች…አዎን በድጋሚ እናደምጣታለን› ብሎ ተስፋ አደረገ። ግን…ብዙ ነገሮች የተገላቢጦሽ ሆኑ። ወርቃማው የብርሃን ጸዳል በደመና ተጋረደ።
እንደ ፀሐይ የሚያበራው ፊቷ ጨለመ። ብርቅርቅ ፈገግታዋ ደበዘዘ። ሰማይ የጉም ጢሱን እየለቀቀ በኩርፊያ አበጠ። ምድርም ዓይኖቿን ደፍታ በሕመም መማቀቅ ጀመረች። ሕይወት ተመሳቀለች። በችንካር ተወጋች። አሜኬላው ጉንጉን የሞት አክሊል ከአናቷ ላይ አረፈ። ጥበብ “ላማ ሰበቅተኒ! …ኤሎሄ! ኤሌሄ!” ስትል ጮኸች። ማናልሞሽ ልክ ደቡብ አፍሪካ ስትደርስ አረፈች። እስትንፋሷ ጭልምልም አለ። ኅዳር 12 ቀን 2002 ዓ.ም ሁሉም ነገር ጸጥ! ረጭ! …በቃ? እኮ ያቺ ጠይም አሳ መሳይ፣ ፍልቅልቅ ውብ ጽጌረዳ? …ይሄው ነው።
ግን…ትንሳኤ አለ። ጠቢባን ለጊዜው የሞቱ ይመስላሉ እንጂ አይሞቱም። ጥበብ አላቸው። ጥበብ ደግሞ ትንሳኤ አላት። ዳግም የሚወለዱ ዳግም አይሞቱም። የጥበብ ሥራዎቻቸው መቃብሩን ፈንቅለው፣ ድንጋዩን አንከባለው፣ ከቀፎው ውስጥ እንደወጣ የንብ መንጋ እየተመሙ ወደ አበባው ይዘምታሉ። አበባዎቹ ላይ ተቀምጠው ይቀስማሉ። አሁንም ማር፣ አሁንም ጣፋጩን ነገር ይሠራሉ። ይህ በታላቅ ሥራ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ተአምር ነው።
ከአራት ዓመታት በኋላ…ሦስቱ የማናልሞሽ ልጆች የነበሩበት ሁኔታ እጅግ ልብ የሚነካ ነበር። ገና በልጅነት ከእናት ፍቅር መነጠል ብቻውን አሳዛኝ የሕይወት ጉስቅልና ነው። ከሚያውቁትና ከሚኖሩበት የኑሮ ደረጃ ቁልቁል ወርደው እንደገና በሌላ አካላዊ ጉስቁልና ውስጥ ነበሩ። ትምህርታቸውን ለመከታተል እንኳን እስከማይችሉ ድረስ ከፋባቸው። መልካም ልቦች ግን አሁንም ሌላ ትንሳኤን ያመጣሉ። በተለይ በዚያን ዘመን እንዲህ ያሉ ምስኪኖችን እንባ በማስተጋባት የሚታወቀው ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ) ደረሰላቸው።
ለስድስት ወራት ያህል የመንግሥት ቤቶችን ደጅ ሲጠና ከቆየ በኋላ፤ የማናልሞሽ ልጆች የመኖሪያ ቤት አገኙ። ከሌላ ታሪክ ጋር የኑሮ ትንሳኤ ሆነ። ሴት ልጇ ሚስጥረም “ጎጆ” በተሰኘው ተከታታይ ሲትኮም ድራማ ትወናን ጀምራ፣ በሌላ ዓይነት ጥበብ እንዲሁም የእናቷን “ድማም ሰው” የሚለውን ነጠላ ዜማ በክሊፕ በመሥራት የእናቷን ጉዞ ጀመረች።
“ጤና ለሰጠው ሰው
ዕድሜውን ላደለው
አውዳመት ደስታ ነው
አውዳመት ጸጋ ነው።
እሰይ! መጣልን /አውዳመት
በዓላችን/ አውዳመት
ለዚህ ያበቃን/ አውዳመት
አምላክ ይመስገን…”
አሁን አውዳመት ብቻ። ደስ የሚያሰኝ የሕይወትና የጥበብ ትንሳኤ። “ባለ ፈረሰኛ ባለ ፈረሰኛ…” ስንት ገባ ዶሮ? እያሉ መደሰት ብቻ። ዳግም ሁሉም መልካም ይሆናል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም