በታሪክ በሀገራችን ባለፈው ሳምንት ከተከሰቱት ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ለዛሬ የደርግ ዘመነ መንግስት ማብቂያና ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ በትረ ስልጣኑን የተቆናጠጠበትን ግንቦት 20ን ይዘን ቀርበናል።ኢህአዴግ በሰሜን ኢትዮጵያ ከመንግስት ሰራዊት / እሱ የደርግ ሰራዊት ሲል ነው የኖረው/ ጋር ሲያደርግ የቆየውን የትጥቅ ትግል አዲስ አበባ በመቆጣጠር የመንግስት ስልጣን የተቆናጠጠው ግንቦት 20 ቀን በ1983 አ.ም ነበር።
የደርግ ውድቀት መባቻ
ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት ያስተዳደረው ወታደራዊ መንግሥት «ደርግ» አማጺ ቡድን እያለ በሚጠራው ኃይል ከሥልጣን የተወገደው ከ31 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነበር:: ከ1966ቱ አብዮት አንስቶ ኢትዮጵያን ለ17 አመታት ሲመሩ የቆዩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በመጨረሻ ማጠፊያው እያጠራቸው መጣ:: አማጺ እያሉ የሚጠሯቸው ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ እየተቃረቡ መጡ:: ከውስጥም ጫና በረከተባቸው::
አንድ የሃይማኖት አባት በመጨረሻው ሸንጎ ኮሎኔሉን እንዲህ ብለዋቸው ነበር:: “…50 ሚሊዮን ህዝብ በጦርነት ባህር ማግደው፣ ቆስቁሰው፣ በእርስዎ ኃላፊነት 18 ዓመት ሙሉ መርተው ሳያደራድሩ፣ ሳያረጋጉ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ለእሳት ዳርገው፣ በአሁኑ ሰዓት ከመሞት በስተቀር፣ የቴዎድሮስን ጽዋ ከመጠጣት በስተቀር ሌላ እድል የለዎትም:: እንደ ሌሎች መሪዎች ኢሮፕ ይፈረጥጣሉ ብዬ እምነት የለኝም:: እግዚአብሄር ምስክሬ ነው:: ይህን ህዝብ አጋልጠው ይሄዳሉ አልልም:: መንጌ፤ ከሷ ወንበር ላይ እንደቋንጣ ደርቀው እንደሚቀሩ አምንብዎታለሁ:: ይህንን ባያደርጉ ግን ታሪክ ይፋረድዎታል::”
ሌፍተናንት ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደሚተርኩት ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በመኖሪያ ቤታቸው ለከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው የእራት ግብዣ አደረጉ:: ግብዣው ሲጠናቀቅ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ሁሉንም ተጋባዥ እንግዶች በራፋቸው ላይ በመሆን አንድ በአንድ እየጨበጡ ሸኙዋቸው። ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም ፕሬዚዳንት መንግስቱ መሉውን ቀን የተለያዩ ወረቀቶችን ቢሯቸው ውስጥ ሲቀዱ ዋሉ:: አመሻሽ ላይ ወደ ዘመቻ መምሪያ በማምራት ለከፍተኛ የጦር አዛዦቻቸው ንግግር አደረጉ።
ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን ወደ ኬንያ ለመሄድ አውሮፕላን እንዲዘጋጀላቸው አዘዙ:: የጉዞ ምክንያታ ቸውም ወደ ብላቴ ማሰልጠኛ በመጓዝ ወታደራዊ ስልጠና በማድረግ ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እጎበኛለሁ የሚል ነበር:: ስለዚህ አውሮፕላኗ ከብላቴ ወደ አስመራ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የሚበቃ ነዳጅ እንድትሞላ አዘዙ:: ብላቴም ሳያርፉ ወደ ኬንያ ኮበለሉ፤ ከዚያም ወደዚምባብዌ አቀኑ።
ግንቦት 13 ቀን 1983 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ስርጭት “ጦርነቱ ያስከተለውን ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል:: ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም:: ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆም፣ ስምምነት እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል:: ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን በመውረድ ሀገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌፍተናንት ጀኔራል ተስፋዬ ወልደ ኪዳን ተክተው ይሰራሉ::” የሚል መግለጫ አስደመጠ::
በሌላ በኩል ግንቦት 19 ቀን 1983 በእንግሊዟ ዋና ከተማ ሎንዶን የኢሕዲሪ መንግሥት ተወካዮች ከኢሕአዴግ ፣ ከሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ)፣ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በአሜሪካ መንግሥት አማካይነት ድርድር ተቀምጠው ነበር:: አደራዳሪው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ሄርማን ኮኸን ናቸው:: ከኢሕዲሪ መንግሥት ተወካዮች ጋር ለመደራደር ሎንዶን የተገኙት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሌንጮ ለታና የህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ህግሓኤ) ዋና ፀሐፊ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ነበሩ::
የሎንዶኑ ኮንፈረስ ለግማሽ ቀን ብቻ ነው የተካሄደው:: አደራዳሪው ሚስተር ሄርማን ኮኸን ተደራዳሪዎቹን በተናጠል ካነጋገሩ በኋላ በማግስቱ ረፋድ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ኮንፈረንሱ መሰረዙን አስታወቁ:: ለኮንፈረንሱ መበተን ምክንያት የሆኑት በመጨረሻው ሰዓት የኢሕዲሪ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሰየሙት ሌፍተናንት ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ናቸው::
ጄኔራል ተስፋዬ ለሚመሩት መንግሥት ባለስልጣናት ሳያስታውቁ ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 1983 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ለአሜሪካ ኤምባሲ “የጦር ሰራዊቱ ከቁጥጥሬ ውጪ ሆኗል፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም ዘረፋ ተጀምሯል” የሚል መረጃ ሰጡ:: ለራሳቸውም የኢጣሊያ ኤምባሲ ገብተው ጥገኝነት ጠየቁ :: ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይሉ ይመኑ፣ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሻምበል ብርሃኑ ባይህ እና የኢሕዲሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሌፍትናንት ጄኔራል ሐዲስ ተድላ አብረዋቸው ወደ ኤምባሲው ገቡ::
የአሜሪካ ኤምባሲም ከጄኔራል ተስፋዬ የሰማውን መረጃ ሎንዶን ለሚገኙት ሚስተር ሄርማን ኮኸን አስተላለፈ:: በዚህም መሰረት ሚስተር ኮኸን ምሽት ላይ በኮንፈረንሱ አካሄድ ላይ ለውጥ መደረጉን አስታወቁ:: አዲስ አበባ እንደ ሞቃዲሾና እንደ ሞኖሮቪያ እንዳትሆን የኢህአዴግ ጦር ወደ ከተማዋ መግባት እንዳለበትም ተናገሩ:: የኢህአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ጦራቸው አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር ትዕዛዝ ሰጡ:: በመሆኑም የኢህአዴግ ጦር ከሌሊቱ 8፡00 ሰአት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀመረ::
ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት “ላውንቸር” በሚል ቅፅል ስም የሚጠራ ወጣት የኢህአዴግ ታጋይ ከኢትዮጵያ ድምጽ ብሄራዊ አገልግሎት እንዲህ ሲል ተሰማ:: “የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባ ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል ፤ ግንቦት 20 / 1983 ዓመተ ምህረት”:: የኢህአዴግ ጦር የኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያን መቆጣጠሩን ያወጀው የዛን ጊዜው ወጣት ታጋይ የአሁኑ ሌተና ኮሎኔል ብርኃነ ገብረ ጻድቅ ናቸው። ኢህአዴግ አዲስ አበባን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ተቆጣጠረ:: ሻዕቢያ ቀደም ብሎ ግንቦት 16 ቀን 1983 ዓ.ም አስመራን ተቆጣጥሮ ነበር::
ከደርግ ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ለአንድ ወር በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግሥትነት አገሪቱን ከመራ በኋላ ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለአራት ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥትን በመመስረት መርቷል:: የኢፌዲሪ ህገመንግስት ተረቅቆ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በህዳር 29 ቀን 1987 አመት ጸደቀ።በዚሁ አመትም የመጀመሪያው ምርጫ ተካሄደ፡፡
ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ገዢ ፓርቲ በመሆን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን እስከ መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ሲመራ ቆይቷል:: ፓርቲው ቀስ በቀስ ተቃውሞ እያጋጠመው መጣ። በ1993 ህወሓት ሁለት ተከፈለ።የእነ መለስ ዜናዊ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ተቀናቃኝ የነበሩት ደግሞ ከፓርቲው ለቀቁ።
ፓርቲው ራሱን በገመገመ ቁጥር ችግሮች እንዳሉበት ይገልጽ ነበር።በስብሰናል ይልም ነበር። ተሃድሶ ሲያደርግ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይህን ተሀድሶ ጥልቅ ተሀድሶ እያለ በማካሄድ በህዝብ ዘንድ ይደርስበት የነበረውን ቁጣ ለማብረድ ሲሞክር ቆየ።የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን የለቀቁትም በዚሁ ወቅት ነበር።ይህ ጉዳይ ሄዶ ሄዶ የ1910ሩን ሀገራዊ ለውጥ ወለደ።የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት / ኦህዴድ/ ሊቀመንበር በመሆን የተሰየሙት ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።ኢህአዴግም ዶክተር አብይ አህመድን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲሾሙ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ምክር ቤቱም ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾማቸው። በፓርላማው ፊትም ቃለ መሀላ ፈጽመው ንግግር በማድረግ በይፋ ስራቸውን ጀመሩ። በአራት የብሄር ድርጅቶች ፓርቲዎች የተመሰረተው ኢህአዴግም ሁሉም ብሄረሰቦች የተካተቱበት ፓርቲ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቶ ኢህአዴግ በብልጽግና ፓርቲ ተተካ።ኢህአዴግም ከሰመ::
ምንጭ አዲስ ዘመን፦ ክምችት ክፍል ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ወቅት/ ታላቁ ቤተመንግሥት አካባቢ፤
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2013