እንደ ማህበረሰብ እኛ ዘንድ ያለ፣ ነገር ግን ከእኛ ብዙ ሊርቅ የሚገባው በጎ ያልሆነ ልማዳችንን አንስተን ያንን ለመግራት የሚያስችል ጥቆማ የምንሰጥበት ገፃችን ላይ ዛሬም አንድ ሀሳብ ለማንሳት ወደድን።በመፍትሄ አመላካች መርፌያችን የምንወጋው በሀሳባችን የምንተቸው የዛሬ ጉዳያችን ሁለት ጥላዎችን ተጠልለው በአስጠላዮቹ ስም የሚነግዱ ከጥላዎቹ አላማ ውጪ የራሳቸውን ግብ የሚፈፅሙ አካላትን እናነሳለን።በብሄርና በሃይማኖት ስር የተጠለሉ ነገር ግን የሃይማኖቱ ስርአትም ሆነ የብሄሩ ባህል ከሚያዘው በጎ ተግባር ውጪ እኩይ ተግባር ፈፃሚዎችን እንመለከታለን።እነዚህ በሁለቱ ጥላዎች ስር ያደሩ አስመሳይ ተጠላዮችን በሽታ ለይተን መርፌ እንወጋለን፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያችን ከውስጥና ከውጪ ኢትዮጵያ ሆና እንዳትቆም በሚፈልጉ አካላት ሴራ ተወጥራለች።ዛሬ አገራችን ከምንጊዜውም በላይ የዜጎችዋን፣ አብሮነት የልጆችዋን ተገንነት የምትፈልግበት ወቅት ላይ ነች።ታዲያ የቤታችን ጉዳይ እናሳድርና ቤታችን ሊንድ አድፍጦ በመጣው የውጪ ጠላት ላይ ትኩረት እናድርግ ሲባል አድሮ በሚፈታ ውስጣዊ ጉዳይ ተተብትቦ እሱንም አገሩንም ሊነጥቅ ከመጣው ጠላት ጋር ላብር ያለው የእናት ጡት ነካሽ ጉዳይ ይገርማል፡፡
የጓዳችን ችግር በኛው የሚፈታ ውሎ አድሮ የሚጠራ ሆኖ ሳለ ስለምን ጓዳችን ሊበረብር ለመጣ ጠላት ማንነታችንን አንትቦ ያለንን ቀምቶ ለሚሄድ ባዕድ ዓላማ የአገር ልጅ በአገሩ ላይ ሊሰራ ማለቴ ሊያሴር ይቻለዋል።ዛሬ ላይ ይህቺን ታላቅ አገር አገር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እልህ አስጨራሽ ትግል የሚያደርጉ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያንን ተግባር የሚያንኳስሱ ትናንሽ ኢትዮጵያዊያን በርክተዋል።
በዚህች ታላቅ አገር የሚኖሩ ትንንሽ ሀሳብ አራማጆች የኔ በሚሉዋቸው ብሄሮቻቸው ስር ተጠግተው አገር የማያሻግር ሀሳብ ይወረውራሉ።ይህንን ታላቅ ህዝብ አስተዳድርበታለሁ የሚለው ሀሳብ ሲርቀው በብሄሩ ጥላ ስር ተደብቆ ወገኔ ሆይ በእነ እንትና ተበድለሀል ተነስ እያለ ለአገር የማይበጅ ተግባር ሲፈፅም ይታያል።በዚህ ጥላ የመሸገው ተጠላይ እርቃኑን ህዝብ ፊት ቢቀርብ ነገ ህዝቡ ሊመራበት ያቀደው አገሪቱን ሊያስተዳድርበት ያለመው እቅዱን ብትጠይቁት ምላሽ ላታገኙ ትችላላችሁ፡፡
ሁለተኛው የጥላው ስር አስመሳይ መሻጊ ደግሞ ወዲህ ነው።የእምነት ተቋምን ይደገፋል፤ አማኞችን እናንተ ብሩህ ናችሁ እምነታችሁም ከሁሉ የላቀ ብሎ ይቀርብና ለራሱ ዓላማና ግብ በማስመሰል የተንጠላጠለበትን መሰላል ይጠቀማል።ምዕመናኑ በመንጋ እንዲፈርዱ አስልቶ መልካም ተግባር ላይ እንዳይዘወትር በአሰራሩ ላይ ከእምነትና አምልኮ ውጪ የራሱን ዓላማ በስውር ጭኖ ሌላውን የሚሰድብ የሚያንቋሽሽና አስተምሮትን በተሳሳተ መልኩ የሚያራምድ የጥላው ስር ሴረኛ ነው።
ሀገር ከሁል ጊዜ በተለየ መልኩ ፀንታ መቆም በሚገባት በዚህ ጊዜ ከብሄርና ሃይማኖት ጥላ ስር ያሉ ተጠላዮች ጉዳያቸውን ረገብ አድርገው ሃይማኖታቸውና ብሄራቸውን ሊዳፈር የመጣውን የሩቁን ጠላት ስለመከላከል አይጨንቃቸውም።በዚህ ወሳኝ ጊዜ እንኳን የሚፈልጉትን ከማድረግ አልተቆጠቡም።ህዝብን ባረባ ነገር ከመከፋፈል ምዕመናን በትክክል ወደ አምላካቸው ተጠግተው ስለ አገራቸው ሰላም እንዲፀልዩ(ዱዓ) እንዲያደርጉ ጊዜ አልሰጡም፡፡
ችግር ቢኖርብን እንኳን ነገ ተነጋግረን የምንፈታው ሆኖ ሳለ በግርግሩ ይበልጥ ላደናግር ያሉ ይመስላሉ።አገር ከሁሉ ከፍ የምትል ዘመንን የምትሻገር መሆንዋን አልተረዱም።አገራቸው ከሌለች ነፃነትዋ ከተደፈረ ማንነትዋ ከተናደ የተጠለሉበት ብሄርም ይሁን ሃይማኖት ነፃነት የሌላቸው መሆኑን አልተረዱ ይሆን።እነዚህ ተጠላዮች ወይም አስመሳዮች ሴራ አስጠላዮቹም ወይም የተጠለሉበት ሃይማኖትም ሆነ የኔ ብለው ለዓላማቸው መሳካት የተለጠፉባቸው ብሄራቸው በወጉ ስለማይረዱ ፈፅሞ አይቃረንዋቸውም።እምነቱን ተጠግተው የእኛ እምነት በሌሎች እየተበደለ ነው ብለው አማኙን ያሳምናሉ፤ ብሄሩን የተጠጋው ደግሞ እኛ የምንበደለው እገሌ በመሆናችን ነው ብለው ያሳምፃሉ፡፡
ወገን አንዴ አይናችን ገልጠን ብናያቸው ጥላውን ገፈን ማንነታቸውን ብንመረምረው እነዚህን የጥላው ስር ሴረኞች ባዶነታቸውን በተረዳን ነበር።ፈፅሞ ለብሄራቸው መብት የማይሰሩ መሆናቸው ለእምነታቸው ያላደሩ አስመሳይ እንደሆኑ ፍንትው ብሎ በታየንም ነበር።ይሄ ግን ጊዜ ይጠይቃል።በተለይ በዚህ አገር በጠላት ተከባ ፈተናዎችዋ በዝተው ሁሉም በስሜት በሚፈርድበት ጊዜ እውነት የያዙ እነሱ ብቻ ይመስላሉ።የተደበቁበት ታላቅ እምነት ወይም ብሄር ለእነሱ መከታ ለስውር ሀሳባቸው መደበቂያ ነውና፡፡
አማኝ ለእምነቱ ያደረ መልካም ነገርን አብዝቶ የሚተገብር ከወገኖቹ ጋር በፍቅር ያለውን የሚጋራ ሆኖ ሳለ ስለምን የሌሎችን እምነት ያንቋሽሻል? ለምንስ መልካም ነገር ከመስበክ ይልቅ የሌላውን እምነት ተከታይ እየሰደበና በሌላው ላይ እየተሳለቀ ከአምላኩ ትዕዛዝ ተቃርኖ ይቆማል? አዎ አማኝ ይህንን በፍፁም አያደርግም።
እምነት በበጎ የሚያዝ ከመጥፎ ነገር የሚከለክል ሆኖ ሳለ ሌሎችን መጥፎ ሁኑ ሊል አይችልም።አማኝ ነኝ ባዩ ይህን ካለ ይሄኔ አማኙ መመርመር ይገባዋል።አማኝ ነኝ ብሎ በእምነት ጥላ የተሸሸገ እንጂ በአምላካዊ በጎነት የታነፀ የእምነቱን ቀኖና የሚያከብር ለሰው ልጆች በጎ የሆነ አስተሳሰብ የለውም።በሀይማኖት ጥላ ስር የራሱን ድብቅ አላማ ማስፈፀም ነው።
ይህን አማኞች ሊያርቁና እውነቱን በመገንዘብ በጎ የሆነው አስተምሯቸውን የሚበርዝን መለየት ለእነሱ ተቆርቋሪ መሰሉ ተቋማቸውን የሚያቆረቁዘውን በበጎ የሚያዘው እምነታቸው የሚሸረሽር መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል።አዎን የሁሉም እምነቶች መሰረት በጎነት የአማኞች ተግባርም መልካምነት ለሰው ልጆች ምቹ መሆንን ማስተማር ነው።ለአገር አብሮ መቆም ለወገን ችግር መድረስ ተደጋግፎም ክፉን ጊዜ መሻገር እንደሚገባ መስበክ ነው ዋንኛ ግቡ።ስለዚህም ነው በዚህ በጎ ጥላ ስር ያለውን መሰሪ መለየት የሚገባው፡፡
ልክ እንደ እምነቱ ሁሉ ሀሳብ ስለራቃቸው ብቻ በብሄሩጥላ ስር ያደሩ ለብሄሬ ተቆርቋሪ ነኝ ለህብረተሰቤ ተሟጋች ነኝ ብለው ራሳቸውን እላይ የሰቀሉ ተቆርቋሪ መሳይ ነገር ግን የተጠለሉበትን ብሄረሰብ የማይመስሉ ለእርሱም እውነተኛ አርነት የማይሰሩ መሆናቸው ግልፅ ነው።
ስለማህበረሰቡ የሚጨነቅ ስለወገኑ የሚቆረቆር ቂምና ጥላቻን በሌላው ላይ አይሰብክም።ማህበረሰቡ ባህልና ወጉ በሌላው እንዲከበር የሌላን ማህበረሰብ ባህልና ወግ ማክበር ወሳኝ መሆኑን በተረዱ ነበር።ለዚህ ግን እነዚህ ተጠላዮች ወከልንህ አልያም እኔ ለአንተ ቆምንልህ ይበሉት እንጂ ተግባርና አካሄዳቸው ሁሉ ማህበረሰቡን ለእንግልት የሚዳርጉ የአብሮነት እሴቱን የሚሸረሽሩ የአገር ህልውናም የሚያናጉ ናቸው፡፡
እነዚህ የሁለቱ ጥላ ስር ሴረኞች ዓላማ ግልፅ ነው።የራሳቸውን እኩይ ዓላማ በተጠለሉበት ማንነት ውስጥ በመሰወር ማስፈፀም ነው።እንደ ህዝብ አንድ ሆነን ቆመን አንድነታችንን ሊንድ እኛን መስሎ የሚቀርበንን በአገራችን ህልውና ላይ አደጋ ሊጥል የሚያሴርን መዋጋት ደግሞ እኛ እንደ ዜጋ የሁላችንም ኃላፊነት መሆን ይገባዋል።ወገን በኛ ስር ተጠልሎ እኛነታችን ሊያስነጥቀን ከባዕድ ጋር የተወዳጀ ጠላታችንን ነቅተን እንጠብቅ።አበቃሁ፤ቸር ይግጠመን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2013