ሳልፍና ሳገድም በርቀት በአድናቆት እመለከተው ነበር። ሰሞኑን ግን ከእግር እስከራሱ ለመጎብኘት ዕድሉን አገኘሁ። በዙሪያው፣ በውስጡ ቀደም ሲል የነበረውን ይዞታ በአይነህሊናዬ አስታወስኩ። ወቅቱ በሚጠይቀው የግንባታ ግብአት በጭቃና በእንጨት የተሰሩ፣ ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ የተጎሳቆሉ፣ ለአካባቢውም የማይመጥኑ ብዙ መንደሮች የሚገኙበት ሥፍራ ነበር። መንደሮቹ ለመልሶ ማልማት ከተነሱ በኋላም በአጥር ተከልሎ ንጽህናው ከመጓደሉም በላይ ፀያፍ የሆኑ ድርጊቶችም ይከናወኑበት እንደነበር የቅርብጊዜ ትውስታ ነው። ይህን ገጽታ የቀየረ፣ ሰዎች ሀሴት የሚያደርጉበት፣ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የባህል እሴቶቻቸውን የሚያሳዩበት፣ ትንሿ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ሆኖ ለአገልግሎት መብቃቱ ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ የቀድሞውንም ያሁኑንም በማየት ምስክር ለመሆን ችያለሁ።
ሳምንቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ሳምንት በመሆኑ የወዳጅነት ፓርክ በሰው ተሞልቶ ደምቆ ነበር የሰነበተው። በጽሁፍ መግለጫና በአስጎብኝዎች የታገዘ በመሆኑም በውስጡ ቆይታ ለማድረግ ምቹ ነበር። በዚህ አረንጓዴ በለበሰ ሥፍራ ውስጥ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየአካባቢያቸውን ባህላዊ ምግብ፣ አልባሳት፣ የመገልገያ ቁሳቁሶች፣ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ መጫወቻ፣ ዘፈኖቻቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎቻቸውን በአጠቃላይ እሴቶቻቸውን ለጎብኝው ሲያስተዋውቁ፣ ሸጠውም በገቢ ሲጠቀሙ ነበር ሳምንቱን ያሳለፉት።
አስሩ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሳምንት ፌስቲቫል ላይ አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት ለማወቅ፣ ከየአቅጣጫው የሚመጣውም ጎብኝ በአንድ ቦታ ሁሉንም ለማየትና ለማወቅ ዕድል የሰጠ ነበር።ሳምንቱ ከመተዋወቅ፣ገቢ ከማግኘት፣ ሀገራዊ ፋይዳውን ከፍ ያደረገ ከመሆኑ በተጨማሪ ፌስቲቫሉ ሰብአዊ ዓላማም ነበረው። ከኢትዮጵያ ሳምንት የሚገኘው ገቢ በተለያየ ምክንያት ከቀዬያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ በማዋል ኢትዮጵያዊ አብሮነት የሚገለጽበት ስለነበር አብዛኛው ጎብኝ በክፍያ ገብቶ በመጎብኘት ወገናዊነቱን ያሳየበት መሆኑ የኢትዮጵያ ሳምንት ፋይዳን የጎላ አድርጎታል።
በዚህ ዘርፈብዙ ዓላማዎችን በያዘው ፌስቲቫል ከብዙ በጥቂቱ የቃኘሁትን እንዲህ አቅርቤላችኋለሁ። በቅደም ተከል ከጎበኘኋቸው መካከል ኦሮሞ ባህል ማዕከል አንዱ ነው። በማዕከሉ መግቢያ ላይ በቀራጭ ባለሙያ የአካባቢውን ባህል በሚገልጽ አለባበስ የሴትና ወንድ ምስል ያገኛሉ። የገዳ አማካሪ የሆኑት አባጨፌ ጫላ ሶሪ ስለምስሉ ተምሳሌት እንደነገሩኝ በአካባቢው ‹‹አባ ገዳ እና ሀደ ገዳ›› ተብለው ይጠራሉ። በምስሉ ላይ አባገዳ በእጃቸው አለንጋና ዱላ ይዘዋል። የአባገዳ የሥልጣን ምልክት የሆነውን ከለቻ የተባለውን በራሳቸው ላይ አስረዋል። ከአልባሳት ጀምሮ ያሉት ነገሮች አባገዳ መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው። ፀበኞችን ለመዳኘት የሚውለውን ሲቄ (ዱላ)፣ የወተት መያዣ ኦኮሌ ይዘው ከአባገዳው ጎን የቆሙት ሀደ ገዳም የአባገዳ ሚስት መሆናቸውን የሚያሳይ መገለጫ አድርገዋል።ምስሉን እንዳለፍኩም ለተለያየ አገልግሎት የሚውል በአለላና በስንደዶ ስፌት የሚሰፉ፣በባህላዊ ወፍጮ (መጅ) እህል የሚፈጩ፣አረቄ የሚያወጡ ልጃገረዶች የአካባቢያቸውን ገጽታ በተግባር ለጎብኝዎች እያሳዩ ነበር። ወጣት ልጃገረዶቹ ሲያሳዩት የነበረው በቴክኖሎጂ ሳይታገዝ ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን መገልገያ ሲሆን፣ ቁሶቹ በከተማ በሌላ እየተተካ ቢሆንም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል።ከፊሎቹ ወጣቶች ደግሞ ለጎብኝዎች ባህላዊ የኦሮሞ ዘፍን ለማሳየት በልምምድ ላይ ነበሩ።
በሸክላ፣ በቅልና በእንጨት ተሰርተው የተለያየ ቀለም ባላቸው ጨሌዎች የተዋቡ በቆዳ የተለበጡ ቁሳቁሶች በመደርደሪያ ላይ ተደርድረዋል። በውስጣቸውም፣ ጭኮ፣ ቡነቀላ የተባሉና ሌሎችም ባህላዊ ምግቦች በውስጣቸው በማዕከሉ ውስጥ ይገኛል።ጎብኝ እንግዶችም እንዲቀምሱ ይደረጋል። ጎብኝዎችም ባህላዊ ምግቡን እያጣጣሙ በቁሳቁሶቹም ውበት እየተደመሙ ነበር ሲጎበኙ ያየሁት። ማንኛውም ሰው ከሚጠቀመው ጀምሮ እስከ ለሀገር ጀብድ የፈጸሙና በአካባቢው የተከበሩ ይገለገሉባቸው የነበሩ አልባሳት፣ ጦርና ጋሻ የሙዚቃ መሳሪያዎችና ሌሎችም ብዛት ያላቸው የአካባቢው መገለጫዎች በማዕከሉ ውስጥ ቀርበዋል።
በፎቶግራፍ ተደግፎ በማዕከሉ ከቀረበው አንዱ ከረዩዎች እርስበርሳቸው ፀጉራቸውን ሲያሳምሩ የሚያሳየው ነበር። ከረዩዎች ፀጉራቸውን በቅቤ ጠቅልለው አፍሮ አበጥረው በማስዋብ ይታወቃሉ። አለባበሳቸውም ከታች ግልድም፣ ከላይ ደግሞ እንደ እንደጋቢ ጣል አድርገው፣ ጌሌ የተባለውን ስለት በቆዳ ውስጥ አድርገው በወገባቸው ላይ ይታጠቃሉ። በተለይም የፀጉር አበጣጠራቸው እጅግ ማራኪ ነው። ለማሳመር የሚጠቀሙበት መሳሪያም የአካባቢ በመሆኑ ባህልን የጠበቀ ነው። በሥፍራው ያገኘኋቸው ከረዩ ውስጥ ደበላ በተባለ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወጣት ቦሩ ፈንታሌና ቦሩ ሀዋስ ስለአካባቢያቸው ባህል‹‹ከረዩ በአለባበሱና በፀጉር አበጣጠሩ ይለያል። ባህሉን የማያውቁትም አይተው አድናቆታቸውን ገልጸውልናል። ባህላዊ ምግቡም ገንፎ በቅቤ ነው። ቡናም በወተት ነው የሚጠጣው።ሰፊ ባህልና ወግ አለን›› በማለት አጫውተውኛል። የአካባቢውን ባህልና ወግ ለሌሎች ለማሳወቅ በወዳጅነት ፓርክ በመገኘታቸውና የሌላውንም ለማወቅ በመቻላቸው ተደስተዋል። በቆይታቸውም አዲስ አበባ ከተማን በመጠኑም ቢሆን ለማየት ችለዋል።ከተሜነት ብዙ ስልጣኔ የሚታይበት እንደሆነም ተገንዝበዋል።
ከከረዩዎች ጋር በመሆን በበጎ ፈቃድ ሲያስጎበኝ ያገኘሁት ወጣት ጋዲሳ ዳባ ከአምቦ ዩኒቨርስቲ በ2012ዓም የተመረቀ ሲሆን፣ በበጎ ፈቃድ ለመሥራት የመረጠው ሥራ እስከሚያገኝ በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ፣ የሥራም ተሞክሮ ለማግኘት ከሁሉም በላይ ደግሞ በተማረው ሙያ በበጎ ፈቃድ ገና አገልግሎት መስጠት በጀመረው ፓርክ ውስጥ ስለአካባቢው የባህል እሴቶች ለማስተዋወቅ መብቃቱ የሌሎችንም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል በሥፍራው ማየት መቻሉ አስደስቶታል።
የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝብች ክልል ወደሚገኝበት የባህል ማዕከል አመራሁ። እዚህም በተመሳሳይ የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ ጨምሮ የባህል አልባሳቱ፣ አመጋገቡና ሌሎችም በፎቶግራፍና በተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር ተደግፎ ነው የቀረበው። ደቡብ ክልል በሽመናም በስፋት የሚታወቅ አካባቢ በመሆኑ ለተጠቃሚው እስኪደርስ ድረስ ያለውን የእደጥበብ ውጤት የሚያሳይ ከነሽመና ቁሳቁሱ ነበር የቀረበው። በማዕከሉ ሲያስጎበኝ ያገኘኋቸው በክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳለ ወልዳማኑኤል በተጨማሪ እንደገለጹልኝ፤ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ባህላዊ እሴቶችን፣ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የመጠቀሚያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በዋናነት አካባቢውን የሚገልጽ ቱባ ባህል የሚያሳይ ነገር ለማቅረብ ተሞክሯል።
በክልሉ ከሚገኙ ብሄረሰቦች አንዱ የሆነው የዳውሮ ባህላዊ መሳሪያ እጅግ የሚገርም ድምጽ የሚያወጣ ከከብት ቀንድና ከቀርከሃ የተሰራው ዲንካ የተባለው ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ቀልብን የሚስብ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ርዝመቱ ከሰው ቁመት በላይ ነው።በቀርከሃው አናት ላይ በሚገኘው የከብት ቀንድም ሆነ ቀርከሓው ላይ ለውበት ተብሎ የተጨመረ ነገር የለም። በራሱ ውብ ነው። የኮንታ ብሄረሰብ የሚጠቀምበት የሙዚቃ መሳሪያም በተመሳሳይ ቁመቱ ረጅም ነው። መሳሪያዎቹ በትንፋሽ ድምጽ የሚያወጡ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊጠቀመው የሚችል አለመሆኑን መረዳት ይቻላል። አያያዙም ቢሆን የራሱ ጥበብ ይኖረዋል። ድንቅ የተፈጥሮ ውበት ማለት እንዲህ ነው።በእንስራ በአፉ ላይ በጎማ ተወጥሮ ለከበሮ የሚያገለግለውና የስልጤ ብሄረሰብ የሚጠቀምበት ከበሮም በማዕከሉ ይገኛል።
የክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችም ከባህል የራቁ አይደሉም።በበርበሬ ምርት የሚታወቀው አላባ ተብሎ የሚጠራው የክልሉ አካባቢ ሴቶች ከሻሽ አስተሳሰራቸው ጀምሮ የለበሱት ቀሚስ ቀልብ ይስባል። በእርከን ሥራ የሚታወቀው የኮንሶ አካባቢም የተፈጥሮ ሥነምህዳር ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆን ድንቅ ሥራ መሆኑን፣ ከአምስት መቶ ሺህ በላይ የዝሆን መንጋ የሚገኝበት የጨበራ ጩርጩራ ፓርክም እንዲሁ መስህብ መሆኑን ከአስጎብኝው ለመረዳት ችያለሁ። በክልሉ ስድስት ብሄራዊ ፓርኮች መኖራቸውንም አስጎብኝው ገልጸውልኛል። ከቀንድና ከእንጨት የተሰሩ መጠጫዎችና ሌሎችም የባህል መጠቀሚያዎች ጥንካሬ ያላቸው ናቸው።እንዲህ ያሉ የአካባቢ ባህል የማስተዋወቅ አጋጣሚዎች ስላላቸው ፋይዳም አቶ እንዳለ እንደነገሩኝ አንዱ የሌላውን ለማወቅና አክብሮ ለመጠበቅ፣ የህዝብ ለህዝብ ተውውቅንና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ሁሉም በባህሉ ኮርቶ እሴቶቹን ለማሳደግና በእሴቶቹም ለመጠቀም እንዲተጋ ያስችለዋል።
ሌላው የጎበኘሁት የአማራ ክልል የአካባቢውን የሚወክል ባህላዊ የወግ ዕቃዎች፣ተፈጥሮአዊ መስህቦችንና የእደጥበብ ውጤቶችን ለጎብኝዎች ያቀረበበትን ማዕከል ነው።የአማራ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ባለሙያ አቶ ሙላት መኳንንት በማዕከሉ ውስጥ ከሚገኙት ባህላዊ መጠጦች መካከል ጠጅ፣ብርዝ፣ ከስንዴ እህል የሚዘጋጀውን ናምራ የሚባለውን የጎጃም አረቄን አንስተውልኛል። ባህላዊ የሆነው አረቄ ልክ እንደ ለስላሳ መጠጦች የተለያየ ጣዕም በሚሰጡ ግብአቶች እንደሚዘጋጁት ሁሉ እንደ ኮሶ፣ነ ጭሽንኩርት ባሉ የእህል ዘርና ዕፅዋቶች እየተዘጋጁ እንደሚቀርቡ አውቃለሁ። ናምራ የሚባለው ግን ለእኔ አዲስ ነው። ናምራ የሚል ስም የተሰጠውም አረቄው ከወጣ በኋላ ድፍርስ የሆነ ነገር ባለመታየቱና ንጹህ ሆኖ መታየቱ እንደሆነ አቶ ሙላት ነግረውኛል።
እንደ አቶ ሙላት ገለጻ፣በአካባቢው ወንዶች በባህላዊ ልብስ አጊጠው በእጃቸው ጭራ መያዝ፣ለምድ የሚባለው ከበግ ፀጉር ተዘጋጅቶ የሚቀርበው የካባ አልባስም እንዲሁ በአካባቢው የተለመደ ነው። ከበግ ፀጉር የሚመረተው አልባስ በክልሉ በደብረብርሃን አካባቢ ነው የሚታወቀው።
የአካባቢውን ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ ተጠቃሚ ለመሆንና ቱባ ባህል ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ እየተደረገ ስላለው ጥረትም አቶ ሙላት ላቀረብኩላቸው ጥያቄ እንዲህ ያሉ የማስተዋወቅ ተሞክሮዎች አዲስ አይደሉም። በተለያየ አጋጣሚ ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል።በጋራ ተባበሮ አንዱ የሌላውን በመጠቀምና በማሳደግ ላይ ከማተኮር የእኔ ይበልጣል የሚለው በመጉላቱ እንደሆነ ይገምታሉ። በዚህ የኢትዮጵያ ሳምንት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው ሀብት በአንድ ሥፍራ እንዲገኝ መደረጉ የአንድ አካባቢ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የውጭ ሀገር ዜጎችም ጭምር እየጎበኙ በመሆናቸው ተጠቃሚነትን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ዕድሎች ይፈጠራሉ። የገበያ ትስስር እንዲፈጠርም መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል።ጊዜው አጭር ባይሆንና በብዛት ማቅረብ ቢቻል ጥሩ ገቢ ሊገኝ ይቻል እንደነበር አቶ ሙላት ይገልጻሉ። ቱባ ባህሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ክልሉ በሚችለው ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሌላው የጎበኘሁት ለቤንሻንጉል ክልል የተዘጋጀውን ማዕከል ሲሆን፣ ትኩረቴን የሳበው የተለያየ የመግቢያ በሮች ያሉት የቤት ቅርጽ ነበር። በክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ ባለሙያና አስጎብኝ አቶ ሱሌይማን አብዱላሂ እንደገለጹልኝ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚገነባበት የሚገኘው የጉባ አካባቢ መሪ የነበሩት ደጃዝማች መሐመድ ባጃ ቤት ነው። ይሄ ቤት በዘመኑ የሥነህንፃ ውበቱ ማራኪ እንደነበር አስመስሎ ከቀረበው ለመረዳት ይቻላል። በወቅቱም በሸክላ ጡብ ነው የተገነባው። ይህ የቅርስቤት በመጎዳቱ ጥገና ያስፈልገዋል። ቤቱን ከጉዳት ለመታደግ የመንግሥትና የበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ ያስፈልገዋል። በጎጆ ቅርስ የተሰራው የሼህ ኦጀሌ የችሎት አዳራሽም በምስል ለዕይታ ቀርቧል።አዳራሹ ተጠግኖ መናፈሻና የተለያየ አገልግሎት እየሰጠ ቅርሱን መጠበቅ መቻሉን አቶ ሱሌይማን ነግረውኛል።
በክልሉ ማኦ፣ ኮሞ፣በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሺናሻ የተባሉ ነባር ብሄረሰቦች ይገኙባቸዋል። በክልሉ ትኩረትን ከሚስቡት አንዱ የቤት አሰራራቸው እና ዙባራ የተባለው ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወቻ ነው። የገጠሩ የቤት ሥራ ላይ ለየት ያለው የዋና ቤት መግቢያቸው በሌላው አካባቢ ለመስኮት የሚያገለግል ነው። ጎንበስ ብለው ነው የሚገቡት። ቤታቸውና አካባቢያቸው ጽዱ መሆኑም ትኩረት ይስባል። ለቤት ግንባታ የሚውለው ግብአትም ቀርከሐና ሳር እንደሆነ አቶ ሱሌይማን አብዱላሂ ገልጸውልኛል። እርሳቸው እንዳሉት አካባቢው ሞቃታማ በመሆኑም አብዛኞቹ ቤቶች አይመረጉም። መስኮትም የላቸውም። በተለይም በማኦ ኮሞ፣ ጉሙዝና በርታ የገጠር አካባቢዎች ሞቃታማ በመሆናቸው ተመሳሳይ የቤት አሰራር ነው ያላቸው።
የሲዳማ ክልልን የሚገልጹ የባህል አልባሳትን በተለያየ ዲዛይን ሰፍተው አዘጋጅተው ለሽያጭ ይዘው የቀረቡት አቶ ታደሰ ቶሎሳ፣ የያዟቸው አልባሳት ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ ከበአላት ውጭ በአዘቦቱም ለመልበስ ምቹ ሆነው የተዘጋጁ የሴትና የወንድ አልባሳትን ነው ይዘው የቀረቡት። እርሳቸው እንዳሉት በተለያየ ቀለማትና እንደጨሌ ባሉ ማስጌጫዎች እየተዘጋጀ የሚቀርበው የባህል ልብስ በአመት እጅግ ውስን በሆኑ ጊዜያቶች በዓላት ተጠብቆ መለበሱ የባህል አልባሳት ጎልተው እንዳይታወቁና የዕደጥበብ ባለሙያውም እንዳይጠቀም አድርጎታል። በመሆኑም ባለሙያውም የተጠቃሚውን ፍላጎት ማዕከል ባደረ ስፌቱን በማሳመር በማቅረብ ላይ ይገኛል። እንዲህ ያሉ የፌስቲቫል አጋጣሚዎች ደግሞ ገበያ በመፍጠር፣ ሸማቹም የየባህሉን አልባስ በአንድ ቦታ ለማግኘትና ለመምረጥ ዕድል ይፈጥራል። እርሳቸውም ከሌሎች ተሞክሮ ማግኘት በመቻላቸው ተደስተዋል።
ከጎብኝዎችም መካከል ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲጎበኙ ያገኘኋቸው በኢራን ኤምባሲ ሰራተኛ የሆኑት ሚስተር አሊ ረዛ‹‹በዚህ ትልቅ ትርጉም ባለው የፌሲቲቫል አጋጣሚ የወዳጅነት ፓርክን በመጎብኘቴ ደስ ብሎኛል። በዚህ አጋጣሚም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋና የባህል ሀብት ለማወቅ ችያለሁ። የአክሱም ስርዎ መንግሥት ስልጣኔ ያላት ሀገር እንደሆነችም በታሪክ አውቃለሁ።›› ነበር ያሉት። የባህል ብዝሐነት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ እንደሆንና በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዕድለኛ እንደሆነችና ጠብቃም ማቆየት እንዳለባት ሀሳብ ሰጥተዋል። ኢራንና ኢትዮጵያ የ71 አመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸውና በባህል፣ በሳይነስና በኢኮኖሚም ጠንካራ ግንኙነት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኢራን ከካይሮ ቀጥሎ ኤምባሲዋን የከፈተችው በኢትዮጵያ እንደሆነም አስታውሰዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2013