ጋዜጠኛ ለመሆን ውስጡ ባደረ ከፍ ያለ ፍላጎት ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ ማወቅ ብሎም መመርመር የጀመረው ገና የ9ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነበር።ያኔ ተማሪ ሆኖ ክፍለሀገር እያለ ጊዜ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ዓምዶች ላይ በመሳተፍ ጽፏል።ለዚህም ነው አዲስ ዘመን ጋዜጣን መነሻዬ ነው የሚለው።አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ውበት አማተር የጋዜጠኞች ክበብን ከስነጽሁፍ ወዳጆቹ ጋር መሠረተ፡፡
12ኛ ክፍል ሲጨረስ ክረምት ላይ መካኒክነት ገባ።በዚያ እየሠራ፤በአፍሪካ ሀገር አቋራጭ ህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ማኅበር የሥራ ዕድል አገኘ ።አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎች ስነጽሁፍ ትምህርት ክፍል የማታ ትምህርት ጀመረ።አንድ ዓመት እንደተማረ የማስሚዲያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተከፈተ።ተወዳድሮ ዕድሉን አገኘና የዩኒቨርስቲውን ትምህርትና ሥራውንም ትቶ ወደ ማስሚዲያ ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ገባ ዥ። “ብር ለምዶ፤ ሥራ ትቶ ወደ ትምህርት መግባት አስቸጋሪ ነበር” የሚለው አስቻለው፤ የጋዜጠኝነት ፍላጎቱ ግን ከፍተኛ ስለነበር ሥራውንና ገቢውን ትቶ ትምህርቱን ጀመረ።ጋዜጠኛ አስቻለው ጌታቸው፡፡
ጋዜጠኛ አስቻለው ባህል ቱሪዝምና የተፈጥሮ ሀብት ላይ በአብዛኛው ትኩረት አርጎ የሚሰራው የማውንቴይንስ ሚዲያ ሃላፊ ነው።ሚዲያው ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው “የዱር ሕይወት” የሚል ፕሮግራም ያዘጋጃል ።
አስቻለው “በተለይ መናኸሪያ ሲሠራ የሃይማኖት ጉዞዎች የመሄድ ሠፊ ዕድል እንደፈጠረለት ይገልፃል፡፡የሄደባቸውንም በወቅቱ አዲስ ዘመን ላይ በነበረው ተጓዥ ዓምድ ላይ ይጽፍ ነበር። ስለ ላሊበላ፣ አክሱም ፣ ስለ ቁልቢ ገብርኤል፣ ስለሐረር፣ ስለጎንደርና ስለወንዶገነት የቱሪስት መዳረሻ የሆኑትን ሙሉ ገጽ አዲስ ዘመን ላይ ይጽፍ ነበር። ”ያ ትልቅ ሞራል ሆኖኛል።አቶ አዲስ የሚባሉ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅም በጣም ያበረታቱኝ ነበረ “ይላል፡፡
ስለምሄደበት ጉዳይ ለጽሁፍ ጭምር አስቤ ማስታወሻ ይዤ በቦታው ለማጣቀሻ የሚረዳኝ መጽሐፍ ካለም ገዝቼ ስመለስም ተጨማሪ መጻሕፍት አይቼ አጣቅሼ ተጓዥ ዓምድ ላይ እጽፍ ነበር።ቅድመ ዝግጅት አድርጌ ነበር የምሄደው። አፍሪካ ትራንስፖርት የሚባል ድርጅት ነበር፤ በዋናው መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ ነው የምሠራው፤ ግን መንፈሳዊ ጉዞዎች ሲኖሩ አብሬ እሄዳለሁ፤ ብዙ ታሪካዊ ቦታዎችን የማየት ዕድሉ ገጥሞኛል ሲል ያብራራል።
ጋዜጠኛው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት እንደተመረቀ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተቀጠረ።በዚያ ለአስር ዓመት ሠርቷል።በአዲስ ዘመን ተጓዥ ዓምድ ላይ ይጽፋቸው የነበሩ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚያስተዋውቅ ስለነበር፤ “ኢትዮጵያን እንቃኛት”ፕሮግራም መመደቤ ተመቸኝ ይላል። ፕሮግራሙ የተቀረጸው ሥራ ከመጀመሬ በፊት ነው የሚለው አስቻለው፤ ሥራ እንደጀመረ ፍላጎቱን ገልጾላቸው ነው ፕሮግራሙ ላይ የመደቡት።የኢትዮጵያን ታሪክ ባህል ቅርሶች የሚያስተዋውቅ ፕሮግራም ስነበር በዚህ ላይ እየሠራ ዕውቅና አገኘ፡፡
ፕሮግራሙን በጣም በደስታና በፍቅር ይሠራ እንደነበር ጠቅሶ፤ “አስር ዓመት ፕሮግራሙ ላይ ስሠራ አንድም ቀን የዓመት ፍቃድ ወስጄ አላቅም ነበር ይላል።ኢትዮጵያን የማወቅ ዕድል ፈጥሮልኛል፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ባህል ቅርስ የምግብና የልብስ ዓይነቶች እንዲሁም ባህላዊ ዘፈኖችና ጭፈራዎቻቸውን የተፈጥሮ ሀብቶችን አይቼበታለሁ። አድማጭ ለፕሮግራሙ በጣም የሚያበረታቱና ሞራል የሚሰጡ ግብረ መልሶች (feedback) ነበሩት።”ሲል ይናገራል፡፡
ፕሮግራሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሠራ ፕሮግራም በመሆኑ ሁሉንም ክልሎች የማየት፤ ባህልና የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ዕድል አለው።ሁሉም ክልሎች በአካል ሄዶ ዐይቶ አናግሮ ይዘግብ ነበር።”የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ሠፊ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን፤ ፕሮግራሙ የሚወደደውን ያህል በጣም ፈታኝ ሁኔታዎችም አሉት።ሁለት ሦስት ቀን በእግራችን የምንሄድባቸው ቦታዎች አሉ።ግን በፍላጎት እንሠራው ስለነበር ሦስት ቀን በእግር ጉዞ ብሄድም ደስተኛ ነበርኩ።መኪና የማይገባባቸው ቦታዎች በእግር መሄድ ግድ ነው።ጫካ ውስጥ ያደርንባቸው ጊዜ አሉ። በገጠር ክሊኒክ ቤት ሲሚንቶ ላይ አድረናል።ቢሆንም ግን ሁሉንም ክልሎች የማየት ዕድሉን ፈጥሮልኛል፡፡ብዙ ባህሎችን እንዳውቅ አድርጎኛል። ስለ ሀገሬ በኩራት እንዳወራ አድርጎኛል።ፈተናዎቹን አልፈንም ፕሮግራሙን ስንሠራው ደስታ ይሰማናል፡፡” ሲል አስቻለው ይገልፃል፡፡
ማውንቴይንስ ሚዲያ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር በመተባበር “የዱር ሕይወት” የሚል ፕሮግራም በሳምንት ረቡዕ ጠዋት 2፡30 -3፡00 ያቀርባል።ብዙ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ብሔራዊ ፓርኮችና ላይ በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስያዝ ነው ሲል ይገልፃል፡፡
“በብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ ነው የምንሠራው፤ ታች ማኅበረሰቡ ጋር የመድረስ ዐቅሙ ከፍተኛ ነው።ማውንቴንስ ሚዲያ የሚለውም ተራሮቻችን በጣም እየተራቆቱ ናቸው። ሰው ቢሆን አልብሱኝ ብሎ ይጮኻል፤ ተራሮቹ ግዑዝ ስለሆኑ ባይጮኹም የእነሱን ድምጽ ለማሰማት ነው።ተራሮቻችን ችግኝ፤ ከፍ ሲል ዛፍ መልበስ አለባቸው። ይህን በማድረግ የሰዉንም የቤት እንስሳትንም ሆነ የዱር እንስሳትን ሕይወት የአየር ንብረቱንም ሙቀት ልናስተካክለው እንችላለን፡፡”
የምሠራበት ፕሮግራም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማሳደግ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት የሚችል ነው።ብዙ ሰው ስለሀገሩ የተፈጥሮ ሀብት ግንዛቤና የመጎብኘት ልምድ እንዲኖረው፤ በመንፈሳዊ ጉዞዎች ሰፊ እንቅስቃሴ አለ፤ ያም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም አስተዋጽዖ አለው።ፕሮግራሙ የሀገራችንን ታሪካዊ ቦታዎችን እና ገዳማት እንዲጎበኙ መረጃ የሰጠን ይመስለኛል።በጣም ሰፊ ብዙ በግለሰብ ደረጃ በድርጅትም እየተሰባሰቡ በሀገር ውስጥ የሚያዩት እየጨመረ ነው፤ የራሳችን በጎ አስተዋጽዖ አለን፡፡
የእረፍት ጊዜ
ብዙውን ጊዜ እረፍት ጊዜዬን ማሳለፍ የምወደው ተፈጥሮዋዊ ቦታዎችን ጫካዎችን በመጎብኘት ነው። ውሃ ዳር እንደ ሐዋሳ ባህር ዳር ቢሾፍቱ ባሉት አካባቢዎች እረፍቴን ማሳለፍ ደስ ይለኛል።መጻሕፍት አነባለሁ፤ ጋዜጦችና ሬዲዮና ቴሌቪዥን ስርጭት እከታተላለሁ፤ ለሥራዬ የሚረዱኝም ከሆነ እጠቀምባቸዋለሁ። ትርፍ ጊዜዬን በጉዞም ስለማሳልፈው እንደ ሥራና መዝናኛ አየዋለሁ ሲል ጋዜጠኛ አስቻለው ይናገራል፡፡
መልዕክት
ወጣቱ ትወልድ በዋናነት ሀገራዊ የሆነ ዕውቀት ላይ ያለውን ግንዛቤ ማስፋት አለበት የሚለው አስቻለው፣ ባህልን ማክበር ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂን ነው እንጂ ከውጪ መውሰድ ያለብን ዕውቀት አላጣንም።ለሌሎች ሊተርፉ የሚችሉ ባህሎች ሀገር በቀል ዕውቀት አለን።ወጣቱ ይህን እንዲጨብጥ ሚዲያው ትልቅ ሚና መጫወት አለበት ሲል ያስገነዝባል፡፡
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት ተጀምሯል፤ ይኼ ፕሮጀክት የኛም ራዕይ ነበር፤ያ በመጀመሩ በጣም ነው ደስ ያለን፤ ከፍተኛ የሆነ የሚዲያ ዘመቻም አካሂደን ነበር።ባጭር ጊዜ የአረንጓዳ አሻራ መጀመሩና ብዙ ሰው መሳተፉ ለኛም ትልቅ ስኬት ነው።ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሀገራችን አረንጓዴ ለብሳ ውሃ ማንቸገርበት፣ ንጹህ አየር የምናገኝበት ትሆናለች። በማለት አገራዊ የሆነ የወደፊት ብሩህ ተስፋውን ገልጧል። ወጣቱ ትውልድ በእዚህ ላይ በበጎ ፍቃደኝነት መሥራት አለበት በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2013