አመሻሽ ላይ መነሻዬን መነን አካባቢ አድርጌ ከስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ጀርባ ቁልቁል ወደ አፍንጮ በር በሚወስደው መንገድ እጓዛለሁ።መምህራን ኮንዶሚኒየም ከሚባለው ሰፈር ከመድረሴ በፊት በስተቀኝ በኩል እናትና ልጆች ከአንዲት የሸራ ቤት በር ላይ ተቀምጠው አየሁ። ሰማያዊ ሸራ በለበሰችው ቤት ላይ የህፃናት ልብሶች ተሰጥተዋል። ቤቷ በአንድ በኩል ተጠግታ የተሰራችበት የግንብ አጥር እንደ ግድግዳም እንደምሰሶም ሆኗታል።ሌላው ጎኗ በስብርባሪ እንጨት ካርቶንና መስታወት ተደጋግፎ ቆሟል። ከበሯ ፊት ለፊት ባለው ፍሳሽ ማስወገጃ ዳርቻ የተጠራቀመ ቆሻሻ ይታያል፤ ተገፎ የተጣለ የበሬ ቆዳ፤ አጥንት፣ በማዳበሪያ ከረጢት የተሞላ ትርኪ ምርኪ እቃ ወዘተ።ከፍሳሽ ማስወጋጃው እና ከተከመረው ቆሻሻ የሚነሳው መጥፎ ሽታ አፍንጫን በጥሶ ይጥላል።
ደመቀችና ልጆቿ ከቆሻሻው ቅርብ ርቀት ተቀምጠው ዓይናቸው አላፊ አግዳሚው ላይ ይንከራተታል።የሚፈልጉት ነገር ያለ ይመስላል፤ ግን ሲጠይቁ አይታይም ፤ አንድ ሁለት የሚሆኑ የመንደሩ ሰዎች ስማቸውን እየጠሩ ሰላምታ እያቀረቡላቸው ሲያልፉ አየሁ።ወዲው በችግር ውስጥ ያሉና በመንደሩ ሰዎች የሚደገፉ እናትና ልጆች መሆናቸውን መገመት አልከበደኝም።እኔም እንደሰፈርተኛው እጅ ነስቼ ጉስቁል ብላ የተቀመጠችውን እናት አነጋገርኳት። ግምቴ ትክክል ነበር፤ ችግር የበረታባትና መውደቂያ ያጣች የሶስት ልጆች እናት ነች።
ከሃያ ዓመት በፊት ትምህርቴን ሳልጨርስ ትዳር አልይዝም በሚል ከገጠር ሸሽታ ወደ አዲስ አበባ የመጣች ነች።አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ሰው ቤት እየሰራች ትምህርቷን ለመማር ትሞክራለች።አሰሪዋ ከትምህርት እያስቀረቻት ስራ እንድትሰራ ታስገድዳታለች።ለትምህርቷ ትልቅ ዋጋ ሰጥታ ከሀገሯ የተሰደደችው ወጣት ምቹ የትምህርት ሁኔታን በመፈለግ ሌላ ቤት ትገባለች።እዚያም ተመሳሳይ ነገር ይገጥማታል።የመማር እድል ካላገኘሁ የተሻለ ክፍያ ያለው ስራ እየሰራሁ እራሴን እቀይራለሁ በሚል በምግብ ቤቶች ውስጥ በእቃ አጣቢነትና በወጥ ቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ መስራት ትጀምራለች።ከዚያም ባላሰበችው መንገድ ወደ ፈራችው ትዳር ገብታ ለችግርና እንግልት መዳረጓን ትናገራለች።ባለታሪኳ የዚህ አምድ እንግዳ ትሆን ዘንድ አስፈቅጃት ካሳለፈችው አሳዛኝ ህይወት እየመዘዘች የነገችኝን ላካፍላችሁ ወደድሁ።
ደመቀች አየለ ትባላለች።የተወለደችው ደቡብ ክልል ነው።ዞኑን በውል አታውቀውም።ከወሳህና እልፍ ብሎ እንደሚገኝና አንጃማና አንጣጣ እንደሚባል ብቻ ነው የምታውቀው።ሁለት ወንድምና አንድ እህት አሏት።ለቤተሰቦቿ የመጨረሻ ልጅ ነች።በተወለደች ጥቂት ዓመታት ውስጥ አባቷ ሞተውባት እናቷ በችግር እንዳሳደጓት ትናገራለች።እናቷ በቂ መሬት የላቸውም፤ ከብቶችንም አያረቡም።የሰዎችን እንሰት በመፋቅና አንዳንዴም የቃጫ ምንጣፎችን እየሰሩ በመሸጥ በሚያገኙት ገንዘብ ያስተዳድሯቸው እንደነበር ታስታውሳለች።ታላላቅ ወንድሞቿም እንዲሁ የቀን ስራ እየሰሩ እናታቸውን ይረዱ ነበር።
ደመቀችም ከለጋ እድሜዋ ጀምራ እናቷን ለመደገፍ ስትል በስራ ተጠምዳ ማደጓን ትናገራለች። በዚህ የተነሳ ጣዕም ያለው የልጅነት ጊዜን አላሳለፈችም።ከፍ ስትልም ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ የቀን ስራ መስራት ትጀምራለች።እንደ ጓደኞቿ ትምህርት ቤት ገብታ ፊደል መቁጠር ሳትጀምር እድሜዋ መግፋቱ ያበሳጫት ነበር። ትምህርት የመማር ህልሟን ለማሳካት ባጠራቀመቻት ገንዘብ ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ ጫማና ልበሷን አሟልታ ትመዘገባለች።እናቷ ግን እንድትማር አይፈቅዱላትም ነበር።
ደመቀች አንድ ቀን እየተማረች አንድ ቀን እየቀረች አራተኛ ክፍል ትደርሳለች። ኋላ ግን ፈታኝ ሁኔታዎች ይገጥሟታል።የስራ ትጋቷንና ታታሪነቷን የተመለከቱ የአካባቢው ወጣቶች ደመቀች ላይ አይናቸውን መጣል ይጀምራሉ።አንዳንዶቹ ህጋዊ የጋብቻ ጥያቄ ያቀርቡላት ጀመር፤ አንዳንዶችም ሊጠልፏት ክትትል ያደርጉባታል፤ ደብዳቤ እየጻፉ የሚሰጧትም ነበሩ።ባለተስፋዋ ታዳጊ ግን በትዳር ታስሮ መቀመጥን ስላልፈለገች አካባቢውን ለቃ በመሄድ ትምህርቷን ዳር ማድረስ እንዳለባት ትወስናለች።
የመሄጃ ቦታዋ የት እንደሆነ ግን አልወሰነችም።እንደአጋጣሚ አንዲት ሴት የመስቀል በዓልን ለማክበር ከአዲስ አበባ ደመቀች ወዳለችበት መንደር ትሄዳለች።ሴትዮይቱ ከደመቀች ዘመዶች ጋር ዝምድና የላትም።ወላጆቿን ለመጠየቅ የመጣች የዚያው አካባቢ ተወላጅ ነች።የደመቀች እናትም ሴትዮይቱ ልጃቸውን ወደ አዲስ አበባ ይዛላቸው እንድትሄድና የቤት ሰራተኝነትም ቢሆን እንድታስቀጥራት ይጠይቋታል።እንግዳዋ ሴት ደመቀችን እራሷ ጋር አስቀምጣት እንደምታስተምራት ቃል ገብታ ይዛት ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች።
ደመቀች አዲስ አበባ ገብታ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ትሆናለች።በዚሁ አካባቢ ወንድማማቶች ትምህርት ቤት ተመዝግባ ትምህርቷን መከታተል ትጀምራለች።ሀሳቧን ያሳካች ስለመሰላትም ደስ ይላታል።ከሀገር ቤት አደራ ተቀብላ አስተምራታለሁ ብላ ያመጣቻት ሴት ግን ለይስሙላ ካስመዘገበቻት በኋላ ከትምህርት ገበታዋ ላይ እያስቀረቻት ስራ እንደምታሰራት ትናገራለች። በዚህ የተነሳ ከአሰሪዋ ጋር መግባባት ያቅታታል።አንድ የሀገሯን ሰው አነጋግራ ሌላ ሰው ቤት ትቀጠራለች።እዚያም ተመሳሳይ ሁኔታ ይገጥማታል። እንደገና በአንድ ሆቴል ቤት ውስጥ በእቃ አጣቢነት ያስቀጥራታል።ደመቀች ከእቃ አጣቢነት ወደ ወጥቤት ሰራተኝነት ትሸጋገራለች።ሙያ እያወቀች ስትሄድ የተሻለ ክፍያ ለማግኘት በማሰብ የተለያዩ ቤቶችን እየቀያየረች መስራት ትጀምራለች።
ህይወቷን በዚህ መልክ እየመራች እያለ አንድ ሰው የጋብቻ ጥያቄ ያቀርብላታል።በቅርበት የምታውቀው ሰው በመሆኑ ተጋግዞ ለመኖር ይሻላል በሚል አግብታ ትኖራለች።ትንሽ ቆይታም ትወልዳለች።የልጇ አባት ግን እርግዝና ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ትቷት ይጠፋል።ደመቀች መውለጃዋ እስኪቀረብ ድረስ እየሰራች በመጨረሻም ክፍለሀገር እናቷ ጋር ሄዳ ትወልዳለች።ልጇን እናቷ ጋር አስቀምጣ ወደ አዲስ አበባ ትመለሳለች።
አዲስ አበባ ከተመለሰች በኋላ አሁንም ሰው ቤት እየሰራች ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ ፕሮሰስ ትጀምራለች።ጉዳይ ለማስፈጸም እላይ ታች ማለቱ ጊዜንና ገንዘብን የሚጠይቅ ይሆንባታል።በአቅም ማነስ ምክንያት የዓረብ ሀገር ጉዞዋን ሰርዛ ከምታገኛት ላይ ለልጇ እየላከች ለመቀመጥ ትገደዳለች።ለጊዜው ሽሮ ሜዳ አካባቢ ማረፊያዋን አድርጋ ስድስት ኪሎ ከመነን ትምህርት ቤት ጀርባ ውሃ ልማት አደራጅቷቸው ከሚሰሩ ሴቶች ድርጅት ውስጥ በጽዳት ሰራተኝነት ተቀጥራ መስራት ትጀምራለች።ማህበሩ እያስከፈለ የመጸዳጃ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ደመቀች እዚያው የጽዳት ስራ እየሰራች ቀኑን ሙሉ ትውላለች።አንዳንዴም ከተጠቃሚዎች ላይ ገንዘብ በመሰብሰብ ለድርጅቱ የማስረከብ ስራ ትሰራለች።እንዲህ አይነት ስራዎችን ስትሰራ ውላ ማታ ወደ ማረፊያዋ ትሄዳለች።
በዚህ የስራ ሁኔታ ውስጥ እያለች አብሯት ከሚውለው የድርጅቱ ጥበቃ ሰራተኛ ጋር ትተዋወቃለች። ትውውቃቸው ትዳር ወደ መመስረት ያድጋል። የአቅም ውሱንነትና የማረፊያ ቦታ ችግር የነበረባቸው ባልና ሚስቶች ድርጅቱን አስፈቅደው ለጥበቃ ሰራተኛ በተሰራው ኮንቴነር ውስጥ መኖር ይጀምራሉ።
ደመቀች ሁለተኛ ልጇን ታረግዛለች።ዓረብ ሀገር ሊልኳት ሲያግዟት የነበሩ ዘመዶቿ ሁለተኛ ባል አገባች መባሉን ሲሰሙ አይንሽ ላፈር ይሏታል። ከሰዎች ተገልላ ኑሮዋን በጠባቧ ኮንቴነር ውስጥ ያደረገችው ደመቀች የመውለጃዋ ጊዜ ይደርሳል።የህክምና ክትትልና ድጋፍ ለማግኘት አቅመ ደካማ መሆኗን የሚገልጽ ደብዳቤ ጠይቃ ታስጽፋለች።በዚሁ መሰረት ምጥ እንደያዛት ለአቡነ ፔጥሮስ ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎላት ሁለተኛ ልጇን እዚያው ትገላገላለች።ከሶስት ዓመት በኋላም ሶስተኛ ልጅ ወልዳ በዚያው ኮንቴነር ውስጥ ትኖር ነበር።ሶስተኛ ልጇን ስትገላገል በቀዶ ጥገና ነው።በዚህ የተነሳ ለወራት ታማ ተኝታለች።ከተነሳችም በኋላ ከበድ ያሉ ስራዎችን መስራት አትችልም።ደመቀች ቀደም ሲል ድርጅቱ ውስጥ ከምትሰራው ስራ በተጨማሪ ልብስ በማጠብም ጥቅም ታገኝ ነበር።አሁን ያ ሁሉ የለም።
ድርጅቱ ይኖሩበት የነበረውን ኮንቴነር ለግለሰቦች ያኮናትራል።እነደመቀች ከኮንቴነሩ ወጥተው እዚያው አካባቢ በአንድ አጥር ስር ሸራ ወጥረው ከልጆቻቸው ጋር መኖር ይጀምራሉ። ባለቤቷ ስራ ካቆመ ወዲህ ለተወሰኑ ወራት የቀን ስራ እየሰራ አብሯት ይኖር ነበር።ከሁለት ወር በፊት ግን የመጀመሪያ ልጁን ይዞ ወዴት እንደተሰወረ አታውቅም።አሁን ከቀድሞ ባሏ የወለደቻትን የስምንት ዓመት ልጇንና የዘጠኝ ወሩን ህፃን ይዛ በሸራ ቤቷ ውስጥ ትኖራለች።
ደመቀች ሆዷ ስፌት ስላለበት ቀደም ሲል የምትሰራውን የልብስ አጠባ ስራ መስራት አትችልም።የአካባቢው ማህበረሰብ እና አላፊ አግዳሚው በሚያደርግላት ድጋፍ ትኖራለች።አልፎ አልፎ ለሰዎች እየተላላከች መጠነኛ ገቢ ታገኛለች።ወፍጮ ቤት እህል በማስፈጨት፣ ከገበያ አስቤዛዎችን በመግዛት ሰዎችን ታገለግላለች።ይህችን ያህል የመስራት እድል የምታገኘው ልጇን ከትምህርት ቤት እያስቀረች ህፃኑን እንድታጫውትላት በማድረግ ነው።
የሸራ ቤቱ ኑሮ እጅግ ፈታኝ እንደሆነባት ትናገራለች።ቀን ቀን ይሞቃል ማታ ማታ ይበርዳል።ቤቱ ለይስሙላ ሸራ ይልበስ እንጂ ከምንም የሚያድን አለመሆኑን ትናገራለች።ከሰሞኑ በጣለው መጠነኛ ዝናብ እንኳን የደረሰባትን እንዲህ ታስረዳለች።‹‹አንድ ቀን ልክ እኩለ ሌሊት ላይ ዝናብ ይጥላል።ሸራውን ዘልቆ መኝታችን ላይ መንዠቅዠቅ ሲጀምር ከእንቅልፌ ነቃሁና ክብሪት አብርቼ ስመለከት ቤቱን አዳርሶታል።ሁሉንም ነገር ትቼ ልጆቼ ከእንቅልፋቸው እንዳይነቁ እላያቸው ላይ ላስቲክ አልብሻቸው ቁጭ አልኩኝ።ነገር ግን ላስቲኩ ላይ የሚወርደውን የፍሳሽ ድምጽ ሲሰሙ ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ። ህፃኑ ያለቅሳል፤ ትልቋም ልጅ ተደነጋግጣ ቁጭ ትላለች።የማደርገው ሲጠፋኝ መኝታውን ሰበሰብኩና ላስቲኩን ለብሰን እላዩ ላይ ቁጭ አልን።ዝናቡ ግን ሊያባራ አልቻለም።ህፃኑን እንዳቀፍኩት ትልቋም አጠገቤ ቁጭ እንዳለች እንቅልፍ ይወስዳቸዋል።ልጆቼን ከእንቅልፋቸው ላለመቀስቀስ ስል እንደዛችው ኩርምት ብለን አድረናል፡፡›› ይህን ሰሞነኛ ክስተት መቼም እንደማትረሳው ትናገራለች።
ደመቀች ሌሎች ችግሮቿንም በመዘርዘር ማስረዳቷን ቀጥላለች፤ ‹‹ደንብ አስከባሪዎች ለምን ሸራ ወጠርሽ እያሉ ቁም ስቅሌን ያሳዩኛል።ብዙ ጊዜ እየመጡ የልጆቼን ሁኔታ ካዩ በኋላ በማስጠንቀቂያ ያልፉኛል።ቀበሌ ቤት እስኪሰጠኝ ድረስ ከዚህ ውጭ መኖር አልችልም እላቸዋለሁ።ቤት እንዲሰጠኝ ካመለከትኩ ቆይቻለሁ።በአካል እየቀረብኩም ያልጠየኩበት ጊዜ የለም።ግን መፍትሄ የሚሰጠኝ ሰው አላገኘሁም።በዚህ አጋጣሚ ቀበሌው እኔን ሳይሆን ልጆቼን በማየት ብቻ ማረፊያ ሰጥቶኝ ሰርቼ የማስተምርበትን እድል እንዲፈጥርልኝ እማፀናለሁ፡፡››
በመጨረሻም ደመቀች መልዕክቷን እንዲህ አስተላልፋለች – ‹‹እኔ ህይወቴ የተበላሸው ባለመማሬ ነው።በዚህ ጉዳይ እናቴን ሁሌም እወቅሳታለሁ።እነዚህ ልጆችም ነገ እኔን እንዲወቅሱኝ አልፈልግም፤ በዚህ ህይወት ውስጥ ሆኜም ትልቋን ልጄን እያስተማርኳት ነው።የልጆቼ መማር ለእነርሱም ለእኔም ተስፋ ነው።ይህን ህፃን ልጅም እድሜው ሲደርስ ትምህርት ቤት ማስገባቴ የማይቀር ነው።ቀበሌው ከቻለ ቤት ይስጠኝ፤ ካልቻለ ግን ሸራሽን አፍርሺ አይበለኝ፤›› ትላለች።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013