ልጅቱ ስለ ፍትህ አብዝታ የምትጠይቅ ነች። ሰዎች ከሚፈጥሩት ኢፍትሃዊነት አልፎ በተፈጥሮ ላይም ጥያቄ ታነሳለች። አንዳንዱ አካባቢ በተፈጥሮ ሀብት ለምልሞ ሳለ ሌላ አካባቢ ደግሞ የተራቆተ ነው ስትል ትጠይቃለች። ሴቶች ከወንዶች የበለጠውን ጫና እንዲቀበሉ ተፈጥሮ ስላደረገችው ኢ-ፍታሃዊነት የትነው የምትጠየቀውም ትላላች። ወንዶች እንደ ሴቶች ሳያረግዙና ሳያጠቡ የልጅ አባት መሆናቸው ይበልጥኑ አይዋጥላትም። ፍትህን ፍለጋ ሰው ሁሉ ቢዘምት እኔ ከቆላ እስከ ደጋ እዘምታለሁ ትላለች፤ ፍትህን ፍለጋ የሆነን ዘመቻ!
ከሰሞኑን ኢትዮጵያውያን የአሜሪካን መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመቃወም ትእይንተ ሕዝብ በምድረ አሜሪካ አድርገዋል። ጥያቄያቸው አሜሪካ ኢትዮጵያን በፍትሃዊነት እየተመለከተች አይደለምና ልታስብበት ይገባል የሚል ነው።
በስፖርት ፌድሬሽኖች ውስጥ ፍትህ ቦታውን አጥቷል ብለው ሲያስቡ በበዛ አታካሮ ውስጥ የሚገቡ ግለሰቦችን በሚዲያው ላይ እናያለን። በቤተእምነቶች አካባቢም እንዲሁ። ወደ ቤተሰብም ብንዘልቅ የበረከተ የፍትህ ጥያቄ። በአጭሩ በሁሉም ስፍራ!
ስለ ፍትህ አብዝታ የምትጠይቀው ወጣት ወደ ጋብቻ ህይወት ገባች። በወንድና ሴት መካከል ፍትሃዊነት የለም በሚለው እምነቷ ውስጥ አሁንም ብትሆንም መጋባት የተፈጥሮ ግዴታዋ ሆኖ ይመስላል ልቧን ከፍታ ወንዱን በባልነት ተቀብላ ጎጆ ቀየሱ። ልጅም ወለዱ።
አንድ ቀን ታዲያ በተፈጥሮ ላይ ያላትን የኢ-ፍትሃዊነት አቋሟን ዳግም እንድትፈትሽ የሚያደርግ አጋጣሚ ተፈጠረ። አጋጣሚውም የወለደቻት ልጅ መታመም ነው። የልጅ ህመም ወላጆችን ግራ ማጋባቱ አይቀሬ ነውና አባትና እናት ጨቅላ ልጃቸው በህመም ውስጥ ሆኖ የሚያሰሙት ለቅሶ ግራ አጋባቸው። ህፃኗን ይዘው ወደ ህክምና ቦታ እንዳይሄዱ ሰዓቱ አመሻሽ ላይ መሆኑ አሳነፋቸው። አዳሯን እንይና ነገ ወደ ህክምና እንሄዳለን ብለውም አሰቡ። ሰዓቶቹ እየገፉ በሄዱ ቁጥር ልጅ ማልቀሷን ማቋረጥ እስክትችል ድረስ ደረሰች። እናት ህፃኗን ታቅፋ ጡት ስታጠባት ህፃኗ ትረጋጋለች። ከእናት እቅፍ ወረዳ አልጋው ሲነካት ግን የልቅሶ ለቅሶ ከቁጥጥር ውጭ ይወጣል። አባት ምንም ማድረግ በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በጭንቀት አብሮ ይቸገራል። እናትና አባት ከእንቅልፍ ጋር ግብግብ ገጥመው ልጃቸውን ሊረዱ እየጣሩ ነው። በዚህ ጊዜ በሚስት አዕምሮ ውስጥ አንድ ሃሳብ ውልብ አለ። ባል እንደ እርሷ ማጥባት የሚችል ቢሆን ብላ አሰበች። ሁለቱም ማጥባት ቢችሉ ኖሩ ተራ በተራ እያጠቡ ተራ በተራ ይተኛሉ፤ ነገር ግን ሁለቱም እኩል ማጥባት የሚችሉ ሆነው ሁለቱም መተኛት ፈልገው አንቺ አጥቢ አንተ አጥባ ቢባባሉ በፉክክር የሚፈጠረው ምስቅልቅልን ለማሰብ ሞከረች። የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው እንደሚሆን አሰበች። በተፈጥሮ ላይ የነበራትን የፍትህ ጥያቄን ወደ ጎን አድርጋ ፍትሃዊነትን ለመገንዘብ ሁለገባውን ማሰብ ተገቢ እንደሆነ ተረዳች። ፍትህ ላይ ጥያቄ ያለኝ ለካንስ አሁን ባለኝ መረዳት ልክ ነው ስትልም አሰበች። አሁን ባለኝ መረዳት በቻልኩት ልክ ነው ፍትሃዊነትን እና ኢ-ፍትሃዊነትን የማየው ስትል ለራሷ ተናገረች።
በመንደርደሪያ ታሪካችን ውስጥ ሁለት ቁልፍ ነጥቦችን ስለ ፍትህ እናስብና እንለፍ። አንደኛው የፍትህ ጥያቄ ሁሉም ቦታ ያለ ጥያቄ መሆኑን ሁለተኛ ነጥብ ፍትህን የሚፈልገው ሰው የሚጠይቀው በገባው ልክ መሆኑን። በፍትህ ፍለጋ ሂደች እኛ እንደ ፍትህ ፈላጊም ሆነን ልንገኝ እንችላለን እንዲሁም ፍትህን ማስፈን የሚጠበቅበት ሰው። ሁለቱንም ስንሆን ሁለቱን ቁልፍ ነጥቦች ማሰብ ይገባናል። የሰመረ የፍትህ ፍለጋ እንዲሆንልን።
ፍትህ ለማን ታስፈልጋለች?
ፍርድቤት ፍትህ በሚታሰብበት ጊዜ ቀድሞ ወደ አዕምሮችን የሚመጣው ተቋም ነው። በአቅራቢያችን ያለ ፍርድቤት ጎራ ብለን ያለውን ሰልፍ እንመልከት። ለዘይት ሆነ ለታክሲ ሰልፍ እንዳለው ሁሉ በፍርድቤትም ሰልፍ አለ፤ ፍትህን ፍለጋ የተወጣ ሰልፍ።
ምርት በማከፋፈል ገቢውን የሚያገኝ ድርጅት በመጋዘን የያዘው ሀብቱ ትኩረት የሚያደርግበት ንብረቱ ነው። በመጋዘኑ ውስጥ ያለውን ሀብት ወደ ገንዘብ ቀይሮ ስለሆነ ገንዘቡን የሚያገኘው። የህክምና አገልግሎት በመስጠት ገቢውን የሚያገኘው ድርጅት ደግሞ የህክምና ባለሙያዎቹ በጥንቃቄ የሚጠብቃቸው ሀብቶቹ ናቸው።
ወደ ፍርድቤት ስንመጣ ፍትህን የሚሰጡት ባለሙያዎች ትልቅ ሀብት ሲሆኑ ከባለሙያዎቹ ቀጥሎ መዝገብቤት ተከምሮ የሚገኘው መዝገብ ሌላው ልዩ ጥበቃ የሚደረግለት ሀብት ነው። እንደ ባለመጋዘኑ የፍርድቤቱ መጋዘን ውስጥ ዶሴዎች አሉ። እያንዳንዱ ዶሴ የከሳሽና የተከሳሽን ክርክር ይዟል። ውሳኔ የተሰጠበት እንዲሁም በሂደት ላይ ባሉት ዶሴዎች ውስጥ ፍትህን ለመፈለግ ስልፍ የወጡቱን እናገኛለን።
ወደ መደበኛ ፍርድቤት ሳይሄዱ በባህላዊ መንገድ በሽምግልና በኩል ፍትህን የሚፈልጉቱም እንዲሁ አሉ። ፍትህን በገዛ እጃቸው ለማምጣት በማስፈራራት የሚገለጡትም ቢሆኑ አካሄዳቸው ትክክል ባይሆንም ወደ ወንጀል የከተታቻው አንዳች የጠፋው ፍትህ መኖሩ ታሳቢ ሊደረግበት ይገባል። የአባቱን ገዳይ ለመበቀል እድሜ ልኩን ኖሮ ብቀላውን አሳክቶ ተንከራታች የሆነ ሰው በምድራችን ሞልቷል። የፍትህ መጥፋት ሌላ ጥፋት እየወለደ እየተባዛም ይቀጥላል።
የሀዘን ጉዞ!
እኛ የሰው ልጆች ሁላችን ፍትህን ፈላጊዎች መሆናችንን መረዳት ይገባናል። ፍትህ ፈላጊነት ለወንድም ለሴትም ነው፤ ፍትህ ፈላጊነት ለወጣቱም ለጎልማሳውም ነው፤ ፍትህ ፈላጊነት ለተማረውም ላልተማረውም ነው፤ ፍትህ ፈላጊነት ለድሃውም ለሀብታሙም ነው፤ ፍትህ ፈላጊነት ለክርስቲያኑም ለሙስሊሙም ነው፤ ፍትህ ፈላጊነት ለባለሥልጣኑም ለዜጋውም ሁሉ ነው፤ ፍትህ ፈላጊነት ለሁሉም!
ሁሉም ፍትህን በሚፈልገበት ምድር ላይ ስንኖር፤ የፍትህ መጓደል ሁሉንም የሚጎዳ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። ፍትህ ለሁሉም ይገባል፤ አዎን ፍትህን ለማስፈን ሁሉም ሊሰራ ይገባዋል። እንዴት? ወርቃማው ሕግ የተሻለው ምላሽ ነው። በእኛ ላይ እንዲሆን የማንፈልገውን በሌላው ላይ አለማድረግ።
በአንተ ላይ እንዲሆን የማትፈልገውን በሌላው ላይ አታድርግ የሚለው ወርቃማው ሕግ ለሁሉም የሚሰራ ስለሆነ የሃይማኖትን ድንበር ተሻግሮ ተቀባይነት አግኝቷል። በፍትህ ተንታኞች ፊት ቀዳሚውን ቦታ የያዘው ይህ አገላለጽ ዛሬ በሁላችንም ልብ ውስጥ ቦታ ሊኖረው ይገባል ፍትህን በመፈለግ ጉዞ ውስጥ።
እኛ የምንጠይቀውን ፍትህ አጠገባችን ያለ ሌላ ሰው እንደሚገባው ማመን አለብን። እኛ የሚጠማንን ውሃ ሌላውም እንደሚጠማው ማወቅ ያስፈልገናል። እኛ የራበንን እንጀራ ሌላውም እንደሚርበው ማሰብ አለብን።
ፍትህን የመግፋት አንራዊ አቅም በየአጋጣሚው ሊገጥመን ይችል ይሆናል። በሥልጣን ላይ ያለ ሰው ዛሬ በሥልጣኑ ምክንያት ፍትህን የመግፋት አንፃራዊ አቅም ሊኖረው ይችላል። ገንዘብ ያለው ሰው በገንዘቡ። በሰዎች ዘንድ እውቅና ያለው ሰው በእውቅናው። በራስ ብሔር መካከል በመኖር ወዘተ። አንፃራዊ ፍትህን የመግፋት አቅምን ተጠቅመን የምናሳድረው ኢፍትሃዊነት ለሌሎች ማቄምና ለበቀል ማድባትን የሚፈጥር ይሆናል። የመገፋትና የመጠቃት ስሜት በሂደት ወደ ጥላቻ አድሮ ለከፍተኛ ቀውስም ምክንያት ሆኖ ይገኛል።
ፍትህን ፍለጋ የወጣ ሰው ፍትህ ለሁሉም እንደሚገባ ማመን አለበት። ፍትህ ለሁሉም የሚገባ መሆኑን የተረዳ ሰው ፍትሃዊነት ለማስፈን ከየትኛውም አይነት የልዩነት መገለጫዎች ወጥቶ ራስ ላይ እንዲሆን የማንፈልገውን በሌላው ላይ ባለማድረግ ሊገለጥ ይገባዋል።
ፍትህ በቀጠነች ጊዜ
በማረሚያ ቤት ውስጥ ያለፈ ግለሰብ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ ስለ ማረሚያ ቤት ሁኔታ ይተነትናል። የማረሚያ ቤት ገጽታ ምን እንደሚመስል ያስረዳል። ማረሚያ ቤት እንዴት ማረሚያ ቤት መሆን እንደሚገባውም ይሞግታል። እርሱን በማረሚያ ቤት ውስጥ ዓመታትን በስር እንዲገኝ ያደረገው ኢ-ፍትሃዊነት እንጂ ፍትህን ፍለጋ አለመሆኑን ይሞግታል። በኢ-ፍትሃዊነት ማረሚያ ቤት ውስጥ መቆየቱ የመኖር የሞራል ልዕልና እንዲይዝ አድርጎት ከእስር ወጥቶ እውነታውን በመጽሐፍ መልክ እንዲያቀርብ አቅም እንደሆነው ይተርካል።
የማረሚያ ቤቱን ቆይታ በጽሁፍ ያቀረበው ግለሰብ በማረሚያ ቤት ውስጥ ስለተዋወቃቸው ሰዎች ያነሳል፤ አንዱ ነፍስ በማጥፋት የተፈረደበት ግለሰብ ነበር። ግለሰቡ እድሜ ይፍታህ ተፈርዶበት እድሜውን በማረሚያ ቤት ውስጥ እየገፋ የሚገኝ ነው። ምህረት ተደርጎለት አንድ ቀን ሊወጣ እንደሚችል ግን ተስፋ ያደርጋል። የሚያገኘው ምህረት መነሻው ምክንያት መታረሙ ከሆነ ግን የሚሆን አይመስልም። ምክንያቱም ግለሰቡ በኩራት የሚናገረው ግድያውን በመፈፀሙ የሚሰማው ደስታ ከፍተኛ መሆኑን ነው። ከእስር ተፈቶ የገደለውን ሰው ደግሞ መግደል ቢቻል ኖሮ አሁንም እንደሚያደርገው ይናገራል። የሚያቀርበው ምክንያት ሟች ያደረገበት የሞራል ጉዳት ነው።
እያንዳንዱ ወንጀለኛ ጀርባ በጥንቃቄ ቢመረመር ወደ ወንጀል የገፋው እውነት ሊኖር እንደሚችል ይታመናል። ስህተትን በስህተት መንገድ ማስተካከል ሆኖ መጠሪያው ወንጀለኛ ሆነ እነጂ። ፍትህ በቀጠነች ጊዜ ፍትህን ፍለጋ የሚኬደው መንገድ ወደ ወንጀል በር ያደርሳል። ፍትህን እንዲያሰፍኑ የሚጠበቁቱ ቸል ባሉ ቁጥር የሚሆነው ፍትህን ፍለጋ በየትኛውም መንገድ ይሄድና ማህበረሰባዊ ምስቅልቅል ውስጥ ይከታል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጥልቅ ፍቅር በሌለበት ስፍራ ጥልቀት ያለው ተስፋ መቁረጥ የለውም ይላል። ከተከዳ ፍቅር ውስጥ የሚወጣ የፍትህ መቅጠን የሚወስደው እርቀት አስከፊ ሆኖ የሚስተዋለው ለዚህ ነው።
ፍትህ በቀጠነች ጊዜ ኢ-ፍትሃዊነት መስፈኑ አይቀሬ ነው። ፍትህ በቀጠነች ጊዜ ፍትህን ፍለጋ በዱር በገደሉ የሚዘምተው በዝቶ ምድር ለመኖር የማትመች ትሆናለች። ፍትህ በቀጠነች ጊዜ ሊለያዩ ፈጽሞውኑ የማይቻሉትን እናትና ልጅን መለያየት ሊመጣ ይችላል። ፍትህ በቀጠነች ጊዜ ሊሆን የተገባው ሳይሆን እንዳይሆን የሚታሰበው አደባባዩን ይቆጣጠረዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሚሆኑት ሀገራዊ የለውጥ ማግስት በከፍተኛ ኢ-ፍትሃዊነት የተሞላ፤ ፍትህ ቀጥና እና ከስታ ለሞት የተዳረገችበት ላይ ደርሳ ሀገር ተራራን በመዞር እንድትሆን ታደረጋለች። አብዮት ያለ ደም አይረጋም ተብሎ ለሀገር በብዙ የደከሙ በቅጽበት ከሞት ጋር እንዲገናኙ ሆነዋል። ተረኛው ወደ ስልጣን ሲመጣ ተመሳሳዩን መንገድ በሌላ ታክቲክ ቀጥሎበታል። የአንድ እናት ልጆች ለፍትህ ቦታን ባለመስጠት ገፊና ተገፊ ሆነው ዓመታትን ይገፋሉ።
ዛሬ በመንደራችን፣ ዛሬ በምንውልበት ቦታ፣ ዛሬ በአምልኮ አካባቢያችን፣ ዛሬ በልቦናችን የውስጠኛው ክፍል ፍትሃዊነት በምን ያህል ከፍታ ላይ ይገኝ ይሆን? ፍትህን የማቅጠኑን ጉዞ የቤት ሠራተኛችንን በምንይዘበት መንገድ እንደሚገለጽ እንረዳስ ይሆን? ፍትህን መልክንና ቁመትን አይተን የምንሰጠው ብያኔ መጨረሻችንን ምን ያደርገው ይሆን? ብለንስ እንጠይቃለን።
ፍትህን ፍለጋ የሚወጡ እነርሱ ፍትህን እንዳትቀጥን ስለማድረጋቸው ማሰብ አለባቸው። ዓመታትን በትምህርት ላይ ያሳለፉ ለሥራ የደረሱ በአቅማቸው ተወዳድረው መቀጠርን ሲያስቡ ያሰቡት እንደማይሆን የሚያደርግ በዝምድና የሆነን አሰራር ሲመለከቱ በልባቸው የሚቋጥሩት ቅሬታ ውሎ አድሮ በዙሪያቸው ያለ ሰው ሁሉ እራስ ወዳድ ሆኖ ይሳልባቸውና ማህበረሰብን ማገለገል ቦታውን እያጣ ይሄዳል።
ፍትህ በአደባባይ ቀጥና በታየች ጊዜ በሂደት ትርጉም እያንዳንዱ ጓዳ የሚደርስ መሆኑን መዘንጋት እንዴት ከባድ ይሆናል? ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማውጣት ሁላችንም በአንድ ልብ ከምንም ልዩነት በላይ ስለ ፍትህ መቆም አለብን። ፍትህን በተገኘንበት የትኛውም ቦታ ላይ ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ አለብን። ፍትህን ከቅጥነት መታደግ አለብን። ፍትህን እንደ መሰረታዊ ለኑሮ አስፈላጊ አቅርቦቶች ለሰው ልጆች ሁሉ የተገባ መሆኑን ማመን አለብን።
ህሊና ታላቁ የፍትህ አደባባይ፣
ሰዎች በስምምነት ከሚቀበሏቸው ነገሮች መካከል አንዱ የህሊናን ዳኝነት ነው። ህሊና በሚል መጠሪያ ስም የሚጠሩ ግለሰቦች ቤተሰቦቻቸው ለምን ይህን ስም እንደሰጧቸው ቢጠይቁ ምናልባት ከፍትህ ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል።
አቅማችን በፈቀደ ለበጎ ብለን አስበን የሰራነው ሥራ በሌሎች ዘንድ ፈጽሞ ባልታሰበ አቅጣጫ ተተርጉሞ ስንመለከት ወደ ህሊናችን ክፍል ዘልቀን እንገባለን። በህሊናችን ክፍል ውስጥ የፍትህ ድምጽ አለ። ወንጀልን ሠርተው በሸንጎ ቀርበው ቅጣታቸውን የተቀበሉ ሰዎች አካላቸው በማረሚያ ቤት ውስጥ ቢገኝም ህሊናቸው ግን በፀፀት አርጩሜ መገረፉ አይቀሬ ነው። ህሊና ታላቁ የፍትህ አደባባይ የሆነውን ለዚህ ነው።
ህሊናው አንዳች ሳይወቅሰው በሰዎች ላይ በደልን የሚፈጥር ሰው፤ ህሊናው አንዳች ሳይወቅሰው ወንጀልን እንደ ውሃ የሚጠጣ ሰው አንዳች የአዕምሮ እክል ውስጥ ያለ ሰው መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ህሊና ታላቁ የፍትህ አደባባይ ነውና ፍትህን ፍለጋ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ከህሊናችን ጋር መምከር መቻል በምንም የማየተካ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ወንጀልን በመሥራት ሥራ ውስጥ በስፋት የሚገኙ ሰዎች በመጠጥ እና በአደንዛዥ እጽ ውስጥ ራሳቸውን ይጨምራሉ። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት የህሊናቸውን ጩኸት ለመደበቅ እንደሆነ አስባለሁ። በጭፈራ ቤቶች ውስጥ ከመጠን በላይ የሚሆነው ጩኸት ጀርባ ለአፍታም ቢሆን ዝም እንዲል የሚፈረድበት ህሊና አለ።
በጤናማው ቦታ ህሊና ድምጽ አላት። ህሊናን አድምጦ የተግባር እርምጃን መራመድ እንዲቻል ለህሊና ድምጽ ቦታን መስጠት ያስችላል። እኔ እዚያ ቦታ ላይ ብሆን ኖሮ የሚለው ጥያቄ ህሊናችን በጤናማነት ምላሽ እንዲሰጥ የሚረዳ ነው።
በትላንትና ውስጥ የሆነውን በምህረት በማለፍ ህሊናን ማስተካከል ጠቃሚ ነው። ምህረትን ማድረግም እንዲሁም ይቅርታን መጠየቅ የህሊናን ጤናማነት ጠብቆ ለመጓዝ ወሳኝ ነው። እውቁ አብርሃም ሊንከን “ምህረት ማድረግ መቻል ከጥብቅ የፍትህ ስርዓት የበለጠውን ፍሬ ሁልጊዜ እንደሚያፈራ አምናለሁ” ይላሉ። ጥፋትን በይቅርታና በምህረት እያከሙ መሄድ አለመቻል ራስን በህሊና ቢስነት ወጥመድ ውስጥ ማግኘት ነው።
ህሊና ቢስ የሚለው ቃል በስድብ ቃላት ውስጥ የሚገኝ ነው። በተጨባጭ ግን ስድብ ሳይሆን እውነታን አመላካች ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ፈጽሞ ህሊና ቢስ ሆነው እራሳቸውን ብቻ ተመልክተው ሌላውን ለመግፋት ወደ ኋላ የማይሉ አሉ። ህሊና ቢስ ሆነው የሌላውን ንብረት የሚዘርፉ። ህሊና ቢስ ሆነው የሌላውን ትዳር ለማፍረስ ፕሮጀክት አድርገው የሚሰሩ። ህሊና ቢስ ሆነው በሥልጣናቸው ፍትህን የሚያዛቡ። ህሊና ቢስ ሆነው የፈጣሪን ቃል ጠምዝዞ ለእራስ አላማ ለማዋል የሚሰሩ ወዘተ አሉ።
ህሊና ቢስነት በምድራችን በሰፊው የሚታይ ቢሆንም ህሊና ቢስነት መንገድ ግን የጥፋት መንገድ መሆኑን መረዳት ይገባል። ህሊና ቢስነትን በመጠጥ ብዛት ማሸነፍ አይቻልም። ህሊና ቢስነትን በአደንዛዥ እጽ ማሸነፍ አይቻልም። ህሊና ቢስነትን በገንዘባችን ብዛት ማሸነፍ አይቻልም። ህሊና ቢስነትን አሸንፎ ጤናማ በሆነ ህሊና ወጥቶ ለመግባት በሌሎች ቦታ ራስን በማስቀመጥ በእኛ ላይ እንዲሆን የማንፈልገውን በሌሎች ላይ እንዳይሆን በማድረግ ነው።
ህሊና ቢስነት ተቆጣጥሮን ስንኖር ዛሬ የከበበን ሁሉ አብሮን እንደሚቆይ የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል። የዛሬ ስልጣን፣ የዛሬ ገንዘብ፣ የዛሬ ዝና፣ የዛሬ ወዘተ አብሮን የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ነው። ሁሉም ከቦታው የሚነሳበት እያንዳንዱ ቀናት ጉዟቸውን ቀይረው በሌሎች የሚተኩበት ወቅት አለ። ጥያቄው ዛሬን ለመኖር ብቻ ህሊናን መጠቀም ሳይሆን ነገን እያሰቡም መመላለስ ነው። ዛሬ የከበበን አብሮን ለሁሌ እንደሚኖር አስበን በሌሎች ጫማ ውስጥ ራሳችንን መጨመር አቅቶን የምንኖረው ኑሮ እርሱ በፀፀት ምዕራፍ ላይ የሚያደርሰን ነው። ዛሬ የነበረን በተበተነ ጊዜ የሚገጥመን ፀፀት ወደ ኋላ ተመልክቶ ከመቆዘም ውጭ ለማስተካከል እድልን የማይሰጥም ሊሆን ይችላል።
የፍትህ ፍለጋውን ጉዞ ከህሊና አሻግረን ስናየው ደግሞ የሁሉ ዳኛ የሆነውን ፈጣሪን እናገኛለን። በሁሉም እምነቶች ውስጥ ማለት እስኪቻል ድረስ የፍትህ ፍለጋው የመጨረሻው መዳረሻ በፈጣሪ ፊት የሚሆነው ዳኝነት ነው። ዛሬን ፍትህን በመፈለግ የምናደርገው ጉዞን ከህሊናችን ባሻገርም አልፈን እያየን በመራመድ እኛ መልካም ለመሆን እንትጋ። ውጤቱም በህሊናችን ክፍል ውስጥ እናገኘዋለን፤ እልፍ ሲል በፈጣሪ ፊት በሚሆነው የፍርድ ሸንጎ።
የታሪካችን መነሻ ያደረግናት ሴት የተፈጥሮ ቅይማትን ትተን በተረዳነው ልክ ለፍትህ እንቁም፤ ልክ እንደምንተነፍሰው አየር።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2013