አንድ ሀገር ለውጭ ሀገራት ከሚሸጠው በላይ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ሲገዛ የንግድ ጉድለት ተከሰተ ይባላል። ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገራት ከምትገዛው በላይ ለመሸጥ የወጪ ንግድ ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ጥረት ብታደርግም ዛሬን ኢኮኖሚዋ በዋናነት የገቢ ንግድ ላይ የተመሰረተ ነው። ከውጭ ወደ ሀገር ለማስገባት የምታወጣው ወጪ፤ ወደ ውጭ በመላክ ከምታገኘው በብዙ እጥፍ ይበልጣል።
ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሀይሎችን ለማበረታታት የሀገሪቱን የገንዘብ የመግዛት አቅምም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ እንዲሄድ ተደርጓል። በደርግ ዘመነ መንግስት አንድ ዶላር በ2 ብር ከሰባ ሳንቲም ይመነዘር ከነበረበት ዛሬ ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ የመጣው የምንዛሪ ተመን ንሮ በባንኮች አንድ ዶላር ከ40 ብር በላይ እየተመነዘረ ነው። በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ተመን ከ50 ብር በላይ ደርሷል።
አሁን የሀገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም የበለጠ እንዲወርድ ግፊት እየተደረገ ነው። ለመሆኑ የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድ ጠቃሚ ወይስ ጎጂ? በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ የብር የመግዛት አቅም መውረድ የራሱ የሆነ ጥቅምና ጉዳት አለው። በገቢ ንግድ ላይ ለተመሰረተው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የብር የመግዛት አቅም መውረድ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲሁም መፍትሄዎችን ጠቁመዋል።
እንደ ዶክተር ሞላ ማብራሪያ፤ የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አንጻር ሲወዳደር ደካማ መሆኑ የራሱ የሆነ ጥቅም እና ጉዳት አለው። ጠቀሜታው በሀገሪቱ ውስጥ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ወደ ውጭ የመላክ ፍላጎት ያላቸው ኢንቨስተሮችን ያበረታታል። በመሆኑም ኢንቨስትመንት እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ሀገራት ሲልኩ በውድ ዋጋ ይሸጣሉ። በመሆኑም ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ያበረታታል ።
በመሆኑም ውጪ ንግድ መሪ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት በተደጋጋሚ የገንዘባቸውን የመግዛት አቅም እየቀነሰ እንዲሄድ እንደሚያደርጉ ያብራራሉ። የገንዘባቸው የመግዛት አቅም የማንሰራራት አዝማሚያ ሲያሳይ መልሰው ወደ ታች እንደሚያወርዱትም ነው የተናገሩት። ይህንን የሚያደርጉት የወጪ ንግዳቸው ከገቢ ንግዳቸው አንጻር በጣም ከፍተኛ ሲሆን ነው።
ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ የምታገኘውን የገቢ መጠን ለማሳደግ የተለያዩ ጥናቶችን ስታደርግ ቆይታለች። በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት ጥረት ተደርጓል። ሆኖም ዛሬም የሀገሪቱ ወጪ ንግድ ከገቢ ንግድ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ስለዚህ የገቢ ንግድ ላይ ጥገኛ ለሆነ ኢኮኖሚ የገንዘብ የመግዛት አቅም እየቀነሰ በሄደ ቁጥር ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በጣም ይጎዳል፤ የህብረተሰቡን ኑሮም ያናጋል። ለአብነት ያህል አሁን አንድ ዶላር በ40 ብር እየተመነዘረ ካለበት ጨምሮ በ60 ብር ይመንዘር ቢባል በሌላ አገላለጽ በአንድ ዶላር የመጣውን እቃ በአሁኑ ወቅት በ40 ብር የሚገዛ ከሆነ በቀጣይ ጊዜያት እስከ 60 በር ከፍ ሊል ይችላል። ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበት ያስከትላል።
መሰል እርምጃዎች በተለይም ቋሚ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በጣም ይጎዳል። በተቃራኒው በወጪ ንግድ ላይ ለተሰማሩት ይጠቅማል። የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከገቢ ንግድ በብዙ እጥፍ የሚያንስ በመሆኑ የምንዛሬ ተመንን አሁን ካለበት ወደ ታች ማውረድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት በገበያ ከሚመራ ከተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይልቅ በብሄራዊ ባንክ የሚወሰን ቋሚ የምንዛሬ ተመን ሲጠቀም መቆየቱን ያብራሩት ዶክተር ሞላ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ተመን እንድትጠቀም ግፊት እየፈጠሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
ተለዋዋጭ የምንዛሬ ተመን መጠቀም ከባድ መዘዝ እንደሚኖረው በመገንዘብ መንግስት ምክረ ሀሳቡን ሳይተገብር ቆይቷል። ነገር ግን መንግስት የብርን የመግዛት አቅም በሂደት ሲያወርደው ነበር። የተወሰነ የመግዛት አቅም በማውረድ ሁኔታዎችን የማየት አቅጣጫ ነው ሲከተል የነበረው።
የንግድ ሚዛን ጉድለት እያስከተለ ያለውን የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድ እና ሌሎች ችግሮችን ለመቋቋም የኢኮኖሚውን መዋቅር ለመቀየር የሚደረግ ጥረት መጠናከር አለበት። ከውጭ የሚገቡትን በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት፣ የወጪ ንግድን በማበረታታት ወጪ ንግድ መር ኢኮኖሚ መገንባት፣ እንዲሁም መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ሲመጣ ቀስ በቀስ ችግሩ እየተፈታ ይሄዳል። ይህ ሲሆን በገበያ የሚመራውን ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሬ ተመንን መጠቀም ይቻላል።
አሁን ባለው ሁኔታ በርካታ ምርት ከውጭ በምናስገባበት ሁኔታ ወደ ተለዋዋጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ ከባድ ነው። ግሽበትን የሚያባብስ ነው የሚሆነው። መንግስት ሙሉ በሙሉ ከመልቀቅ ይልቅ እያስተነፈሰ መቀጠል ነው ያለበት። በማስተንፈስ የውጭ ሀይሎች ግፊትን መቋቋም ይቻላል። ከምንም በላይ ግን የኢኮኖሚ መዋቅሩን ለመቀየር የከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም