የሰው ልጆችን በታማኝነት የምታገለግለውን የቤት እንስሳ በመጠቀም የተዋቀረው ይህ ሕዝባዊ ብሂል እንስሳዋ የምታበረክተውን ግዙፍ አስተዋጽኦ ለማንኳሰስ ታስቦ የተፈጠረ ሳይሆን ለሞራል ትምህርታችን እንዲጠቅምና ምናባዊ አቅሙም ከፍ ማለቱ ከግምት ውስጥ ገብቶ ይሁንታ በማግኘቱ ይመስለኛል። ማንኛውም ሕዝባዊ ብሂልም ሆነ ሥነ ቃል በቤት እንስሳ፣ በዱር አራዊቶች፣ በተፈጥሮ ልዩ ልዩ ክስተቶች፣ በሰው ልጆች፣ በመላዕክትና በጻድቃን ስም እንኳን ሳይቀር በጥበብ ቃላት እየተመሳጠረ መነገሩ ያለና የነበረ የባህሎቻችን አንዱ የጋራ መለያ ነው። ብሂሎቹን ማን? ለምን? በምን ምክንያት? እንዴት? መቼና የት ቦታ ፈጠራቸው የሚሉ መሟገቻዎች በሥነ ቃል ጥናት ሲመዘኑ እጅግም “የባለቤትነት” መብት አያሰጣቸውም። ለምን ቢሉ “የሕዝቡ የጋራ ሃብት ስለሆኑ” መልስ ይሆናል።
ይህንን የአህያይቱን ብሂል ያስታወሰኝ “በዲሞክራቲክ ፓርቲው” የሚመራው የዛሬው የአሜሪካ መንግሥት ሰሞኑን ሀገሬ ላይ ያወጀውና ያጸደቀው “የጉዞ ማዕቀብ” ጉዳይ ግራ አጋቢ ሆኖ እንደ ማንኛውም ዜጋ እንቅልፍ ስለነሳኝ ነው። ብሂሉ ከአህያ ጋር ሊያያዝ ያስፈለገበት ዋነኛ የመነሻ ሃሳብም ይሄው “ታላቋን አሜሪካ” እየመራ ያለው የዲሞክራቲክ ፓርቲው መለያ ምልክቱ አህያ መሆኗ ትዝ ስላለኝም ጭምር ነው።
የአሜሪካው ዴሞክራቲክ ፓርቲ መለያውን “አህያ” አድርጎ መቀበል የጀመረው ፕሬዚዳንት አንድሪው ጃክሰን ለፖለቲካ ቅስቀሳ አህያን በምልክትነት መጠቀም ከጀመሩበት እ.ኤ.አ ከ1828 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ይሄው የፓርቲው ወካይ ምልክት ላለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት ያህል ባለጉዳዮቹ አባላት ሳያፍሩበትና ሳይሸማቀቁበት አክብረውና አሞካሽተው በመቀበል እንደ መለያ አርማ እየተገለገሉበት ስላሉ ጫን ብለን ተምሳሌትነቱን ከእነርሱም ሆነ ከእኛ ዐውድ ጋር እያዋዛን ብንጠቃቅስ ሊያስወቅስም ሆነ ሊያስተቸን የሚገባ አይመስለኝም።
የአህያይቱን ምልክት በማውለብለብ “የንስር ተምሳሌቱን” የአሜሪካንን መንግሥት እየመራ ያለው የጆ. ባይደኑ የዲሞክራቲክ ፓርቲ በምንና ለምን ምክንያት የሀገሬን ሉዓላዊነት ዝቅ አድርጎ ልክ እንደ ተራጋጯ አህያ በውይይትና በማስረጃ መንግሥትን ከመሞገት ይልቅ ክብራችንን በመደፍጠጥ እብሪት የተሞላበት የማዕቀብ ውሳኔ እንዳሳለፈ ከእንቆቅልሽ በላይም ግራ የሚያጋባ ክስተት እንደሆነ ይታመናል። በአህያ ምልክትነት በቅርቡ ምርጫውን አሸንፈው የአሜሪካንን መንበረ ስልጣን የተቆናጠጡትና “ዓለምን ካልመራን ባይ ያኒኪዎቹ የአንክል ሳም (Uncle Sam) ጌቶች” ይህን ውሳኔ ሲያሳልፉ ኢ-ዲሞክራሲያዊ እርምጃ መሆኑ ጠፍቷቸው ነው ተብሎም አይታመንም።
“አህያ የምትሸከመውን አትበላም” እንዲሉ እነርሱ የተሸከሙትና የሚመጻደቁበት ዲሞክራሲ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እየታወቀ በአንድ ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ “የእርጎ ዝንብ” እንዲሉ ጥልቅ ብለው ይህንና ያንን ካላደረጋችሁ “የጉዞ ማዕቀብ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ ሽቀባና ዕቀባ” እንፈጽምባችኋለን ብሎ መወሰን ጭፍን ያለ እብደት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል። “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” ተረት ቢተረትባቸው ቢያንስባቸው እንጂ ይበዛባቸዋል የሚባል አይደለም።
የኢትዮ – አሜሪካ ታሪካዊ ግንኙነትን በጨረፍታ፤
ታላቁ የአሜሪካ ሕዝብና መንግሥት ከሀገሬ ጋር ኦፊሴላዊ ወዳጅነት የመሠረተበትን ዕድሜ ስናሰላ ከአንድ ክፍለ ዘመን ከሩብ በላይ እንዳስቆጠረ የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጡልናል። ስለ እነዚህ ሁለት ሀገራት ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት በርካታ መጻሕፍትንና ሰነዶችን ለዋቢነት ማመሳከር ቢቻልም በግሌ ግን አንድ ለየት ያለ መጽሐፍ ይበልጥ ቀልቤን ይስበዋል። ምናልባትም እንደዚህ መጽሐፍ የሳቡኝ ሌሎች መጻሕፍትን አንብቤም ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።
የመጽሐፉ ርዕስ “ታላቁ ጥቁር፤ ኢትዮ – አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ፤ 2010 ዓ.ም” የሚል ሲሆን ደራሲው ደግሞ ወዳጄና ጓደኛዬ ንጉሤ አየለ ተካ ነው። ይህንን ድንቅ መጽሐፍ በተመለከተ ነዋሪነታቸው በኒውዮርክ ከተማ የሆነው ዶ/ር ግርማ አበበ የተባሉ ጎምቱ ዲፕሎማት የሚከተለውን ግዙፍ እማኝነት ሰጥተዋል “እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያንና የዩናይትድ ስቴትስን ቀደምት ግንኙነት በዚህ ደረጃ አስፍቶና አጥልቆ ያስረዳ መጽሐፍ እስካሁን አላየሁም።”
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር እንደቀረበው የኢትዮ – አሜሪካ ኦፊሴላዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1800ዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ዓመታት ጀምሮ እንደሆነ ማስረጃዎቹ በአግባቡ ተሰድረዋል። “በመንግሥት ደረጃ በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ መሃል ኦፊሴላዊ ግንኙነት እንዲመሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሳብ የቀረበው እ.ኤ.አ በ1846 ዓ.ም ነበር። ከአሜሪካ ታሪክና ዕድሜ አንጻር ይህን መሳዩን የኦፊሴል ግንኙነት ከአንድ አፍሪካዊት ሀገር ጋር ለመፍጠር በዚያ ዘመን መታሰቡ፤ ምናልባትም ቀደም ያለ እርምጃ ነበር ማለት ይቻላል።…ይህንን የግንኙነት ሃሳብ ያቀረበው ኤሮን ኤች ፓልመር (Aaron H. Palmer) የተባለ የዩ. ኤስ አሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ኤጀንሲ ኃላፊ የነበረ ሰው ነው።” (ገጽ 61)።
መነሻውን ከዚህ ታሪካዊ ፈር የሚጀምረው የሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ቅርርብ ወደ እውነታነት የተቃረበው በ26ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና ከፕሬዚዳንቶች ሁሉ ቀድመው የኖቤል ሽልማት አሸናፊ በሆኑት በቴዎዶር ሩዝቬልት ዘመን ነበር። ፕሬዚዳንቱ ሮበርት ሲኪነር የተባሉትን የልዑካን ቡድን መሪ ወደ ኢትዮጵያ ልከው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር ግንኙነቱ ፈር እንዲይዝ አድርገዋል። የምኒልክ ከፍተኛ አድናቂና አክባሪ የነበሩት ሩዝቬልት ለሀገራችንና ለመንግሥታችን የነበራቸው ፍቅር በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጸው እጅግ በሚማርክ አቀራረብ ነው። ግንኙነቱና ከዚያ በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው ቅርርብ ምን ያህል በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሠረተ እንደነበር መጽሐፉን በማንበብ መረዳት ይቻላል።
ይሄው ግኝኙነት ይበልጥ መሠረቱ ሊጠብቅ የቻለው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1947 ዓ.ም አሜሪካንን በኦፊሴል ከጎበኙ በኋላ ነበር። ከዚያ ቀደም ባሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከሚያዝያ 4 ቀን 1943 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ጊዜያት ያህል በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ስር የዘመተው የቃኘው ሻለቃ ጦር የተዋቀረው በአሜሪካ የጦር መሪዎች እዝ ስር ስለነበር የዘማቹ ጦራችን ጀግንነትና አይበገሬነት ከፍተኛ አድናቆት ፈጥሮባቸው ስለነበር በተከታታይ ዓመታት እያደገ ለሄደው ለኢትዮ- አሜሪካ ወዳጅነት ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም።
የአሜሪካ የሰላም ጓድ አባላት (Peace Corps) በብዛት ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ በከተሞች አካባቢ ብቻም ሳይሆን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ጭምር በትምህርትና በእርሻ ዘርፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው በራሱ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን መቀራረብ አመላካች ነበር። አንዳንዶች ይህንን መሰሉን ተልዕኮ በአሉታዊ ዓይን ይመለከቱት እንደነበር መካድ ባይቻልም። በተለያዩ ሰፋፊ የትምህርትና የልማት መስኮች ይተገበሩ የነበሩ መረዳዳቶችና መደጋገፎችም ለወዳጅነቱ መጠናከር የራሳቸውን በጎ አሻራ ማሳረፋቸው አልቀረም።
በርካታ ሚሲዮናዊንና የተራድኦ ድርጀቶች በገፍ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው፣ አንዳንድ የአሜሪካ ተቋማት በሀገራችን ውስጥ ጎልተው መታየታቸው ወዘተ. እና እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ በፖለቲካ ስደተኝነት፣ በትምህርት ፍለጋና በዲቪ ሎተሪ አማካይነት ወደ አሜሪካ የተደረገው የዜጎቻችን ፍልሰትም ሁለቱ ሀገራት ልብ ለልብ ተግባብተው እንዲደጋገፉ ያደረገው አስተዋጽኦ እንዲሁ ሳይጠቀስ አይታለፍም።
በግሌም ቢሆን አሜሪካና አሜሪካዊያንን በተመለከተ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ከተከታተልኩበት የወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) ጀምሮ ከፍተኛ ትምህርቴን ለመከታተል ዕድል ባገኘሁበት አሜሪካ ቆይታዬ ድረስ የአሜሪካ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የበጎነትና የቸርነት ምሳሌ መሆኑን ባልጠቅስ ህሊናዬን ይወቅሰኛል። የአሜሪካ ሕዝብ ያለምንም ማጋነን ደግ፣ ሩህሩህና መልካም ሕዝብ ነው። ሀገሬ በልዩ ልዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ወለድ በሆኑ ችግሮች በተጠቃችባቸው ዓመታትም ፈጥኖ በመድረስ ያደረጉልን ድጋፍና ርህራሄም በፍጹም የሚዘነጋ አይደለም።
መሠረታዊ እውነታው ይህን ይምሰል እንጂ ሥልጣን ላይ የወጣው የአሜሪካ አስተዳደር በሙሉ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን በጎ ይመኝ ነበር ለማለት ግን ያዳግታል። በዘመነ ዚያድ ባሬ የተስፋፊው የሶማሊያ ጦር ሀገራችንን በግፍ በወረረበት ወቅት በጊዜው የነበረው የአሜሪካ አስተዳደር በግዢ የተፈጸመውን የጦር መሣሪያ እንዳናገኝ ክህደት ፈጽሞ ለወራሪው ጠላት እንዳጋለጠን የሚዘነጋ ብቻም ሳይሆን የቅርብ ጊዜ መራራ ትዝታችን ጭምር ነው።
የአሜሪካ አመራር በሉዓላዊ ሀገራት ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና የሴራ ጉንጎና በማድረግ ምን ያህሉን ሕዝብ ለመከራ እንደዳረገ ብዙ ማጣቀሻዎችን ማስታወስ ይቻላል። በቬትናም፣ በኩባ፣ በሰሜን ኮሪያ፣ በኢራቅ፣ በሊቢያ፣ በሶማሊያ፣ በሶሪያና በየመን ወዘተ. ሉዓላዊ ሀገራት ውስጥ እጁን በማስገባት የፈጸማቸው የጥፋትና የውድመት ክፋቶች በዓለም ታሪክ ጥቋቁር መዛግብት ውስጥ በየጊዜው እየተመዘገቡ ለትውልድ እንዲተላለፉ እየተደረገ ነው።
አልፎም ተርፎ በጥቃቅን ጉዳዮች ውስጥ ሳይቀር እጁን እያራዘመ ሲፈጽማቸው የኖረው ሸርና ተንኮል ይዘርዘሩ ቢባል የጋዜጣውን ገጽ ያጣብቡ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ምራቁን የዋጠ ዜጋ ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም። ይህ ጸሐፊ በኮሚቴ አባልነት ያገለግለበት የነበረውን የአሜሪካ ተማሪዎች ማኅበር እንደምን በረቀቀ ስልት እንዲኮላሽ አድርገው እንዳፈራረሱት ሳስብ እያሳቀ ያስገርመኛል። ለምን ምሁራኑ ተሰባስበው ስለ ሀገራቸው ይመክራሉ በሚል ቅንነት በጎደለው ሴራ አንድን ተራ ማኅበር በተልእኮ አስፈጻሚዎቻቸው አማካይነት እንዲፈራርስ ማስደረግ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ለመረዳት ይከብዳል። ያ ማኅበር ዛሬ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ጥቂትም ቢሆን አንዳች ቁም ነገር በፈጸመ ነበር እያልኩ አስባለሁ።
በሀገሬ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና በኤርትራ መንግሥትም ላይ ሳይቀር ኢፍትሐዊ የሆነ “የጉዞ ማዕቀብ” ያሳለፈው “የአህያ ምልክት ባለቤቱ የዲሞክራሲ ፓርቲው ሹማምንት” ነገ ተነገ ወዲያ በታሪክ ፊት ተዋርደው እንደሚቀሉ አልተረዱትም ለማለት ያዳግታል። አንድ ታላቅ ሀገር የሚመራ መንግሥት በሌላው ሀገር ጣልቃ ገብቶ “ይህንን አድርግ፤ ያንን አታድርግ” ብሎ ለማዘዝና እጅ ለመጠምዘዝ ስልጣኑን ማን ሰጠው? እርግጥ ነው የተጣሱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሲስተዋሉ ሀገራት የተፈራረሙትን ቃል ኪዳን እየጠቀሱ መተራረምና የጋራ ሕጉ የሚፈቅደውን ውሳኔ ማሳለፍ ይቻላል። ነገር ግን ለህሊናም ሆነ ፊርማቸውን ካኖሩበት ዓለማቀፋዊ ኮንቬንሽኖች ጋር በሚቃረን ሁኔታ እንዴት በአንድ ሉዓላዊት ሀገር ላይ በተጨፈነ ዓይን ውሳኔ ይተላለፋል።
“የዲያቢሎስ ውላጅ” ከነበረው፣ ከሞተውና በስብሶ ከተቀበረው አሸባሪ የወያኔ ርዝራዦች ጋር እንደምንስ ሀገራዊ መግባባት ሊፈጠር ይችላል? የሀገራዊ ምርጫውን አካሄድ በተመለከተስ “እንዲህና እንደዚያ አድርጉ” የማለቱን መብት ማን ሰጣቸው? ያለምንም ማጋነን አሜሪካ እየፈጸመችብን ላለው ሴራና ተንኮል ታሪክ ብቻም ሳይሆን የራሷ ሀገር ዜጎች ሳይቀሩ እውነቱን የተረዱ ዕለት አደባባይ ወጥተው መንግሥታቸውን እንደሚያወግዙ ጥርጥር አይገባንም።
“ያስጨነቅኸን ለመልካም ሆነልን” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፤ ኢትዮጵያና እኛ ኢትዮጵያዊያን በዘመናት ውስጥ በመከራ ተሞርደንና እንደ ወርቅ ነጥረን የምናልፍ ስለሆነ ችግሮችን ተጋፍጦ መራመዱ ለእኛ ብርቃችን አይደለም። የእውነት አምላክም እየረዳን ክፉ ዓመታትን መሻገር ተለማምደናል። ይብላኝ በዲሞክራሲ ስም የግፍ ዋንጫ እየተጎነጩ በንፁሐን የዓለም ዜጎች ላይ የመከራ ዶፍ ለሚያዘንቡት። ይብላኝ በአላፊ ጠፊ የዳረጎት ጉርሻ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን ለመሸጥ ገበያ መሃል ለሚንቀዋለሉ ባንዳዎች። ኢትዮጵያዊነት እነርሱ እንደተሸመኑበት ስሪት “Melting Pot” ይሉት ዓይነት ባህርይ የለውም። ኢትዮጵያዊነት የሚመዘነው በአልማዝ ባህርያትና ካራት ምሳሌነት ነው። “ለአህያ ማር አይጥማትም” ብሂል ተጠናውቷቸው እንጂ ሀገሬ የጀመረችው አበረታች የልማት ጅምሮች፣ የዲሞክራሲ ዳዴያችንና ራሳችንን ለመቻል የምናደርገው መፍጨርጨር ባስደሰታቸው ነበር።
ጠላቶቻችንን እንቅልፍ የነሳቸው የታላቁ ህዳሴ ግድባችን ህልም የሚፈታው በቅርቡ መሆኑ ቢገባቸውም አላስደሰታቸውም። በሩቅና በቅርቡ ያሉት ታሪካዊ ጠላቶቻችን የተሸነፍን መስሏቸው ለመሳቅ ጥርሳቸውን ቢያገጡም ነገ ስኬታችን እውን ሲሆን የእንባ መዋጮ እየተበዳደሩም ቢሆን ማልቀሳቸው አይቀርም። መንግሥታችንም ቢሆን ከውጭና ከውስጥ ዲፕሎማሲ ጥረቱ እንዳይዘነጋ፣ ዛሬም ሆነ ወደፊት እንተገብረዋለን ለሚሉት “የማዕቀብ ጋጋታ” እንደማይበገር ጽናቱን ማረጋገጥ አለበት። ውጭ ውጭውን ብቻም ሳይሆን ይህንን የሰሞኑን ውዥንብር እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር በኢኮኖሚውና በገበያ ሥርዓቱ ላይ “ሳቦታጅ” የሚሰሩ እኩይ የገበያ ተዋናዮችና የፖለቲካ ምንዱባን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ እንደ ዜጋ ምክራችንን እንለግሳለን። በተለይም የሀገሪቱ ውስን ሀብት በአስረሽ ምቺው ስብሰባና የውሎ አበል እንዳይባክንም ቁጥጥሩ ሊጠብቅ ይገባዋል ባይ ነን። “መከራና ጉም እያደር መቅለሉ አይቀርም” – ሰላም ይሁን።
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም