በህዝብ እንደራሴዎች አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለመታደግ በማሰብ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችው ማዕቀብ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ጥቅም የሚሳጣት ስለመሆኑ ይናገራሉ። ኢትዮጵያን ሳትይዝ በቀይ ባህር አካባቢ ስኬታማ የመሆን ዕድል የላትም። አሁን ያለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ በደላሎችና ግለሰቦች በህወሓት ቡድን ላይ የተመሰረተ ነው። አሁን ያሉት ግለሰቦች የአሜሪካን ጥቅም ወደ ጎን ትተው እየሄዱ ነው። ግንኙነቱ መሻከሩ የሚጎዳ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅምና ሉዓላዊነት አይበልጥም። ህሊና ካላቸውና ለሰብዓዊነት የሚቆረቆሩ ከሆነ ህወሓት በማይካድራ ያካሄደው ጭፍጨፋ በቂ ነው ይላሉ። ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ያወረደ እንደሆንም ይገልፃሉ።
ኢትዮጵያ በቀጠናውም ሆነ በቀይ ባህር አካባቢ ያላት አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነ ይጠቁማሉ። በተፈጥሮ ሃብት ያላት ሚናም ትልቅ ነው። ኢትዮጵያ ከማህፀኗ የሚወጡ 12 ወንዞችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ትልካለች። ሸበሌ ወንዝ ወደ ሶማሊያ፣ ኦሞ ወንዝ ወደ ኬኒያ፣ ገናሌ ወንዝ ወደ ኬኒያ እና ሶማሊያ፣ ዓባይ ወንዝ ደግሞ በርካታ ሀገራትን እየነካካ የሚያልፍ መሆኑ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። በዓለም ረጅም ወንዝ ባለቤት መሆኗ በድፕሎማሲው ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ትኩሳት የሚሰጣት ሀገር መሆኗን ይናገራሉ። እነዚህን የተፈጥሮ ሃብቶችን ደግሞ ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ዓላማ መጠቀም የሚቻል ነው። የዚሁ ትኩሳት የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዳሴ በእጅ አዙር ለማዕቀብ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ በዘለለ ግን ማዕቀቡ ለኢትዮጵያ የማንቂያ ደወል እንደሆነና ዲፕሎማሲውን መፈተሽ ብዙ ሥራ መስራት እንደሚገባም አመላካች መሆኑን ይገልጻሉ የዛሬው የወቅታዊ አምድ እንግዳችን።
እንግዳችን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የትምህርት ቤቱ ኃላፊ የሆኑት አቶ እንዳለ ንጉሴ አማን ናቸው። አቶ እንዳለ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ ከላይ ለተነሱና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች የሰጡትን ሙያዊ ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን አሜሪካ ያደረገችው የቪዛ እገዳ መንስኤ ምንድነው ይላሉ?
አቶ እንዳለ፡- መጀመሪያ የኢትዮጵያ ሁኔታ መቃኘት አለብን። ኢትዮጵያ ረጅም የመንግስት ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ከእነ ግብፅም የቀደመ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በዲፕሎማሲም ረገድም ጥሩ ልምድና ታሪክ አለን። ከአክሱም ዘመነ መንግስት በፊትም ሆነ በአክሱም ዘመነ መንግስት፣ በመካከለኛው ዘመን ብሎም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ቅኝ ግዛት በተጧጧፈበት ወቅትም ኢትዮጵያ በራሷ ጉዳይ ካልሆነ በሌሎች ጣልቃ ገብታ አታውቅም። ቅድሚያ የምትሰጠው ለዲፕሎማሲ ነው። ለዚህ ሁሉ ሺህ ዓመታት የኖረችው የኢትዮጵያ ህዝብ በነፃነቱ ተደራድሮ ስለማያውቅ ነው። ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ፈተና ገጥሟት አያውቅም ማለት አይደለም።
ኢትዮጵያ ካላት ሃብትና የተፈጥሮ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተነሳ በርካታ ሀገራት በጋራ የመሥራት ፍላጎት አላቸው። ይህም ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። ሀገራት ይህን የሚያደርጉት ብሄራዊ ጥቅማቸውን በማሰብ ነው። በዚህ ሂደት ብዙ መጥተዋል፤ ብዙ ሄደዋል፤ ኢትዮጵያውያን ግን በብሄራዊ ጥቅማቸው ተደራድረው አያውቁም። ይህ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። የቅርብ ጊዜውን ብናነሳ እንኳን ግብፆች የዓባይን ውሃ መነሻ ለምን አንይዘውም ብለው በ1875 እና በ1876 በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ከፍተው አልሳካ ብሏቸው ተመልሰዋል። ዓድዋ ጦርነትንም ብንመለከት ከአፍሪካ ተመርጣ ቅድሚያ መያዝ አለባት ተብሎ ነበር። ግን ኢትዮጵውያንን ማንበርከክ አልተሳካም። የሱማሊያው መሪ ዚያድ ባሬ ለወረራ ወደ ኢትዮጵያም የመጣው ከዚህ የተነሳ ነው። ‹‹የቅኝ አስተሳሳብ ያላቸው በኢትዮጵያ ላይ ጥርስ ይነክሱባታል፤ ሌሎች ደግሞ እንደ ሞዴል ይቆጥሯታል።›› ስለዚህ በዲፕሎማሲ ሁሉን ይዛ ነው የምትሄደው። ኢትዮጵያ በሂደት እንድትዳከም የሚፈልጉና እንድትበታተን የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ የኢትዮጵያን መጠናከር በእጅጉ የሚሹ ሀገራት አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን ማዳከም ለምን አስፈለገ?
አቶ እንዳለ፡- የመጀመሪያው ምክንያት ለጥቁሮችና ለዓረቡ የነጻነት ተምሳሌት ናት። ኢትዮጵያ ስለ ነጻነት ቀን አታወራም፤ ስለ ድል ቀን እንጂ። ይህ በራሱ የሚሰጠው ትርጉም አለ። በዚህም በማንኛውም ጉዳይ የመወሰን ነፃነት አለን። ግብፅ እና ሱዳንን ጨምሮ በርካታ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ ሀገራት በራሳቸው ሀገር ፖሊሲና ጉዳይ ጭምር መወሰን አይችሉም። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በነፃነት የምትወስን ሀገር ናት። ግብጽና ሱዳን የመሳሰሉት ግን የማንነት ቀውስም አለባቸው።
ሁለተኛው ኢትዮጵያ አቀማመጧ ለቀጠናው ፖለቲካ በጣም ወሳኝ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ አራቱ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ሀገራት ተብለው የሚታወቁ ናቸው። ይህ ቀጠና ቀይ ባህር ጋር ያገናኛል። ኢትዮጵያ ደግሞ የቀጠናው ዕምብርት ናት። ይህ አካባቢ ደግሞ ከህንድ ውቅያኖስና ቀይ ባህር ጋር ይገናኛል። በሌላ እይታ ቀይ ባህር ደግሞ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና ኤዥያን አህጉራት ያገናኛል። በዚህ ላይ ትልቅ የንግድ አካባቢ ሲሆን የበላይነትን ማሳያ ትልቁ ቀጠና ነው። ስለዚህ ዛሬም ሆነ ነገ በዚህ ቀጠና ኢትዮጵያን ሳይዙ መጓዝ ትርፋማ አያደርጋቸውም። ሀገራትም ኢትዮጵያን የሚጠጉትም ለብሄራዊ ጥቅማቸው ነው፤ በመሆኑም ኢትዮጵያን መያዝ ብሄራዊ ጥቅማቸውን ትርፋማ ማድረግ ነው።
ሦስተኛው በኢትዮጵያ የሚኖሩ ህብረተሰቦች ተመልሰው በእነዚህ ወሳኝ በሚባሉ የቀጠናው ሀገራት የሚኖሩ ህብረተሰብ ክፍሎች ቋንቋ ተናግረው ባህል ተላብሰው የሚኖሩና ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው። ይህም ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው ጥሩም ይሁን መጥፎ ክስተት በእነዚህ ሀገራት ላይ ሚናው የጎላ ነው።
አራተኛው ኢትዮጵያ ያላት ተፈጥሮ ሃብት፣ የመልክዓ ምድር ስፋትና የህዝብ ብዛት ሀገራት ትኩረታቸውን እንዲጥሉባት አድርጓል። የኢትዮጵያ አየር ፀባይና የአየር ንብረት ባህሪ በሌሎቹ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። ህዝብም ትልቅ ሃብት ነው፤ በተለይ ደግሞ በነፃነት የኖረ የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም ወሳኝ ነው።
በተፈጥሮ ሃብት ያላት ሚናም ትልቅ ነው። ኢትዮጵያ ከማህፀኗ የሚወጡ 12 ወንዞችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ትልካለች። ሸበሌ ወንዝ ወደ ሶማሊያ፣ ኦሞ ወንዝ ወደ ኬኒያ፣ ገናሌ ወንዝ ወደ ኬኒያ እና ሶማሊያ፣ ዓባይ ወንዝ ደግሞ በርካታ ሀገራትን እየነካካ የሚያልፍ መሆኑ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። በዓለም ረጅም ወንዝ ባለቤትም ናት። እነዚህን የተፈጥሮ ሃብቶችን ደግሞ ለጥሩም ሆኖ መጥፎ ዓላማ መጠቀም የሚቻል ነው። በቀጠናው ያሉ ህዝቦች ባህልና ቋንቋ ተመሳሳይነት አላቸው። ሀገራትም ይህን ማወቅ አለባቸው፤ ለዚህም ከኢትዮጵያ ጋር መስራት አለባቸው። በእርግጥ ኢትዮጵያ መሰል ችግር ሲገጥማት የመጀመሪያዋ አይደለም።
አሁንም በኢትዮጵያ ላይ ደባ እየሰሩ ያሉት ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በምትገባበት ጊዜ በተቃራኒ የሚቆሙ ስለመሆናቸውና በቁርጥ ቀን ኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው እንደማያውቁ ታሪክ ምስክር ነው። በዓድዋ ጦርነትም ሆነ ጣሊያን ዳግም ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ ቆመዋል። ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ ነበሩ።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካንዚምና የነጻነታቸው ምልክት ናት። 20 የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማቸው ከኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለም የተቀዱ ናቸው። ዓድዋን ያላሰበ ነፃነት የለም። ላለፉት 40 ዓመታት ለኢትዮጵያ አጀንዳ እየሰጡና ለማዳከም ሲሠሩ ቆይተዋል። የእነርሱ ምሁራንና ሚዲያዎቻቸውም ኢትዮጵያን በመከፋፈል ላይ የተጠመዱ ናቸው። በተለይ በብሄር እና ሃይማኖት መልክ መከፋፈሉን በጣም ሲሰሩ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ነፃነት ለቀኝ ገዥዎች ጥሩ ስሜት አይሰጣቸውም። ፖሊሲ በነፃነት በማውጣት ኢትዮጵያ ምሳሌ ናት። ኢትዮጵያን ለማዳከም ደግሞ በአምሳላቸውና በዓላማቸው ልክ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የሚባል ቡድን መስርተው ነበር። የዚህ ቡድን አዕምሮ የተቀረፀው ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም።
ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጦርነቱን ሲጀምር የምዕራባውያንን ድጋፍ ተማምኖ ነው። በዓለም ታሪክ የሀገሩን መከላከያ ሠራዊት የወጋ የለም። በኢትዮጵያ ባለፉት 4000 ዓመታት ይህን መሰል ታሪክ ሆኖ አያውቅም። በጦርነቱ መከላከያ ብቻ አይደለም የተመታው ኢትዮጵያውያን ህልውና እና ሉዓላዊነት ነበር። ግን ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን በደማቅ ቀለም ጽፈውታል። ቀደም ሲል የህወሓት ቡድን እጅግ ዘግናኝ ጥፋት ሲፈፅም ምዕራባውያን ማዕቀብ መጣል ቀርቶ የባሰውን የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። ይህም የሚያሳየው የእነርሱን ዓላማ የሚያሳካ ከሆነ አንዳችም ነገር ማድረግ አይፈልጉም። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ስላልተስማማቸው እንደ ሽንፈት በመቁጠራቸው በጊዜ ማዳከም ያስባሉ። ለዚህም አሁን ማዕቀብ መጣል ጀምረዋል። ለውጡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ዋጋ ከፍለው ያመጡት ለውጥ መሆኑን እውቅና መስጠት አይፈልጉም።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪ ብሎ ከተፈረጀ ቡድን ጋር ተደራደሩ የሚለውን ሃሳብ ለምን ማንሳት ፈለጉ?
አቶ እንዳለ፡- የአፍሪካ ቀንድ ወሳኝ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። ለውጡ ወደፊት እንዲሄድ አይፈልጉም። ይህ ለውጥ በቀጠናው እና በአፍሪካ እንደ አህጉር ለውጥ እንደሚያመጣ ያውቃሉ። ሱዳንን ጨምሮ የቀጠናው ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ፈልገዋል። ግን በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መሰረት ከፋፍሎ መግዛትና በሚዲያዎቻቸው የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ መከፋፈል ነው። በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ እንኳን ሚዲያዎቻቸው ነገሮችን በእጅጉ አጣመው ሲያቀርቡ ነበር።
ከኤርትራ ጋር የፈጠርነው መልካም ጉርብትና እና ትብብርም ምዕራባውያን ፈፅሞ መፍቀድ አይፈልጉም። ለራሳቸው ጥቅምና ለረጅም ጊዜ ግጭት መንገድ ሲያመቻቹ ነበር። ዓላማቸው በመከፋፈል ጥቅማቸውን ማስከበር ነው። ከዚህ በዘለለ ዓላማቸውን የሚያሳካውን ህወሓት ቡድን ወደ ስልጣን መመለስ ነው። ይህ ቀጠና ከተረጋጋ የጦር መሳሪያ መሸጥ አይችሉም። በመሆኑም ከፋፍሎ መግዛትና በውሸት ግጭት ማጋጋል ነው ፍላጎታቸው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
በሰሜኑ የህግ ማስከበር ዘመቻ አካባቢውን በማረጋጋትና ብቸኛውና እርዳታ በመስጠት 70 ከመቶ የሚሆነው የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት ነው። ግን በእርዳታ ስም እነርሱ ህወሓትን መታደግ ፈልገዋል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ለማዳከም የሚሄዱበት መንገድ እንዲሳካ ቡድኑን ለመታደግ ለፍተዋል።
የህወሓት ጁንታ ቡድን ኢትዮጵያ እና ኤርትራን በማጋጨት የምዕራባውያንን ጥቅም ያስከብር ስለነበር ባለውለታቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሰሜን ዕዝ ላይ ለተጀመረው ጦርነት ከህወሓት በስተጀርባ የምዕራባውያን ድጋፍ ይኖር ይሆን?
አቶ እንዳለ፡- በደንብ እንጂ! የህወሓት ቡድን ጦርነቱን ሲከፍት በቂ ማስረጃ አላቸው። በወቅቱ የአሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ተወካይና በአምባሳደሩ በኩል መግለጫ ሲሰጡ ህወሓት ስህተት ሰርቷል ብለው ነበር። የነጭ ወራሪ ጦርን አሸንፎ በሽንፈት የሸኘን የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ከህወሓት ቡድን ጋር በማነፃፀር ትንሽ ሊያደርጉት ይፈልጋሉ። ይህ ቡድን ከሀገር መከላከያ ጋር ለአንድ ሰዓትም መዋጋት አልነበረበትም። ይህን እኩይ ቡድን ለዚህ ያበቁት እኮ እራሳቸው ናቸው። በገንዘብም በስትራቴጂም እጃቸው አለበት። ወልደው ያሳደጉት በስትራቴጂ የደገፉት ምዕራባውያን ናቸው። ከኤርትራ ጋር የነበረን ሠላማዊ ግንኙነት ዓለምን ያስደመመ ነበር። ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ያላቸው ይህን መቀበል አልፈለጉም።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ደረጃ የኢትዮ-ኤርትራ ወዳጅነት የሚያንገበግባቸው ከሆነ ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በስተጀርባ የምዕራባውያን እጅ ነበረበት ማለት ነው?
አቶ እንዳለ፡- እንዴት አይኖርም? እነርሱ እኮ የሚያካሂዱት የእጅ አዙር ጦርነት ነው። ሁለቱ ሀገራት ምን የሚያጣላቸው ነገር ነበር። ጦርነቱ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ድንበር ተወረረ ብለው ነበር። ግን ስህተት ነበር። በወቅቱ ድንበር አልነበረም። ድንበር የተበጀውና የተፈረመው ከአልጀርሱ ስምምነት በኋላ ነው። ይህ ደግሞ የፈረሙት አቶ መለስ ናቸው። በወቅቱ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ወደብ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋል ብለው ሲሞግቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ወደብ አያስፈልገንም ነው ያሉት። ይህ በዓለም ታሪክ ሆኖ አያውቅም።
ጦርነቱ በሁለቱም በኩል ትልቅ ጉዳት አድርሷል። በሠላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻለውን ነው ወደ ጦርነት የተገባው። በዚህ ቀጠና ብዙ ነገር ነው ያደረጉት። የደከመ ሀገር ሃብቱን መጠቀም አይችልም። ለዚህም እነርሱ በመካከላችን ችግር ፈጥረው ለራሳቸው መጠቀም ይፈልጋሉ። ማዕቀቡን ስንመለከት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የአሜሪካ ግዛት እስከሚመስሉ ድረስ ነው የተወሰነው። በተባበሩት መንግስታት ቻርተርም መሰረት ሀገራት ሉዓላዊ ናቸው፤ በውስጥና በውጭ ጉዳያቸው የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው ይላል። ግን ይህ ማዕቀብ ከዚህ በተቃራኒው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወዳጅነት መጠናከር በሂደት ወደ መዋሃድ ይሄዳሉ ብለው ያሰጋቸዋል ማለት ነው?
አቶ እንዳለ፡- ይህን ማቆም አይቻልም! እንደሚሆን ይገምታሉ። ሁለቱም ሀገራት ከችግራቸው ተምረዋል። ያ! ሁሉ ወታደርና የጦር መሣሪያ ድንበር ላይ ተከማችቶ ለ20 ዓመት እንደዚያ ሲሆን በጭካኔ ዝም ብለዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ለዚያ ችግር መፍትሄ ላመጡት መንግስታትና እና ህወሓትን ያስወገደ መንግስት ሽልማትና ድጋሜ ድጋፍ ይገባቸው ነበር፤ ግን የሆነው በተቃራኒው ነው። ህወሓት ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለአሜሪካም ቢሆን አይጠቅምም ነበር። አሜሪካውያን 176 ዓመት ቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ችግሩን ያውቁታል። ህወሓት ደግሞ ቅኝ ግዛት ስሜት ውስጥ የነበረ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን በሚታሰብበት ጊዜ እና ግብፅ ከፍተኛ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ላይ ባለችበት ወቅት ማዕቀቡን መጣል እሳቤው ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፡- የህዳሴ ግድብን በተመለከተም እኛ በጋራ እንጠቀም ብለን ነው የተነሳነው። የራሷን ሃብት በጋራ እንጠቀም ስትል ኢትዮጵያ በዓለም የመጀመሪያዋ ሀገር ናት። ግብጽ ምንም አስተዋፅኦ የላትም ግን ትልቁን ከዓባይ ውሃ የምትጠቀም ናት። ሱዳንም በተመሣሣይ ብዙ ድርሻ የላትም። አሜሪካ፣ ፈረንሳይ ወይንም ኢንግሊዝ በኢትዮጵያ ቦታ ቢሆኑ ጠብታ ውሃ አያስነኩም። ኢትዮጵያ ግን አሁንም ቢሆን በዲፕሎማሲው ነው እየሄደች ያለው።
ማዕቀብ መጣል ካስፈላገ በየቀኑ በሺዎች የሚገደልባት ግብፅ አለች። አንድም ጊዜ የመረጡት መንግስት አላስተዳደራቸውም እስካሁን በወታደር ነው የሚተዳደሩት። በዓለም ትልቁ እስር ቤት ያለበት ሀገር ነው። በሱዳንም በተመሳሳይ ዴሞክራሲ የሌላበት ሀገር ናት። ሱዳን በግብፅ እየተመራች የኢትዮጵያን መሬት ወራለች። አሜሪካ ገለልተኛ እና በዓለም አቀፍ ህግ የምትመራ ብትሆን በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ገብታ ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት ለቃ እንድትወጣ ትናገር ነበር። ወይንም በሠላማዊ መንገድ ለማደራደር ጥረት ታደርግ ነበር። ሱዳን ሁለት ትልቅ ግዛቶቿን በግብጽ ተቀምታለች ግን ስለዚያ አታነሳም። አስዋን ግድብ 25 በመቶ ያረፈው በሱዳን መሬት ላይ ሲሆን ኑቢያ የሚባል ህዝብን ያጠፋ ነው። በዚህ ላይ ምንም አይሉም።
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያን እና አሜሪካ ለምን በዚህ ደረጃ ለግብፅና ሱዳን ለመወገን ተገደዱ?
አቶ እንዳለ፡- ምዕራባውያን ኢትዮጵያን የጠየቁት ሁሉ ምላሽ አግኝቷል። ያልተመለሰ ነገር የለም። ይህ በጣም ነው ያናደዳቸው። በእነርሱ ፍላጎት ጦርነቱ እንዲራዘምና እንደፈለጉት ሊፈተፍቱ ነበር፤ ግን ሊሆን አልቻለም። የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ እና በቀይ ባህር ከፍተኛ የስትራቴጂ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ግድቡን ህወሓት ጀምሮት ነበር፤ ግን እንደማይጨርሰው ያውቃል። እነርሱም እንደማይጨርሰው ስለሚያውቁትም አልተቆጡም ነበር። ግን ለውጡ ከመጣ በኋላና ችግሮች መፍትሄ ሲያገኙ በእጅጉ ተቆጡ።
ዓለምን ሲዞር የነበረው ዲፕሎማሲ ወደ አፍሪካ መምጣት ለኢትዮጵያ ድል ነው። የመጀመሪያው የውሃ ሙሌትም ተከናወነ። ሦስቱ ሀገራት እ.ኤ.አ 2015 በተደረገው ሥምምነት መሰረት ግብፅና ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብት እንዳላት ያመነችበት ወቅት ነው። ግብጽ ስለ ስምምነት ብታወራም እንዲተገበር አትፈልግም። ሁለተኛው ዙር ከሞላ እያንዳንዱ የዓለም ሀገራት ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያዞራሉ። ሱዳንም ለራሷ ጥቅም ስትል ወደ ኢትዮጵያ መመለሷ አይቀርም።
አሁን ምዕራባውያን የሚሰጉት ኢትዮጵያ የበላይ እንዳትሆን ነው። እነርሱ በቀኝ ግዛት መንፈስ የቀረጿቸው ሱዳንና ግብፅ መሰል ሀገራት እንጂ በራሳቸው መንገድ እና ነፃነት የምትንቀሳቀስና የምትወስን ኢትዮጵያን ማየት አይፈልጉም። በሀገር ውስጥም በጣም ተወጥሮ የነበረው ዘረኝነትና የዘውጌ ፖለቲካ መስመር እየያዘና ሚዛናዊ አካሄድን የምትከተል ኢትዮጵያ እየተፈጠረች በመሆኑ ዓላማቸውን ለማሳካት ስለማይበጃቸውና ኢትዮጵያን የሚመጥን ፖለቲካ እየተመሰረተ በመሆኑ አልፈለጉትም። ህወሓት 86 ከመቶ የሀገሪቱን የጦር መሣሪያ ይዞ በመሸነፉ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑት በሙሉ በጣም ተናደዋል።
ግብፅ ብዙ መልዕክተኞች ወደ አዲስ አበባ ልካ ነበር። ሁሉም ተመሳሳይ አቋም ይዘው የነበረ ሲሆን ግፊታቸው ኢትዮጵያ የተሳሳተ ውሳኔ እንድትወስን ነበር። ግን አሁን ያለው የለውጥ ቡድኑ ይህን አልተቀበለም። አሜሪካን ጨምሮ የህወሓት ቡድን በመሸነፉ አዝነዋል። አዲስ አበባ ጥሩ ነገር ተናግረው እዚያ ሲሄዱ ህወሓትን ወክለው ይናገራሉ። አሜሪካም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ላይ ተይ ይቅርብሽ ብላ ነበር። ግን ሕወሓትን የሚመስል መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖሩ ዓላማቸውን ማሳካት አልቻሉም።
አዲስ ዘመን፡- የቻይና እና ኢትዮጵያ ወዳጅነት አሜሪካ ለዚህ ማዕቀብ ያነሳሳት ሌላኛው ምክንያት እንደሚሆን የሚገምቱ አሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ እንዳለ፡- ዋናው በለውጡ ምክንያት ነው። ደካማ መንግስት መመስረት ፈልገው አልተሳካለቸውም። የህዳሴን ግድብ ጨምሮ ፍላጎታቸው ግብ አልመታም። አሁን ባለው የኃይል አሰላለፍ አሜሪካ በወጉ ቦታዋን አላወቀችም እየተወዛገበች ነው። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የአሜሪካ የበላይነት በብዙ መንገዶች ይታይ ነበር። በቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ወቅትም ራሺያ እና አሜሪካ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ይወስኑ ነበር። የቀዝቃዛው ጦርነት ጋብ ሲል ራሺያ ደከም ስትል ለተወሰነ ጊዜ ዓለምን ስትመራ የነበረችው አሜሪካ ናት። ከዚያ ራሺያ፣ ቱርክ፣ ህንድ እና ቻይና እየተጠናከሩ ሲመጡ አሜሪካ የመወሰን አቅሟን እየተፈታተነው ነው። ታዲያ ይህን ጊዜ አሜሪካ ወደ ውስጧ ማየት ነበረባት።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካውያን ለኢኮኖሚ ዕድገታቸውና ዲፕሎማሲ ቻይና፣ ቱርክና ሌሎች ሀገራት ሲጠጉ ለውጥን ማየት ይቻላል። አሜሪካ እና ምዕራባውያን ግን በእርዳታ አደንዝዘው መቀጠል ይፈልጋሉ። በዚህም የኃይል አሰላለፍና ጎራው ወደ ሌላ እያጋደለ ነው። ፕሮጀክቶች ቢኖራቸው እንኳ መልሰው በእጅ አዙር ይወስዱታል።
አዲስ ዘመን፡- ምዕራባውያንና አሜሪካ በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶቻቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ማብዛታቸው ማንን ለማገዝ ነው?
አቶ እንዳለ፡- ይህ ዋና ዓላማው ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን ለመጫን ነው። አንድነትን ማዳከም፣ የማህበራዊና የፖለቲካ መዋቅርን ማፍረስ ያነገቡ ናቸው። በዚያ በኩል የሚመጡ ዕርዳታዎችም ከእነርሱ ጥቅም አኳያ የተቃኙ ናቸው። የእነርሱ ዕርዳታ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም። ሌላው ቀርቶ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለመገንባት የታሰበው በአፄ ኃይለስላሴ አስተዳደር ዘመን ነበር ግን ማሳካት አልተቻለም።
እነርሱ የሚያግዙት በቀኝ ግዛት የሚያሽከረክሯቸውን እንደግብፅ የመሰሉ ሀገራትን ነው። በመሆኑም አሁን የተጣለው ማዕቀብ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አሜሪካን ይጎዳል። ኢትዮጵያን ሳትይዝ በቀይ ባህር አካባቢ ስኬታማ የመሆን ዕድል የላትም። አሁን ያለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ በደላሎች ግለሰቦችና በህወሓት ቡድን ላይ የተመሰረተ ነበር። አሁን ያሉት ግለሰቦች የአሜሪካን ጥቅም ወደ ጎን ትተው እየሄዱ ነው። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከሩ የሚጎዳ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅምና ሉዓላዊነት አይበልጥም። ህሊና ካላቸውና ለሰብዓዊነት የሚቆረቆሩ ከሆነ ሀወሓት በማይካድራ ያካሄደው ጭፍጨፋ በቂ ነው።
እነርሱ አልቃይዳን አሸባሪ ብለው ሲፈርጁ ማንንም አላስፈቀዱም። እኛ የበደለንንና የከፋፈለንን ህወሓት የሚባል ቡድን በፓርላማ አሸባሪ መሆኑን ስንወስን መቀበል ግዴታቸው ነው። ይህ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ድክመት ማሳያ ነው። በመሆኑም የዴሞክራቶችን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ መያዝ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅጣጫና አሠራር ያመጣው ለውጥ አለ?
አቶ እንዳለ፡- የፈሩት ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ የቀረፀችው የዲፕሎማሲ ፖሊሲ አቅጣጫን ነው። ቀደም ሲል የነበረው ኢትዮጵያን የሚያዋርድና ለንግድና ግለሰቦች ጥቅም የተቀረፀ ነው። በድምሩ ዲፕሎማሲው ያገለግል የነበረው ለአንድ ቡድን እንጂ ለኢትዮጵውያን አልነበረም። በአሁኑ ወቅት በዲፕሎማሲው አጀንዳ ከመቀበል ወደ አጀንዳ መስጠት ተለውጧል። እንደ ቀድሞ ከተወሰኑ ሀገራት ጋር ብቻ ሳይሆን ጥቅሟ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስለሆነ ለዚያ የሚመጥን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተከተለች ነው። በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ማዕቀቦች አቅም እየተዳከሙ ነው። ይህ የሆነው ሌሎች ሀገራት ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መፍጠር ስለሚቻልና ጠንካራ ሀገራት እየተፈጠሩ በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማዕቀቡን እንደ መልካም አጋጣሚ መውሰድ ይቻላል?
አቶ እንዳለ፡- ኢትዮጰውያን ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል። በየሀገሩ ያሉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ወደ ዜጎች ቀረብ ብለው መሥራት አለባቸው። የሀገርን ጥቅም በማስቀደም በጋራ መንቀሳቀስና መሥራት ይገባል። በመላ ሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት መፈጠር አለበት። እንደ መንግስት ሃብት አጠቃቀማችንን በሚገባ ማጤን እንዲሁም እርስ በእርስ መከባበር አለብን። ዕርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ ሀገር ውስጥ ያለውን አቅም መጠቀምና ስትራቴጂ ነድፎ ሌት ተቀን መስራት ይገባል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ዘርፈ ብዙና ግንኙነቱም ከተለያዩ ሀገራት ጋር መሆን አለበት። እንደ እውነቱ ከሆነ ማዕቀብ መጣል የነበረባቸው በሱዳንና ግብፅ ላይ ነበር። አሜሪካውያን ዴሞክራሲ የሚሉት ለራሳቸው ጥቅም ብቻ መሆኑን ማወቅ አለብን። የሆነው ሆኖ ግን የአሜሪካ መንግስት በህዳሴው ግድብ ላይ ፖሊሲው እንዳልተቀየረና በአፍሪካ ህብረት አደራደሪነት መፈታት እንዳለበት ማመናቸው ሌላው ከግምት ውስጥ መግባት አለበት። ከዚህ በዘለለ ማዕቀቡ ለኢትዮጵያ የማንቂያ ደወል ነው። ዲፕሎማሲውን መፈተሽና ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚገባም አመላካች ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ እንዳለ፡- በርቱ! አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም