ምርጫ በአንድ ሀገር ላይ የዘመናዊነትና የስልጣኔ ምልክት ነው፡፡ በተለይ በሀሳብ ብልጫ ሲሆን በዛች ሀገር ላይ ያሉ ማህበረሰቦች ይበልጥ ተጠቃሚ የመሆን እድላቸው የሰፋ ይሆናል፡፡ ምርጫ የራስንም የሀገርንም መጻኢ እድል የምንወስንበት እድላችን
ነው፡፡ አስተዋይና ልባም ዜጎች የሚበጃቸውን መሪ ለመምረጥ ይጠቀሙበታል፡፡
በሀሳብ የበላይነት የሚመራ ካልሆነ ምርጫ ብቻውን ትርጉም አለው ብዬ አላምንም፡፡፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆነን ያለፉትን የሀገራችንን አምስት ምርጫዎች ማየት በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የምርጫ ሥርዓት ታውቁታላችሁ.. የዘንድሮውን ሳንቆጥር እስካሁን ድረስ በሀገራችን አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ ሁሉም ምርጫዎች ግን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደውና በሚያዘው መሰረት የተከናወኑ አልነበሩም፡፡ የይስሙላ ምርጫ ታውቃላችሁ? ልክ እንደዛ ነበር፡፡ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የገነነበት፣ የሕዝቦች ተሳትፎ ያልታየበት፣ በብዙ ውሸትና በብዙ ማጭበርበር የተሞላ ነበር፡፡
እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ነበረ ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም ብዙኃኑ መራጭ ከሚፈልገው ይልቅ የማይፈልገውን እንዲመርጥ የሚገደድበት ሥርዓት ስለነበር ነው፡፡ ምርጫ ማለት ሕዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ ካለምንም ተጽዕኖ በነጻነት መምረጥ ሲችል
ነው፡፡ ምርጫ ማለት የሕዝቦች ነጻ ተሳትፎ ነው፡፡ በርካታ ሀሳቦች ቀርበው ከነዛ በርካታ ሀሳቦች መካከል በሕዝብ የበላይነት አንዱ አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ያኔ ምርጫ ተካሄደ ማለት እንችላለን፡፡ ምርጫ ወቅቱን የጠበቀ፣ ተአማኒነት ያለውና የብዙኃን ተሳትፎ የተረጋገጠበት ሲሆን ነው ሕጋዊ የሚሆነው፡፡
ባለፉት ምርጫዎች ደግሞ ይሄ አልነበረም፡፡ ጥቂት ግለሰቦች፣ ጥቂት የመንግሥት ካድሬዎች ራሳቸው ጀምረውት ራሳቸው የሚጨርሱት ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ አይነት የህጻን ጨዋታ ነበር፡፡ ሰሚ በሌላቸው በሚያልጎመጉሙ በታፈኑ ድምጾች በርካታ ዓመታትን በዚህ ሁኔታ
አሳልፈናል፡፡ ምርጫ አስተሳሰብ ነው… አስተሳሰብ ስላችሁ የወረደ አስተሳሰብ ማለቴ አይደለም ከምንም በላይ የሰላ..አስተሳሰብ ማለቴ
ነው፡፡ ሕዝብ ያልመረጠው፣ በሕዝብ ይሁንታን ያላገኘ ፓርቲና መንግሥት አገር ቢመራ ትርፉ ኪሳራ ነው
የሚሆነው፡፡ ነገም ዛሬም ሁሌም ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ያስፈልገናል፡፡ ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ያወቀ ፓርቲ ሁሌም አሸናፊ
ነው፡፡ ቅሉ ግን አንዳችንም ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ አለማወቃችን ነው፡፡ እንዲያውም እላለሁ አብዛኞቻችን ከሕዝብ በተቃራኒ የቆምን ነን፡፡ ለየትኛውም ሕዝብና ፓርቲ ህዝብ..ምን ይፈልጋል የሚለው ቀዳሚ ጥያቄው ነው፡፡
የዘንድሮው ምርጫ ለብዙዎቻችን የተስፋ ጮራን የፈነጠቀ ነው…ዜጎች ከመምረጣቸው በፊት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በሀሳብ የበላይነት ማመን መቻል አለባቸው፡፡ በሀሳብ የበላይነት የማያምን ዜጋ ምርጫን እንደ ነውጥ እንጂ እንደ ለውጥ አያየውም፡፡ በመሰረቱ ምርጫ የለውጥ ጅማሬ ነው፡፡
ዜጎች ፍትሕ የሚያገኙበት፣ ከጭቆና የሚወጡበት፣ የተሻለ ነገን የሚያዩበት አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ምርጫ በብዙ አስተሳሰቦች መሀል የሚያልፍ በስተመጨረሻም በአንድ ሀሳብ የበላይነት የሚጠናቀቅ የሕዝቦች የውሳኔ ፍጻሜ ነው፡፡ የተለያዩ ሀሳቦች፣ የተለያዩ አመለካከቶች የሚንሸራሸሩበት የሕዝቦች የዳኝነት ውጤት ነው፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ልታካሂድ ሽር ጉድ ላይ ናት፡፡ እንደነገርኳችሁ ምርጫ በአንድ ሀገር ላይ የራሱ የሆነ ትልቅ ሚና አለው፡፡ ለአገርም ሆነ ለማህበረሰብ የሚጠቅም ምርጫ በሀሳብ ብልጫ የበላይነት ያገኘ እንጂ በማጭበርበር የሆነ አይደለም፡፡ በየትም ቦታ ላይ ሕዝብ ታላቅ ሚና አለው፡፡ ለምንም ነገር የሕዝብ ድምጽ መሰማት አለበት፡፡ ሕዝብ ይሁንታ ያልሰጠው መንግሥትና ሥርዓት ወደ ስልጣን ቢመጣ እንኳን ጨቋኝና አምባገነን ከመሆን ውጪ ጥቅም የለውም፡፡ ያለፉት አምስት የኢትዮጵያ ምርጫዎች ግለሰብን እንጂ ሕዝብን መሰረት ያደረጉ አልነበሩም፡፡ ለምንም ነገር ላይ ሕዝብ መቅደም አለበት፡፡
የአንድ ፓርቲ ምርጥነት የሚለካው በአስተሳሰቡ ውስጥ ሕዝብ ሲኖር ነው፡፡ ሕዝብ የሌለበት ሀሳብና ራዕይ ፍጻሜው መሸነፍ ነው፡፡ ከእንግዲህ ባለው ዘመናችን እና ከእንግዲህ በምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝብ እንዲቀድም ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ የሌለበት ሀሳብ የመከነ ነው፡፡
ምርጫ የሚደረገው እኮ ሕዝብ ለማስተዳደር ነው፡፡ የምረጡኝ ቅስቀሳ የምናደርገው እኮ ሕዝብ በሀሳባችን አምኖ እንዲመርጠን ነው፡፡ የወጣነው እኮ ከሕዝብ አብራክ ነው..ሕዝብን ረስተን የምንፈጥረው ተዓምር የለም፡፡ መጀመሪያ ሁላችንም ወደ ሕዝብ መመለስ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ መጀመሪያ የምንመራውን ሕዝብ ማወቅ አለብን፡፡ ያለፉት ምርጫዎች የብዙኃን ድምጽ የማይሰማባቸው ሕዝብ አልባ ነበሩ ፡፡ ለዛም እኮ ነው የአንድ ፓርቲ የበላይነት የገነነው፡፡ ለዛም እኮ ነው ተዓማኒነት የጎደለው ምርጫ ሲካሄድ የቆየው፡፡ ምርጫ ሕዝብን ከማወቅና ከመረዳት የሚጀምር ነው ፡፡ በሀሳብ ብልጫ የተቃኘ ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲኖር ሕዝብን ያከበረ ሀሳብ ያስፈልጋል ባይ ነኝ ፡፡ መነሻችን ሕዝብ እንደሆነ ሁሉ መድረሻችንም ሕዝብ ነው ፡፡ ከሕዝብ አብራክ በቅለን ሕዝብ የምንዋሽበት ምንም ምክንያት አይታየኝም፡፡
ያለፉት ምርጫዎች ብዙ ነገር ያስተማሩን ሆነው ያለፉ ናቸው ፡፡ በዚህም መጪው ስድስተኛ ምርጫ ብዙዎቻችን እንደምንናፍቀው በሀሳብ የበላይነት ተጀምሮ እንደሚጠናቀቅ እናምናለን ፡፡ ወደ ፊት ለምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ድንቅ ሀሳብ ነው የሚያስፈልጋት ፡፡ እስካሁን ድረስ በከሰሩ ሀሳቦች ከስረን ኖረናል ፡፡ ከእንግዲህ ግን ለአገርም ለሕዝብም በሚጠቅሙ ትውልድ አሻጋሪ ሀሳቦች መመራት አለብን፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ብዙ መልካም ነገሮችን ያሳየናል ብዬ አምናለሁ ፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ በነጻነት የሚመርጥበት ከሁሉ የተሻለ መልካም እድል ይዞ መጥቷል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሕዝብን ያገናዘበ፣ ሕዝብን መሰረት ያደረገ የፓርቲ ስብስብ የታየበት ስለመሆኑም እምነት አለኝ፡፡ እንዳለፉት ምርጫዎች በውሸትና በማጭበርበር ሳይሆን በሀሳብ ልዕልና የሚመራ ሆኖ መጠናቀቅም ይኖርበታል ፡፡
ትላንት አልፏል ፡፡ ዛሬ አዲስ ቀን ነው ፡፡ በዚህ አዲስ ቀን ላይ አዲስ አስተሳሰብን እንሻለን ፡፡ ከዘመኑ ጋር የዘመነ፣ ለትውልዱ የሚመጥን አሻጋሪ ሀሳብ ያስፈልገናል ፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኳችሁ መነሻችንም መድረሻችንም አገርና ሕዝብ መሆን አለበት ፡፡ የአሁኑ ምርጫ ከግለሰባዊነት ወጥተው ለአገርና ሕዝብ የሚሆን የነጠረ ሀሳብ ላላቸው ፓርቲዎች የተሻለ እድል አለ ብዬ አምናለሁ ፡፡ በአሸናፊ በሀሳብ የበረቱ፣ መቼም የትም ሕዝብን መሰረት ያደረጉ እነርሱ ለሁላችን ያስፈልጋሉ፡፡ እንዳለፈው ጊዜ በውሸትና በማጭበርበር የሚሆን ነገር የለም ፡፡ ሥልጣን የሕዝብ ነው፡፡ ዜጎች በዚህ እድል ተጠቅመው የነገ መሪያቸውን መምረጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁላችንም የምንፈልገውን ለመምረጥ ይሄን መልካም አጋጣሚ መጠቀም
አለብን፡፡ ለምንፈልጋት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ድምጻችን ዋጋ አለው፡፡ እንዲያውም ስህተት የምንሰራው በዚህ ምርጫ ላይ መሳተፍ ካልቻልን ነው እላለሁ፡፡
ኢትዮጵያ..ኢትዮጵያ ለምንል ሀገር ወዳዶች ሁሉ ይህ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ ምቹ ጊዜ ነውና ድምጻችሁን ለምትፈልጉት ፓርቲ በመስጠት ሀገር ወዳድነታችሁን ማሳየት አለባችሁ እላለሁ ፡፡ እድላችሁን ተጠቅማችሁ ካልመረጣችሁ ነገ ላይ ሌሎች በመረጡት ፓርቲ እየተገዛችሁ እንደሆነ አስቡት፡፡ እድላችሁን ተጠቅማችሁ ዛሬ ካልመረጣችሁ ነገ በሌሎች አስተሳሰብ ስር እንደሆናችሁ እንዳትረሱት፡፡ ይህ እንዳይሆን እድላችሁን ተጠቀሙ፡፡ የእያንዳንዳችን ድምጽ ዋጋ አለው፡፡ እንዳለፈው ጊዜ ምርጫ በጥቂቶች ድምጽ የብዙሃኑ እጣ ፈንታ የሚወሰንበት እንዳይሆን ሁላችሁም አሻራችሁን አሳርፉ፡፡ ከምንም በላይ የሕዝብ የበላይነት የገነነበት ምርጫ ያስፈልገናል ፡፡
የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በፈለግናት ልክ እንድትፈጠር ከሕዝብ ለሕዝብ የሆነ ፓርቲ ያስፈልገናል፡፡ ለዚህም የእያንዳንዳችን ድምጽ ወሳኝነት አለው፡፡ ነገ ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው ምርጫ ነው ፡፡ በዚህ ምቹ ጊዜ ላይ በንቃት መሳተፍ ያልቻለ አገሬን እወዳለሁ ቢል ውሸት ነው የሚሆነው ፡፡ አገር መውደድ እኮ በአገር ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ነው ፡፡ ከፊታችን ያለው ምርጫ ደግሞ አገራችንን ለመውደዳችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከድሮነት መውጣት አለብን ዘመኑ የሚመጥነውን ሀሳብ ለሕዝባችን ማድረግ አለብን፡፡ ከዚህ በፊት እንደነበሩት ምርጫዎች ሕዝብ የሚወናበድበት ሥርዓት አይኖርም፡፡ ብዙ አይኖች እውነትን ማየት ናፍቀዋል፡፡ ብዙ ጆሮዎች እስከ ዛሬ ሰምተው የማያውቁትን እውነት መስማት ሽተዋል፡፡ ብዙ ልቦች..ብዙ ነፍሶች በኢትዮጵያ ታሪክ በሀሳብ የበላይነት የሚመራን ምርጫ ናፍቀው እየጠበቁ ነው፡፡
እርግጠኛ ነኝ እኔም እናንተም ናፍቀናል፡፡ እኔና እናንተ ብቻ አይደለንም በቀጣዩ ምርጫ መልካም ነገር ለማየትም ሆነ ለመስማት ያሰፈሰፉ ብዙ ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ የሚሆነው ግን እያንዳንዳችን የመምረጥ መብታችንን ተጠቅመን መምረጥ ስንችልና ጥፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ራሳችንን ስናቅብ ነው፡፡ ምርጫን በተመለከተ ብዙ ኃላፊነትን ለመንግሥት ሰተን ተመልካች የሆንን ብዙዎች ነን፡፡ ምርጫ የአገር ጉዳይ እስከሆነ ድረስ የእያንዳንዳችን ንቁ ተሳትፎ ወሳኝነት አለው፡፡ ካለው ኢ-ፍትሐዊነት አንጻር በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ተስፋ ቆርጠን የነበርን ብዙዎች ነን ፡፡
በዛው ልክ በአዲስ ተስፋ በአዲስ አስተሳሰብ ቀጣዩ ምርጫ የኢትዮጵያ የአዲስነት ምዕራፍ የሚጀምርበት እንደሆነ በማመንም ነገን የምንጠብቅ ሞልተናል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ከትላንት የተሻለ ምርጫ እንጠብቃለን፡፡ ሕዝብ የሚደመጥበት፣ አገር የቀደመችበት ብሔርተኝነትና ተረኝነት የወደሙበት፣ እኔነትና መሰል ነቀርሳዎቻችን የሻሩበት አዲስ ቀን እንናፍቃለን፡፡
በሀሳብ የበላይነት የምትመራ፣ በአንድነትና በእኩልነት የምትደነቅ ቀዳማይት በኩር አገር ህልማችን ናት፡፡ ለጋራ ጥቅም የተባበሩ ክንዶች የበረቱባት፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት የተመቸች ልዕለ ኃያል ኢትዮጵያን እንሻለን፡፡ ይህ እንዲሆን መንግሥት ብቻ ሳይሆን እኛም እናስፈልጋለን፡፡ ይህ እንዲሆን ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዳችን ግድ ይለናል፡፡ የእስካሁኗ ኢትዮጵያ በጥቂት አገር ወዳድ ዜጎች የቆመች ናት፡፡ ብዙዎቻችን በምን ያገባኛል ህመሟን ሳንታመም፣ ስቃይዋን ሳንሰቃይ ኖረናል፡፡ ከእንግዲህ ለምትፈጠረው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ግን ሁላችንም እናስፈልጋለን፡፡ በጥቂቶች የምትፈጠር አገር የለችም፡፡ በጥቂቶች የምትለማ አገር የለችም፡፡ በጥቂቶች የሚበለጽግ ሕዝብ የለም፡፡ ለምንም ነገር የሁላችንም ድምጽ ያስፈልጋል፡፡ ህልማችን በብዙ ነገሯ የምትደነቅ አገርን መፍጠር ከሆነ መጀመሪያ ሁላችንም ሀገራችንን በተመለከተ አንድ አይነት ህልም ማለም ይኖርብናል፡፡ በጎ የሆነ አንድ አይነት ሀሳብ ማሰብ ግድ ይለናል፡፡
አንዱ እየጠላ አንዱ እየወደደ፣ አንዱ እየገነባ ሌላው እያፈረሰ የምትፈጠር ምርጥ አገር
የለችም፡፡ ምርጥ አገር ለመፍጠር ከሁሉ በፊት እኛ ምርጥ እንሁን፡፡ ምርጥ ትውልድ ለመፍጠር ከሁሉ አስቀድመን እኛ በሀሳብ የበላይነት የምናምን
እንሁን፡፡ ከሁሉ ትልቁን ፍቅርን እንወቅ፡፡ በጋለ የአገር ፍቅር ስሜት ከፊታችን ባለው ወሳኝ ምርጫ ላይ እንሳተፍ፡፡ መንግሥት ምርጫው ተአማኒነት ያለው እንዲሆን እየሰራ ነው፡፡ እኛም የምንፈልገውን በመምረጥ ኃላፊነታችንን እንወጣ፡፡
አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በምናደርገው ሂደት የሁላችንም አስተዋፅዖ ወሳኝነት አለው፡፡ በአባቶቻችን ስርዓት ወደ ፊት እንሂድ..አዲሷ ኢትዮጵያ ከፊት ነው ያለችው፡፡ ህልማችን ውብ አገር ከሆነ፣ ህልማችን ስልጡን ሕዝብ ከሆነ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን
እንወጣ፡፡ በፍቅር በአንድነት የምንመኛትን ኢትዮጵያ በተባበረ ክንድ እንስራት እያልኩ ላብቃ፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2013