የግልና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ለጤና ፍቱን መድኃኒት ስለመሆኑ ዛሬ በኮሮና ዘመን በብዙ ቢነገርም ከጥንት ከጠዋቱ ኢትዮጵያውያን ከእንዶድ ቅጠል ጀምረው ሳሙናን ሰርተው የግል ንጽህናቸውን ጠብቀዋል። በየዘመኑ ሌሎችንም የንጽህና መጠበቂያን አገልግሎት ላይ አውለዋል። ሞራን እንደ ግብአት በመጠቀም ዛሬም ድረስ የሞራ ሳሙና ተብሎ የሚጠራውን የልብስ ማጠቢያ ሳሙና ማምረት ችለዋል። ከዘመኑ ጋር እኩል በመዘመንም አሁን ላይ በተለያዩ ቀለማት ያማሩ፣ የደመቁና ያሸበረቁ እንዲሁም መልካም መዓዛን የተጎናጸፉ በርካታ የፈሳሽ ሳሙናን በተለያየ መጠን ተመርቶ ለገበያ እየቀረበ ይገኛል።
በዛሬው የስኬት ገጻችንም በጎጆ ኢንደስትሪ ተሰማርተው በቤት ውስጥ በልምድ የሞራ ሳሙና ብለን የምንጠራውን የልብስ ማጠቢያ ሳሙና አምርተው ለገበያ በማቅረብ የታወቁና ውጤታማ መሆን የቻሉ ሰው ናቸው። እንግዳችን በውስጣቸው የነበራቸውን ራዕይ እውን ለማድረግ ከማህበረሰቡ ይሰነዘርባቸው የነበረውን ተፅዕኖን ተቋቁመው በመምህርነት ሙያቸው ላይ ደርበው ሳሙና በቤት ውስጥ ማምረታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው አስቀጥቷቸዋል። ተስፋዬ ሞራ የሚል ቅጽል ስምም ወጥቶላቸዋል። እኩለሌሊት ላይ እንቅልፍ አጥተው ከጅብ ተጋፍተው በሚሰሩት የሳሙና ሥራ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ባለቤታቸውም ከሰዎች ጋር በነበራቸው ማህበራዊ ተገፍትረዋል።
እነዚህንና መሰል ችግሮችን ተቋቁመው በማለፍ ራእያቸውን ዕውን አድርገው ዛሬ ላይ የፋብሪካ ባለቤት መሆን የቻሉት በሀዋሳ ከተማ የሚገኙት መምህር ተስፋዬ አበበ ናቸው። ከ1965 ዓ.ም ጀምረው የመምህርነት ሞያን የተቀላቀሉት አቶ ተስፋዬ፤ ከመምህርነት ሥራቸው ጎን ለጎን የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት ጉጉትና ፍላጎት የነበራቸውና የሞከሩ ሲሆን የሳሙና ሥራው ግን ተሳክቶላቸው ዘልቀውበታል። ከአራት አስርት ዓመታት በፊት በቤት ውስጥ በእጅና በሰው ጉልበት ይመረት የነበረው የሳሙና ምርት ዛሬ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በተለያዩ ማሽኖች ከደረቅ እስከ ፈሳሽ ሳሙናን ማምረት ችለዋል።
የቋንቋ መምህር የነበሩት እና የኢታብ ሳሙና ፋብሪካ መስራችና ባለቤት መምህር ተስፋዬ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ አለመሆናቸው ሳሙናን ከማምረት አላገዳቸውም። ለሦስት ዓመታት ካገለገሉበት ከቀድሞው ከባሌ ክፍለ ሀገር ተዘዋውረው ወደ ዛሬው ሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ በመጡበት አጋጣሚ ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ ሳሙናን በቤት ውስጥ ማምረት ጀምረዋል። ጊዜው ከገንዘብም ሆነ የቴክኖሎጂ ሁኔታ ወደኋላ የሚጎትት ቢሆንም እሳቸው ግን አሁን ላይ ማሽን የሚሰራውን ሥራ በእጃቸው ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። የራሳቸው ጥረትና አልደክምም ባይነት ቢኖርም የግብዓቶች በቀላሉ አለማግኘት ፈተና ሆኖባቸዋል ። በተለይም ኬሚካልና የተለያዩ ሽቶዎችን ለማግኘት ችግሩ ከባድ ነበር ።****
ወቅቱ ዜጎች ከተወሰነ መጠን በላይ ንብረት ማፍራት የማይፈቀድላቸው የነበረበት የደርግ ጊዜ በመሆኑ የግል ሥራ የማይደገፍ ነበር። ይሁን እንጂ መምህር ተስፋዬ፤ ከመምህርነት ሥራቸው በተጨማሪ ሞራ ተጠቅመው በድብቅ ሳሙና በቤታቸው ያመርቱ ነበር። ያመረቱትን ሳሙናም በድብቅ ይሸጡ ነበር። በወቅቱ በተለይም መምህር ሆኖ ተጨማሪ ሥራ መስራት የሚያስከስስ በመሆኑ ጎረቤት ጭምር እንዳያውቅ በጥንቃቄና በድብቅ ሰርተዋል።
ሳሙናን በቤት ውስጥ ለማምረት መነሻቸው ታላቅ ወንድማቸው የተለያዩ ሰርቶ ማሳያዎችን ዝርዝር የያዘ ጥራዝ ወደ ቤታቸው ማምጣቱና እርሳቸው ደግሞ ጥራዙን አንብበው በመረዳታቸው ነው። አንብበው ከተረዱት የአሠራር ሂደቶችም በቤት ውስጥ ሳሙናን ለማምረት ጥረት አድርገዋል። ጥረታቸውን ውጤታማ ለማድረግም የተለያዩ መሰናክሎችን አልፈዋል። በወቅቱ ምርቱን ለማምረት የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን በቀላሉ ማግኘት አይቻልም ነበር። በቀላሉ የሚገኘው ጥሬ ዕቃ ሞራ ብቻ ሲሆን ሌሎች ኬሚካሎችና ሽቶዎችን ማግኘት እንደዛሬው ቀላል አልነበረምና ከትምህርት ቤት ወረቀት አጽፈው ለማግኘት ሞክረዋል።
መምህር ተስፋዬ፤ የሳሙና ምርትን ለማምረት የተጻፉ ነገሮችን በማንበብና በመረዳት፣ ያላወቁትን የኬሚስትሪ መምህራንን በመጠየቅና ዕውቀት ነው ብለው ያሰቡትን ሁሉ መዝግበው በመያዝ እንዲሁም ደጋግመው በመሞከር ውጤታማ መሆን ችያለሁ ይላሉ። በማንበብ በመጠየቅ በመሞከር የሳሙና ምርትን በየጊዜው አሻሽለዋል። እስከዛሬ በነበራቸው የምርት ሂደትም በሰውም ሆነ በአልባሳት ላይ ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጥሩ ሳሙናን እያመረቱ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ለተገልጋዩም አማራጭ ሳሙና አቅርበዋል።
ለምርቱ አስፈላጊ የሆኑ ከሞራ ውጪ ያሉ ጥሬ ዕቃዎችን ለማግኘት ያለውን ችግር ተቋቁመው በወቅቱ ከነበረው ሥርዓት ጋር ድብብቆሽ ተጫውተው እስከ 200 ኪሎ ግራም መጠን ያለው ሳሙና አምርተው ለገበያ ያቀርቡ ነበር። ለውጥ እስኪመጣ ድረስ በዚህ ሁኔታ ሳያቋርጡ ሞራ ሳሙና ሲያመርቱ የነበሩት መምህር ተስፋዬ፤ 1983 ዓ.ም ሥራቸውን ይፋ ማውጣት ቻሉ። በወቅቱ በቤተሰብ አቅም ብቻ በድብቅ ይመረት የነበረው ሞራ ሳሙና በመንግሥት ድጋፍ በነፃነትና በስፋት ሊመረት ጊዜው ሆነ። እንዲህ ያለውን ቀን ሲናፍቁና ዘርፉን ትልቅ ደረጃ ለማድረስ የነበራቸውን ራዕይ ዕውን ለማድረግም የመንግሥት በሆነው ፕሮግራም ጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጁ።
ተደራጅተውም በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛውና የመጀመሪያው ተበዳሪ በመሆን 2000 ብር ከሲዳማ ክልለ ማይክሮ ፋይናንስ አግኝተዋል። በዚህ ወቅትም ማምረቻ ቦታቸው መኖሪያ ቤታቸው ሲሆን ሞራ ሲያቀልጡ ከሌሊቱ ሰባትና ስምንት ሰዓት ላይ ከጅቦች ጋር እየታገሉ ነበር። ምክንያቱም የአካባቢው ሰው በሞራ ሽታ እንዳይረብሽ በሚል ነው። በዚህ ጊዜ ከጎረቤቶቻቸው ሳይደበቁ ማምረት ችለዋል። ሞራውንም ቢሆን የአካባቢው ሰው እርድ በፈጸመ ጊዜ ያቀብላቸው ነበር። በተለይም በበዓላት ሰሞን የሚያውቁ ሰዎች በሙሉ እቤታቸው ድረስ ሞራውን ያቀርቡላቸዋል። ከዘይት ፋብሪካም እንዲሁ የተለያዩ ተረፈ ምርቶችን በግልጽ ማግኘት የሚችሉበት ጊዜ ተፈጠረ።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ኬሚካሎችንና ሽቶዎችን በፈለጉ ጊዜ በግልጽ መግዛት በመቻሉ ሥራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጣ። ከመምህርነት ጎን ለጎን በድብቅ ይሰሩት የነበረው ሥራ በአደባባይ መስራት በመቻላቸው አንደግፍም ሲሏቸው የነበሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በሙሉ አለንህ ማለቱን ቀጠሉ። የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ተስፋ ሰንቀውና ዘርፉን ወደ ፋብሪካ የማሳደግ ራዕይ ይዘው የተጓዙት መምህር ተስፋዬ፤ ፋብሪካ ገንብተው ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን የተለያዩ ማሽኖችን ገዝተው የማምረት አቅማቸውን አሳድገዋል።
መምህር ተስፋዬ፤ ከመምህርነት ሙያቸው በጡረታ እስከተገለሉበት 2002 ዓ.ም ድረስ በጥምር ሥራ ውጤታማ ሆነዋል። አሁን ደግሞ ከጡረታ በኋላ ሙሉ ጊዜያቸውን በኢታብ ሳሙና ፋብሪካቸው ላይ አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ። የሳሙና አመራረት ሙያን በቤት ውስጥ እየተመለከቱ ያደጉት ልጆቻቸውም የሚያግዟቸው ሲሆን በተለየ ሁኔታም ወደ ዘርፉ የተቀላቀለ ልጅ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
ማንኛውም ነገር ከትንሽ ወደ ትልቅ ያድጋል የሚል እምነት ያላቸው መምህር ተስፋዬ፤ ከታላቅ ወንድማቸው ያገኙት ጥራዝ ለበርካታ ሥራዎች መነሻ ሆኗቸዋል። የተረዱትን ነገር ሁሉ የመሞከር ዝንባሌ ያላቸው በመሆኑም ከሳሙና ውጪ የሻማ፣ የወረቀት ሥራና ሰም ማምረት እንዲሁም የተለያዩ ሙከራዎችን በቤታቸው ውስጥ ሲሞክሩ ኖረዋል። የጎጆ ኢንዱስትሪን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረትም ቤታቸው በቅጽል ስሙ ቤተ ሙከራ ይባል ነበር።
በቤታቸው ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን ለመስራት በመሞከራቸው ልጆቻቸው ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚናገሩት መምህር ተስፋዬ፤ በቤት ውስጥ የሚሰራውን ነገር ሁሉ ለመስራት ሲሞክሩ ቆይተዋል። አጠቃላይ በነበራቸው ተሳትፎም ተጠቃሚ ሆነዋል። በመሆኑም መስራት የሚፈልጉትን ሥራ ገና በጠዋቱ መምረጥ እንዲችሉ ሰፊ ዕድል ሰጥቷቸዋል። በዚህም አስቀድመው በሳሙና ማምረት ሥራ ተሰማርቼ ውጤታማ መሆን እችላለሁ ብለው በመወሰን ውጤታማ መሆን ችለዋል። ምንም ዓይነት ካፒታል ሳይኖር እችላለሁ እሰራለሁ ብሎ መወሰንና ለውሳኔው ዕውን መሆን መትጋት ካሰቡበት ያደርሳል ያሉት መምህር ተስፋዬ፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ብቻ ይሰሩት በነበረው የሳሙና ሥራ ውጤታማ በመሆን በአሁኑ ወቅት የተሻሻለ የሳሙና አምራች ሆነዋል።
የሳሙና ሥራ ጥርሴን የነቀልኩበት ሥራ ነው የሚሉት መምህር ተስፋዬ፤ ኢታብ ሳሙና ፋብሪካ በተሰኘው በፋብሪካቸው ውስጥ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሆነው ያገለግላሉ። ፋብሪካውን በማቋቋምም ሆነ በማምረት ሂደት ውስጥ ልጆቻቸው ከፍተኛ ጥረት የነበራቸው ቢሆንም የእርሳቸው ድርሻ ግን የላቀ ለመሆኑ መጀመሪያው ከሌለ መጨረሻ የለም በማለት አስረድተዋል። በመሆኑም ወላጆች ያላቸውን ነገር ሁሉ ለልጆቻቸው በማካፈል ነገን ማስቀጠል ይገባልም ይላሉ።
በወቅቱ ከፍተኛ የተባለውን ሁለት ሺ ብር ብድር ወስደው በግልጽ ሳሙናን በቤት ውስጥ ሲያመርቱ የነበሩት የኢታብ ሳሙና ፋብሪካ መስራችና ባለቤት መምህር ተስፋዬ፤ በአሁኑ ወቅት ያላቸው ካፒታል ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል። ሳሙና ለግል ንጽህና ወሳኝ በመሆኑ ገበያው ሰፊ ነው። ፍላጎቱም ዕለት ዕለት እየጨመረ መጥቷል። በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በሳሙና ምርት ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ታይቷል። ስለዚህ ሰፊ ገበያን በመፍጠር በስፋት እንዲመረት ምክንያት ሆኗል። ነገር ግን ገበያው በሚፈልገው ልክ ማቅረብና ማጣጣም አልተቻለም። ለዚህም ምክንያቱም ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎችን በፍጥነትና በሚፈለገው ጊዜ ማግኘት ባለመቻሉ ነው።
ኢታብ ሳሙና ፋብሪካ በሥራ ዕድል ፈጠራም ሰፊ ድርሻ እያበረከተ የሚገኝ ፋብሪካ ሲሆን ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት 400 ለሚደርሱ ዜጎች በምርት ክፍል እንዲሁም 100 ለሚደርሱ ዜጎች ደግሞ በቢሮ አገልግሎት የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ፋብሪካው በቅርቡ የፈሳሽ ሳሙና ማምረት የጀመረ በመሆኑም ለ300 ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር በድምሩ 800 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ወደፊት ደግሞ ኦሞ ወይም የዱቄት ሳሙናን ለማምረት በዝግጅት ላይ ሲሆኑ በዚህ ጊዜም የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ይሆናል።
ሥራን አለመናቅ በተለይም ልጆችን ከቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ ማለማመድና ከትንሽ እንዲነሱ ማድረግ ያስፈልጋል። የጓሮ አትክልትም ሆነ የማምረቻ መሣሪያ ተጠቅመው በአቅማቸው ልክ እንዲሰሩ አቅጣጫ ማሳየት አለብን የሚሉት መምህር ተስፋዬ፤ በቤት ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎችን ልጆች እንዲለምዱና እንዲሰሩ ማበረታታትና ማገዝ እንደሚያስፈልግ መክረው ይህም ውጤታማ ሊያደርጋቸው የሚችል እንደሆነ ልጆቻቸውን ምሳሌ ያደርጋሉ።
ዛሬ ትላልቅ ናቸው የሚባሉት ኢንዱስትሪዎች ከቤት ውስጥ ከጎጆ ኢንዱስትሪ የተነሱ ስለመሆናቸው የሚያምኑት መምህር ተስፋዬ፤ ብዙ ካፒታል ባይኖርም በአነስተኛ ገንዘብ በጥንካሬና ትጋት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል። ስለዚህ ኅብረተሰቡ ልጆቹ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ፍላጎታቸውን በመደገፍ ልጆቹን ለሥራ ዝግጁ ቢያደርግ አገርም ተጠቃሚ ትሆናለች። በተለይም ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ሰርቶ ማሳያዎችን በማዘጋጀት ተማሪዎች በሚፈልጉት ዘርፍ አልያም እንደየዝንባሌያቸው እንዲሳተፉና በተሳተፉበት ነገር ደግሞ ውጤታማ ሆነው እንዲደሰቱ የማድረግ ሥራን ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን ሊሰራበት ይገባል በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013