
የዛሬው የስኬት ዓምድ እንግዳችን አቶ ተስፋዬ ገብረሕይወት ይባላሉ። የተወለዱት ከአዲስ አበባ 175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በዝግባቦቶ ቀበሌ ነው። በወቅቱ ቤተሰቦቻቸው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ስለነበሩ ተስፋዬን ማስተማር ባለመቻላቸው የያኔውን ታዳጊ እድሜው ስምንት ዓመት ሲሞላ በእረኝነት ሆለታ ከሚገኙ ዘመዶቹ ቤት ተቀጥሮ እንዲሠራ አደረጉት፤ በእረኝነቱም ለሶስት ዓመታት አገለገለ፤ እነዚህ ዘመዶቹም ሊያስተምሩት ባለመቻላቸው አዲስ አበባ በሚገኝ ሌላ ዘመድ ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ።
‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም!›› እንደሚባለው ሁሉ አዲስ አበባ የመጣበት ቤተሰብም ለታዳጊ ተስፋዬ ምቹ አልነበረም። ቀን ሱቅ ውስጥ እየሠራ በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር እድል አገኘ። ይሁንና ከሥራው ጫና ጋር በተያያዘ ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል ተሳነው።
ስለሆነም ራሱን ለመቻል ወሰነና ጫማ ጠራጊ ወይም አሳማሪ /ሊስትሮ/ ሆነ፤ ይህም አላዋጣ አለው፤ ተስፋ ግን አልቆረጠም። ብርቱካንና ሌሎች ፍራፍሬዎችን እያዞረ መሸጥ ጀመረ። የዚህም ገቢ አነስተኛ ሆነበትና ኑሮውን ከባድ አደረገው።
እንግዳችን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ እየገፋ ባለበት በዚያ ጊዜ ሌላ አንድ የቅርብ ዘመዱ ጅማ በሚገኘው ሱፐር ማርኬታቸው ሊቀጥሩት እንደሚፈልጉ ይነገረዋል፤ ሊያስተምረውም ቃል ይገባለታል። ይህ ጥያቄ በለጋ እድሜው ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ለሚለው ተስፋዬ ትልቅ የምስራች ሆነለት፤ ሳያመነታ ጥያቄውን ተቀብሎ ጅማ ገባ።
እንግዳችን በአባ ጅፋሯ ጅማ ከተማ የዘመዱ ሱፐር ማርኬት እያገለገለ ጎን ለጎንም በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርቱን ቀጠለ። በትምህርቱም ጎበዝና ታታሪ ነበረና ከቀን ተማሪዎች ጋር ተወዳድሮ አሸነፈ።
ይህንን በአቶ ተስፋዬ ጥረት የተገኘውን ውጤት የተመለከተው ይኸው ቤተሰብ አዲስ አበባ በመላክ በቀኑ ክፍለ ጊዜ እንዲማር አደረገ። ተስፋዬም በርትቶ ትምህርቱን በመከታተሉና በማጥናቱ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን 100 አምጥቶ ማለፍ ቻለ፤ ይህም ውጤቱ በወቅቱ ጎበዝ ተማሪዎች ለብቻ እንዲማሩ በሚደረጉበት አዲስ ከተማ ትምህርት ተመድቦ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዲከታተል በር ከፈተለት።
ይሁንና የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናውን በጥሩ ውጤት ማለፍ ሳይችል ቀረ። ይህንን የተመለከቱት ዘመዱ ወጣቱ ተስፋዬ ተስፋ እንዳይቆርጥ በማሰብ አሁንም ወደ ሱፐር ማርኬቱ ተመልሶ እንዲያግዝ ጠየቀው። እሱም በሱፐር ማርኬቱ ለአራት ዓመታት ካገለገለ በኋላ ይኸው ዘመዱ እቁብ ጥሎለት ባገኘው ገንዘብና ከቤተሰብ በተደረገለት ድጋፍ በ146 ሺ ብር የራሱን የመኪና መለዋወጫ መደብር እንዲከፍት አገዙት። በትምህርቱ ተስፋ ያልቆረጠው እንግዳችን ጎን ለጎንም ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የመጀመሪያ ዲግሪውን በማኔጅመንት መያዝ ችሏል።
የመኪና መለዋጫዎችን ከዱባይ በማምጣትና በመሸጥ ለአስር ዓመታት ያህል የቆየው የስኬት እንግዳችን፣ ሥራው እየሰፋ፤ በስሩ ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ እንዲሁም የፋይናንስ አቅሙ እየጎለበተ ሄደ። በመሆኑም ተጨማሪ የሥራ መስክ ላይ መሰማራት እንዳለበት አመነ።
ይህንንም ጉዳዩን አብሮት ለተማረ አንድ ጓደኛው አማከረው፤ በአጋጣሚ ደግሞ ይኸው ጓደኛው በአበባ ልማት ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ የደች ዜጎችን ያውቅ ነበርና በአበባ ልማት ቢሰማራ አዋጭ እንደሚሆንለት መከረው። በወቅቱ ደግሞ መንግሥትም ለዘርፉ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ በመስጠት ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ያበረታታ ስለነበር እሱም በዘርፉ ይበልጥ ተሳበ።
ይሁንና ሥራው ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የሰው ኃይል ብሎም በዘርፉ እውቀት ያለው ሰው እንደሚፈልግ በማሰብ ውጤታማ ላልሆን እችላለሁ የሚል ስጋት አደረበት። ስለሆነም ስለጉዳዩ አብረውት ሊሠሩ ይችላሉ ብሎ ያሰባቸውን አምስት ጓደኞቹን አማከረ፤ ሃሳቡም ተቀባይነት አግኝቶ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ። የሚሠሩበትን ቦታ የተወለዱበትን ቀዬ ምርጫው አደረገ። በተለይም አካባቢው ምንም እንኳ ለማንኛውም እርሻ የሚመች መሬት፣ የአየር ንብረትና ሰፊ የውሃ ሀብት ቢኖርም፣ ምንም አይነት መሰረተ ልማት አልነበረም። ይሁንና ማኅበረሰቡም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖር መሆኑን ተረድቶ፣ አካባቢውንም ሆነ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በማለም በሀሳቡ ገፋበት።
በወቅቱ በአካባቢው ምንም አይነት መሰረተ ልማት አለመኖሩ ላሰበው እርሻ ልማት እንደ ችግር የሚታይ ቢሆንም፣ ባለው አካባቢውን የማልማትና የመቀየር ሕልም በመሰረተ ልማቱ በኩል የሚመጣውን ኪሳራ በፀጋ ለመቀበል ወሰነ።
ሀገርን የማልማትና የመቀየር ሕልም እንደነበረው የሚናገረው አቶ ተስፋዬ፤ የአበባ ኢንዱስትሪ ለሀገር ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ግንዛቤው አስቀድሞም እንደነበረው ተናግሯል። በርካታ የሰው ኃይል የሚቀጥርና አካባቢው ላይ አዲስ የኢኮኖሚ ከባቢ የሚፈጥር ስለመሆኑ ተረድቷል። በዚህ ልማት ቢሰማራ ተግዳሮት ሊያጋጥም ይችላል በሚል ወስኖ ሥራውን በድፍረት እንደገባበት አስታውሷል።
በዚህም መሰረት አቶ ተስፋዬ ከልማት ባንክ ያገኙትን ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በሁሉም አባላት በተገኘው መዋጮ በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል ‹‹ቲናው›› የአበባ ልማትን በመመስረት የአበባ ልማት ኢንዱስትሪውን ተቀላቀሉ።
በአምስት ሄክታር መሬት ላይ 250 ሠራተኞችን በመያዝ አበባ ማልማት የጀመሩት አቶ ተስፋዬና ጓደኞቻቸው፤ ብዙም ሳይቆዩ የመሬቱን ስፋት ወደ ሰባት ሄክታር ከፍ አደረጉ። በአሁኑ ወቅት 35 ሄክታር መሬት በማልማት በዓመት ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን አበባ በቀጥታ ወደ ሆላንድ፣ ጀርመን፣ ኖርዌይ ደቡብ ኮሪያ፣ ሳውዲአረቢያ፣ ኦማን፣ ዱባይና ሌሎችም ሀገራት ይልካሉ። ከዚያ ውስጥ ከስምንት እስከ አስር ሚሊዮን ዶላር ለሀገር ገቢ ያደርጋሉ።
በዚህም ሳይወሰኑ የአበባ እርሻቸውን የማምረት አቅምና መዳረሻ ሀገራትን ጭምር እያሰፉ፤ ሲልኩም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን ከፍ ባለ መልኩ እንዲሆን አደረጉ። ይህንን ጊዜ የቲናውን አበባ እርሻ ልማት ሥራ የተመለከቱ የውጭ ባለሀብቶች ደግሞ የ‹‹አብረን እንሥራ›› ጥያቄ አቀረቡላቸው። እነ አቶ ተስፋዬም በሃሳቡ ተስማሙና ከፍተኛ መዋዕለንዋይ በመመደብ አሁን እየተመረተበት ያለውን እርሻ ከ70 ሄክታር በላይ ለማድረስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ 15 እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገቢ ለሀገር ለማስገባት አቅደዋል። ድርጅቱ ዘንድሮን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በታማኝነት ግብር በመክፈል ለሀገር እድገት ባበረከተው አስተዋፅኦ በርካታ የእውቅና ሰርተፍኬትና ዋንጫዎችን ማግኘት ችሏል።
ከአንድ ዓመት በኋላ በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው የሚልከውን አበባ መጠን በእጥፍ እንደሚያድግ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ የሠራተኞቻቸውም ቁጥር ከ900 ወደ ሁለት ሺ እንደሚደርስ ጠቁመዋል። የአበባ እርሻው በአሁኑ ወቅት 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት ማፍራት የቻለ ሲሆን፤ በዚህም ሳይወሰን በአካባቢው የአበባ እርሻ መንደርለመመስረትና ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ራዕይ ይዞ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከአበባ እርሻ ልማቱ ጎን ለጎን ፍቅር ውሃ የተሰኘ ፋብሪካም በአካባቢው ገንብቷል። በዚህ ሁሉም ለ300 ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በተጨማሪም የአቦካዶ ዝርያ በማባዛት አምስት ሺ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ችግኞችን በየዓመቱ በመስጠት እንዲያለሙ እያደረገ ሲሆን፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በድርጅቱ ማሳ አቦካዶ በስፋት በመትከልና በማልማት፤ በጥሬውም ሆነ የአቦካዶ ዘይት በማምረት ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርቷል።
ሥራውን ሲጀምሩ የሠራውን ራዕይ ተገንዝቦ ለማስፈፀም የሚተጋ ሠራተኛ ማግኘት ትልቅ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር የሚያስታውሱት እንግዳችን፤ ይሁንና ከጓደኞቻቸው ጋር በመማካከር በሙያው ልምድ ያለው ሥራ አስኪያጅ በመቅጠር ሥራውን እንዲመራ በማድረጋቸው ስጋቱን ማስቀረት መቻላቸውን ገልጸዋል። ሥራቸውም እየተስፋፋ፤ የድርጅቱ አቅምም እየጎለበተ መጣ።
የተወለዱበትን ቀዬና ማሕበረሰብ ኑሮ የማሻሻል የልጅነት ሕልም የነበራቸው አቶ ተስፋዬ በአካባቢው የመጀመሪያ ኢንዱስትሪ መመስረታቸው፤ እንደ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃና መሰል መሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉ በማድረግ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም የአካባቢውን ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ከሌላ አካባቢ የመጡ ባለሀብቶችንም ዐይን በመክፈት ረገድ የበኩላቸውን እንዳበረከቱ ይሰማቸዋል። አሁን በርካታ ባለሀብቶች በተለያዩ የልማት ሥራዎች ተሰማርተው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠሩም ምክንያት ሆኛለው ብለው ያስባሉ።
በተለይም ከሶስት ሺ በላይ ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ያደረገ ቦኖ ውሃ በአካባቢው በመገንባት ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ብዙ ኪሎ ሜትር ይጓዙ የነበሩ እናቶችንና ተማሪዎችን ድካም ማስቀረት መቻላቸው ትልቅ ደስታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል። በትምህርት ቤት ግንባታና እድሳት ሥራ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በዚህም የመማር ማስተማሩ ሂደት መደገፍ መቻላቸውን፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በየጊዜው በመደገፍ የዜግነት ግዴታውን እየተወጡ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሖ ግብርም እንዲሁ ድርጅታቸው ቲናው የአበባ እርሻ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በየዓመቱ ከ30 ሺ በላይ ችግኞችን ይተክላል፤ ችግኞቹን ለማኅበረሰቡ በማሰራጨት እንዲተክሉ ያደርጋል። ባለሙያዎችን በመመደብ በአካባቢው የተጎዳ መሬትን የማልማት ሥራ ይሰራል።
የአየር ብክለትን ከመከላከልና የአካባቢውን ማሕበረሰብ ከብክለት ከመታደግ አኳያም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የአበባ እርሻ ድርጅቱ ለአካባቢው ማሕበረሰብ እያደረገ ባለው ድጋፍና የማምረት ሂደቱ ከአየር ብክለት ነፃ በሆነ መንገድ እንዲካሄድና በአረጓዴ አሻራ እያበረከተ ባለው አስተዋፅኦ በአውሮፓ የሚሰጠውን ‘ፌር ትሬድ’ እና ሌሎችንም ዓለም አቀፍ ሰርተፍኬቶችን ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ ተስፋዬ በዘርፉ በተሠማሩባቸው ዓመታት ስለአጋጠማቸው ተግዳሮቶች ሲያብራሩ እንደጠቆሙት፤ ከአራት ዓመታት በፊት የዓለምን ኢኮኖሚ ያናጋው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት እንደማንኛውም ኢንዱስትሪ በድርጅታቸው ዘንድም የመክሰር ስጋት ነበረ። ይሁንና በወቅቱ ሌሎች ሀገራት አበባ መላክ በማቆማቸውና በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ባለማቋረጡ ምክንያቱ ከአንድ ወር መንገራገጭ በኋላ ከስጋት ይልቅ ተስፋ የሚያጭር ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል። ከበፊቱ ይልቅ የገበያ ተፈላጊነት ማግኘት መቻሉንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም እንደ አንድ የዘርፉ ተዋናይ ሥራውን ሲጀምሩ ችግሮች አጋጥመዋቸው እንደነበር የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፣ ከካርጎ ጭነት ጋር በተያያዘ የገጠማቸውን ችግር አስታውሰዋል። ወቅቱ በካርጎ ጭነት ሥራ ገብተው የነበሩት የግል ባለሀብቶች ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ይጠየቁ የነበረበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ድርጊት አብዛኞቹን የአበባ አልሚዎች ፈተና ውስጥ ጥሎ እንደነበር አመልክተዋል። አንዳንዶቹም ኪሳራ ውስጥ በመግባታቸው እርሻቸውን እስከ መዝጋትና እስከመሸጥ የደረሱበት ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል።
ድርጅታቸው ኃላፊነት በመውሰድ ከቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በመነጋገር ስብሰባ እንዲጠራ በማድረግ፤ የሆርቲካልቸር ኮርሬቲቭ እንዲቋቋም በማድረግ በአንድ ኪሎ አበባ ላይ ይከፈል የነበረውን ሁለት ዶላር ከ20 ሳንቲም ወደ አንድ ዶላር ከ70 ሳንቲም እንዲቀንስ በማድረግ አምራቾችን መታደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
አሁንም ለዘርፉ ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶች ከውጪ ሲገቡ ጉምሩክ አካባቢ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ እንደሚጠየቅ የሚጠቁሙት እንግዳችን፤ እንዲህ አይነቱ ሁኔታ አምራቾችን ተስፋ የሚያስቆርጥና ለኪሳራ እየዳረገ ያለ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል። መንግሥት በሆርቲካልቸር ዘርፍ ከፍተኛ ቁጥጥርና ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ይሄ ዘርፍ በርካታ የሰው ኃይል የተሸከመና፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር የሚያስገባ መሆኑን ገልጸው፣ የመንግሥት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም