
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና አምራቾችን ጠቀሜታ ዘላቂ ሊያደርግ፣ የቡና ምርትና ጥራትን ሊያስጠብቅና የውጭ ምንዛሬን ሊያሳድግ የሚያስችለውን የመጀመሪያውን የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ግብይት ሥርዓት ይፋ አደረገ::
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አዱኛ ደበላ ትናንት እንዳስታወቁት፤ ሥርዓቱ በአይነቱ የተለየ ፤ ለቡና አምራቾች ዘላቄ ጥቅምን የሚያስገኝ፣ የቡና ምርትን ጥራትና በዘረፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ የሚጨምር ነው ::
ኢትዮጵያ የቡና አምራችና የቡና መገኛ አገር ብትሆንም አምራቹም ሆነ አገሪቱ ከዘርፉ የሚገባቸውን ጥቅም አግኝተዋል ለማለት አያስደፍርም ያሉት ዶክተር አዱኛ፣ ሥርዓቱ መዘርጋቱ ለዘርፉ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነት ገልፀዋል:: ተሳታፊ የሚሆኑት ቡና አምራቾች የምርታቸው ጥራት በቡና ቀማሾች ተረጋግጦ ከ 85 በመቶ በላይ ያስመዘገቡ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል::
የግብይት አማራጩ የሚጀመረው ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው የባለ ልዩ የቡና ጣዕም ቅምሻ ውድድር ላይ ተሳትፈው በብሔራዊ ደረጃ አሸናፊ ሆነው የተለዩትን የአርሶ አደሮች ቡና በማገበያየት ነውም ብለዋል::
ባለስልጣኑ ከአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት ዩ ኤስ አይ ዲ ፊድ ፊውቸር፣ ከቡና ላኪዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ሥራዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል:: ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቀረቡት አንድ ሺህ 848 የቡና ናሙና ውስጥ 150 የመጀመሪያውን ዙር አልፈው የተገኙ መሆናቸውንም አመልክተዋል::
ለመጨረሻ ጊዜ በጥራታቸው ማለፍ የቻሉት 40 ናሙናዎች ናቸው:: ይህም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ለመጀመሪያ ጊዜ ለናሙና ከቀረበው በ 400 ይልቃል:: በዚህ ረገድ በቡና ጥራታቸው ከ87 በመቶ በላይ ያመጡ 30 ያህል ሲሆኑ ከዚህም ውስጥ አምስቱ ከ 90 በላይ ውጤት በማስመዝገብ ፕሬዚዳንሺያል አዋርድ የተባለውን እውቅና ማግኘት የቻሉ ናቸው ብለዋል::
ከአምናው ጋር ሲነፃፀር እውቅና ያገኙት በሁለት ብልጫ ያሳዬ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከአምስቱ የላቀ ውጤት ካስመዘገቡ አሸናፊዎች አራቱ በሲዳማ ክልል የሚገኙና አንዱ ከኦሮሚያ ክልል መሆኑንም ገልፀዋል::
የኢትዮጰያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ በበኩላቸው፤ ተግባራዊ የሚሆነው የግብይት ሥርዓት የተሻለ ዋጋ የሚከፍሉ ተገበያዮች የሚመጡበት፣ የውጭ ንግድን የሚያጠናክርና የገበያ ዕድሎችን ማስፋት የሚያስችል ነው ብለዋል::
ለውድድሩ የሚቀርቡ ቡናዎች የሚገኙትም ለውድድሩ ተብሎ በተዘጋጁ በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ እና ጅማ ባሉ ልዩ መጋዘኖች መሆኑንም ነው የጠቆሙት:: ሥርዓቱ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ወደፊትም ጥራት ያለው ቡና ተፈላጊነቱን የሚያስገነዝብ እንደሚሆንም ጠቁመዋል::
የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች ቡና አምራቾችና ላኪዎች ፕሬዚዳንት ዶክተር ሁሴን አምቦም፤ ስለ ቡና ለማውራትም ሆነ ከዘርፉ አስፈላጊውን ጥቅም ለማግኘት ቡና አምራቹን አርሶ አደር ማክበርና ለልፋቱ ተመጣጣኝ ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል::
ለምርት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ወይም ቁሳቁሶችን ከማቅረብ ባሻገር ፖሊሲዎች ሊቀረጹ ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል::
መሰረት በኃይሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም