ሀገራችን ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በርካታ ተግባሮችን ስታከናውን ቆይታ በወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች። ምርጫው በብዙ መልኩ በመራጩ ሕዝብ እና በተመራጮቹ ፓርቲዎች ዘንድ ተስፋ የተሰነቀበት ነው። ይህ ምርጫ በ2013ቱ ተስፋ እንዲያጭር ምክንያት ከሆኑ አመክንዮዎች መካከልም አገሪቱ በለውጥ ማግስት ይህን ምርጫ ማዘጋጀቷ፣ ሰፊ የውድድር ሜዳ መኖሩ ፤ ፓርቲዎች አላማቸውን በነጻነት ማስተዋወቅ፣ ምርጫ ቦርድ በአዲስ መልክ መዋቀሩ ፣ የምርጫ አዋጁ ተሻሽሎ መዘጋጀቱ የሚሉት ይገኙበታል።
ከተስፋዎቹ መካከል አንዱ የምርጫ አዋጁ ነው፤ አዋጁ ደግሞ ከያዛቸው አንቀጾች መካከል የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ስለማካሄድ የሚለው ይገኝበታል። በአንቀጹ ላይ እንደተመለከተው፤ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉትን መገናኛ ብዙኃን ማለትም ሬድዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጦችን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ አድልዎ የመጠቀም መብት አላቸው። እጩዎች በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ነፃ የአየር ጊዜ አግኝተው የመጠቀም መብት አላቸው። መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምን በተመለከተ ቦርዱ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን ባሳተፈ አካሄድ በሚያወጣው የድልድል መመሪያ መሠረት ይከናወናል ይላል አንቀጹ።
አዋጁ ስለቅስቀሳው ይህን ካለ በኋላ ክልከላውንም አስቀምጦታል። በቤተ ክርስቲያኖች፤ በመስጊዶች፣ በወታደራዊ ካምፖች እና ፖሊስ ጣቢያዎች፤ የመማር ማስተማር ሂደት ተግባር እየተከናወነ በሚገኝበት ወቅት በትምህርት ቤቶች እና በትምህርት ቤቶች አካባቢ በሁለት መቶ ሜትር ርቀት ዙሪያ ቅስቀሳ ማድረግን አዋጁ ከልክሏል። ሕዝብ የዕለት ተለት ግብይት በሚፈፅምባቸው እና በተወሰኑ ቀናት በገጠርም ሆነ በከተማ በይፋ ገበያ እየተካሄደ በሚገኝባቸው ቦታዎች በሁለት መቶ ሜትር ዙሪያ ክልል፤የመንግሥት ወይም የሕዝብ መደበኛ ሥራ በመከናወን ላይ የሚገኙባቸው የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መደበኛ የሥራ ሰዓት እና ቦታ፣ ሌላ ሕዝባዊ ስብሰባ እየተካሄደ ባለባቸው ቦታዎች እና አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግን በጥብቅ ይከለክላል።
እየተካሄደ ያለውን የምረጡኝ ቅስቀሳ በዚህ አዋጅ መሰረት ስመለከተው በአብዛኛው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ማለት ይቻላል። በአደባባዮች ፣ በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ቅስቀሳዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። አንዳንድ ፓርቲዎች ግዙፍ ድምጽ ማጉያዎችን በመጠቀም ጭምር ፕሮግራሞቻቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ። ድምጾቹ ከአደባባይና ጎዳናዎች አልፈው የሚሰሙ በመሆናቸው በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳርፉ ቢችሉም ፣ እስከ አሁን ባለኝ መረጃ መሰረት በዚህ መልኩ ቅስቀሳ በማድረግ በኩል የተስተዋለ ግዙፍ ችግርም አልሰማሁም፤አላስተዋልኩም።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያውያን በመቻቻል ላይ ተመስርተው ሁሉንም ሥራዎቻቸውን ማከናወን እንደሚችሉ ነው። በተለይ አዲስ አበባን ስንመለከት ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም እስከ አሁን ሲፈትኑ አልታየም።
እንደሚታወቀው በከተማዋ አደባባዮችና ዋና ዋና ጎዳናዎች ከእምነት ተቋማት፣ ከመንግስታዊ መስሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ከመሳሰሉት ያላቸው ርቀት የአፍና የአፍንጫ ያህል ነው። በአብዛኛው ማለት ይቻላል ተቋማቱ ያሉበት ስፍራና ሕጉ ለቅስቀሳ የፈቀደው ክልል በአደባባዮችና ጎዳናዎች ላይ ቅስቀሳ ማካሄድ የማያስችል ይመስለኛል። እንዲያም ሆኖ ግን ቅስቀሳው በተሳለጠ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። ይህን እንደ ትልቅ ስኬት መያዝ ያስፈልጋል።ይህ መቻቻል የምርጫው ጉዳይ እስከ ሚጠናቀቅ መቀጠል ይኖርበታል።
ይህ ማለት ግን ችግር የለም ማለት አይደለም። አንዳንድ ክፍተቶች ይታያሉ። መቻቻሉን ሊጎዱ ከሚችሉ ከእነዚህ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ ያስፈልጋል። ክፍተቶቹ ከወዲሁ በመሙላት ሊኖር የሚችል ኮሽታን ማስወገድ ይገባል። አዋጁን ሳስበው የአንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ያሳስብኛል። እነዚህ ፓርቲዎች አዋጁን አላነበቡት ይሆን? ወይስ በሚገባ አያውቁት ይሆን? ወይስ አውቆ እንዳላወቀ ሆነው ነው? የሚያሰኝ ቅስቀሳ እያካሄዱ ይገኛሉ። የእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ምክንያት ደግሞ በአዋጁ ላይ የሰፈሩትን በተለይ በምረጡኝ ቅስቀሳ ክልከላ ላይ ያሉትን ድንጋጌዎች/ አንቀጾች/ እየጣሱ ያሉበት ሁኔታ ነው።
ቅስቀሳቸው ከትምህርት ቤቶች ፣ የእምነት ተቋማት ወዘተ. ሁለት መቶ ሜትር ርቀት ላይ ካልሆነ በቀር ቅስቀሳ እንዳይደረግ ቢደነግግም፣ ከዚህ የርቀት ክልል ባነሰ ቦታዎች ላይ ቅስቀሳ ሲደረግ ይስተዋላል። ይህ የሆነው ምናልባትም ተቋማቱ እና አደባባዮችና ጎዳናዎች ያላቸው ርቀት ከሁለት መቶ ሜትርም ያነሰ ሆኖ ሊሆን ይችላል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ቅስቀሳውን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማካሔድ ያስፈልጋል። እስከ አሁን ከተፈቀደው ክልል አልፋችሁ ለምን ቅስቀሳ አረጋችሁ ብለው ቅሬታ ያቀረቡ አካላት ያሉ አይመስለኝም። ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ተነስተው በመቻቻል አልፈውታል ብሎ መውሰድ ይቻላል። ሁኔታው ምቹ በሆነባቸው አካባቢዎች ግን የሁለት መቶ ሜትር ርቀት ገደቡን መጠበቅ ይገባል።
ፓርቲዎቹ በመኪና ላይ ከፍተኛ ድምጽ የሚያወጡ የድምጽ ማስተጋቢያዎችን (ሞንታርቦ) በመጫን፣ የመኪና ጡሩንባ እያሰሙ እየቀሰቀሱ ያሉበት ሁኔታ ግን በእጅጉ ያሳስባል። ድምጹ ተቋማትን በእጅጉ እየረበሸ ነው። በየቤቱ፣ በየተቋሙ ስራ ላይ ለሚገኘው እንዲሁም ገበያ ላይ ያለውን ሕዝብ ታሳቢ ያደረገ ድምጽ የሚለቁም ነው የሚመስለኝ። ይህ መታረም አለበት።
ይህ ብቻ አይደለም አዋጁ የምረጡኝ ቅሰቀሳው ከገበያ ቦታ ልክ እንደ እምነት ተቋማቶቹ ሁለት መቶ ሜትር ርቀት እንዲካሄድ የሚያዝ ቢሆንም አንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለበዓል እና ለተለያዩ አነስተኛ እና ጥቃቅን አምራቾች ተብለው በሚዘጋጁ ባዛሮች አካባቢ ያለ አንዳች ከልካይ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ይስተዋላል፤ የመቀላቀል ነገር ይታያል።
ቅስቀሳው በአብዛኛው ቅዳሜና እሁድ ነው እየተካሄደ ያለው ። የዚህ መነሻው ቅዳሜና እሁድ የእረፍት ቀናት ናቸው ተብሎ ሊሆን ይችላል። ቅዳሜ ከሰአት በፊት የሚሰሩ ተቋማት ጥቂት እንዳልሆኑ ሊታይ ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ ቅዳሜ ከሰአት በፊት በስራ ገበታ ላይ የሚገኙ ሰራተኞች እየታወኩ ይገኛሉና የሚታረምበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። ሰራተኛው ወቅቱ የምርጫ ወቅት ነው መታገስ ያስፈልጋል እያለ በመቻሉ ነው እንጂ ድምጹ በስራ ላይ ጫና ሳያሳድር ቀርቶ አይደለም።
እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተከለከሉ ቦታ እየሄዱ ቅስቀሳ ሲያካሄዱ ዝም በተባሉ ቁጥር ለአለመግባባት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚቻሉ መታወቅ ይኖርበታል፤ ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚባለው ምንም አይነት አለመግባባት ሳይከሰት እንዲህ ያሉ የስርዓት እና የአዋጅ መጣሶች አንድ ሊባሉ ይገባል።
የእስከ አሁኑን በመቻቻል አልፈናል። ይህን ማጠናከር ያስፈልጋል። አብሮነት፣ መከባበርና መቻቻል የፌደራል ስርዓቱ እሴቶች ናቸው፣ በርግጥ አብሮነት ከተፈለገ መከባበርና መቻቻል መኖር የግድ ይላል፣ የአገሪቱ ሕገ መንግስትም እነዚህን እሴቶች በግልፅ አስቀምጧል። በእዚህ መልኩ በመቻቻል ጭምር ምርጫችንን ማሳከት አንድ ነገር ሆኖ አዋጁን መሰረት ባደረገ መልኩ መንቀሳቀስ ግዴታ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
የልቤ ደርሶ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013