በዓለማችን በትምህርት ዘርፍ የላቀ ደረጃ የደረሱ ሀገራት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችን ወደ መሬት በማውረድ ከስኬት ማማ ላይ መድረስ መቻላቸውን መረጃዎች ይነግሩናል። ሀገራቱ ከተቋማቶቻቸው በየዘርፍ የሚፈልቁትን የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለዕድገታቸው ምርኩዝነት መጠቀም መቻላቸውን ሳይሸሽጉ ይናገሩታል።
ሀገራቱ በትምህርት ዘርፍ የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ይነስም ይብዛ በየትኛውም ተቋም ለሚመዘገቡ ስኬቶችም ሆነ ውድቀቶች አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን በጽኑ ያምናሉ። ስለዚህ የተቋማቶችን አቅም በተገቢው ደረጃ ተጠቅሞ የምርምር ውጤቶች ተግባራዊ ቢደረግ መዳረሻ ውጤቱም ያማረ ይሆናል ሲሉም ምክረ ሐሳብ ይለግሳሉ። በርግጥም መሰል ሀገራቶች በተለያዩ ዘርፎች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በቀላሉ ሲሻገሩ እንታዘባለን። በዚህ ረገድ ከውጪውም ዓለም ወደ ሀገራችን በመመለስ ተግባራዊነቱን እንፈትሽ።
በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጅማሮ 70 ዓመታት መቆጠሩ ይታወቃል። ይህም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉት ጥናትና ምርምሮችን ታሪካዊ ዳራ ሰባት አሥርት ዓመታት ያሻግረዋል። በዚህ መሠረት በተቋማቱ የሚደረጉት ጥናትና ምርምሮችን እንደየአስፈላጊነቱ ወደ ተግባር በመለወጥ ሀገርን መለወጥ ተችሏልን? የሚለውን ስንጠይቅ ˝የምርምር ሥራዎቹ በመደርደሪያ ላይ አቧራ ጠግበው ነው የሚቀሩት̋ የሚለው ምላሽ ከፍ ብሎ ይደመጣል።
የተወሰኑ አካላት ደግሞ በተቋማቱ የሚፈልጉት የምርምር ውጤቶች ተግባራዊነት መሻሻል ማሳየቱንና ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች አሉ በማለት ይመልሳሉ። በመንግስት በኩል ያለውን ሁኔታ እንመልከት። በሀገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች እያንዳንዳቸው በየአመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርምሮችና ጥናቶች ቢያደርጉም፤ ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን አይክድም። ነገር ግን በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ መሻሻሎች የታዩ መሆኑን ይሞግታል።
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የምርምር አቅምን ማሳደግ እንዳለባቸው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተቋማቱ የትምህርት ጥናትና ምርምር ማዕከላትን አቋቁመው ወደ ተግባር በመግባታቸው መሻሻሎች ሊታዩ መቻላቸውን ያብራራል። በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዶ በነበረው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የምርምር ስራዎችን ከይስሙላነት ባለፈ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ውስንነቶች እንዳሉበት ተመላክቷል። ችግሩ ከተመራማሪው ጀምሮ ውጤቱን ሰርቶ ለሚያባዛው አካል ተደራሽ እስከማድረግ ባለው ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ቢሆኑም፤ በሀገሪቱ ከነበረው ልምድና ተሞክሮ አንጻር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልቅ መሻሻሎች የታዩ መሆኑ በአብሮነት ቀርቧል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸሰቀ ላምቦሬ የእርሳቸውን ተቋም ዋቤ በማድረግ፤ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የሚደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች ተግባራዊነት ውስንነቶች ቢኖሩትም መሻሻል መታየቱን ይናገራሉ። ዩኒቨርሰቲው የአካባቢውን ስነ ምህዳር መሰረት በማድረግ ከማህበራዊ ዘርፍ በተጨማሪ ሰባት ምርምር ማዕከላት በማቋቋም እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ይገልጻሉ። ˝በተለይ ለግብርናና መድሐኒትነት በሚጠቅሙ እጽዋት፣ የደጋ ፍራፍሬና አካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እስካሁን በተደረገው ጥረት ውጤት እየተገኘ ነው̋ ያሉት ዶክተር ጸሰቀ፤ በተያዘው ዓመት በተቋሙ የማህበረሰቡን ችግር በመለየት 129 ምርምሮች መካሄዳቸውን ያስታውሳሉ። በምርምሩ ከተገኙት ውስጥ የተመረጡ 21 ውጤቶች ለኮንፍረስ፤ ከቀረቡት መካከል ፋይዳቸው ታይቶ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚደረጉ ይሆናል ̋ሲሉ ነበር ያብራሩት።
ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው በዩኒቨርሲቲዎች ለምርምር ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን በአንድ ወገን አመላካች ነው። ይህም ተቋማቱ በተስፋ ውስጥ ያሉ መሆኑን የሚያሳይ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በየዩኒቨርሲቲዎች የሚደረጉት የምርምር ውጤቶችን በብዛት ቢሆንም ወደ መሬት እንዲወርዱ የሚደረጉት ከቁጥር በታች መሆናቸውንም ያሳየናል። የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቱ እንዳስቀመጡት፤ በተቋሙ በአንድ ዓመት ብቻ ከአንድ መቶ በላይ ምርምሮች ተደርገዋል።
በከፍተኛ በጀት፣ እውቀት፣ የሰው ጉልበት፣ የቁሳቁስ ወጪ ተደርጎባቸው ከተሰሩት ምርምሮች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የታሰቡት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው /ተግባራዊነታቸውም አጠራጣሪ ነው/። ይህ የዩኒቨርሲቲውን ተሞክሮ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ወቅታዊ መልክን ለመመልከት መስታወት ይሆናል። በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶች ላይ ተስፋና ስጋት መኖሩን ይነግረናል። ለዚህ ደግሞ በኮንፍረንሱ ላይ የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ሰለሞን ቢኖር አስተያየት ለዚህ ሀሳብ ማጠናከሪያ ይሆናል።
ዶክተር ሰለሞን እንደተናገሩት፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተሰጣቸው ተልዕኮ አንዱ ጥራት ያለው ምርምር በማድረግ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ማድረስ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ረገድ በተቋማቱ የሚካሄዱ የምርምር ስራዎችን ከይስሙላነት ባለፈ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተመራማሪው ጀምሮ ውጤቱን ሰርቶ ለሚያባዛው አካል ተደራሽ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች የሚታዩ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ሰለሞን ፤ ˝በየአካባቢው የሚደረጉ ምርምሮች የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት አቅም የተላበሱ እንዲሆኑ ብዙ ርቀት ተጉዞ ውጤት መታየት ጀምሯል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘርፉን ለማጠናከር እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን፤ ተቋማቱን የተለያየ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ከመደገፍ ባሻገር ፤ በሂደት የሚገጥሙ ችግሮች ለመፍታት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የተሻለ የምርምር ስራዎች እንዲካሄዱ ጥረት እየተደረገ ነው ̋ ሲሉ ዘርፉ በመንታ መንገድ ላይ እየተጓዘ መሆኑን ያብራሩት።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶች የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችን ወደ ተግባር መለወጥ ላይ ሰፊ ክፍተት እንደነበረ ያመለከቱት ደግሞ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከፍተኛ መሻሻሎች መታየታቸውን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጅማሮ 70 ዓመታት መቆጠሩን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በእነዚህ ዓመታት የምርምር ስራዎች ቢካሄዱም ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ክፍቶች እንደነበሩ ይገልጻሉ። ነገር ግን ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ተግባራዊነት በመከታተል ረገድም ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ይናገራሉ። የዘርፉን የጥራት ችግር ለማቃለል በፖሊሲዎችና በአሰራር ላይ የተከናወኑት ማሻሻያዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የተቻለ መሆኑንም ያመላክታሉ።
በዘርፍ የመጣውን ለውጥ ሲገልጹ፤ በጤና፣ በግብርና እና በአፈር ጥበቃ ሥራዎች በኢትዮጵያዊያን የተሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን አግኝተው እየተተገበሩ ይገኛሉ። በጤናው ዘርፍ በቆላማ አካባቢ የሚከሰተውን ሌሽማኒያ የተሰኘውን በሽታ ከአዲስ አበባ፣ አርባ ምንጭና ጎንደር ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ጥናት አድርገዋል። የጥናት ውጤታቸውን ተከትሎም ለበሽታው ይሰጥ የነበረው የህክምና ጊዜ ከ30 ቀናት ወደ 17 ቀናት ዝቅ እንዲል ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል። የጥናት ውጤቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
በአጠቃላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ተግባራዊነት በመንታ መንገድ ላይ እየተጓዘ ይገኛል። ዘርፉን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚሰሯቸው የጥናትና ምርምሮች ስኬታማነት የትምህርት ጥናትና ምርምር ማዕከላትን እስከ ማቋቋም መድረሳቸው በበጎነት ይጠቀሳል። ነገር ግን በዘርፉ የተቋማቱ አቅም ከሚፈለገው ደረጃ አንጻር ገና ብዙ ሥራዎች ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ማዕከላት በመሆናቸው የሚያከናውኑት የመማር ማስተማር ሂደት ከምርምሩ ጋር ቁርኝት ማድረግ ፈጠራንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያበረታታ እንዲሁም በወቅታዊ መረጃዎች እና ችግሮች ላይ የተመሰረተ ማድረግ ይገባል ባይ ነን።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም