የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ በአራት መርከቦች ላይ ጥቃት አደረሱ

የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ በአራት መርከቦች ላይ ጥቃት አድርሰዋል።

የሀውቲ ታጣቂዎች በህንድ ውቅያኖስ ላይ ስትጓዝ የነበረችውን ኤምኤስሲ ኦሪዎን እቃ ጫኝ መርከብን በድሮን ማጥቃታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ይህ ጥቃት የሀውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት በሚል በዓለምአቀፍ የመርከብ እንቅስቃሴ ላይ እያደረሱ ያሉት የጥቃት ዘመቻ አካል ነው ተብሏል።

የኤልኤስኢጂ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የፖርቹጋል ሰንደቅ ዓላማ ስታውለበልብ የነበረችው ኤምኤስሲ ኦሪዎን መርከብ ከፖርቹጋሉ ሲነስ ወደብ ኦማን ወደሚገኘው ሰለላህ ወደብ እየተጓዘች ነበር።

መርከቧን በባለቤትነት የሚያስተዳድራት ዞዲያክ የተባለው ማሪታይም ኩባንያ ነው። እስራኤላዊው ባለሀብት ኢያል ኦፈር ከዚህ ኩባንያ ድርሻ እንዳለው ይገለጻል።

በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎቸ ከባለፈው ህዳር ወር ወዲህ በቀይ ባህር፣ በኤደን ባህረ ሰላጤ፣ በባብኤል ማንዴብ የባህር ወሽመጥ ተደጋጋሚ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት በማድረስ የመርከብ ኩባንያዎች መስመር እንዲቀይሩ እና ለከፍተኛ ወጪ እንዲዳረጉ አስገድደዋል።

ባለፈው መጋቢት የሀውቲ ቡድን መሪ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በህንድ ውቅያኖስ በኩል እንዳያልፉ የሚያደርሱትን ጥቃት እንደሚያሰፉ ገልጾ ነበር።

የቡድኑ መሪ በትናንትናው ዕለት በቴሌቪዥን ባስተላለፈው መልእክት እንዳስታወቀው፤ በቀይ ባህር ሳይክላድስ የንግድ መርከብን እና በሁለት የአሜሪካ ዲስትሮየርስን አጥቅቷል። የእንግሊዝ ማሪታይም ሴኩሪቲ ኩባንያም የማልታ ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ ከጅቡቲ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ጅዳ ስትጓዝ የነበረች መርከብ ሰኞ እለት ጥቃት እንደደረሰባት ቀደም ብሎ ሪፖርት አድርጓል።

አሜሪካ እና እንግሊዝ የሀውቲ ታጣቂዎችን ለመበቀል በይዞታቸው ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እያካሄዱ ናቸው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You