ቻይና ሃማስና ፋታህን ማደራደር ጀመረች

ቻይና የፍልስጤም ተቀናቃኝ ቡድኖች የሆኑትን ሃማስ እና ፋታህ ማደራደር ጀመረች፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ተወካዮች በቤጂንግ ያደረጉት የመጀመሪያው ንግግር “ተስፋ ሰጪ” ውጤት የታየበት መሆኑንም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊ ጂያን ተናግረዋል።

ቃልአቀባዩ በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ዝርዝር ጉዳዮችን ባይጠቅሱም፤ የሃማስና ፋታህ ተወካዮች በቻይና ጋባዥነት ቤጂንግ በመገኘት ልዩነታቸውን ለማጥበብ ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

“ሁለቱም አካላት የፍልስጤማውያንን አንድነት ለማረጋገጥና ጥምረት ለመፍጠር ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ ተስማምተዋል” ም ነው ያሉት። ቤጂንግ የፍልስጤማውያንን ውስጣዊ አንድነት ለማጠናከርና የረጅም ጊዜ ነጻ ሀገር የመመሥረት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የምታደርገው ጥረት በሃማስም ሆነ በፋታህ ተወካዮች መደነቁን መግለጻቸውንም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ለእስራኤል ነጻ ሀገርነት እውቅና መስጠት የማይፈልገውና በስድስት ቀናቱ ጦርነት በእስራኤል በሃይል የተያዙ ቦታዎች ተለቀው ነጻዋ ፍልስጤም ትመሠረታለች የሚለው ሃማስ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመው የማህሙድ አባሱ ፋታህ ጋር ግንኙነቱ የሻከረ ነው።

በተለይ በፈረንጆቹ 2006 በተካሄደው ምርጫ ሃማስ ማሸነፉን ተከትሎም ዌስትባንክን ከሚያስተዳድረውና ፋታህ ከተቆጣጠረው የፍልስጤም አስተዳደር ጋር ልዩነቱ መስፋቱ ይታወሳል።

ሁለቱ ቡድኖች ተከታታይ ድርድር አድርገው የአንድነት መንግሥት ለመመስረት መስማማታቸውም አይዘነጋም።

ስምምነቱ ሃማስ የፍልስጤም አስተዳደር ከእስ ራኤል ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት እንዲያከብር የሚያደርግ ቢሆንም ለእስራኤል ሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና ያልሰጠበት በመሆኑ እስራኤልና አሜሪካ የአንድነት መንግሥቱን እውቅና አንሰጠውም ብለው ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ጥለው ነበር።

ይህም የሃማስና ፋታህ የአንድነት መንግሥት በአጭር ጊዜ እንዲፈርስና ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።

እስራኤልና ምዕራባውያን አጋሮቿ ሃማስን በሽብርተኝነት በመፈረጅ ዌስትባንክን ለሚያስተ ዳድረው ፋታህ ደግሞ ዓለምአቀፍ እውቅና በመስጠት የፍልስጤም የነጻነት ትግልን በሁለት ጎራ እንደከፈሉት ይነገራል።

ሰባተኛ ወሩን በያዘው የጋዛ ጦርነት አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ለቴል አቪቭ የሚያደርጉት ወታደራዊ ድጋፍ በፍልስጤማውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ስትኮንን የቆየችው ቻይና ለፍልስጤም ነጻ ሀገርነት እውቅና ትሰጣለች።

የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎችን በማደራደር የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ በምዕራባውያን ብቻ መዘወሩ ሊያበቃለት ይገባል ብላለች።

ቤጂንግ ባለፈው ዓመት ሳኡዲ አረቢያ እና ኢራንን በማደራደር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ዳግም እንዲጀምሩ ያደረገችው ስኬታማ ጥረትም ሁነኛ ማሳያ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You