መብት መጠየቅን ያስለመደው የላብ አደሮች ቀን

ነገርየው ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ መልክ የነበረው ነው፡፡ ምንም እንኳን የተጀመረው በአሜሪካና አውሮፓ ሀአገራት እንደነበር ቢነገርም እየቆየ ሲሄድ ግን የሶሻሊስት ሀገራት ንቅናቄ መስሏል፡፡ በእርግጥ ነገሩን ያጧጧፉትም የሶሻሊስት ሀገራት ናቸው፡፡ ብዙ ዝርዝር ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም በጥቅሉ ሲታይ ግን፤ የፊውዳል ሥርዓት የድሃ ጉልበት ይበዘብዛል የሚል ነው፡፡ በሀገራችን ዓውድ ስናየው፤ የባላባት ሥርዓት ጭሰኛውን ‹‹እርቦ›› እና ‹‹ሲሶ›› እያሳረሰ ይበዘብዝ ነበር፤ ሠራተኛው የልፋቱን ያህል አያገኝም እንደማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የተማሪዎችን ንቅናቄ አስጀማሪዎች የ60ዎቹ አብዮተኞች ‹‹መሬት ለአራሹ›› የሚል መፈክር ማንሳታቸው፡፡ የላብ አደሮች ቀንም መከበር የጀመረው ንጉሣዊ ሥርዓቱን ባስወገደው የደርግ መንግሥት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ ግን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው፡፡ በአውሮፓ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ የተከሰተ ነው፡፡ ይህ ቀን በአሜሪካ ‹‹የሠራተኛ ቀን (Labor day) በሚል ሲከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ‹‹ሜይ ዴይ (May day›› በሚል ይታወቃል፡፡ ይህም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ግንቦት 1 መሆኑ ነው፡፡ በተለያዩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከበር ያስጀመሩት ንቅናቄ ነው፡፡ በመላው አሜሪካም በመስከረም ወር ይከበራል። እነሆ በኢትዮጵያ ደግሞ በደርግ ዘመነ መንግሥት በደማቁ፣ ከዚያ ወዲህ ደግሞ ቀዝቀዝ ባለ ሁኔታም ቢሆን ይታሰባል፡፡ ሙሉ ታሪኩን ለታሪክ ዓምዳችን እንተወውና ለመሆኑ በአሀገራችን የሠራተኛ መብት ምን ይመስላል? የሚለውን እንታዘብ፡፡

ምንም እንኳን የላብ አደሮች ቀን መከበር ያመጣው ነው ለማለት ባያስደፍርም አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የሠራተኛ መብት አይከበርም ለማለት አያስችልም፡፡ ችግሩ ግን በመንግሥት ተቋም ውስጥ ያለው እና በግል የንግድ ቤቶች ውስጥ ያለው ሁኔታ እጅግ የተራራቀ መሆኑ ነው፡፡ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ሠራተኛው በሕዝብ በጀት ሲቀልድ፣ በግል የንግድ ተቋማት ውስጥ ደግሞ ባለሀብቶች በድሃ ጉልበት ይጫወታሉ፡፡ በተለይ እንደ አነስተኛ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ መጠጥ ቤቶችና ሌሎች ንግድ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን እንዴት እንደሚያደናብሩ በቀላሉ ማንም ሰው የሚታዘበው ነው።

መጀመሪያ በመንግሥት ተቋማት በኩል ያለውን እንመልከት፡፡ የተደራጀ የአሠራር ሕግና ደንብ አለው፡፡ ተቋማቱ የየራሳቸው የሠራተኛ ሕግና ደንብ አላቸው፡፡ ለሁሉም ሠራተኛ የወጣውን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅም ያከብራሉ፡፡ በጣም አልፎ አልፎ ሕግና ደንቡን የተላለፈ የመንግሥት ተቋም ካለ መክሰስ ይቻላል፤ ከክሱ በላይ የመንግሥት ተቋም ሆኖ ሕግና ደንብን አለማክበሩ ስለሚያስወቅሰው አስቀድሞ ለስሙ ሲል ይጠነቀቃል፡፡ በዋናነት ግን የሠራተኛው መብት በሕግና ደንቡ መሠረት ይከበርለታል፡፡ ለምሳሌ፤ አንዲት ሴት ስትወልድ የሚሰጣት የወሊድ ፈቃድ በመንግሥት ተቋም ውስጥ እና በግል የንግድ ድርጅት ውስጥ እኩል አይደለም፡፡ ይህ መንግሥት ካለበት ሀገራዊ ኃላፊነት አንፃር የሚገርምም ሆነ የሚደንቅ ሊሆን አይገባም፡፡

በመንግሥት ተቋም ውስጥ ያለው ልክ ያልሆነ ነገር ግን የሠራተኛ አያያዝ ዝርክርክነት ነው፡፡ መብትን ማክበር እንዳለ ሆኖ፤ የመንግሥትና ሕዝብ ጊዜና ንብረት የሚባክንበት ዝርክርክ አሠራር ግን መብት ማስከበር ሳይሆን ብዝበዛ ነው ሊባል የሚገባው! ለምሳሌ፤ የንብረት አያያዝ ላይ አደገኛ ችግር አለ፡፡ የመንግሥት ንብረት ሲባል የሆነ የባዕድ ንብረት አይነት ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ይህ የሠራተኛውም የአስተዳዳሪዎችም ችግር ነው፡፡ በእንዲህ አይነት አሠራር የሰዎች የዓመት እረፍትና የወሊድ ፈቃድ ቢከበርም በሕዝብ በጀት የሚገዛ ዕቃ ግን ይባክናል፡፡ በሕዝብ በጀት የሚሠራ የመገልገያ ቦታ (ለምሳሌ መጸዳጃ) በግዴለሽነት ስለሚያዝ በተደጋጋሚ ይበላሻል፣ በተደጋጋሚ ይጠገናል፡፡

በዚህ ሁሉ ውስጥ ለዚያውም የሚዘረፈውን ገንዘብ (ሙስና) ሳንቆጥር ነው፡፡ ከሕግና ደንብ አሠራር ውጭ የሆኑ ወጪዎች ይደረጋሉ የሚባለው ወቀሳ በየመድረኮች የምንሰማው ነው፡፡ ለንብረት መግዣ ወጪ የተደረገ ገንዘብ ተገቢውን ጥራት ያለው ዕቃ ሳይገዛ ገንዘቡን በመቀሸብ (መቀነስ) ለግል ጥቅም ማዋል እና በቀላሉ የሚበላሽ ዕቃ መግዛት በተደጋጋሚ የሚሰማ ወቀሳ ነው። በዚህ ሁኔታ የዘራፊው ሠራተኛ መብት ሲከበር የሕዝብ መብት ግን ተጣሰ ማለት ነው፡፡ ዘራፊው ይህን ስለዘረፍኩ ብሎ ተጨማሪ ሰዓት አይሠራም፡፡

ሌላው በመንግሥት ተቋም ውስጥ ያለው ትልቁ ሀገራዊ ክስረት ‹‹የኔ›› ብሎ የመሥራት ሞራል የሌለ መሆኑ ነው፡፡ በሠለጠኑት ሀገራት የመንግሥት ሠራተኛ በሀገሪቱ ትልቁ የኃላፊነት ስሜት የሚሰማው እና ለሥልጣኔ አርዓያ የሆነ ነው፡፡ በሀገራችን ዓውድ ካየነው ግን የመንግሥት ተቋም ውስጥ መቀጠር ‹‹የአርባ ቀን ዕድሌ›› የሚባልባት እየሆነ ነው፡፡ እንደ ሀገራዊ አገልጋይነት አይታይም። በኃላፊነት ላይ ያሉትም በግል ጥቅም የሚታሙ ናቸው።መብቱን ብቻ ሲያሳድድ ግዴታዎቹን ግን አይወጣም፡፡ ለመብቱ የሚታገለውን ያህል ግዴታዎቹን ሲጥስ ግን ልብ አይለውም፡፡ ስለዚህ መብትም ይከበር፣ ግዴታም ይከበር፡፡

የሠራተኛ መብት በከፍተና ሁኔታ የሚጣሰው እና ኢ-ሠብዓዊ የሆነ ድርጊት የሚፈጸመው በግል ንግድ ቤቶች ነው፡፡ የግል ንግድ ቤት ባለቤቶች ‹‹በገዛ ንብረቴ!›› የሚሉት የስግብግብነት ሞራለ ቢስ ባህሪ አላቸው፡፡ በጣም ሲከፋ አሰርተው ገንዘብ የሚከለክሉ ሁሉ አሉ። የእሱ ንብረት መግዣ አንድ ሳንቲም እንዳይጎድል ወር ሙሉ ሲለፋ የነበረ ሠራተኛ የዕለት ጉርሱን የሚያገኝበትን ገንዘብ እንዳያገኝ ይራዘምበታል፤ ሲከፋ ደግሞ ጭራሹንም ይከለከላል፡፡ የሁለትና ሦስት ወር አዘግይቶ መክፈል በተደጋጋሚ ከብዙ ሠራተኞች የምንሰማው ቅሬታ ነው፡፡ ባለሀብቱ ለተሻለ ትርፍ የዕቃ መግዣ ካጠረው የዕለት ጉርስ የሌላቸው ሠራተኞች እርሱ ‹‹አሁን ተርፎኛል›› እስከሚል ድረስ መጠበቅ አለባቸው፡፡ ህሊና እና ይሉኝታ፣ ሠብዓዊነት ከሌለ ደግሞ መቼም ቢሆን ገንዘብ ‹‹አሁን ተርፎኛል›› ሊባል አይችልም፡፡

የሠራተኛን ጉልበት ስለሚበዘብዙት እያወራን ስለሆነ እንጂ ከደሞዙ በላይ ትርፍ ጨምረው (ጉርሻ ይሉታል) የሚሰጡ መኖራቸውን አልዘነጋነውም፡፡ ሠራተኛው ከተቀጠረበት ውል ውጭ ሌሎች ወጪዎቹን የሚሸፍኑለት አሰሪዎች እንዳሉ እናምናለን፡፡ በቅርበት የማውቀውን አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስ፡፡ በአንድ የግል ባለሀብት ንግድ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ አብሮ አደግ ጓደኛዬ ከሁለት ዓመት በፊት ሲያገባ ያሠራው የነበረው ባለሀብት 30 ሺህ ብር ሰጥቶት በወቅቱ ብዙ አመስገነናል፡፡ ደሞዝ የሚከለክሉ እንዳሉ ሁሉ እንዲህ አይነቶችም አሉ ለካ ብለን ተገርመናል፡፡ ያንን ብር የሰጠው ብድር አይደለም! ‹‹ለዚህ ቁም ነገር ከበቃህ!›› ብሎ በሰዋዊነት ነው፡፡ ይህ አንድ ነጠላ ምሳሌ ነው፤ የዚህ አይነት ብዙዎች አሉ፡፡

እንደዚህ ማገዙ ቢቀር እንኳን (የሕግ አስገዳጅነት ስለሌለው) ሕግ እየጣሱ የሠራተኛ ደሞዝ የሚከለክሉ፣ የደሞዝ ቀን ሲደርስ ሰበብ አስባብ ፈልገው የሚያባርሩ ሕግንም፣ ሞራልንም ሊፈሩ ይገባል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You