ዛሬ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን ሜይ ዴይ ነው፡፡ ይህ በዓል በሀገራችን ለ49ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ይውላል፡፡ የሠራተኛው ማህበረሰብ ሲነሳ ደግሞ በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) አማካኝነት የሚካሄዱ የሠራተኞች የስፖርት ውድድሮች በአንጋፋነታቸው ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዘመናት ለኢትዮጵያ ስፖርት ታላላቅ ስፖርተኞችን በማፍራት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው መዘንጋት አይቻልም፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኞች የስፖርት ውድድር ዛሬም ቢሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የሠራተኛ ማህበራትን በማሳተፍ ደማቅ የስፖርት መድረክ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ኢሰማኮ በየዓመቱ የበጋ ወራት ውድድሮች፣ የሜይ ዴይ መታሰቢያ ውድድሮችና ሀገር አቀፍ ውድድሮችን በየዓመቱ በማካሄድ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
የሠራተኞች የበጋ ወራት የስፖርት ውድድር ባለፈው ጥር 19-2016 በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከተጀመረ ጀምሮም በደማቅ ሁኔታ መካሄዱን እንደቀጠለ የኢሰማኮ ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ፍሰሃፂዮን ቢያድግልኝ ይናገራሉ። እንደ እሳቸው ገለፃ፣ የዘንድሮው ዓመት የሠራተኞች የበጋ ወራት ውድድሮች እግር ኳስና ቮሊቦልን ጨምሮ በተለያዩ የቤት ውስጥ ውድድሮች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ቀጥሏል። ኢሰማኮ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እጥረት ቢኖርበትን የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ዳግማዊ ምኒልክና ስብስቴ ነጋሲ ትምህርት ቤቶችና ሌሎችም ሊመሰገኑ የሚገባቸው ተቋማት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመፍቀድ የሠራተኛው ስፖርት በድምቀት እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህም ሠራተኞች በጥሩ የስፖርት ስሜት የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ስፖርቱን ለጤና፣ ለወዳጅነትና ለምርታማነት ብሎም ለሰላም እየተጠቀሙት እንደሚገኙ ሃላፊው ያስረዳሉ፡፡ ሠራተኛው በሀገራችን ለ49ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሠራተኞች ቀን ሜይ ዴይን ዛሬ የሚያከብሩትም በዚህ ስሜት ነው። በዓሉ ሲከበርም የዘንድሮው መሪ ቃል ‹‹ለሰላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሄ እንሻለን›› በሚል ሃሳብ ነው። ይህን ምክንያት በማድረግም በዚህ ሳምንት የተለያዩ መርሃግብሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
‹‹ሠራተኛው ሰላምን አጥብቆ ይሻል፣ የኑሮ ውድነቱም እንዲቃለልለት መፍትሄ ይፈልጋልና በየስፖርት ሜዳውም ይሄን ድምፁን እያሰማ ይገኛል። ይሄንን ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን ሜይ ዴይ መታሰቢያ ስናከብር ሠራተኛውም አሰሪውም አጥብቆ ለሚፈልገው ሰላም መትጋት አለበት፣ መንግሥትም የኑሮ ውድነቱ እንዲቃለል የበለጠ ጥረት እንዲያደርግ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በቅድሚያ ሰላም ለማስፈን ጥረት ማድረጉን መቀጠል አለበት። በዚህ አጋጣሚ መንግሥትና ሠራተኛው በመወያየት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መሥራት ተገቢ ይሆናል። ባለፈው ነሐሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከኢሠማኮ ሥራ አስፈፃሚ ጋር ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላም ከሠራተኛው ጋርም የሚነጋገሩበት እድል እንደሚኖር እናምናለን፡፡›› በማለት አቶ ፍሰሃፂዮን ገልፀዋል፡፡
ስፖርት ለሰላም፣ ለወዳጅነትና ለምርትማነት እንደመሆኑ ሠራተኛውም ስፖርቱን በእነዚህን መርሆች መሠረት በተለያዩ ክልሎች ቅርናጫፍ ፅህፈት ቤቶች እያካሄዱ ይገኛል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሜይ ዴይን በተመለከተ የሚካሄዱ ውድድሮችን በአንድ ላይ በማካሄድ ለማክበር አሁን ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ባሉ የፀጥታ ስጋቶች አልተቻለም፡፡ ወደፊት ግን ይህ ስጋት ሲቀረፍ የሜይ ዴይ ውድድሮች የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ የሜይ ዴይን የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ዘንድሮ ባህርዳር ነበር ለማክበር የታሰበው፣ ይሁን እንጂ ከፀጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ማካሄድ አልተቻለም። ወደፊት ግን የሰላሙ ሁኔታ ሲስተካከል ውድድሩም እንደሚመለስ አቶ ፍሰሃፂዮን ይናገራሉ፡፡ እስከዚያው ግን ሠራተኛው ሳምንቱን በበጋ ወራት ውድድሮች ቀኑን በድምቀት እያከበረ ይገኛል፡፡
የኢሰማኮ የስፖርት ክፍል ሃላፊው አቶ ዮሴፍ ካሳ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው የበጋ ወራት ውድድር ከተጠበቀው በላይ በድምቀት መካሄዱን እንደቀጠለ ያስረዳሉ፡፡ በአስር የስፖርት አይነቶች በርካታ የሠራተኛ ማህበራት የስፖርት ቡድኖችም የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በዓመት ሦስት የሠራተኛው የውድድር መድረኮች የሚካሄዱ ቢሆንም ከበጀት እጥረትና ከሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ ዘንድሮ የሜይ ዴይን ውድድር ማድረግ አልተቻለም። ለረጅም ጊዜ የሚቆዩት የበጋ ወራት ውድድሮች ግን በተለያዩ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ጥሩ ፉክክር እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ እንደ አቶ ዮሴፍ ማብራሪያ፣ ቀደም ሲል በጥሎ ማለፍ ውድድር የሜይ ዴይ ፉክክሮች ይካሄዱ ነበር፣ ዘንድሮ ይህን ማድረግ ባይቻልም የበጋ ወራት ውድድሮች አጠቃላይ ድባብ ያንን እንዲተኩ አድርገዋል፡፡ ባህርዳር፣ አዳማ፣ መቀሌ፣ሐዋሳና ጅማ የኢሠማኮ የተለያዩ ቅርናጫፍ ፅህፈት ቤቶች ባሉበት የሜይ ዴይ ውድድሮች በየዓመቱ ሲካሄዱ ሠራተኞች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ እርስበርስ የሚገናኙበትና ተጨማሪ የውድድር አማራጭም የሚያገኙበት ነው፡፡ ይህም በቀጣይ ዓመታት አሁን ያሉ ችግሮችና የፀጥታ ስጋቶች ሲቀረፉ ውድድሩም እንደሚመለስ ተስፋ አላቸው፡፡
ከሠራተኛው ባሻገር አሰሪዎችም ሠራተኞቻቸውን ወደ ስፖርቱ በመላክ ጥሩ ለውጥ እያሳዩ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ዮሴፍ፣ የስፖርት መድረኩ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት በመሆኑም እድሉን እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም