“ሰበዝ” የተሰኘው መጽሀፍ በዶክተር አለማየሁ ዋሴ የተደረሰ ነው:: መጽሀፉ በ2012 ገጾች የተዘጋጀ የደራሲው የጉዞ ማስታወሻ የሚመስል አጫጭር ድርሰቶችን ይዟል:: የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የዘመን ጥበብ አምድ ይህን ሥራ ይዳስሳል።
እንደ መግቢያ
የፊት ሽፋኑ በአረንጓዴ መደብ በሰንደዶ፣ በሰበዝ እና በአክርማ ውብ ተደርጎ እየተሰራ ያለ አንደ ሰፌድ ይታያል:: ሀሳቦች ሲተሳሰሩ አንድ ትልቅ መልክ ያለው ነገር እንደሚሰጡ የሚያሳይ ይመስላል::
ዶክተር አለማየሁ ዋሴ በተፈጥሮ ሣይንስ ዘርፍ የዕፅዋትና የአካባቢ መስተጋብር ተመራማሪ ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በስዊድን ሀገር የዶክትሬት ዲግሪቸውን በኔዘርላንድ በተፈጥሮ ሣይንስ ዘርፍ ተከታትለዋል። ዶክተር አለማየሁ በሙያቸው የተወሰኑ አይደሉም:: በሥነጽሁፍ ሥራቸውም ይታወቃሉ::
በ2007 ዓ.ም እመጓ፣ በ2009 ዓ.ም ዝጎራ፣ በ2010 ዓ.ም ደግሞ መርበብት በሚሉ ርዕሶች ሦስት ልቦለድ ነክ ሆነ ታሪክን፣ ባህልን፣ በመንፈሣዊነትን፣ ሚስጥራዊነትን፣ ሣይንስን የሚያጣቅሱ መጽሀፎችን ለሕትመት በማብቃት በኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ አሻራቸውን አስቀምጠዋል።
ትውልድና ዕድገታቸው በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል በመሆኑም የአደጉበትን አካባቢ ባህል፤ የሞራል ዕሴት ፣ለትምህርት በውጭ ሀገር በቆዩባቸው ዓመታት እና በምርምርዎቻቸው እንዲሁም በንባብ ያገኙት ዕውቀት፤ልምድና ገጠመኝ መፃህፍቶቻቸውን ለህብረተሰቡ ለማድረስ እንደረዳቸው ይናገራሉ።
በባህሪያቸው በጎ ዓላሚ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ፤ ቂም በቀልንና ጥላቻን በመፃፍ ነውርን ለህብረተሰብ ከማከፋፈል ይልቅ፤ የህብረተሰቡን የሞራል ዕሴቶች የሚጠብቁ ተስፋን የሚዘሩ የማህበረሰቡን ሕፀፅ የሚነቅሱ፤ ትውልድን የሚገነቡ ጉዳዮች ላይ አትኩሮ መጻፍ ለመጭው ትውልድና ለሀገር ግንባታ ይጠቅማል የሚል እምነት አላቸው። በአንድ ወቅት ለዶቼቪሌ በሰጡት ቃለመጠይቅ ይህንን ሃሳብ አንስተውት ነበር። ይህ ከሆነ “ከዛሬ የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ ይቻላል” ይላሉ። እምነታቸውንም በዕለት ተዕለት ህይወታቸውና በተለያዩ መድረኮች ተጋብዘው ባደረጓቸው ንግግሮች ጭምር ሲያንፀባርቁ ይታያሉ።
“ሰበዝ” የደራሲው አራተኛ ሥራ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከአቀረብኳቸው ከሦስቱ መጽሐፍቶች በቅርጽም በይዘትም ይለያሉ:: ቀደም ብለው ከአንባቢያን የደረሱት ሦስቱ የደራሲው ሥራዎች አንድ ጭብጥ እንዲኖራቸው ሆነው የተዘጋጁ ነው:: ሰበዝ ግን የተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ያላቸውን የደራሲውን ገጠመኞች አሰባስቦ የያዘ መጽሐፍ ነው:: የ“ሰበዝ” መጽሐፍ ውልደትን ደራሲው ሲያስረዱ በሥራ እና በኑሮ ሂደት የገጠማቸውን በቅርብ ለሚያገኛቸው ወዳጆቹ አንዳንዶቹን እያነሱ ሲያጫውታቸው “ለምን በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅተህ አታቀርባቸውም” ስላሏቸውና በፈጠሩባቸው ግፊት ምክንያት ይህ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ጉልበት እንደሆናቸው ደራሲው ጠቅሷል::
በ“ሰበዝ” የተካተቱት አጫጭር ታሪኮች በተለያዩ ጊዜያት ካገኟቸው አስገራሚ ሰዎች፣ ከሰሟቸው፣ ከጎበኟቸው ፣አገራት ከአደረጓቸው ጉዞዎች፣ ከተመለከቷቸው በኑሮው እና በሥራው ከገጠሟቸው ጉዳዮች በአዕምሮ ተቀርፀው የቀሩትን እና በማስታወሻ ከትበው ካኖሯቸው መካከል ለትምህርት ይሆናሉ፤ ግንዛቤ ይፈጥራሉ፤ ያስገርማሉ፤ ዘና ያደርጋሉ፤ ያሏቸውን እንዲሁም ነቆራ መሰል ትዝብቶቹን እና በተለያዩ መድረኮች ተጋብዘው ካደረጓቸው ንግግሮች መካከል መርጠው እንደ ሰበዝ አንድ ላይ ሰፍተው ያቀረቡት ሥራ ነው::
“ሰበዝ” ማለት በአገራችን መሶብ አገልግል ሰፌድ እና የመሳሳሉ ሲሰሩ በአለላ እና አክርማ ወይም ክር አንድ በአንድ እየተሳካና እየተጠቀለለ የሚሰፋበትን ሣር ወይም ሰንደዶ ያመለክታል:: ሣሮቹ እያንዳንዳቸው ትንንሽ ቢሆኑም አንድ ላይ ሲገመዱና ሲሰፉ ውብ እና ጠንካራ ቁስ ይፈጥራሉ:: ምናልባት በዚህ መጽሐፍ የቀረቡትን ትንንሽ ሐሳቦች ወደ ትልቅ ሐሳብ ሊያድጉ ይችሉ ወይም የመወያያ አጀንዳ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው::
ከሰበዝ ጥቂት እንምዘዝ
አብዛኞቹ ታሪኮች መቼታቸው በኢትዮጵያ የገጠሪቱ ክፍል እና የተወሰኑ የአውሮፓ አገራት ናቸው፤ ከእነዚህ አጫጭር ታሪኮች አንዱ “ባለቁምጣው መሀንዲስ” ነው ታሪኩ እንዲህ ነው። ደራሲው በአንድ ትልቅ የአበባ እርሻ በሚያለማ ድርጅት ውስጥ በስራ አስኪያጅነት ይመደባሉ፤ ታዲያ ይህ የአበባ እርሻ ለመቋቋም 40 ግሪን ሀውስ መገንባት ያስፈልጋል። ደራሲው ታዲያ ለዚህ የሚሆን ባለሙያ መሀንዲስ በውድ ዋጋ በማምጣት ማሰራት ይጀምራል፤ ታዲያ ይህ መሀንዲስ 8 ግሪን ሀውስ ከሰራ በኋላ የተሻለ ስራ እንዳገኘ እና ይህን ስራ እንደሚያቆም ይናገራል።
ደራሲው በወቅቱ ግራ ገብቶኝ ነበር። ታዲያ ለመሀንዲሱ ረዳት እንዲሆን እና ዕቃ እንዲያቀብለው የተመደበ አንድ ወጣት ገበሬ ነበር። ታዲያ ገበሬው ዶክተር አለማየሁ አታስብ፤ እኔ እሰራዋለሁ ከዚህ በፊትም የነበረው ሰውዬ አንዱን ብቻ ነው እሱ የሰራው፤ ሌላውን የሰራሁት እኔ ነኝ በማለት ሀላፊነቱን ወስዶ ቀሪውን ሥራ ሲሰራ የሚያሳይ ታሪክ ሲሆን፤ ደራሲው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ትኩረት ከተሰጣቸው አገሪቱን ሊለውጡ የሚችሉ በርካታ ወጣቶች እንዳሉ ይህን ወጣት ማሳያ አድርጎ ያቀርባል::
ሌላኛው ልንመዘው ያሰብነው እና ድንቅ ታሪክ ያለበት ደግሞ “የእኔ ፕሮፌሰር” የምትለው አጭር ታሪክ ናት። በዚህ ታሪክ ውስጥ እንዴት ደራሲው ለዶክትሬት ትምህርት ሄዶ ያልገባውን ገባኝ ብሎ፤ ነገር ግን እንዳልገባው እና እንዴት ያንን ትምህርት በቀላሉ መረዳት እንዳለበት በኔዘርላንድ የሚገኙ ፕሮፌሰሮች እንዳስተማሩት የሚተርክ ጽሑፍ ነው፤ ደራሲው እንዲህ ይላል “…እንዲህ የተጣመመ ልብ የሚያቃኑ፤ ሰነፍ አዕምሮ የሚያበረታቱ መምህራንን ማግኘት የሎተሪ ዕጣ ያህል እድሉ ትንሽ ነው:: ሲገኙ ግን ለትውልድ ሕመም ፈዋሽ መድኃኒት ናቸው!!” ይህ የደራሲው ሀሳብ ልክም እውነትም ነው፤ ከመጽሐፉ ለቅምሻ ይህን አነሳው እንጂ አንዱም የማይጣልለት ድንቅ ታሪክ በየታሪኮችም አስገራሚ ትምህርቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው::
ማጠቃለያ
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ይህ አጭር ጽሑፍ የመጽሐፍት አስተውሎት እንጂ ግምገማ አይደለም:: “ሰበዝ” መጽሐፍ እያንዳንዱ አጭር ታሪክ ለህይወት የሚሆን መልካም ምክሮችን የያዘ ከፀሐፊው ስህተት እንድንማር ከስኬቱ ደግሞ ለእኛ የሕይወት መስመር የሚሆነንን ፍለጋ እንድንከተል የሚረዳ ነው:: መጽሐፉ በገጠመኝ ውስጥ ታሪኩን እየተረከ ደራሲው የነበረበትን የዚያን ዘመን ሽታ እያሸተተን ትላልቅ ዘመን ተሻጋሪ ትምህርቶችን ለአሁኑ ዘመን የሚያስተምሩ ታሪኮችን የያዘ ነው:: ስለዚህ ማንኛውም ግለሰብ ይህንን መጽሐፍ ቢያነብ ለሕይወቱ ወሣኝ እውነቶችን ይካፈላልና እነሆ ግብዣችን ነው እንጋብዛለን:: ሠላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2013