ማሕሌት አዘነ የ”ስፒችና ላንጉዌጅ ቴራፒስት” ስትሆን ከተለያዩ የጤና ችግሮች ጋር የተወለዱ ህፃናትን በሚመለከት በንግግር ሥልጠናዎች ትረዳለች። በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን ከምትፅፋቸው ሀሳቦች ባሻገር በአዲስ ዘመን ጋዜጣም ሁለተኛዋ የሆነውን ምክሯን ለወላጆች አካፍላናለች።
በመጀመሪያ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመርዳት ስለ ኦቲዝም ምንነት በሚገባ ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። አጠቃላይ ኦቲዝም ምን እንደሆነ፣ ምልክቶቹና ህክምናዎቹ ላይ ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል። በቤት ውስጥ እንደ ወላጅ ከኦቲዝም ጋር የሚኖርን ልጅ እንዴት እረዳዋለሁ? የሚለውን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ይኼንንም ለመጀመር የልጆቻቸውን ጠንካራ እና ደካማ፣ ጎን የሚወዱትና የሚጠሉት፣ የሚችሉት እና የማይችሉትን ነገሮች ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ይህ የሚጠቅመን ሁሌም ለእነርሱ ቴራፒዎችን (ህክምናዎችን) ስንሰጥ ወይም ራሳቸውን ለማስቻል ስንሰራ የምንጀምረው ከሚችሉት ወደማይችሉት፣ ከሚወዱት ወደማይወዱት እና ከጠንካራ ጎናቸው ወደ ደካማ ጎናቸው በመሄድ ስለሆነ እነዚህን ነገሮች ለይቶ ማወቅ እና መመዝገብ ይገባል።
በሦስተኛነት የምንጠቅሰው ልጅዎት የእጅ ምልክት መጠቀሙን፣ ወላጆች የሚያደርጉለትን ደግሞ ለማድረግ መሞከሩን፣ የዓይን ግንኙነቱን፣ የጋራ ትኩረት መኖሩን፣ የመረዳት ክሂሎቱን፣ ትዕዛዝ መቀበል አለመቀበሉን፣ ባህርይውን፣ ከሰዎች ወይም ከእኩዮቹ ጋር ያለውን ቀረቤታ፣ የመግለፅ ክሂሎቱንና የመሳሰሉትን መከታተል እና ማወቅ ያስፈልጋል።
ይህን ካልን ምን ምን ተግባሮችን ማከናወን ይጠበቅብናል? ወደሚለው እንሂድ። ከቋንቋ በፊት ልናደርጋቸው ወይም ልናስተምራቸው የሚገቡን ክሂሎቶች ሲሆኑ፤ ለወደፊቱ የልጁ የንግግርና ቋንቋ ክሂሎቶች እድገት ጠቃሚዎች ናቸው፡፡ እነሱም፤
1. ልጅዎ የእጅ ምልክቶችን እንዲረዱና እንዲጠቀሙ ማገዝ፤ ይህ ማለት ሲሄድ የስንብት እጅ ምልክት ማሳየት፣ የሚፈልጉትን ነገር ስጪኝ/ስጠኝ ብለው በእጃቸው መጠየቅ እንዲችሉ ማሳየት፣ የሚፈልጉትን ምግብ ወይም እቃዎች በመጠቆም እንዲያሳዩ ማድረግ ይጠቀሳሉ።
2. የጋራ ትኩረት፤ ልጆች ለሰዎች፣ ለዕቃዎች ወይም ለዝግጅቶች ያሏቸው ፍላጎት ለጋራ ትኩረት ይጠቅማል፡፡ ለአብነት ያህልም ኳስ መጫወት በእጅዎ ምልክት በማሳየት “ኳሱን ወደ እኔ ወርውር” ማለትና የመሳሰሉት ናቸው።
3. የዓይን ግንኙነት፤ ይህ ለጥሩ ተግባቦትና ንግግር ጥሩ ምሣሌ ነው፡፡ ድምፅ የሚያወጡ ዕቃዎች ማስጮህና ከዚያ ማቆም፤ ይህን ደግመው ከመጀመርዎት በፊት ልጅዎ እርስዎን እስኪያይ ድረስ ይጠብቁ፡፡ “አየሁሽ/አየሁህ” ጨዋታን የህፃናት መዝሙሮችን ወይም/እና ዘፈኖችን አብሮ ማድመጥ።
4. ሰው የሚያደርገውን ማድረግ፤ ልጅዎ እርስዎን እያየ የእጅ ምልክቶችን እንዲያሳይ፤ የፊት ሥሜቶችን እንዲያነብና እንዲያደርግ ማድረግ፣ የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎችን ከእርስዎ በማየት እንዲያደርግ ማገዝ።
ምሣሌ፡- ጥርስ መቦረሽ፣ ድምፆችን መድገም፣ አናባቢ ወይም ተናባቢ ድምፆችን እርስዎን እያየ መልሶ እንዲደግም ማገዝ፣ ዘፈኖች ወይም መዝሙሮች እንዲሉ መርዳት። በሀገራችን ልጆች ዘንድ የሚታወቁ ቀይዋ ወፍ፣ ወንድሜ ያዕቆብ እና የመሳሰሉትን እንዲዘምሩ ማድረግ።
5. ተራን መጠበቅ፤ ተራን በመጠበቅ መጫወት፣ ማውራት፣ መዝፈን። ለምሣሌ፡- እቴሜቴ፣ እንቆቅልሾች ወዘተ። የተለያዩ ጨዋታዎችን ከልጆች ወይም ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር እንዲጫወቱ ማገዝ። ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆችን እንደ ሌሎች ልጆች “ይኼን አድርግ”፣ “ይኼን አድርጊ” ብለን የምንተዋቸው ሣይሆኑ እነሱ ባሉበት አለም ሁሉ በመግባት እያንዳንዱን ተግባር ማስተማር ነው ያለብን። ስለዚህ ለእነርሱ የቀን ልምዶች ፕሮግራሞችን ማውጣት በጣም ጥሩ መፍትሔ ነው። ወላጆችም ልጆቻቸውን እንደ ሥጦታ በመቁጠር ያሉ ችግሮች የሚሻሻሉበትን መንገድ በትዕግስት መሞከር ይገባቸዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2013 ዓ.ም