የዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ እንግዳችን ተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ይባላል። የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ጋዜጠኛ ነው። በቅርቡ በይፋ እውቅና አግኝቶ የተቋቋመው የቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበርም መስራችና አመራር ነው። ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዘዋወር የጉዞ ማስታወሻዎችን ለአንባቢያን በማቅረብ ይታወቃል። በዘርፉም ሙያው የሚፈቅደውን በማድረግ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። የዝግጅት ክፍላችን በእርሱ ህይወትና ሙያዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ!
ጋዜጠኛ ሄኖክ – በህይወት መንገድ
ከልጅነቴም ጀምሮ ከጋዜጠኝነት ጋር የተቆራኘ ታሪክ አለኝ የሚለው ሄኖክ አድጎ ዘጋቢ የመሆኑን ጉዳይ ተጠራጥሮ እንደማያውቅ በልበ ሙሉነት ይናገራል:: ይሁን እንጂ በመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች በተለይ ደግሞ ዜና የሚዘገብበት መንገድ ይረብሸው እንደነበር ያስታውሳል:: ይህም ከዜና ነክ ጉዳዮች እንዲርቅና ጥሩ ዘገባ ለመሥራት የሚጓጓ ጋዜጠኛ እንዳይሆን እንዳደረገው ይገልፃል:: ስፖርትን የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ለእሱ በእጅጉ ሩቅ ናቸው:: የኋላ ኋላ ግን ሸገርን የመሳሰሉት መገናኛ ብዙሃን ለየት ባለ መንገድ ዜናዎችንና መረጃዎችን ለአድማጭ ማቅረብ መጀመራቸው እንዳስደሰተው ይናገራል።
“ብዙ ጊዜ እመኝ የነበረው የጦርነት አሊያም የጉዞ ጋዜጠኛ መሆን ነው:: የሥነ-ጽሑፍ ፍቅርም ስለነበረኝ በትረካ የበለጠ ለሚደምቁ ዘገባዎች አደላለሁ” የሚለው ጋዜጠኛ ሄኖክ፣ የጦርነት ዘጋቢነቱን የግጭት ጠባሳ ሲያንከራትታትና ሲጠብሳት በቆየች፤ ጦርነቷ ሁሉ እርስ በእርስ በሆነ ሀገር እያደገ ሲመጣ ሊወደው አልቻለም:: ይልቁንም ልቡ ለጉዞና ለጉብኝት ጋዜጠኝነት እያደላ መጣ:: ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ስላደገ ቅርስ፣ እሴት፣ ባህል፣ እንስሳት ዕጽዋትና የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ ወደራሳቸው ያስጠጉት ጀመር::
ይኼ መሻቱ ሲሆን መንገዱ ግን “ህይወቴ ጋዜጠኝነት” ከሚባለው ጎዳና የወጣ አለመሆኑ ነው:: አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ በፋና ራዲዮ በከርሞ ሰው ፕሮግራም በጋዜጠኛ ሸዋዬ ደቻሳ አማካይነት ሥራዎቹን ሲያቀርብ፤ ቆይቶም ውበት አማተር የጋዜጠኞች ክበብን ተቀላቀለ:: ከአማተር ጋዜጠኝነት እስከ ጉዞ ቱሪዝም ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት ሰርቷል፤ ሰሞኑን ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት ሆኖ ኃላፊነትን ተቀብሏል:: እንዲህ እያለ ከሙያው ደጃፍ ሳይርቅ እዚህ የደረሰ ሕይወት የገባበት ታሪኩ ነው::
የጉዞ ገጠመኞች
በቱሪዝም ሥራ ወደተለያዩ ቦታዎች ስትሄድ ምን የተለየ ነገር አጋጠመህ? በሚል ጠይቀነው ሲመልስ “ብዙ ሰዎች እንዲህ ላለው ጥያቄያቸው መልሱ የሚመስላቸው የእባቡ ንድፊያ፣ የአንበሣው ሁኔታ፣ የውሃው ሙላት፣ የሽፍታው፣ ምናምን ነው፤ ይህ ግን አይደለም:: በቱሪዝም ሥራ ወደተለያዩ ቦታዎች ስሄድ ሁሌም የሚያጋጥመኝ የተለየ ነገር ሀገሬ የተለያየች፣ የታደለች፣ ያልተፈተሸች መሆኗ ነው:: አንዳንድ ጊዜ በአካባቢው ተወልደው፣ ተምረው፣ ሥራ ይዘው ከእኔ እኩል የማየት እድል የሚገጥማቸው ሰዎች አይቻለሁ:: እንኳን እኔ ፍለጋ የሄድኩትን አጠገቡ ያሉትን ጭምር ተሸሽጎ የኖረው ሐብታችን ብዛት ያስገርመኛል:: የሁሌም ገጠመኜ ነው” በማለት ምልከታውን አጋርቶናል።
ቱሪዝምና መዝናኛ
ተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ ቱሪዝም መዝናኛ ብቻ አይደለም:: እየተማርን የምንዝናናበት ነው ይላል:: በቀላሉ መስቀልን ከጉራጌ ጋር ስናሳልፍ፤ ማንም ሰው ከአዲስ አበባ ወደ ጉራጌ ገጠሮች ቢገባ ሲመለስ ተዝናንቶ ብቻ አይደለም የሚመለሰው፤ ባህል አይቶ እውቀት ገብይቶ እንጂ:: ሀገር አይቶ ቃኝቶ መሆኑን ይናገራል። “ሌላውን ብንተወው” ይላል ሄኖክ፤ ምግብና ጭፈራ ላይ ያለው ዕውቀት እንኳን ከነበረው ጋር ተቀይሮ የሚጠብቀን ብዙ ነገሮችን የሚያሳውቀን ነው:: “አክሱም ሐውልት ስር ፎቶ ስትነሳ ትዝናና ይሆናል:: ግን ደግሞ በዚያው ቅጽበት የሀገርን ገናና ታሪክ ትማራለህ::” በሚል ያስረዳል:: ስለ ቱሪዝምና የኢትዮጵያ ሐብቶች አውርቶ አይጠግብም።
የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ጥቅሙ ብዙ ነው:: ትዝናናለህ ግን እየተማርክ ነው:: በምትማረው ትተዋወቃለህ:: የሚተዋወቅ ለመግባባት አያዳግተውም:: የተግባባ ደግሞ በአንድ ሀገር ለመኖርና ለአንድ ሀገር እኩል ብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም እንዲሁም ወንድማማችነቱን ለማጎልበት የሚያዳግተው ነገር የለም:: ቱሪዝም ሀገር ይሠራል ሲል ያብራራል::
ሥነ ፅሁፍና ጋዜጠኛው
ተጓዥ ጋዜጠኛ ሄኖክ የሚሰበስበውን መረጃ በዶክመንተሪና በራዲዮ ብቻ ገድቦ የሚያደርስ ሳይሆን በህትመቱም በሥነ ፅሁፍ ላይ የቱሪዝም መጽሔት ያዘጋጃል። በጋዜጠኝነቱ ብቻም አልተገታም፤ ወደ ደራሲያን ጎራም ተቀላቅሏል:: ሁሉም ጉዞና ጉብኝት ላይ ያተኩራሉ:: ከሌሎች ጋር በኅብረት በሁለት መጻሕፍት ሥራው አሳትሟል:: አንዱ ደቦ ይባላል፤ ስድሳ ደራሲያን አሉበት:: በዚህም ሄኖክ ኮንሶን የተመለከተ የጉዞ ማስታወሻ ሥራ አቅርቧል::
ሌላው አቦል የሚባል ሲሆን፤ በዚህም ላይ የተለያዩ ደራሲያን ሥራዎቻቸውን ያወጡበት ነው:: በዚህም ተጓዡ ጋዜጠኛ አንድ የኢትዮጵያ ብሔር ጎሳ አባል ሆና ከመጥፋት ስለተረፈች የዱር እንስሳና የታደጋት ባህል እንዲሁም “የቃጥባሬ የረመዳን” ድባብን የተመለከቱ ሁለት ሥራዎች ሰርቷል:: የመንገድ በረከት፣ ጎንደርን ፍለጋ እና ሀገሬን በግሉ በተከታታይ ለህትመት ያበቃቸው መጻሃፍቱ ናቸው::
የእረፍት ውሎ
የቱሪዝም ሰው ስለሆነ የሚያማርርና እረፍት የሚያስመኝ ሥራ እንደሌለው ይናገራል:: ሰዎች የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቦታ እርሱ የአዘቦት ህይወት ቀጠና ነው:: በጉዞ የሚያሳልፈው ጊዜ አለ፣ በንባብ የሚያሳልፈው ጊዜ አለ:: ከዚያ ውጪ ያለውን ከጓደኞቹ ጋር ሻይ ቡና እያለ ጥሩ ጥሩ ወግ ይጨዋወትበታል:: በተረፈ ብዙው ሰዓቱን ሥራው ላይ ነው የሚያሳልፈው:: ሃሳቡን በማጠቃለያው ገደማ ለወጣቱ መልካም መንገድ ነው ያለውን መልዕክት እንዲህ በማለት ያስተላልፋል።
ወጣቶች ንባብን ባህላቸው እንዲያደርጉና ራሳቸውን አንዲያውቁ ከማህበራዊ ገጾች እርባናቢስ ወሬዎች ሱሰኝነት ራሳቸውን እንዲጠብቁና እንዲያርቁ እመክራለሁ የሚለው ሄኖክ፤ ኢትዮጵያ እንዳትጎድል፤ ፀጋዋ ዘፈንና ሥዕል ብቻ ሆኖ እንዳይቀር፣ የተሰጠንን ለመቀበል በፍቅር፣ በሥራ መንፈስና በሰለጠነ ልቦና በጋራ ቆመን ለሚቀጥለው ትውልድ ትልቅ ሀገር እናስረክብ በማለት ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላልፋል::
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2013