ምንም እንኳን ባህላዊውን የቡርሳሜ ምግብ እና ማባያውን ጌኢንቶ (እርጎ) ባናዘጋጅም የእነርሱን የአክብሮት አቀባበል ተውሰን ዳኤቡሹ (እንኳን ደህና መጣችሁ) ብለን፣ ይዘው ከመጡት ባህላዊ ምግብና እርጎ ተቋድሰን፣ በባህላዊ ጭፈራቸውም ተደስተን ፍቼ ጫባላላ የዘመን መለወጫ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ በዕለተ ቅዳሜ ግንቦት 7 ቀን 20013 ዓ.ም አብረን በማክበር አሳለፍን:: ከሸክላ የተሰራው የባህላዊ ምግብ ማስቀመጫ ሻፌታ የተባለው ባህላዊ ዕቃም ከውበቱ በተጨማሪ ለምግቡ ጣዕም ሰጥቶታል::
የእንሰት ውጤት ከሆነው ቆጮ በቅቤ ታሽቶ የተሰራው ቡርሳሜ ተበልቶ አይጠገብም:: ማባያው እርጎም ከማጥንቱ ቃና ጋር የመብላት ፍላጎትን ይጨምራል:: እርጎው ከቅል በተዘጋጀ የመጠጫ ዕቃ ነው የሚቀርበው:: እንግዳ ሆነን በማንኪያ ተጠቀምን እንጂ የባህሉ ባለቤቶች የቡርሳሜ ምግቡን በእጃቸው እያነሱ ነበር የተመገቡት:: ቱባው ባህል ባለበት በገጠሩ ለምግቡ መሸፈኛም ሆነ መመገቢያ ሳህን ሆኖ የሚያገለግለው የኮባ ቅጠል (እንሰት) ነው:: ምንም እንኳን እንግዶችን እንደፍላጎታቸው ለማስተናገድና በገጠሩ የሚገኘው በከተማው ባለመኖሩ እንደሆነ ብገነዘብም ባህል ወደ ከተማ ሲመጣ እንዴት እንደሚሸረሸር የተረዳሁበት አጋጣሚ ነበር::
ቱባ ባህልን ማስጠበቅ የሚቻለው በቦታው ብቻ ነው? የሚለው ሊያነጋግር ይችላል:: ፍላጎቱ ካለ በቦታ ሳይገደቡ ባህሉን የማስጠበቅ ጥንካሬም ሊዘነጋ አይገባም:: ባህላዊ አልባሳት፣ ባህላዊ ምግቡ፣ ጭፈራው በተለይም የባህል ተጫዋቾቹ ሲጫወቱ የነበረው የታዳሚው ስሜት፣ በሲዳማ ቋንቋ ይደረግ የነበረው የሀሳብ ልውውጥ በሲዳማ ክልል ውስጥ የተገኘሁ ያህል እንዲሰማኝ አድርጎኛል::
ከአባቶች እንደተረዳሁትና ስለበዓሉ ከተጻፉ በራሪ ጽሁፎች ያገኘሁት መረጃ እንደሚያመለክተው የፍቼ ጫምበላላ በዓል ለአንድ ሳምንት ይቆያል:: በነዚህ ቀናትም በተለያየ ሥያሜ የሚጠሩ ክንውኖች በመኖራቸው በየተራ ይፈፀማል:: ከነዚህ መካከል አንዱ ፊቺ ፉሎ ይባላል:: የፊቺ ፉሎ በዓል በጋራ ባህላዊ አደባባይ በድምቀት የማክበር ሥነ-ሥርዓት ሲሆን፣ ሐዘን ላይ ያለና አራስም አይቀርም:: ሁሉም ሰው ይገኛል:: ሁሉም አምሮና ደምቆ የበለጠ የሚታየው በዚህ ቀን ነው:: የጭሜሳዎች ምርቃት፣ ሕብረ ዜማ፣ ቄጤላ፣ የፈረስ ውድድር የበዓሉ ማድመቂያ ክንውኖች ናቸው::
ሌላው ኪፊቼ የሚባለው ሥርዓት ነው:: ከኪፊቼ እና ከፊቺፉሎ በኋላ ማህበረሰቡ ተሰብስቦ ዳግም ባህላዊ ምግብ በሻፌታ ተዘጋጅቶ ቀርቦ ይመገባል:: ፊቼ ጂጂ እየተባለ ነው የሚቀርበው:: የደስታ ጊዜ በመሆኑ በበዓሉ ጊዜ የእርሻ ሥራ አይሰራም:: ከብቶች ለግጦሽ አይሰማሩም:: ከወራት በፊት ለበዓሉ ተብሎ ተከልሎ ወደ ተዘጋጀላቸው ካሎ በተሰኘ ለምለም መስክ ላይ ይሰማራሉ:: በግጦሹ ላይ ቦሌ የተባለ ግብዓት ይጨመራል:: ከብቶቹ ቢያስቸግሩ ጀርባቸው ላይ ዱላ ወይንም ጅራፍ አያርፍም::
በዚህን ቀን እረኛ ከብቶቹን እንዲጠብቅ አይገደድም:: አባት ወይንም ሽማግሌ የባህል ልብሱን ለብሶ ቅቤ አናቱ ላይ አድርጎ በቀዬው ሆኖ ከብቶቹን ይጠብቃል:: ገበሬውም እንዲሁ ከግብርና ሥራ ነፃ ነው:: ሁሉም ሰው እየበላና እየጠጣ በጨዋታ ያሳልፋል:: ስድብና ፀብ በዚህ ወቅት የተወገዘ ነው:: ቂምና ቁርሾ ይዞ ከዘመን ወደ ዘመን ወይም ወደ አዲስ ዘመን ለመሸጋገር መሞከር አይታሰብም:: የተጣላ ይታረቃል:: የጠፋም ሰው ተፈልጎ በዓሉን ከቤተሰቡና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እንዲያከብር ይደረጋል:: ልጃገረዶች በየመንደሩ እየዞሩ አይዴ ጫምባላላ (እንኳን አደረሳችሁ) ይላሉ::
ተቀባዮቹ ወይንም የቤቱ ባለቤት ኢሌ ኢሌ ብለው ይቀበሏቸዋል:: እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አደረሳችሁ ማለት ነው:: ባህላዊ ምግብ ያቀርቡላቸዋል:: አጥግበው ይሸኟቸዋል:: ለፊቼ ጫምባላላ የዕርድ ሥርዓት አይከናወንም:: ሊታረድ ቀርቶ ከበዓሉ በፊት በቤት ውስጥ የገባ ሥጋ ካለ ከቤት ውጭ እንዲቀመጥ ይደረጋል። ምንም እንኳን የእንስሳት ተዋጽኦ በበዓላት ወቅት የተለመደ ቢሆንም ፍቼ ጫምባላላ የአዲስ ዓመት፣ አዲስ ሀሳብ፣ የአዲስ ትውልድ፣ ለሰው ልጅና ለሌላውም ፍጥረት ሠላም እንዲሆን የሚገለጽበት የተለየ ቀን በመሆኑ ለሁሉም ክብር ይሰጣል::
ዛፍ አይቆረጥም:: የዱር እንስሳት አይታደኑም:: ልጆች ጥፋት ቢያጠፉ እንኳን አይቀጡም:: ከእንስሳት ተዋፅኦ ቅቤ ነው በሥፋት ለምግብ የሚውለው:: የበዓሉ ታዳሚዎችም በበዓሉ አምረውና ደምቀው ለመታየት ሁሉም ተመሳሳይ የሆነ አልባስ አይጠቀምም:: ወንዱ፣ ሴቱ፣ ሕፃናት፣ አዋቂዎች፣ አርበኞች የሁሉም በተለያየ ስፌት የተዋበ ባህላዊ ልብስ ነው የሚደምቁት:: ሴቶች የሚዋቡባቸው ጌጣጌጦችና የፀጉር ሥራ እንደየዕድሜያቸው ይለያያል::
በሲዳማ በክብር የተጠራ እንግዳ ሁሉቃ በተባለው ውስጥ አልፎ ነው ወደ በዓሉ ዝግጅት የሚቀላቀለው:: ሁሉቃ ለማለፊያ በሚሆን መልኩ ተቆልምሞ መሬት እንዲይዝ ተደርጎ የተሰራ ሲሆን፤ በአረንጓዴ ይሸፈናል:: ሁሉቃው የተሰራበት ግብዓት በገጠርና በከተማ ስለሚለያይ እንጨት ወይንም ብረት ሊሆን ይችላል:: የዕለቱ እንግዶች በዚህ ውስጥ አልፈው በሀገር ሽማግሌዎች አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር የታደሙት:: በባህል አልባሳቶቻቸው የደመቁት ሲዳማዎች በእንግዶቻቸውም አንገት ላይ ውብ የሆነውን የእጅ ስራ ውጤቶቻቸውን አልብሰው አንድነታቸውን የገለጹበት የበዓል ድባብ ነበር:: በዓሉ የተከበረበት ስፍራ የጊዮን ሆቴል የቅጥር ግቢው ሥፋት በአረንጓዴ ልምላሜ ማማርና ነፋሻው አየር ለክብረ በዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥቶታል::
በዕለቱ ልዩ የክብር እንግዳቸው ከነበሩት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አንዷ ነበሩ:: ለእሳቸው ያላቸውን አክብሮት የገለጹበት መንገድም የሲዳማዋን የንግስት ቱራ ምስል በማበርከት ነበር:: ‹‹ንግስት ቱራ በ16ኛው ክፍለዘመን የነበረች፣ በዘመኗም የሴቶችን እኩልነት ያስከበረች:: የወንድ የበላይነትን ለማስቀረት የታገለች:: የአሁኑን በብዙ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ያደገን ዘመን ቀድማ በዚያን ጊዜ የማይጠበቅ ጀብድ ፈጽማለች ተብላ የሚነገርላት የሲዳማ ሴት ናት››:: ተምሳሌቱም ወይዘሮ አዳነች በአመራርነት ላይ ያላቸውን ጥንካሬና ቆራጥነት ለማሳየት ነው:: ለወይዘሮ አዳነችም ተጨማሪ አደራና ሀላፊነት ጭምር ነበር የተበረከተላቸው ለማለት ይቻላል::
ወይዘሮ አዳነችም የሲዳማን ባህልና ወግ በአጠቃላይ እሴት ለማስተዋወቅ በአዲስ አበባ ከተማ የባህል ማዕከል እንዲገነባ በመፍቀድ ለግንባታ የሚውል መሬት ካርታ አስረክበዋል:: በዚሁ ወቅትም እንደተናገሩት በከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባ ከተማን ልክ እንደፓሪስ የባህል ማዕከል የማድረግ ዕቅድ ተነድፏል:: ኢትዮጵያ ታይተው የማይጠገቡ የቱባ ባህል ባለቤት መሆኗን ምስክር መቁጠር አይጠበቅም:: ባህሉን ተንከባክቦና ጠብቆ ለትውልድ ማሸጋገር ብሎም የገቢ ምንጭ ማድረግ ከዜጎች ይጠበቃል::
አዲስ አበባ ከተማን የቱባ ባህል መገኛ ማዕከል ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ ሲታቀድ የቱሪዝም ፍሰቱ ተቋዳሽ እንድትሆን ነው:: የሐብት ምንጩ እያላት ነገር ግን የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስጠበቅ ገንዘብ ማነቆ ሲሆንባት ማየት ቁጭት ውስጥ ይከታል:: በገንዘብ እጥረትም ፕሮጀክቶች በጅምር ይቀራሉ:: አዲስ ለመጀመርም አይቻልም:: በዓለም ላይ ኢትዮጵያን ያስተዋወቋት ቱባ የባህል እሴቶች አሁን ላይ መባከን የለባቸውም:: የውጭ ምንዛሪ ምንጮች፣ ከድህነት የመውጫ መንገዶች መሆናቸውን ተገንዝቦ ከመቼውም ጊዜ በላይ መሥራት ይጠበቃል::
‹‹ፍቼ ጫምባላላ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ሊከበር እንደሆነ በሰማን ጊዜ የሲዳማ ህዝብ ለሁላችንም የሰጠን በዓለምም ላይ ሁላችንንም ያስተዋወቀን ስለሆነ አዲስ አበባ የሁላችንም ስለሆነች ስለመጣችሁልን እናመሰግናለን:: ፍቼ ጫምባላላን የዓለም የሳይንስ፣ ባህልና ትምህርት ድርጅት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መዝግቦ ሲቀበለው እንዴት ነው አዲስ አበባ ከተማ ላይ የባህል ማዕከል እንዲኖር የማንፈቅደው:: የባህል ማዕከሉ ፈጥኖ ወደ ግንባታ ሥራ እንዲገባ የከተማ አስተዳደሩ በሚችለው ሁሉ ያግዛል›› ሲሉ ቃል በመግባት ነበር ወይዘሮ አዳነች ለሲዳማዎች አቀባበል ያደረጉት::
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞም የከተማ አስተዳደሩን በማመስገን የሲዳማን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ ባህልና ሌሎች እሴቶች የሚያስተዋውቅ የባህል ማዕከል አዲስ አበባ ከተማ ላይ ለመገንባት ክልሉ ሲያቅድ ፍቼ ጫምባላላ የሁሉም ባህል እንደሆነ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ገልጸዋል::በሲዳማ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ስለባህል ማዕከሉ ግንባታ የተላለፈው መልዕክትና የግንባታ ቦታ የካርታ ርክክብ ታዳሚውን ከመቀመጫው ያስነሳና በደስታ ስሜት ያስፈነደቀ ነበር::
በአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረው ፍቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ ከታደሙት መካከል የሀገር ሽማግሌዎች በባህላዊ አለባበሳቸው፣ የዕድሜ ባለፀጋም መሆናቸው ከሌሎቹ ጎልተው ይታያሉ:: ከሲዳማ ባህላዊ እሴቶች አንዱ የሀገር ሽማግሌዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ሚና ይጠቀሳል:: እንዲህ እንደፍቼ ጫምባላላ ያሉ ክብረ በዓሎች ላይ በመገኘት ስለሰዎች፣ ስለሀገር ሠላምና ፍቅር ፀሎት ያደርጋሉ:: ይመርቃሉ፣ ይገስፃሉ፣ መልካም ይመኛሉ:: በህዝባቸው የሚከበሩ በመሆናቸውም ተሰሚነት አላቸው:: የፍቼ ጫምባላላ በዓልም የተጀመረው በእነዚህ አባቶች ነበር:: ከነዚህ አባቶች መካከልም በሲዳማ ክልል መልካ ወረዳ ውስጥ የሚኖሩት አቶ ኡዋዱ ዳሞቱ አንዱ ነበሩ::
አቶ ኡዋዱ እንደነገሩን በባህሉ መሠረት የሀገር ሽማግሌ መልጋ ተብሎ ይጠራል:: ዋና ተግባሩም በአካባቢው የተጣላን ማስታረቅ፣ የተበደለ ፍትህ እንዲያገኝ ማድረግ፣ ከጎረቤትና ከአካባቢ አልፎ ለሀገር ስጋት የሚሆን ችግር ካጋጠመም መክረው፣ ዘክረው ችግሩን ከሥር አጥንተው መፍትሄ በማፈላለግ ከመንግሥት ጋር ይሰራሉ:: በዚህ ረገድ በተለይ ጉዳያቸው ወደ መንግሥት ተቋማት ፍርድ ቤት ሳይሄድ በመፍታት ብዙ አስተዋጽኦ አበርክተዋል:: እያበረከቱም ይገኛሉ::
በሽምግልናው የሴቶችም ሚና የማይናቅ እንደሆነ የተረዳሁት በበዓሉ ላይ ያገኘኋቸው በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ኑሬ ወዬሱ ባጫወቱኝ ጊዜ ነው:: እርሳቸውም እንዳሉት በኦሮሞ ባህል ሴቶች ሲቄ ብለው የሚጠሩት ዱላ ዓይነት በሲዳማም ሴቶች በተመሳሳይ ዱላ ይዘው ፀብ የተፈጠረበት ቤት ይሄዳሉ:: ፀቡ በባልና ሚስት መካከል ወይንም በሌላ ሊሆን ይችላል:: ሴቶች ዱላቸውን ይዘው በመሄድ ፀቡ እንዲረግብና እርቅ እንዲፈጠር ያደርጋሉ:: በዚህ መልኩ የቆየው የማስታረቅ ባህል ዛሬም ቀጥሏል::
ወይዘሮ ኑሬ ጠንካራ ሴት መሆናቸውን ገጽታቸው ቢመሰክርም በዕድሜ የገፉ ናቸው:: ዕድሜያቸውን በጠየኳቸው ጊዜም ‹‹እኔ ምን አውቃለው 40 ይሁን 80 ዕድሜ የሚሰጠው ፈጣሪ ነው›› ብለው ፈገግ አደረጉኝ:: የሲዳማ አባቶችና እናቶች ዓመቱ የስኬት፣ ልጅ ተወልዶ የሚያድግበት፣ ከብቶች የሚረቡበት፣ ስለሀገራቸው ቸር ነገር ወይንም ሠላም የሚሰሙበት፣ የእርስ በርስ መተሳሰብና አብሮነት እንዲጠነክር፣ ያለው ለሌለው እንዲያካፍል፣ ያጣ እንዲያገኝና እንዲከብር ተመኝተዋል::
ፍቼ ጫምባላላ በየዓመቱ በተመሳሳይ ወቅት አይውልም:: በዓሉን አስመልከቶ በተዘጋጀው በራሪ የሰፈረው ጽሁፍ እንደሚያመለክተው የበዓሉ ጊዜ የሚታወቀው በባህላዊ የቀን ቆጠራ ሥሌትና የሥነ ከዋክብት ምልከታ ሲሆን፤ የሥነ ከዋክብት ምልከታውን የሚያከናውኑት ደግሞ አያንቶ የተባሉ ባህላዊ የሥነ ከዋክብት ጠበብቶች ናቸው:: አያንቶዎች ቀኑን ከለዩ በኋላ ለሀገር ሽማግሌዎችና ለጎሳ መሪዎች ያሳውቃሉ::
አያንቶች እንደሚሉት የፊቼ ጫምባላላ መድረስ የሚታወቀው ጨረቃና ቡሱ የተሰኘ የህብረ ከዋክብት ፉክክር ወይም የከዋክብቱ ከጨረቃ የመቅደምና ወደ ኋላ የመቅረት ሁኔታ በትኩረት በመከታተል ሲሆን፤ ይኼ ክስተት በዓመት አንዴ ነው የሚያጋጥመው:: በዚህ የዘመን ስሌት የዘንድሮው የፍቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል ግንቦት ወር ላይ ሊውል ችሏል:: እንደ ጽሁፉ መረጃ ጫምባላላ ከፈጣሪ ቀጥሎ ይመጣል:: በዕለተ ጫምባላላ ንጋት ላይ በሸክላ በተሰራ ፍኒንቾ በተሰኘ ዕቃ ውሃ ተጨምሮ በአፍ ቅቤ ተይዞ በሁለት እጅ ፊት ይቀባል:: አዲሱ ዓመት የአንድነት፣ እንዲሆን፣ የመልካም መልዕክት ይተላለፋል:: እኛም እንደ ሲዳማዎቹ መልካሙን ተመኘን::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2013